የነፃው ፕሬስ አሣታሚ ድርጅቶች ለፍ/ቤት ተቃውሟቸውን አቀረቡ
Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. December 26, 2008)፦ “ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለመናድ” በሚል፣ በእነ ኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል የክስ መዝገብ ተከሳሽ የነበሩት፤ “ሰርካለም አሣታሚ ድርጅት” 120 ሺህ ብር፣ “ሲሳይ የሕትመትና የማስታወቂያ ድርጅት” 100 ሺህ ብር የተጣለባቸውን ቅጣት እንዲከፍሉ፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ለቀረበባቸው አፈፃፀም ክስ፣ ጉዳዩ በይቅርታ የተቋጨ በመሆኑ ልንጠየቅ አይገባም ሲሉ መከራከሪያቸውን ለፍርድ ቤት አቀረቡ። ፍርድ ቤቱ መከራከሪያው ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደርሶት ለሰኞ መልስ እንዲሰጥበት አዟል።
ሰርካለም አሣታሚ ድርጅት እና ሲሳይ የሕትመትና የማስታወቂያ ድርጅት፣ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት “ቅጣቱ ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም” ሲሉ ያቀረቡት የመከራከሪያ ሃሳብ፤ አንደኛ፦ በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ፋይል የተከሰሱ እና ሐምሌ 9 ቀን 1999 ዓ.ም. ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች በሙሉ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2001 ዓ.ም በይቅርታ ሥነ ሥርዓት ዓዋጅ ቁጥር 395/1996 መሠረት በይቅርታ በነፃ ተሰናብተዋል። በአሣታሚ ድርጅቶቹ ሥር የሚታተሙት የ”ምኒልክ” እና የ”ኢትኦጵ” ጋዜጣ አዘጋጆች፣ የዕድሜ ልክ እስራታቸውም በይቅርታ ሕጉ ተሽሯል፤ በዕለቱ ቅጣቱ ያልተጣለባቸው በዚሁ ፋይል የሚገኙ ሌሎች ተከሳሾችም በተመሳሳይ ውሳኔ እንዳገኙ በይቅርታ ሕግ-መሠረት ከእስር ተለቀዋል፤ ተከሳሽ ድርጅቶችም ሐምሌ 9 ቀን 1999 ዓ.ም. ውሳኔ ያገኙ በመሆኑ በይቅርታ ሕጉ ድንጋጌ አንቀፅ 2/7 እና አንቀፅ 12/6 መሠረት ይቅርታ ስለተደረገላቸው ቅጣቱ ተሽሮላቸዋል።
በይቅርታ ሥነ ሥርዓት ዓዋጅ ቁጥር 395/1996 አንቀፅ 12 ንዑስ አንቀፅ ስድስት ደግሞ “በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 እና 2 መሠረት የይቅርታ ጥያቄ የቀረበበት ፍርድ ግብረ አበር ወይንም አባሪ ያለበት የሆነ እንደሆነ የይቅርታ ጥያቄው እነሱን የሚመለከት ተደርጎ ይወሰዳል” ይላል። በዚሁ የይቅርታ ሥነ ሥርዓት ዓዋጅ በአንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 7 ሥርም፣ ከላይ የተመለከተውን በሚያጠናክር ዓረፍተ ነገር፤ “ይቅርታ ጠያቂ ማለት ይቅርታ የተጠየቀበት ፍርድ የሚመለከተው ሰው ሲሆን፤ ወንጀሉ ግብር አበር ወይንም አባሪ ያለበት ከሆነ ግብረ አበሩን ወይንም አባሪውን ይጨምራል” ይላል።
በዚህም መሠረት በወንጀል መዝገብ ቁጥር 43246 የተከሰሱ ሰዎችና በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላት ሁሉ፣ ጉዳያቸው ሐምሌ 12 ቀን 1999 ዓ.ም. የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ባሳረፉት የይቅርታ ደብዳቤ ፊርማ ተቋጭቷል። በዚህ የይቅርታ ውሳኔ መሠረትም በሁለቱ አሣታሚ ድርጅቶች ሥር የሚታተሙት ጋዜጦች ዋና አዘጋጆች ሐምሌ 13 ቀን 1999 ዓ.ም. ከእስር ተለቀዋል። ይቅርታው ሲሰጥ በይቅርታው ላይ የተለየ ሁኔታ ባለመጠቀሱም ለአዘጋጆቹ የተሰጠው ይቅርታ አሣታሚ ድርጅቶቹንም ይጨምራል፤ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 231/2 የሠፈረውም ይህንኑ ያስረዳል። አንቀጽ 231/2 “ይቅርታን ወይም ምሕረትን በሚሰጠው ትዕዛዝ ላይ በተለየ ሁኔታ ካልተገለጸ በስተቀር፣ ለመንግሥት ሊከፈል የሚገባውና ገና ያልተከፈለ ኪሳራ በይቅርታው ወይንም በምሕረት ይሰረዛል” ይላል።
“ምርጫ 97ትን ተከትሎ በሀገሪቱ የሰፈነውን አለመግባባትና ውጥረት፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሚሊኒየሙ ዋዜማ በሕግ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፈቃደኛነትም ዘግተናል፣ ተብሎ በአደባባይ የተነገረ መሆኑም ለሁላችንም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ሐምሌ 13 ቀን 1999 ዓ.ም. በኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የክስ ፋይል የተፈረደባቸው ተከሳሾችን ከእስር መለቀቅ ተከትሎ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ በሰጡት መግለጫ “የ97 ምርጫ ችግሮች የመጨረሻ ምዕራፍ ብቻ ሳይሆን የአዲስ ምዕራፍ በር ከፋች እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ነበር ያሉት፤ የተዘጋው ምዕራፍ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በኋላ እኛ ላይ የሚከፈትበት ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ምክንያት የለም” ብለዋል አሣታሚ ድርጅቶቹ።
በሁለተኛነትም ያቀረቡት የመከራከሪያ ሃሳብ፣ በይቅርታ ሕግ ዓዋጅ ቁጥር 395/1996 መሠረት የተጣለው የገንዘብ ቅጣትም ሆነ፣ ድርጅቶቻችን እንዲፈርሱ የተወሰነው ውሳኔ በይቅርታ የተሻረ ቢሆንም፣ ድርጅቶቹ እንደገና እንዳይንቀሳቀሱ ከሕግ ውጭ ታግደዋል፤ ከቢሮ እና ከመኖሪያ ቤታችን የተወሰዱ ኮምፒውተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ ፋክስ ማሽን፣ ስካነር፣ ካሜራ፣ ሞባይል፣ ... አልተመለሱልንም ወይንም ከሕግ ውጭ ተወርሰዋል። በፍርድ ቤት ውሳኔ በነፃ የተለቀቅነው የድርጅቶቹ ባለቤቶችም የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥትና ሌሎች ሕጎች በአደባባይ ተጥሰው በዜግነታችን የመሥራት መብት ተከልክለንም እንገኛለን።
“ጉዳዩ በሀገሪቱ ሕግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቋጨ በመሆኑ እንጂ በዚያ መልክ ባይቋጭ እንኳን ድርጅቶቻችን በመፍረሳቸው፣ ሌላ ድርጅት እንዳናቋቁምም በመከልከላችን ቅጣቱን መክፈል አንችልም” የሚል ነው።
የክስ ፋይሉ በይቅርታ ሕጉ መሠረት መቋጫ በማግኘቱ፣ ተከሳሾቹ ድርጅቶች ፍርድ ቤቱ ያሳለፈውን የቅጣት ውሳኔም በመቃወም ይግባኝ አለማለታቸውን፤ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 4 ቀን 1999 ዓ.ም. የሰጠው የቅጣት ውሳኔ የድርጅቶቹን የመከራከር መብት ገድቦ የተላለፈ እና ሐምሌ 9 ቀን 1999 ዓ.ም. የተሰጠውም የቅጣት ውሳኔ ያንን መሠረት ያደረገ ቢሆንም፤ ጉዳዩ ሐምሌ 13 ቀን 1999 ዓ.ም. በይቅርታ ስለተቋጨና እነሱም ጉዳዩን በዚሁ መሠረት ያቆሙ መሆናቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
በመሆኑም የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በሁለቱ ድርጅቶች ላይ በሕግ የተደገፈ የሚያስፈጽመው ነገር ስለሌለ ፍ/ቤቱ መዝገቡን ዘግቶ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም ለቀረበው የመከላከያ ሃሳብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚሰጠውን ምላሽ ለመጠባበቅ ለሰኞ ታህሳስ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።



