በኢትዮጵያ ያሉ የግል ጋዜጦች በድምፅ አልባ መሣሪያ ተመቱ
Ethiopia Zare (ዓርብ ጥር 1 ቀን 2001 ዓ.ም. January 09, 2009)፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጋዜጦች የሚታተሙበት ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት፣ ወደ 12 በመቶ የሚሆን የዋጋ ጭማሪ አደረገ። በርካታ አሣታሚዎች ጭማሪው ፕሬሶችን “ወደ ጉድጓድ የሚከት ነው፣ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል” ብለዋል።
ባለፈው ሰኞ ዕለት ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት በጋዜጦች ማተሚያ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርግና የነፃው ፕሬስ ጋዜጦች ማክተሚያ ጊዜ መቃረቡን መዘገባችን አይዘነጋም። ዘገባውን ባስነበብን በማግስቱ ማክሰኞ ዕለት ማተሚያ ቤቱ ለጋዜጣ አሣታሚዎች በበተነው ደብዳቤ፣ የወረቀት ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ከጥር 1 ቀን 2001 ቀን ጀምሮ ጭማሪ እንደሚደረግ የሚያሳስብ ነው።
በየሣምንቱ ቅዳሜ የሚታተመው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ሠለሞን ገ/እግዚአብሔር ጉዳዩን አስመልክቶ እንደገለጸው፣ የኅትመት ጭማሪው በድርጅቱ ላይ የኪሳራ ሥጋት መፍጠሩን ነው።
ምክንያቱንም ሲያስቀምጥ በአዲስ አበባ ከተማ ተዘጋጅተው በመላው ኢትዮጵያ የሚሠራጩ ጋዜጦች የሚታተሙበት ብቸኛው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት፣ በተደጋጋሚ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉና በ2001 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ለመቋቋም ከባድ መሆኑን ነው። ባለፈው የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ ገፅ በመቀነስና ዋጋ በመጨመር የተቋቋሙት መሆኑን ገልፀው፣ ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት አማራጮችን መውሰድ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጿል።
ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ሀገራት የሚታተሙ ጋዜጦች የኅትመት ወጪያቸው 30 ከመቶ ብቻ መሆኑንና ሌላው 70 ከመቶ የሚሆነው ወጪ የሌሎች ነገሮች እንደሆነ ገልጾ፣ በኛ ሀገር ግን 60 ከመቶ የሚሆነው የኅትመት ወጪ ሲሆን፣ 40 ከመቶ የሚሆነውና አነስተኛ ወጪ በማብቃቃት እንደሚሠራ አብራርተዋል።
አሁን በተደረገው ጭማሪ የኅትመት ወጪው እየበዛ መሄዱ፣ ቀስ በቀስ ከጥቂት ጋዜጦች በስተቀር አብዛኞቹን ከገበያ እንደሚያስወጣቸው ጠቁመዋል። ስለዚህም ባላቸው መረጃ መሠረት የወረቀት ዋጋ እየቀነሰ መሄዱን ገልፀው፤ በዚህ ላይ ደግሞ የኅትመት ዋጋ ማለት ወረቀት ብቻ ባለመሆኑ ማተሚያ ቤቱ የወረቀቱን ዋጋ በሌሎች ነገሮች በማጣጣት ጭማሪውን ሊያስተካክል እንደሚገባ ጠቁሟል።
የፎርቹን ጋዜጣ ባለቤትና ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ታምራት ገ/ጊዮርጊስ በበኩሉ፤ ጋዜጣው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ ጋዜጣው ታትሞ በመሸጥ ከሚገኘው አትርፈውም ሆነ የኅትመት ወጪውን ሸፍኖ እንደማያውቅ ገልፆ፣ በቀጣዩ ሣምንት ስለሚታተመው ጋዜጣ በምሳሌ ሲያስረዳ፣ አንድ ጋዜጣ ለኅትመት ብቻ 8 ብር ከ20 ሣንቲም የሚያወጣ ሲሆን፣ ለአከፋፋይ የሚሸጥበት ዋጋ 2 ብር ከ40 ሣንቲም ነው። ጋዜጣው ገበያ ላይ ሲወጣ የሚሸጠውም በሦስት ብር ብቻ እንደሆነና፣ ጠቅላላ ወጪውን ከማስታወቂያ ከሚገኝ ገቢ እንደሚጠብቅ ጠቁሟል። እንዲህም ሆኖ የኅትመት ዋጋ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ከማስታወቂያ የሚገኘው ገቢ ኅትመቱን ደጉሞና ለዝግጅቱ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ሸፍኖ መቀጠሉ ለኪሳራ ሊዳርግ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለው አስረድቷል።
ምንጊዜም ዋጋ በጨመረ ቁጥር ኮፒ የሚቀንስ ሲሆን፣ ኮፒ ሲቀንስ ደግሞ አንድ ጋዜጣ የሚታተምበት ዋጋ ይጨምራል፤ በዚህም ምክንያት የኅትመት ዋጋ የተጠናከሩ ጋዜጦች ላይ የኪሳራ ሥጋት እንደሚፈጥር፣ ሌሎቹን ደግሞ ከገበያ ሊያወጣቸው እንደሚችል ገልጿል።
ብርሃንና ሠላምን የሚፎካከር ሌላ ማተሚያ ቤት ባለመኖሩ ወደየትም መሄድ እንደማይቻል ገልፆ፤ ብርሃንና ሠላም እንደ የሰው ኃይል፣ የማሽን፣ የቀለምና የመሳሰሉትን ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ ከቶና የወረቀት ዋጋ ጭማሪውን በነሱ በማጣጣት እንዲሁም በዓለም ላይ ያለውን የወረቀት መቀነስ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ጭማሪውን ሊያነሳ እንደሚገባ አሳስቧል።
የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ዐብይ ተ/ማርያም በበኩሉ፤ “የኢትዮጵያ ፕሬስ የራሱ የሆነ ኢኮኖሚክ አለው” ይላል። በሀገሪቱ ውስጥ ከሚታተሙ ጥቂት ጋዜጦች በስተቀር፣ የጋዜጦቹ ገቢ ከችርቻሮ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ኪሳራ የሚያስከትል ነው ብሏል።
በሌሎች ሀገራት ጠንካራ የሆነ የጋዜጣ ማስታወቂያ ባህል እንዳለ የሚናገረው ዐብይ፣ በኛ ሀገር ግን ድርጅቶች ማስታወቂያ ለማውጣት ከኅትመት ሚዲያው ይልቅ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው እንደሚያደሉ ያስረዳል።
ስለዚህም አብዛኛው የግል ሚዲያ እስካሁን የቆየው የኅትመት ዋጋው መጥፎ የሚባል ባለመሆኑ፣ በችርቻሮ ከሚያገኘው ትርፍ እያጣጣ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነት ተደራራቢ የዋጋ ጭማሪ ሲያገኘው ግን ፕሬሱ ሳይወድ በግድ ከገበያ ለመውጣት እንደሚገደድ አስረድቷል።
አዲስ ነገርን እንደምሳሌ ሲያስቀምጥ፣ ጋዜጣው ሲጀመር ከታሰበው የኅትመት ዋጋ አሁን 54 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና 33 በመቶ የሚሆነውን ዋጋ አንባቢዎቻቸው ላይ በመጨመርና ገፅ በመቀነስ፣ 21 በመቶውን ደግሞ ከትርፋቸው ላይ በማጠጣት እንደተቋቋሙት ይገልፃል።
በዚህ ላይ እንዲህ ዓይነት ጭማሪ ሲመጣ ያለው አማራጭ፣ ከሚጨመረው ዋጋ የተወሰነውን ሽርፍራፊ አንባቢዎች ላይ መጨመር እንደሆነና ይህ ሲደረግ ደግሞ አንባቢዎች እንደሚቀንሱ ወይም ደግሞ ኪሳራውን ወደነሱ በማዞር ሠራተኞቻቸው መቀነስ እንደሆነ ገልፆ፤ ይህ ደግሞ ጋዜጣው ጥራቱን ይዞ እንዳይቀጥል ስለሚያደርገው ሁለቱንም መንገዶች ቢጠቀሙ ጭማሪው ወደ ጉድጓድ ይዟቸው የሚወርድ መሆኑን ይገልፃል።
መንግሥት ማድረግ የሚገባውም ቀደም ሲል “ኒውጀርሲ” ውስጥ ተከስቶ የነበረውን በምሳሌ ሲያስቀምጥ፣ “ኒውጀርሲ ውስጥ የወረቀት ዋጋ በመጨመሩ፣ ትልልቆቹን ጋዜጦች ከገበያ የሚያስወጣበት ሁኔታ ተፈጠረ። በዚህን ጊዜም ጋዜጦቹ ተሰባስበው መንግሥትን “ኒውጀርሲ ጠቅላይ ፍርድ ቤት” ከሰሱት ክሱ፤ መንግሥት በወረቀት ላይ ቀረጥ በመጫን፣ በእጅ አዙር የመናገር ነፃነትን ተፃሯልና ቀረጥ ሊያነሳ ይገባል የሚል ክስ ነበር። ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ጭብጥ ስላመነበት፣ ከወረቀት ዋጋ ላይ ቀረጥ እንዲነሳ ወሰነላቸው” ብሏል።
ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም ሲመጣም እንደ ኢንተርኔት ያሉ አማራጭ የመረጃ ምንጮች በሌሉበት ሁኔታ፣ መንግሥት ጋዜጦችን፣ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፤ ስለዚህም የዲሞክራሲያዊ መብቶች አንዱ አካል የሆነው ፕሬሱ እንዳይጎዳ ከጋዜጣ ማሣተሚያ ወረቀት ላይ ቀረጥ ሊያነሳ እንደሚገባ ይጠቁማል።
የአውራምባ ታይምስ ም/ዋና አዘጋጅ ወንድራድ ደብረጽዮን በበኩሉ፤ ጋዜጣቸው መታተም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያሁኑ ጭማሪ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን ገልፆ፣ እስካሁን በነበረው ጋዜጣው ላይ ጭማሪ በማድረግ እንደቀጠሉ አስረድቷል። በዚህም እስካሁን አንባቢዎቻቸው እንዳላሳፈሯቸውና አሁንም ዋጋ በመጨመር ለመቀጠል እንደወሰኑ አስረድቷል። በዋጋ ጭማሪውም በተወሰነ ሁኔታ ኮፒ ሊቀንስ እንደሚችል አብራርቷል።
በርካታ ጋዜጦችን ላለፉት 10 ዓመታት አከፋፋይ የሆነው ፍቃዱ ማህተመወርቅ እስከዛሬ የነበረውን ልምድ ሲያካፍል፣ በአሁኑ ወቅት የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ተደጋጋሚ በመሆኑ እንዳለፈው ሁሉ አሁንም ከገበያ የሚያስወጣቸው ጋዜጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላካች ነው ብሏል።
ምክንያቱም የጋዜጣ መሸጫ ዋጋ በጨመረ ቁጥር፣ አንባቢው አቅም ስለማይኖረው ተከራይቶ ማንበብን ይመርጣል፤ ያ ደግሞ የኮፒ መቀነስ ያስከትላል፣ ኮፒ ሲቀንስ ደግሞ የአንድ ጋዜጣ የማሣተሚያ ዋጋ ስለሚጨምር ኪሳራውን መቋቋም የሚያቅታቸው ፕሬሶች ከገበያ ሊወጡ ይችላሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ይዳከማሉ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የንግድ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳሙ ኃይሌ በበኩላቸው ስለአሁኑ ጭማሪ ሲያስረዱ፤ በመስከረም ወር ላይ ወረቀት ሲገዙ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ ይህንኑ ለደንበኞቻቸው ማሳወቃቸውን ገልፀው፤ በዚህ መሠረት ከጥር 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ ማሳወቃቸውን አስረድተዋል። በመቶኛ ምን ያህል ጭማሪ እንደተደረገም ተጠይቀው ጅቡቲ ላይ የደረሰው ወረቀት ስላልገባ ጭማሪው ምን ያህል እንደሆነ ዛሬ (ዓርብ) ወይም ሰኞ እንደሚያሳውቁ አስረድተዋል። ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮም ጭማሪው ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ያነጋገራቸው በስደት የሚገኙ የነፃው ፕሬስ አባላት ድርጊቱን “ፕሬሱን በድምፅ አልባ መሣሪያ የመምታት ያህል ይቆጠራል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።



