የሕትመት ዋጋን በመጨመር ነፃው ፕሬስ ላይ ጥቃት ሊሰነዘር ነው

Ethiopia Zare (ሰኞ ታህሳስ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. January 05, 2009)፦ በመንግሥት የሚተዳደረው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ከጥር አንድ ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በጋዜጦች ላይ የሕትመት ዋጋ የሚጨምር ሲሆን፣ ከምርጫ 97 በኋላ የተቋቋሙት ጥቂት የፕሬስ ውጤቶች ከገበያ እንዲወጡ የሚያደርጋቸው መሆኑ ታወቀ። “ፕሬሱን ለማዳፈን የታለመ ነው” ተብሎ ተተችቷል።

 

የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት አስተዳዳሪዎችና ባለሥልጣናት “የዓለም የወረቀት ዋጋ ስለጨመረ” በሚል ሰበብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ የፊታችን ዓርብ ጥር 1 ቀን የሕትመት ዋጋ ሊጨምሩ መሆኑን ምንጮቻችን ጠቆሙ። የዓለም የወረቀት ዋጋ በአሁኑ ወቅት ያልጨመረ ቢሆንም፤ ይህ የመንግሥት የሆነው ማተሚያ ቤት “የዓለም የወረቀት ዋጋ ጨመረ” በሚል ሰበብ የሕትመት ዋጋ መጨመሩ የነፃው ፕሬስ ጋዜጦች ላይ ሆን ተብሎ የተቃጣ ጥቃት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልፀዋል።

 

ምርጫ 97ን ተከትሎ ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ በርካታ የነፃው ፕሬስ ጋዜጦች እንዳይታተሙና ሥራ እንዲያቆሙ ካደረገ በኋላ ጋዜጠኞቹንና አሣታሚዎቹን በመክሰስና በማሰር እንዲሁም ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ ማድረጉ አይዘነጋም። ከዚያም በተጨማሪ የፕሬስ ሥራ ፈቃድ መስጠት ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ለጥቂት ጋዜጦች ፈቃድ ተሰጥቷል።

 

ከእነዚህ ጥቂት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ከነበሩ ጋዜጦች ውስጥ ሁለቱ ባለፈው ነኀሴ ወር ላይ ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ባደረገው የ50 በመቶ የማሣተሚያ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ከገበያ ለመውጣት መገደዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

 

በዚህ ሣምንት ከዓርብ ጀምሮ በሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ለጊዜው ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ የተቻለ ባይሆንም፤ በጣት የሚቆጠሩትና ከምርጫ 97 በኋላ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሥራ የጀመሩት የነፃው ፕሬስ ውጤቶች በዚህ የዋጋ ጭማሪ ከገበያ እንደሚወጡ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ወገኖች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልፀዋል። ለጊዜው ምን ያህል የነፃው ፕሬስ ጋዜጦች ሊያቆሙ እንደሚችሉ የተረጋገጠ ነገር የለም።

 

ምናልባትም አንድ ሁለቱ ከተሳካላቸው ለአንባብያን የመሸጫ ዋጋቸውን በመጨመርና የቅጃቸውን ቁጥር በመቀነስ ገበያውን ለመቋቋም ሊሞክሩ እንደሚችሉ ለመረዳት ችለናል። ይህ ስትራቴጂም ቢሆን ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊያስገኝላቸው ይችላል ብሎ እንደማይታመን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ወገኖች ገልፀውልናል።

 

እነኝሁ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ፤ አሁን በገበያ ላይ ካሉት አዳዲሶቹ ጋዜጦች ውስጥ ብዙዎቹ በዚህ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ከሕትመት ውጪ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል። \

 

በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የነፃው ፕሬስ ወዳጆች “ፕሬሱን ለማዳፈን ሆን ተብሎ የታለመ ጥቃት ነው” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነውታል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ