የሕትመት ዋጋ 50% ጨመረ

ሁለት ጋዜጦች ከገበያ ውጭ ሆኑ

Ethiopia Zare (ኀሙስ ነኀሴ 29 ቀን 2000 ዓ.ም. September 04, 2008)፦ ከመስከረም ጀምሮ የዋጋ ጭማሪ ስለምናደርግ ተዘጋጁ ሲል ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ባለፈው ሣምንት ለደንበኞቹ በጻፈው ደብዳቤ ያሳውቃል። በሁኔታው የተደናገጡ ጋዜጦችም ምን ያህል ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል ለማወቅ ባደረጉት ጥረት 100% ሊሆን እንደሚችል ይነገራቸዋል።

 

የዋጋውን ጭማሪ ለማወቅ ወደ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በመሄድ ያጣሩት የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች እንደገለጹት በያዝነው ሣምንት 50% ጭማሪው የፀና ሲሆን፣ ሃያ ገጽ ባለው አንድ ነጠላ ጋዜጣ ላይ የ58 ሣንቲም ጭማሪ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል። ይህ ማለት የአንድ ጋዜጣ ማሣተሚያ ከ2 ብር ከ30 ሣንቲም ወደ 2 ብር ከ88 ሣንቲም ከፍ ያለ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት ጋዜጦች 48 ሣንቲም ኪሳራ ሲኖራቸው የ10 ሣንቲም ትርፍ ይኖራቸዋል።

 

በዚሁ የዋጋ ጭማሪ የተነሳ ሁለት ጋዜጦች ሣይታተሙ የቀሩ ሲሆን፣ አንዳንዶችም ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት መቀየራቸው ታውቋል። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለያዝነው ሣምንት የዋጋ ጭማሪ አዲስ ያስገባነው ወረቀት በውድ ስለተገዛ ነው የሚል ሲሆን፣ በቅርቡም 50% የነበረው ጭማሪ ወደ 100% እንደሚቀጥል ታውቋል።

 

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከስፖርት ጋዜጦች በስተቀር ብዛት ያላቸው ጋዜጦች የሚታተሙበት እንደመሆኑ መጠን ብዙ ጋዜጦች አደጋ ውስጥ ይወድቃሉ ያሉን አንድ አስተያየት ሰጭ፤ አቶ መለስ በአፍሪካ ሀገራት በአንድ ፓርቲ መንቀሳቀስን አስመልክቶ በቅርቡ ያቀረቡት ጽሑፍና ከሰሞኑ በአገዛዙ ታላላቅ ባለሥልጣናት ውይይት ከምርጫ 97 ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጋዜጦች መለየት ጋር ተያይዞ የመጣ በትንሹ የተጀመረውን ፕሬስ ድራሹን የማጥፋት እንቅስቃሴ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ