Teddy Afroበውጭ ሆኖ እንዲከራከር ጠየቀ

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ታህሳስ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. December 27, 2008)፦ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ሰው በመኪና ገጭቶ በመግደል እና የተገጨን ሰው ባለመርዳት በሚል ለቀረበበት ክስ፣ የተጣለበት የስድስት ዓመት እስር እና የ18 ሺህ ብር ቅጣት ተነስቶ፣ በነፃ እንዲሰናበት ያቀረበው ይግባኝ ለጥር 18 ተቀጠረ። የቀረበው ይግባኝ ውሳኔ እስኪያገኝም ድረስ፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ ታግዶ በውጭ ሆኖ እንዲከራከር እንዲወሰንለት የሚጠይቀውን አቤቱታ ዓርብ ገቢ አድርጓል።

 

አርቲስት ቴዲ በጠበቆቹ አማካኝነት፣ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው የይግባኝ ማመልከቻ፣ ለዓቃቤ ሕግ ደርሶት መልስ እንዲሰጥበት የታዘዘ ሲሆን፣ ጥር 18 ቀን በሚኖረው ቀጠሮ ሁለቱም ወገኖች ቀርበው በፍርድ ቤቱ የቃል ክርክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

በተጨማሪም በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ፤ ለጠቅላይ የቀረበው ይግባኝ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ እንዲታገድ የሚጠይቀውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ በጠበቆቹ አማካኝነት ትናንት ዓርብ ታህሳስ 17 ቀን ማስገባቱን ለማወቅ ችለናል።

 

አቤቱታው በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ አፈፃፀም ታግዶ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል የሚጠይቅ ነው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ