ወ/ት ብርቱካን ካለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ ተጠየቀ
በስዊድን የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ ማኅበር መግለጫ አወጣ
Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. January 02, 2009)፦ በስዊድን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የድጋፍ ሰጪ ማኅበር የወ/ት ብርቱካንን መታሰር አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ሊቀመንበሯ ካለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ ጠይቋል።
ማኅበሩ ባወጣው በዚሁ መግለጫው ኢህአዲግ በሠላማዊ መንገድ በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ሊታገል የተነሳውን የአንድነት ፓርቲን ደብዘ ለማጥፋትና ለማኮላሰት የሚፈጽመው የእብሪት ጥቃት እጅግ አሳዛኝና አስቆጪ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል።
መግለጫው የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎችን አቋም በአራት ነጥቦች ያስቀመጠ ሲሆን፣ “የህዝብ አደራና ኃላፊነትን የተቀበላችሁት የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባላትና ደጋፊዎች በደረሰው ሁኔታ ሳትናወጡና ሳትረበሹ የሠላም ትግሉንም ጥያቄ ውስጥም ሳታስገቡ የተቀነባበረ ሠላማዊ ትግል እንድታደርጉ” የሚል መልዕክት በሀገር ውስጥ ለሚገኙት የፓርቲው አመራሮች መልዕክት አስተላልፏል።
በስዊድን የሚገኘው የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ሰጪ ማኅበር ያወጣውን ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
የሠላም ዘንባባ በአምባገነኖች እሳት አይለበለብም
(ከስዊድን የአንድነት ድጋፍ ሰጪ ማኅበር)
አምባገነንነቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣው የኢህአዲግ መንግሥት የቅንጅትን መንፈስ አንግቦና የሠላም ዘንባባ አንጥፎ በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ሊታገል የተነሳውን የአንድነት ፓርቲን ደብዛ ለማጥፋትና ለማኮላሸት የሚፈጽመው የእብሪት ጥቃት እጅግ አሳዛኝና አስቆጪ ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህ እብሪተኛ መንግሥት የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በጎሣ በመከፋፈል መንግሥት አገዝ በሆነ ግፊት የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠር የኅብረተሰቡን ሠላማዊ ኑሮ ለማመሰቃቀሉ ያለፈው የአሥራ ሰባት ዓመት የአገዛዝ ቆይታው ምስክር ነው። በዚህም ምክንያት ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ድሃ ሊያሰኝ ከሚችል ኑሮ በታች እንዳይኖሩ እንኳን ተስፋቸው ተሟጧል።
ይሁን እንጂ እነዚህን መመሰቃቀልና ቀውሶች በሠላምና በመወያየት ለመፍታት በብሔራዊ ተቆርቋሪነት በመነሳት ልዩነትን አቻችሎ በመሥራት ሀገርን መለወጥ ይቻላል በሚል ተስፋ አያሌ የፖለቲካ ድርጅቶች ሠላማዊ ትግል መጀመራቸው አልቀረም። ከነዚህም አንዱ የቀድሞው ቅንጅት የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ነው። ሆኖም ገዢው መንግሥት በዚህ ፓርቲ ላይ በተለያዩ ጊዚያቶች የፈጸመበት የጥቃት ዘመቻ ሳያንስ የፓርቲውን ሊቀመንበር ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን አስሯል። በፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ላይ ድብደባ ፈጽሟል፣ በሌሎችም የአመራር አባላትና ደጋፊዎች ላይ የጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ተነሳስቷል። በመሆኑም እኛ በስዊድን የምንገኝ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች
1. ሊቀመንበሯ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በአውሮፓ ጉብኝታቸው ወቅት ያደረጓቸው ንግግሮችና ማብራሪያዎች በሙሉ ከሕግ ሙያቸው ብቃት አንፃር ትክክለኛና እውነተኛ በመሆናቸው ይህንን መናገርም ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ስለሆነ አለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ፣
2. አሁንም በኢትዮጵያ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው አስተማማኝ የሆነ መልካም አስተዳደርን እንዲሁም ድህነትን ለመቅረፍና ማኅበራዊ ዕድገትን ለመፍጠር የሚቻለው በሠላማዊ ትግል እንደሆነ ስለምናምን፤ የህዝብ አደራና ኃላፊነትን የተቀበላችሁት የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባላትና ደጋፊዎች በደረሰው ሁኔታ ሳትናወጡና ሳትረበሹ የሠላም ትግሉንም ጥያቄ ውስጥም ሳታስገቡ የተቀነባበረ ሠላማዊ ትግል እንድታደርጉ፣
3. ዛሬ በአንድነት ፓርቲ ላይ የደረሰውን ሕገ-ወጥ እርምጃ መላው ሠላም ወዳድ ሁሉ እንደራሱ ጥቃት ቆጥሮ በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኢህአዲግን የዘር ፖለቲካና የከፋፍለህ ግዛ መርኅን፣ ያለሕግ መታሰርን፣ ግድያንና አፈናን በመቃወም ለዓለም ኅብረተሰብ ለማሳወቅ በምናደርገው ጥረት ላይ ድጋፋችሁን እንድትሰጡን፣
4. ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ትላንት የመለያየትና የመተላለቅ ሴራ ሲፈጸምበት በአርቆ አሳቢነቱ በወገን ፍቅሩ ጸንቶ በማንኛውም እኩይ ተግባር እንዳልተሸነፈ ሁሉ አሁንም ከሠላም ታጋዮች ጋር አብሮ በመቆም ለነፃነቱና ለዜግነት መብቱ መከበር ትግሉን እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በስዊድን የአንድነት ድጋፍ ሰጪ ማኅበር
ታህሳስ 24 ቀን 2001 ዓ.ም.
ስዊድን



