Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. January 02, 2009)፦ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑትና የ34 ዓመቷ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታሰሩበት ያለፈው ሰኞ ታህሳስ 20 ጀምሮ ሁለት በሁለት በሆነ ክፍል ውስጥ ለብቻቸው የታሰሩ ሲሆን፣ ላለፉት አምስት ቀናት በረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ጠቆመ።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫ 97ን ተከትሎ በቅንጅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርነታቸው ወቅት የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው በሽምግልና መለቀቃቸው አይዘነጋም። የኢህአዲግ መንግሥት ተደርጎላቸው የነበረውን ይቅርታ በማንሳት የዕድሜ ልኩ ፅኑ እስራት እንዲፀናባቸው በመወሰን ያለፈው ሰኞ አዲስ አበባ ውስጥ ቃሊቲ ወደሚገኘው እስር ቤት እንዳወረዳቸው መዘገባችን አይዘነጋም።

 

ወ/ት ብርቱካን ቃሊቲ ከታሰሩበት ከሰኞ ዕለት ጀምሮ የረሃብ አድማ ላይ ሲሆኑ፣ ቤተሰቦቻቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በረሃብ አድማ ላይ እንደነበሩ አያውቁም ነበር። ቤተሰቦቻቸው የሚያደርሱላቸውን ምግብ ስለማይበሉት እስከዛሬ ቤተሰቦቻቸው ምግብ ቋጥረው የወሰዱላቸው የምግብ ዕቃዎች ለቤተሰቦቻቸው ባለመመለሱ ምክንያት የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ቤተሰቦች ወይዘሪቷ በረሃብ አድማ ላይ መሆናቸውን እንዳወቁ ለመረዳት ችለናል።

 

በዚሁ በረሃብ አድማው ምክንያት የወ/ት ብርቱካን ጤና በመልካም ሁኔታ ላይ እንደማይገኝ ለማወቅ ችለናል። የአዲስ አበባ ወሕኒ ቤቶች አስተዳደር ባለሥልጣናት ወ/ት ብርቱካንን ለማነጋገር የሞከሩ ቢሆንም፤ ከረሃብ አድማቸው እንዲታቀቡ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካላቸውም።

 

ሰኞ ዕለት ወ/ት ብርቱካን የታሰሩት ለብቻቸው አንዲት ጠባብና ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር በምትሆን ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ በዚያች ክፍል ውስጥ ከዚህ በፊት የአቶ ክንፈ ገብረመድህን ገዳይ ሻለቃ ፀሐዬ ወልደሥላሴ ታስረውበት የነበረ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል።

 

በ1993 ዓ.ም. የህወሓትን (ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) ለሁለት መሰንጠቅ ተከትሎ፤ የህወሓት ነባር ታጋይ የነበሩት ሻለቃ ፀሐዬ ወ/ሥላሴ፣ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባል የነበሩትንና የኢህአዲግ መንግሥት የደህንነት ኃላፊ የነበሩትን አቶ ክንፈ ገ/መድህንን ግንቦት 4 ቀን 1993 ዓ.ም. መግደላቸው አይዘነጋም። ሻለቃ ፀሐዬ ወ/ት ብርቱካን በታሰሩበት ክፍል ውስጥ ታስረው በነበሩበት ወቅት በክፍሉ ውስጥ የሚፈጠረውን ሙቀት መቋቋም እያቃታቸው ይጮሁ እንደነበርና፤ አልፎ አልፎ ከክፍሉ እንዲወጡ ይደረግ እንደነበር ለማወቅ ችለናል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ