በወ/ት ብርቱካን እስር ዙሪያ የተጠናከረ ዘገባ
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ወ/ት ብርቱካንን እንዳይጎበኝ ተከለከለ ወ/ት ብርቱካን የታሰሩት የአንድነት ፓርቲን እንቅስቃሴ ለማዳከም ታስቦ ነው የእንግሊዝ ኤምባሲ የወ/ት ብርቱካን እስር እንዳሳሰበው ገለፀ “የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 21 ሊከበርላቸው ይገባል” አቶ አበበ ወርቄ የኢሰመጉ ሊቀመንበር መድረክ የወ/ት ብርቱካንን መታሰር አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ |
Ethiopia Zare (ሰኞ ጥር 4 ቀን 2001 ዓ.ም. January 12, 2009)፦ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እናት የ72 ዓመቷ ወ/ሮ አልማዝ ገ/እግዚአብሔር፣ “በሕግ ስለተያዘው ጉዳይና ስለፖለቲካ የማውቀው ጉዳይ የለኝም፤ ግን ለሌላው እንደተፈቀደው ለልጄም ሰው ገብቶ እንዲጠይቃት ይፈቀድልኝ” ሲሉ መንግሥትን ተማፀኑ።
ወ/ሮ አልማዝ ገ/እግዚአብሔር እንደገለፁት፣ ወ/ት ብርቱካን መታሠሯን ከሰሙበት ሰኞ ታኅሳስ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. ማግስት ጀምሮ፣ ምግብ እየያዙ ቃሊቲ ወደሚገኘው ማረሚያ ቤት ሲሄዱ መቆየታቸውን ገልፀው፣ ነገር ግን ቅዳሜ ታኅሳስ 25 ቀን 2001 ዓ.ም. እሳቸውና የወ/ት ብርቱካን የአራት ዓመት ሕፃን ልጅ የሆነችው ሐሌ ሚደቅሳ ብቻ እንዲገቡና እንዲጠይቋት በተፈቀደው መሠረት፣ ሣምንቱን ሙሉ ሲያስገቡ የነበረው ምግብ እንዳለ እንደተመለሰላቸው ተናግረዋል።
በዕለቱም ይዘውት የነበረውን ምግብ አልቀበልም በማለቷ ፈሳሽ ነገር ብቻ ሰጥተዋት እንደተመለሱ ገልፀው፣ በማግስቱ እሁድና ከትናንት በስቲያ በዋለው የገና በዓል ብቻቸውን ገብተው እንደጠየቋት አስረድተዋል።
የሚገቡበትና የሚጠይቁበት በር የተለየ መሆኑንና፣ የታሰረችውም ለብቻዋ በቆርቆሮ በተከለለች እስር ቤት መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ አልማዝ፣ “የገባችባትን ነገር እንድትተውልኝ ደጋግሜ ነግሬያታለሁ፤ እኔ ትምህርትም እውቀትም የለኝም። ስለሕግና ፖለቲካ አላውቅም፤ ነገር ግን ለሌላው እስረኛ እንደተፈቀደው ሁሉ ለልጄም ሰው ገብቶ እንዲጠይቃት ይፈቀድልኝ” ሲሉ መንግሥትን ተማጽነዋል።
ሊጠይቋት ሲገቡ በአካሏ ላይ የመዳከምም ሆነ የመረበሽ ምልክት እንዳላዩባት የሚናገሩት ወ/ሮ አልማዝ፣ እሳቸው ግን ሰውነታቸው ከመንቀጥቀጥና ከመደናገጥ ውጭ ተረጋግተው ሊያናግሯት እንዳልቻሉ ይገልፃሉ። “ለሊትና ቀን እንቅልፍ የለኝም። ሳለቅስ ውዬ ሳለቅስ ነው የማድረው” የሚሉት ወ/ሮ አልማዝ፣ “የሚመለከተውን አካል እንደው በባንዲራው ይዣለሁ፣ ቢያንስ ለአራት ዓመት ልጇ ሲል እንደማንኛውም እስረኛ ሰው ገብቶ እንዲጠይቃትና ከሰው ጋር ተቀላቅላ እንድትጫወት ይፈቀድልኝ ሲሉ” በእንባ በታጀበው ንግግራቸው ተማጽነዋል።
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ወ/ት ብርቱካንን እንዳይጎበኝ ተከለከለ
የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ “የፓርቲያችን ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እስካሁን በቀጠሉበት የረሃብ አድማ የተነሳ በሕይወት የመቆየታቸው ዕድል አጠራጣሪ ሆኖብናል” ሲሉ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል። የሊቀመንበሯ መታሰርም የፓርቲውን እንቅስቃሴ ለማዳከም ታስቦ ነው ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን ገልፀዋል።
ሊቀመንበሯን እያደረጉት ባለው የረሃብ አድማ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎሳቆሉ አድርጓቸዋል የሚሉት ዶ/ር ኃይሉ፤ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር እንዲጎበኛቸው ቢጠይቁም እንዳልተፈቀደላቸውና እንደተከለከሉ አክለው ገልፀዋል።
ወ/ት ብርቱካን የታሰሩት የአንድነት ፓርቲን እንቅስቃሴ ለማዳከም ታስቦ ነው
ፓርቲያቸው የሊቀመንበሯን መታሰር አስመልክቶ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መሆኑንና ሃያ አባላት ያለው አራት ኮሚቴ ማቋቋሙን የገለጹት ዶ/ር ኃይሉ፤ የፓርቲው የዲፕሎማሲና የዲያስፖራ ኮሚቴ ዲፕሎማቶችንና ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እያነጋገረ መሆኑን፣ በውጭ ሀገር የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማትንና በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን እና በውጭ ሀገር የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያ የሆኑ ወገኖችን እያስተባበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከዚህም ሌላ በፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና የሕግ ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊው በዶ/ር ያዕቆብ የሚመራው የሕግ ጉዳይ ኮሚቴ ከሊቀመንበሯ መታሰር ጋር በተያያዘ ከሕግ አንፃር በጉዳዩ ላይ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች በማጥናት ላይ እንደሆነና፤ የሚደርስበትን ውሳኔ ይፋ እንደሚያደርግ ዶ/ር ኃይሉ ገልፀዋል።
ሌላው ደግሞ የተቋቋመው በኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የሚመራውና የማኅበራዊ ጉዳይ ኮሚቴ ሲሆን፣ ይኸው ኮሚቴ በፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅ የሚመራውን የሽምግልና ቡድን አባላትን የሚያነጋግርና የወ/ት ብርቱካንን ቤተሰብ እንዲከታተል መወሰኑን ገልጸዋል። ፓርቲያቸው የይቅርታ ዕድሉ የሕግ ሂደትን ባልጠበቀ መንገድ እየተሰረዘ ባለበት ወቅት በዝምታ የሚመለከተው ባለመሆኑ ይህንን ኮሚቴ ማቋቋሙን አመልክተዋል። የህዝብ ግንኙነቱም ያለውን ሁኔታና ሂደቱን እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ዶ/ር ኃይሉ አስረድተዋል።
ፓርቲው ሕጋዊ ፈቃድ ካገኘበት ጊዜ እንስቶ በመላው ኢትዮጵያ ቢሮዎችን የመክፈትና የማደራጀት ሥራው በወ/ት ብርቱካን መታሰር ለጊዜው ቢስተጓጎልም፤ በቅርቡ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ዶ/ር ኃይሉ ገልፀዋል። ዶ/ር ኃይሉ የወ/ት ብርቱካንን የታሰሩት የፓርቲውን እንቅስቃሴ ለማደከም ታስቦ እንደሆነ ፓርቲያቸው እንደሚያምን አልሸሸጉም።
የእንግሊዝ ኤምባሲ የወ/ት ብርቱካን እስር እንዳሳሰበው ገለፀ
በአዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት መዳረጋቸው እንዳሳሰበው አስታውቆ፣ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።
ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በመሃከላቸው ያለውን ችግር ተቀራርበው በውይይትና በመደራደር እንዲፈቱ የእንግሊዝ መንግሥት እንደሚፈልግ የገለጹት ጌቨን ኩክ የተባሉት የኤምባሲው የፖለቲካና የመረጃ ጉዳይ ኃላፊ ናቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን፣ ህዝቧ ሃሳቡን የመግለጽ፣ በኑሯቸውና በሀገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ ሆነው ማየት እንግሊዝ እንደምትፈልግና በኢትዮጵያ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ የተቻላትን እንደምታደርግ የሥራ ኃላፊው ገልጸዋል።
“የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 21 ሊከበርላቸው ይገባል” አቶ አበበ ወርቄ የኢሰመጉ ሊቀመንበር
የኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበበ ወርቄ የወ/ት ብርቱካንን ቃሊቲ እስር ቤት ለመጠየቅ የሄዱ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዳይጠይቁ መከልከልን አስመልክቶ “የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 21 ሊከበርላቸው ይገባል” ማለታቸው ታወቀ።
ከወ/ት ብርቱካን ወላጅ እናት ወ/ሮ አልማዝ ገ/እግዚአብሔር እና ከልጃቸው ሐሌ ሚደቅሳ በስተቀር ወደታሰሩበት ቃሊቲ እርስ ቤት ሊጠይቋቸው የሄዱ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ አመራር አባላት፣ ደጋፊዎችና ወደጅ ዘመዶች እንዳይጠይቋቸው መከልከላቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።
የሕግ ባለሙያና የኢሰመጉ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበበ ወርቄ በእስር ላይ ለሚገኙት ለወ/ት ብርቱካን እንዲከበርላቸው የጠየቁት የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 21 ንዑስ ቁጥር 2፤ “በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች፤ ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጐበኟቸው ዕድል የማግኘት መበት አላቸው” የሚለው እንደሆነ ታውቋል።
መድረክ የወ/ት ብርቱካንን መታሰር አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ
በሌላ በኩል መንግሥት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ፣ ከኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት (ኢዲኃኅ)፣ ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዲን)፣ ከዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት (ዓረና)፣ የሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት (ሶዲኃቅ) የተባሉ መድረክን የፈጠሩ አራት ፓርቲዎች በጋራ በወጡት መግለጫ ወ/ት ብርቱካን ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።
በዓለም ላይ በየትኛውም ሀገር ያሉ የፓርቲ መሪዎች፣ በተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ፓርቲያቸውን ወክለው አስተያየቶችን፣ መግለጫዎችን እንደሚሰጡ የገለፀው የመድረኩ መግለጫ፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር የሆኑት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳም፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪ እንደመሆናቸው በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ፖለቲካዊ አስተያየቶች መስጠት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ መሠረትም የቀድሞው ቅንጅት አባላት (እሳቸውን ጨምሮ)፣ መንግሥት ባደረገላቸው ይቅርታ ስለተፈቱበት ሁኔታ እንዲሁም የይቅርታው ጥያቄ ስለቀረበበት አግባብ ሲጠየቁ የማብራራትና መልስ የመስጠት ሕገመንግሥታዊ መብት እንዳላቸው እናምናለን ብሏል።
መግለጫው አክሎም “ወ/ት ብርቱካንም በውጭ ሀገር ባደረጉዋቸው ስብሰባዎች በመንግሥት ይቅርታ መፈታታቸውን እንዳልካዱ በሀገር ውስጥ ለሚታተሙ የመገናኛ ብዙኃን ከሰጡት መልስ ላይ ለመረዳት ችለናል። በተጨማሪም መንግሥት የቀድሞው ቅንጅት አመራሮችንና አባላትን በይቅርታ ሲፈታ ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አፍርሰዋል በማለት ማረጋገጫ እንዲሰጡ በተጠየቁበትም ወቅት፣ መንግሥትንና ህዝብን ይቅርታ ጠይቀው መፈታታቸውን እንዳልካዱና እንደማይክዱ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አስረድተው መመለሳቸውን የሚገልጽ ዜና በተለያዩ የዜና አውታሮች ላይ ተጽፎ ተመልክተናል። በመሠረቱ በቀድሞው የቅንጅት አመራርና አባላት ላይ የተመሰረተባቸው ክስ “ሕገመንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል የመለወጥ ሙከራ አድርገዋል” የሚል እንደነበረ ሲታወቅ፣ ይቅርታ የተደረገላቸውም በዚሁ የወንጀል ክስ በተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ላይ መሆኑ አይዘነጋም።” ሲል የመድረክ መግለጫ ዘርዝሯል።
በመቀጠልም “ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዳግም በተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት ላይ ተሰማርተው እስካልተገኙ ድረስ፣ በውጭ ሀገር በተደረገ ስብሰባ፣ የይቅርታ ጥያቄው ስለቀረበት ሁኔታ ከተናገሩዋቸው ዓረፍተ ነገሮች አንድ ሐረግ መዞ “ይቅርታ አልጠየኩም” ብለዋል በሚል ምክንያት ይቅርታው ተሰርዞ እንደገና ለዕድሜ ልክ እሥራት መዳረጋቸው እጅግ አሳስቦናል። ይህ የመንግሥት እርምጃ በሀገራችን ውስጥ የተረጋጋ ሠላማዊ የፖለቲካ ውድድር የሚካሄድበት ሁኔታ መፍጠር፣ ወሳኝ በሆነበት በአሁኑ ወቅት በመወሰዱ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሳሳቢ ሁኔታ እየጠበበ የመጣውን የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ምህዳር ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይከተው ከፍተኛ ስጋት አሳድሮብናል። ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ወ/ት ብርቱካንና አብረዋቸው የነበሩት ዜጎች በተያዙበት ሰዓት ተወሰደ የተባለው ሕገ-ወጥ የኃይል እርምጃ ያደረሰው እንግልትና ጉዳት ነው። በዚህ ረገድ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ተይዘው ሕግ ፊት መቅረብ ካለባቸው በሕጉ አግባብ ከፍ/ቤት የመያዣ ትዕዛዝ አውጥቶ መሆን ሲገባ፣ ማንነታቸውን ባላሳወቁ እና ሕጋዊ መጥሪያ ባላሳዩ ኃይሎች ተገደው እየተንገላቱ መወሰዳቸው፣ የሕግ የበላይነትን የጣሰና በብዙ ወገኖች ዘንድም ስጋት የጫረ እርምጃ መሆኑ በሀገራችን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ ያደርገዋል” ሲል የፓርቲዎቹ መግለጫ ያመለክታል።
ይኸው የመድረክ መግለጫ በማጠቃለያው “መንግሥት ካለበት የዜጎችን መብት የማስጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ፣ ውሳኔውን እንደገና መርምሮ እና አጢኖ የተሰረዘው የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይቅርታ ውድቅ ሆኖ ቀደም ሲል የተሰጣቸው ይቅርታ ፀንቶ ከወህኒ እንዲለቀቁ እንዲያደርግ አበክረን እንጠይቃለን” ሲል የአራቱን ፓርቲዎች ማኅተም አያይዞ መግለጫውን በትኗል።
“ሰው ገብቶ እንዲጠይቃት ይፈቀድልኝ” ወ/ሮ አልማዝ ገ/እግዚአብሔር የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እናት 


