የቫንኩቨር ነዋሪዎች የሻማ ማብራት ስነሥርዓት አካሄዱ
ወ/ት ብርቱካንና ሌሎች የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቀዋል
Ethiopia Zare (ሰኞ ጥር 25 ቀን 2001 ዓ.ም. February 2, 2009)፦ የቫንኩቨር ካናዳ ነዋሪዎች በቃሊቲ እስር ቤት 37ኛ ቀን የሆናትን የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርን ጨምሮ ሌሎች የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ በመጠየቅ በከተማዋ እምብርት በሆነው ሮብሰን ስትሪት በመሰባሰብ የሻማ ማብራት ስነሥርዓት አካሄዱ። ለህሊና እስረኞቹም አጋርነታቸውን በማሳየት በየሀገራቱ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩበት ቦታ ላሉ የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ በመሄድ የእስረኞቹን ሁኔታ እንዲያስረዱ ባወጡት መግለጫ ጥሪ አቀረቡ።
ብርቱካን፡ እውነትም “ብርቱ ካህን”
ይህንን በተለይ በሴቶች ተሳትፎና በስላማዊ ትግሉ ላይ የተቃጣውን የእብሪት ጡጫ አጥብቀን እናወግዛለን!!
አምርረን አዝነናል፦ ቫንኩቨር፡ የብርቱካንን መታሰር በሰማች ግዜ አምርራ አዝናለች። እነሆ ብርቱካን ከታሰረች ዛሬ 36ኛ ቀኗን ያዘች። ከቃሊቲ አልነበርንምና ሲበርድ ከሚቆረጥመው፡ ሲሞቅም ከሚለበልበው የቆረቆሮ እስር ቤት ለብቻ መዘጋት ምን ያህል ሞራልን እንደሚነካ፡ ምንስ ያህል ስሜትን እንደሚጎዳ ልንስለው አይቻለንም። በዚህ ቅጽበት፡ ሁላችሁም በአይነ ህሊናችሁ አስር ሺህ ማይሎች ተጉዛችሁ ብርቱካንና ሌሎች መሰል የህሊና እስረኞችን ታስቧቸው ዘንድ ይሁን።
ፈተና የበዛበት ፈተና የዚህች ለሁለተኛ ግዜ ከእስር ቤት የተዘጋባት ታላቅ ሴት የስላማዊ ትግል ጉዞ ቀላል አልነበረም። ሰላማዊ ትግሉን በሚጠራጠሩ ወዳጆችም ለስላማዊ ትግሉ ባላደሩጠላቶችም የተፈተነ እንጂ። የሚያስሩ፡ የሚገድሉ፡ የሚያሰድዱና አካል የሚያጎድሉና ለራሳቸውም ህግ የማይገዙ አምባግነኖችን በሰላማዊ መንገድ እንፋለማለን፡ በኢትዮጵያም ከጠብ-መንጃ መለስ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እናመጣለን፡ ብሎ መነሳት ቀላል አልነበረም። የሚከፍቷቸው ቢሮዎች ቢዘጉ፡ የሚጠሯቸው ስብሰባዎች ቢስተጓጎሉ፡ የሰበሰቧቸው ሰዎች ቢታሰሩም፤ ብርቱካንና የተቀረው የአንድነት አመራር፡ ከአምባግነንነት ጋር የተጋቡትን እልህ በሰላም ብቻ እንጂ ያለ አመጽ ከመታገል ወደኋላ አላሉም።
ይቅርታው ያኔ በ2007 ዓ.ም፡ ከሀያ ወር እስራት በኋላ ከእስር ሲፈቱም ይሁን ከተፈቱ በኋላ ወ/ት ብርቱካንም ይሁን የትግል አጋሮቿ በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቅው መውጣታቸውን፡ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመታገል ያላቸውን እምነት ከመግልጽ አልቦዘኑም። በአውሮፓ ጉዟቸውም ወቅት ስለ ይቅርታው አስጣጥ ሂደት አጥብቀው ለሚጠይቁ ታዳሚዎችም የይቀረታውን ሂደት ለማብራራት ሞከሩ እንጂ ይቅርታ መጠየቃቸውን አልካዱም። ከዚያም ለጥቃ፡ ወ/ት ብርቱካን “በሶስት ቀን በአውሮፓ ሀገራት አድርገሽው የነበረውን ንግግር የሚያስተባብል እርማት ካላደረግሽ፤ ይቅርታ ተደርጎልሽ የነበረው ተነስቶ እስር ቤት ትገቢያለሽ" የሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በተሰጣት ጊዜ በጻፈችው “ቃሌ” የተሰኘ መጣጥፍ ይቅርታ መጠየቋን ከቶም አልካደችም።
ይቅርታ ይቅርታ ነው ስለ ይቅርታው ሂደት ሽማግሌዎች አንድ ነገር ኢህአዴግም ሌላ ነገር ቢል፤ ወ/ት ብርቱካንም እንዲሁ ሌላ ማብራሪያ ብትሰጥ መቀበል አለመቀበል እንጂ በምንም መልኩ ይቅርታን ሊያስነሳ የሚችልና የእድሜ ይፍታህ ቅጣትን ሊያመጣ የሚችል አልነበረም። የሆነ ሆነና የሴቶች ተሳትፎ በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች አናሳ በሆነበት አገር አንዲት ሁላችንንም ያኮራች የአራት አመት ህጻን ልጅ እናት የ72 ዓመት ባለጸጋ ባልቴት እናቷን ጧሪ፤ ጎበዝ ሴት ብትነሳ እሷንም ከእስር መክተት እጅግ አሳዝኖናል።
ታስሮ የሟሟ የለም ብርቱካንም ከእስር ብርቱ ካህን ሆና ትወጣለች እንጂ አሳሪዎቿ እንደሚያስቡት አትሟሟም። ደግሞስ ብርቱካን ብትታሰር በቅሌት አይደለም። በስርቆትም አይደለም። በሙስናና በዝርፊያም አይደለም። ለመብቷና ለእውነት ለኢትዮጵያዊያን መብትም ባደረገችውና በምታደርገው ተጋድሎ እንጂ። ብርቱካንም ትሁን ጓደኞቿ የማንንም ዘር ለማጥፋት አልተነሱም። በዘር ማጥፋት ወንጀል መከሰስ ካለበት፤ መከሰስ ያለበት ራሱ ኢህአዴግ ነው። የዘርና ብሄር ፖለቲካ ወደአገራችን ያስተዋወቀ ዘረኛ መንግስት። ራሱ ባመጣው ጣጣ ሳትጠለፍ፡ እነሆ ዘርንና ብሄርን ተራምዳ ኢትዮጵያዊነትን የምታራምደውን ብርቱካንን በዘር ማጥፋት ከሶ አዎን አጥፍቻለሁ በይ ብሏት ሲያበቃ እንደገና ደግሞ አሁንም ድገሚው፡ ያለበለዚያ ትገቢያታለሽ ማለት የጥጋብ ሁሉ ቁንጮ ነው። አሁንም በፊትም ብርቱካን መታሰሯን የምታውቅ እስረኛ ነች። ይሄ እስራቷም የትግል አጋሮቿን ሊያታግል፤ እኛን ሊያስተባብር ይችላል እንጂ ፈጽሞ ወደ ኋላ አይዘንም።
ይሄ የትግሬዎች አይደለም… መሰል የህሊና እስረኞችም ብርቱካንም ብቻ አይደለችም፡ በዚህ ሰአት፡ ያለአግባብ የታሰሩት እነ አቶ በቀለ ጅራታ፡ እነ ቴዲ አፍሮ እና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን እንዲፈቱ ሌት ተቀን እንታገላለን። ይሄ የቅንጅት ጉዳይ አይደለም። ይሄ የአንድነትም ብቻ አይደለም። ይሄ የኢህአዴጎችም ጭምር ነው። ይሄ የሴቶች ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ ልጆች ያላቸው ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ የእናቶች ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ የክርስቲያኖች ብቻ አይደለም። ይሄ የእስላሞችም ብቻ አይደለም። ይሄ የኦሮሞዎች ብቻም አይደለም። ይሄ የአማራዎችም አይደለም። ይሄ የኢትዮጵያዊያን ብቻም አይደለም። ይሄ የሂላሪ ክሊንተንም ነው። አልልላት ብሎ እንጂ ይሄ የአቶ መለስ ባለቤት የሀዜብ ጎላም ጭምር ነው። እንግዲህስ ይህቺ ስለኢትዮጵያዊነትና ስለፍቅር ስለእኩልነትና ስለሰብአዊነት እንደ ነቢይ ልትተነብይ፤ እንደ አዳኝም ልትሰዋ የተዘጋጀች ሴት ተስፋዋ ማነው? እኛ አይደለንምን?
ልጇንና እናቷን አደራ፤ ብንረሳሽ ቀኛችን ትርሳን ስልካችሁን አንሱ፡ ወደ ኮምፒውተራችሁ ሂዱ፡ ባካባቢያችሁ ለሚገኙ የተወካዮች ምክርቤት ወይንም ሴኔት ወይንም ኮንግረስ፡ ወይንም ፓርሊያሜንት አባላት ደውሉና የሆነውን ንገሯቸው። ስለፍቅርና ሰላም የቆመች አንዲት ምስኪን ሴት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪ ታሰረች በሏቸው። በዚህ ሰልፍም ስለተገኛችሁ ብድር ይግባችሁ። ደጋግመን እንሰለፍ። ባንድ ሌሊት ባንድ ቀን ሰልፍ ባንድ ስልክ ጥሪ የሚመጣ ለውጥ አይኖር፡ ብርቱካንም አትፈታ ይሆናል። ግን የምንፈልገው ትልቁ ለውጥ የምናደርጋቸው ትንንሽ ድርጊቶች ጥርቅምና ውጤት ነው። ባንሰለፍም ዝም ብንልም ግን አንድ ነገር ርግጥ ነው። ከዚህ በኋላ ማስመሰል አንችልም። ፕሮፌሰር መሳይ እንዳለው “እሷም እስር ቤት ገባች እኛም የተለመደ ህይወታችንን እንቀጥል ይሆናል። ነገር ግን ብርቱካን ውስጣችን ነች። በምንም መልኩ ያሳየችውን አኩሪ ጀግንነት ልንረሳው እንዳላየ ልናልፈው አይቻለንም። ሁላችንንም የምትኮሮኩር. በአፏ ሳይሆን በስራዋ፤ በጪኸቷ ሳይሆን በኩራቷ የምትናገር የምትፈታተን፣ የማትፈራ የምታኮራ መሪ ነች። ብርቱካን ኮራንብሽ።
በብርቱካን መታሰር ያዘኑ፣ የተከፉ፣ የቫንኩቨር ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን፡ Feberuary 1st 2009, Vancouver, Canada



