የቫንኩቨር ሴቶች ብርቱካንን አልረሷትም

Ethiopia Zare (ሰኞ የካቲት 02 ቀን 2001 ዓ.ም. February 9, 2009)፦ ትናንት እሁድ ፌብርዋሪ 8 ቀን በቫንኩቨር ካናዳ የሚኖሩ ሴቶች ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እናትና ለሕፃን ልጇ መርጃ ይሆን ዘንድ ባዘጋጁት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ምሽት አምስት ሺህ የካናዳ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አሰባሰቡ።

 

 

በቦታው ብዛት ያላቸው ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን፡ ሦስት በከተማው ነዋሪ የሆኑ አርቲስቶች የሳሏቸው ስዕሎች ለሽያጭ ቀርበው ከ300 እስከ 1000 ዶላር ከመሸጣቸውም በላይ የወ/ት ብርቱካን ልጅ ሐሌ ሚደቅሳ ለእናቷ ስትፀልይ በአጋጣሚ የተነሳችውን ፎቶግራፍ አንዲት የሐሌ እኩያ የሆነች ሕፃንና አባቷ 400 ዶላር በጨረታ አሸንፈው ወስደዋል።

 

በሰብዓዊነት ተነሳስተው የወ/ሪቷን ቤተሰቦች ለመርዳት የተሰባሰቡት እነኝሁ ሴቶች ባቀረቡት የመግቢያ ንግግር ላይ፤ “ይሄ ከቀጥተኛና ድርጅታዊ ፖለቲካ የፀዳ ዝግጅት ዓላማው ግልጽና አንድ መሆኑን፤ የቤተሰቧ ብቸኛ አስተዳዳሪ ያለአግባብ ለእስር በመዳረጓ ምክንያት የእናቷና የልጇ ሁኔታ በእጅጉ ስላሳሰበን የገንዘብ ማሰባሰብ ምሽቱን ለማድረግ ተነሳስተናል” ሲሉ ገልጸዋል።

 

የሴቶቹን የገንዘብ ማሰባሰብ ምሽት በሚመለከት "ይህ በሀገሪቱ ውስጥ በፖለቲካም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳይ፣ በሰብዓዊ መብትም ይሁን በተራድዖ በሀገር ቤት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ሞራል በእጅጉ የሚገነባና አለኝታነትን የሚያሳይ ተግባር ነው" ሲሉ አንዳንድ አስተያት ሰጭዎች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልፀዋል።

 

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም “ይህ የቫንኩቨር ነዋሪ ሴቶች ተግባር ድምፃቸው ለማይሰማውና ላንቀላፉት፤ ነገር ግን አያሌ ሴቶች ለሚገኙባቸው ከቅርብ እንደ ሲያትል ላሉ ጎረቤት ከተሞች፣ ከሩቅ ደግሞ እንደ ዲሲ፣ ዳላስ፣ ቦስተን፣ ቺካጎ፣ አትላንታና ሌሎችም፤ ታላቅ የአሜሪካና የአውሮፓ ከተሞች አርኣያ ከመሆናቸውም ሌላ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረገው የዲሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለፍትህ የበላይነት መረጋገጥ ለሚደረገው እንቅስቃሴ አጋዥ ነው” ብለው መልካም ምሳሌነታቸውን መስክረዋል።

 

ይሄንን ዝግጅት ከማናቸውም ፖለቲካ የፀዳ ለማድረግ ነበር የቫንኩቨር ሴቶች የመጀመሪያ ዕቅድ። ነገር ግን ሃሳብ እንዲሰጡ ዕድል ሲሰጣቸው በስፍራው የተገኙት ሁሉም ሴቶች ስሜታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ነበር። መድረኩ ባንድ በኩል ያሳዝን፣ ያስለቅስ በሌላ በኩልም ያስደስት ነበር።

 

አንዲት የ5 ዓመት አካባቢ ሕፃን ልጅና ወላጇ የብርቱካንን ልጅ “የሐሌ”ን በአጋጣሚ የተነሳችውን ጉርድ ምስል በአራት መቶ ዶላር ተጫርተው ሲገዙና ሕፃኗም የሐሌን ስሜት ስትጋራ ማየት ያስደስት ነበር። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሰው የአክሱም፣ የላሊበላና የጎንደር ኃውልቶችና ህንጻዎች በአንድ ሺህ ያለጨረታ ሲገዙ መመልከት ተስፋ ይሰጣል።

 

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች አስተያየት ሲሰጡ የነበረ ሲሆን፤ የብርቱካን መታሰር እንደ እግር እሳት የፈጃት አንዲት ኢትዮጵያዊትና በዚያኑ ምሽት ወላጅ አልባ ለሆኑ ሕፃናት መድኃኒቶችን ለመላክ ስታስተባብር የዋለች ድንቅ እህት፣ “መንግሥት መሥራት የሚገባቸው ሌላ አያሌ ነገሮች ነበሩ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ሲጋራ ገዝቶ እንዳያጨስ፣ መጠጥ ቤት ገብቶ እንዳይጠጣ፣ የ13 ዓመት ሴት በከተማ በቡና ቤት ገብታ እንዳትሠራ የሚያግድ ሕግ የለም። ዛሬ ሴት እህቶቻችን በሴተኛ አዳሪነት እየተንገላቱ፤ በሥራ አጥነት ሲሰቃዩ መንግሥት ያንን ሁሉ መሥራት ሲገባው አንዲት ለስንቶቻችን አርኣያ ልትሆን የምትችል ሴት ማሰር ያቃጥላል።” ስትል የተናገረች።

 

ሌላዋ እህት ደግሞ በመቀጠል “ኖ ኖ ፖለቲካም ቢሆን መብታችን ነው። እኛ የምንጠላው የጥላቻ ፖለቲካ ነው። እኛ የማንሰብከው የጥላቻ ፖለቲካ። አንዱ አንዱን የሚያንቋሽሽበትን የጥላቻ ፖለቲካ። ሴት ልጅ ፖለቲካ አይጥማትም ያለው ማነው?” ብላለች።

 

“እኔ ፖለቲካ አላውቅም። ይሄም ዝግጅት በሰብዓዊነት ተነሳስተን ያደረግነው ነው። በርግጥ ፖለቲካውም ቢሆን እንዲያስጠላን እንዲያስፈራን የሆነው ፖለቲከኞቹ እርስ በርሳቸው የሚጣሉ የሚባሉ ስለሆኑ ነው።” ስትል ተደምጣለች።

 

ከሕፃናት እስከ አዋቂ፣ ከፖለቲከኛ እስከ ፖለቲካ ፈሪው የተሳተፉበት ይሄ ዝግጅት የተሳካ ነበር። ስኬቱ በገንዘብ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ሴቶቹ ወደፊትም እርስ በርሳቸው የሚገናኙበትን መንገድና የተሻለ ሥራም የሚሠሩበትን መንገድ ቀይሶ የተጠናቀቀ ነበር። ከሴቶቹ ጥቂቶቹ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ ኢትዮጵያ በሻንጣዎች ያገለገሉ ልብሶችን ልከው ነበር። አሁን ደግሞ በኮንቴይነር ለመላክ ዝግጅታቸውን ከወዲሁ ጀምረዋል። ብርቱካንና ቤተሰቦቿንም ቢሆን በየጊዜው ለመርዳትና ለማሰብ ቃል ገብተዋል።

 

መቼም የኢትዮጵያ ጉዳይ የሴቶች ወይንም የወንዶች ተብሎ የሚገደብ አይደለም። በዚህ በብርቱካን ገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ ያስተዋልነው ነገር ቢኖር አብዛኞች ወንዶች ከመሯቸው የከዚህ ቀደም መድረኮች ሁሉ ይሄኛው በተሰብሳቢው ቁጥር ከፍተኛውን ሥፍራ የያዘ፣ የተለየና የላቀ ነበር። በዚህ ዝግጅት ከገንዘቡም ባሻገር ሁሉም ያለውን ወርውሯል። ግማሹ ዳቦ ይዞ መጥቷል። አዘጋጆቹ ሳምቡሳ አቅርበዋል። ግማሾቹ ሴቶች ውሀና ቡና እንዲሁም ሻይ ለተሳታፊዎች ይዘው ቀርበዋል። አንድ በስፍራው የነበረ ግለሰብ በወንዶቹ ሚና ከማዘኑ የተነሳ ወንድነቱን ሲያማርር ተስተውሏል።

 

ዝግጅቱ ከቀኑ 10 ሰዓት (4 P.M.) እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት (7 P.M.) የነበረ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች ዝግጅቱ ሊጠናቀቅ ሲል በመምጣታቸው ሊረዱ ያሰቡትን አሰባስበው በቅርቡ ለአዘጋጅ ኮሚቴው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል። እነሆ ቫንኩቨር ቃል ገብታ ነበር። ብርቱካንን ላለመርሳት፤ በተግባርም አሳየች። ይቀጥላልም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ