የወ/ት ብርቱካን ጠበቃ ክስ ተቀባይነት አገኘ
ወ/ት ብርቱካን ፍርድ ቤት አልቀረበችም
Ethiopia Zare (ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን 2001 ዓ.ም. March 19, 2009)፦ ከታህሳስ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰማኒያ ቀናት በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ በእስር ላይ የምትገኘው የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከወዳጅ ዘመዶቿና ከጠበቃዋ ጋር እንዳትገናኝ ከመደረጉም በላይ በእስር ቤት የሰብዓዊ መብት አያያዛዟ ሁኔታ አግባብ አይደለም ሲል ጠበቃዋ ማረሚያ ቤቱን በመጀመሪያ ደረጃ የልደታ ፍርድ ቤት የከሰሰ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም ትላንት ረቡዕ መጋቢት 9 ቀን በዋለው ችሎት ክሱ ተቀባይነት እንደገኘ ታወቀ።
ወይዘሪት ብርቱካን በደህንነቶች ታፍና ቃሊቲ ከወረደችበት ዕለት ጀምሮ በማረሚያ ቤት በቆየችባቸው ጊዜያት አያያዟ የዓለማቀፍ እስረኞችን ሕግ የጣሰ ከመሆኑ በላይ፣ በተለይ ከእናቷና ከአራት ዓመት ህጻን ልጇ በስተቀር ማንንም እንዳታነጋግርና እንዳትገናኝ መደረጓ የእስረኞችን መብት የጠበቀ አለመሆኑን በመጠቆም በፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ መከራከር የጀመረው የወ/ቷ ጠበቃ ሲሆን፤ በችሎቱ ወ/ት ብርቱካን እንዳልቀረበች ለማወቅ ችለናል።
ዳኛው ክሱ እግባብነት ያለው ነው ሲሉ ውሳኔ የሰጡ ሲሆን፣ ጠቅላላ ውሳኔ ሰጥቶ እስረኛዋ በተገኘችበት እንዴት የክሱ ሂደት ሊቀጥል እንደሚችል ለመወሰን ለመጋቢት 24 ቀን 2001 ዓ.ም. ቀጠሮ የተሰጠ መሆኑን ሪፖርተራችን ከአዲስ አበባ ዘግቧል።



