ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም ስዊድን ገቡ
ቅዳሜ ማርች 28 በስቶክሆልም ከኢትዮጵያውያን ጋር ይወያያሉ
By Matias Ketema
Ethiopia Zare (ሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2001 ዓ.ም. March 23, 2009)፦ የስዊድን የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና የኡሎፍ ፓልመ ኢንስቲትዩት በጋራ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ በሚደረግ ስብሰባ ላይ ገለፃና ማብራሪያ ለመስጠት ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም ዛሬ ስዊድን ዋና ከተማ ስቶኮልም ገብተዋል። የፊታችን ቅዳሜ ማርች 28 ቀን በስቶክሆልም ከኢትዮጵያውያንን ጋር ህዝባዊ ውይይት ያደርጋሉ።
ፕሮፌሠር መስፍን ስቶኮልም እንደደረሱ የስዊድን የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ራስወርቅ መንገሻ ከፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የሥራ ኃላፊነት የሠሩና የኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔን) መስራች ሲሆኑ፣ የቅንጅት የዓላማ ወራሽ የሆነው የአንድነት ፓርትም የላዕላይ ምክር ቤት አባል ናቸው።
ፕሮፌሠሩ የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ኀሙስ ማርች 26 ቀን በስቬያቬገን 68 የስብሰባ አዳራሽ ከጠዋቱ 10፡00 (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 4፡00 ሰዓት) ጀምሮ በመገኘት በተያዘላቸው ሰዓት ለተሰብሳቢው በአፍሪካ ቀንድ ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ ዙሪያ ገለፃና ማብራሪያ ይሰጣሉ።
ነገ ማክሰኞ ማርች 24 (መጋቢት15) ቀን ከጠዋቱ 8፡00 (A.M.) ሰዓት የሊብራል ፓርቲ የፓርላማ እና የፓርቲው የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ብርጊታ ኡልሶንን ያነጋግራሉ። እንዲሁም ረቡዕ ማርች 25 (መጋቢት 16) ቀን የሶሻል ዲሞክራት የፓርላማ አባልና የውጪ ጉዳይ ተወካይ የሆኑትን ካሪና ሄግን ያነጋግራሉ።
በዚሁ ዕለት ከሰዓት በፊት 10፡00 (A.M.) ሰዓት ደግሞ በስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተገኝተው፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ጉዳይ ኃላፊ ከሆኑት ፔተር ጋር እንደሚወያዩ ለማወቅ ችለናል። በተጨማሪ ከሰዓት በኋላ በ15፡30 (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 9፡30) ሰዓት ላይ የሶሻል ዲሞክራት የውጪ ጉዳይ የፓርላማ አባላትን በሙሉ ያነጋግራሉ።
ቅዳሜ ማርች 28 (መጋቢት 19) ቀን ደግሞ ከ13፡00 ሰዓት ጀምሮ በስቬያቬገን ABF ሁሰት አዳራሽ በተለይ ከኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ያደርጋሉ። በተጨማሪ ዓርብ የሞድራትንና የግራ ፓርቲ ተወካዮችን እንደሚያገኙ ታውቋል።
ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም በታሪካዊው ምርጫ 97 የቅንጅት መሥራች አባል የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ፣ ኢህአዴግ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ለሁለት ዓመታት በእስር ካቆያቸው የፓርቲው መሥራቾችና ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ አንዱ እንደነበሩ አይዘነጋም።