Ethiopia Zare (ኀሙስ መጋቢት 17 ቀን 2001 ዓ.ም. March 26, 2009)፦ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም ከስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለሥልጣናት፣ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ከፓርላማ አባላት ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ረቡዕ መጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. ተወያዩ።

 

በስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ ከሆኑት ፔተር ስቨንሰን ፕ/ር መስፍንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ለአንድ ሰዓት ያህል ያነጋገሯቸው መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

ፕ/ር መስፍን ከፔተር ስቨንሰን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ከተነሱት ነጥቦች ውስጥ የወ/ት ብርቱካን እስር፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በአንድነት ፓርቲ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና፣ የመያዶች (መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች) አዲስ ሕግ፣ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ስላለው የኃይማኖቶች ግጭት፣ ሀገሪቱን ካለማቋረጥ እያጠቃት ስላለው ድርቅ፣ ስለኢትዮጵያዊው ስደተኛ፣ ... ዋና ዋናዎቹ ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩ።

 

የወ/ት ብርቱካንን እስር አስመልክቶ ፕሮፌሠሩ፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለአንዲት ሴት የማይገባ የሚሊተሪ ኃይል ማንቀሳቀሱን፣ አስገድዶ ማሰሩን፣ እስሩ በሚከናወንበት ወቅት ድብደባና ማስፈራራት ተካሂዶ እንደነበር አብራርተዋል። ሊቀመንበሯ በእስር ቤትም እያሉ የተከለከሉትን የአንድ እስረኛ መብቶች ሳይሸሽጉ አስረድተዋል።

 

የአንድነት ፓርቲ በሀገር ውስጥ ተመዝግቦ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ላይ መንግሥት እያደረሰበት ያለውን ጫናና አብራርተዋል። ለዚህም በምሳሌነት ከጠቀሷቸው ውስጥ አንዱ የፓርቲው አባላት ካለምንም ምክንያት እንደሚታሰሩ ነው።

 

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ መያዶችን አስመልክቶ በቅርቡ ያጸደቀው ሕግ ከሁሉም አቅጣጫ ተቃውሞ እንደቀረበበት ፕ/ር መስፍን አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት የሚከተለው የፖለቲካ መስመር በአፍሪካ ቀንድ ያሉትንም ሀገራት ፖለቲካዊ አካሄድ እየቀየረውና እያናጋው መሆኑንና ሌሎቹም ሀገራት የኢትዮጵያን መስመር ተከትለው እየተጓዙ እንደሆነ ፕ/ሩ አስረግጠው አስረድተዋል።

 

ፕ/ሩ እነዚህ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ሀገራት መንግሥታት ሕግን ከለላ በማድረግ በህዝባቸው፣ በቀንዱ ብሎም በአፍሪካ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ገልፀዋል።

 

ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ እያጠቃት ያለውን ድርቅ አስመልክተውም የድርቅን አመጣጥ ካብራሩ በኋላ፤ ምንም እንኳን ድርቁ የተፈጥሮ ቢሆንም በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር አለመኖሩ እንዳባባሰውና መፍትሔ እንዳያገኝ እንዳደረገው አብራርተዋል።

 

በርካታ ኢትዮጵያውያን ሀገር ጥለው እየተሰደዱ መሆኑንና አንዷም የመሰደጃ ሀገር ስዊድን መሆኗን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ የተሻለ ሁኔታ ቢኖር ኢትዮጵያዊው ሀገሩን ጥሎ እንደማይሰደድ ተናግረዋል።

 

ፕ/ር መስፍን ለተጠቀሱት ችግሮች መፍትሔ ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን ሃሳቦች ሳይሰነዝሩ አላለፉም። የስዊድን መንግሥት በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥትም ሆነ ለማንም ሳይወግንና ሳያዳላ ሁሉንም በእኩል ዓይን እንዳለበት ፕሮፌሠር መስፍን አሳስበዋል።

 

ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ከስዊድን መንግሥት ባለሥልጣናትና ከአንዳንድ የፓርላማ አባላት ጋር ተገናኝተው በበርካታ ጉዳዮች የተወያዩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የፓርላማ አባልና የውጭ ጉዳይ ተወካይ የሆኑት ካሪና ሄግ ይገኙበታል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ