“ባህላችን ለባርነት እንድንመቻች አድርጎናል” ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም
Ethiopia Zare (ሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2001 ዓ.ም. March 30, 2009)፦ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በስዊድንና በአካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ቅዳሜ መጋቢት 19 ቀን 2001 ዓ.ም. በስቶክሆልም ከተማ በኢትዮጵያ ወቅታዊና ታሪካዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል። ውይይቱ የተለያዩ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት፣ ትምህርታዊ፣ አዝናኝና ታሪካዊ ነበር።
ውይይቱ በኢትዮጵያዊ ባህል መሰረት እንደተለመደው አንድ ሰዓት ዘግይቶ የተጀመረ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ተናጋሪ የነበሩት በስዊድን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የድጋፍ ሰጪ ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ራስወርቅ መንገሻ ነበሩ። አቶ ራስወርቅ፣ ፕ/ር መስፍንን ጨምሮ ለስብሰባው ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ ነበር ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት።
የውይይቱንና የዕርዳታ ማሰባሰቢያውን ዓላማ ሲያስረዱ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ታጣቂዎች ከመንገድ ላይ ታፍና ተወስዳ ወህኒ የወረደችበትን ሦስተኛ ወር በኀዘን ለማስታወስ ነው ብለዋል።
በዚህ የከፋ አገዛዝ ዘመን የተወለዱት ልጆች ዛሬ የ18 ዓመት ጎልማሶች መሆናቸውን የገለጹት አቶ የራስወርቅ፤ “ይህ ትውልድ ወያኔ ባጠመደው የባርነት ወጥመድ ተተብትቦ ህልውናውን እንዳይሸጥና ኢትዮጵያዊነት ማለት ለነፃነቱ፣ ለክብሩና ለአንድነቱ ቅደሚያ የሚሰጥ የኩሩ ህዝብ መለያ መሆኑን አውቀው እንዲያድጉ ለማድረግ ተችሏል። ለዚህም ማስረጃው የ1997ቱን ምርጫ ዋቢ ማድረግ ይቻላል።” ብለዋል።
ከአቶ የራስወርቅ በመቀጠል “ወለላዬ” በሚል የብዕር ስም የሚታወቀው ገጣሚ ማትያስ ከተማ “እህ ዛዲያማ!” በሚል ርዕስ ግጥም ያሰማ ሲሆን፣ ከዚያ በመቀጠል ፕ/ር መስፍን አንድ ሰዓት የፈጀ ሰፋ ያለ ትምህርታዊ ንግግር አድርገዋል። ፕ/ር መስፍን ሠላምታና ምስጋና ካቀረቡ በኋላ፣ በዚህ ህዝባዊ ውይይት ላይ የተገኙት ፓርቲያቸውን (አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህን) በመወከል ሳይሆን፤ በግላቸው መሆኑን በመግለጽ ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት።
ፕ/ር መስፍን በዚህ ትምህርታዊና ታሪክ ቀመስ ንግግራቸው፤ “... ባህላችን ለባርነት እንድንመቻች አድርጎናል። ‘ነፃነት’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አለብን። ማወቅ አለብን። አባት፣ እናቶቻችን እኛ የደረስንበት የሀብት ደረጃ ላይ አልደረሱም፣ ደሃዎች ነበሩ። ነገር ግን ኩሩዎች ነበሩ። ክብራቸውን ይጠብቁ ነበር። ክብራቸውና ኩራታቸው በምንም ነገር አይለውጡም ነበር። ...” በማለት የቀድሞው ጊዜ ምን ይመስል እንደነበር ከገለጹ በኋላ፤ እኛ ግን በራሳችንና በወላጆቻችን ሀብት ክብራችንን ሸጠን እየኖር ነው ብለዋል። ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም
“... ነፃነት በቀላሉ የሚገኝ ሀብት አይደለም። አንድ ሰው ነፃነት ለማግኘት፣ ራሱን “ሰው ነኝ” ብሎ ማሳመንና ማመን አለበት። ሰው ነኝ የሚል እምነት ካለው፣ ከዚያ በኋላ ነፃነቱን ማንም ሊነፍገው አይችልም። መሬቱ፣ ገንዘቡ፣ ሹመቱ፣ ... ይቀራል እንጂ፤ ሰው ሆኖ ነፃ ሆኖ ይኖራል። የሰውነት የመጨረሻው ሀብቱ፣ ነፃ መሆኑ ነው። እንደፈለገው ሃሳቡን ለመግለጽ፣ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት፣ ... ይሄ ነፃነት ነው በኢትዮጵያ ውስጥ የሌለው። ...” በማለት ፕሮፌሠር መስፍን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ያሉ የኃይማኖት ተቋማትንና የኃይማኖት አባቶችን አስመልክቶ ፕ/ር መስፍን የሰላ ሂስ ሰንዝረዋል። በኢትዮጵያ ያሉት የኃይማኖት ተቋሞችና አባቶች፤ “ሰዎች በግፍ ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ፣ ... አላይም! በእግዚአብሔር/በአላህ ፊት ይሄ ልክ አይደለም!” የሚሉ አለመሆናቸውን ገልጸው፤ “ውድቀታችን እዚያ ደርሷል” ብለዋል። በአንፃራዊነት ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ደቡብ አፍሪካንና ሌሎች ሀገራት የሚገኙ የኃይማኖት አባቶች ፖለቲከኞችንም ሆነ መንግሥትን ሳይፈሩ የሰላ ሂስ እንደሚሰነዝሩ፣ የዜግነትና የኃይማኖት አባትነታቸውን ኃላፊነታቸውን የሚወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ካህናት በወርቅ ተሸልመው፣ የወርቅ መስቀል በአንገታቸው አጥልቀው፣ ደረታቸው ላይ የሚያደርጉት መስቀል ከጌጥነት እንደማያልፍ የገለጹት ፕ/ር መስፍን፤ ታላቅ ክብር ለሚሰጡትና እንዲሰጠው ለሚፈልጉት መስቀል መስዋዕትነት የማይከፍሉ ናቸው ሲሉ በተለይም በኢትዮጵያ ያሉትን የክርስትና ኃይማኖት አባቶች ተችተዋል።
በዚህ ህዝባዊ ውይይት ላይ በሦስት ዙር ለፕ/ር መስፍን ከተሰብሳቢዎች በርካታና የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተውባቸዋል። ጥያቄዎቹና ውይይቱ ልዩ ትኩረት ሰጥተው የነበሩት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ባህል፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ በዳያስፖራው፣ ... ላይ የነበረ ሲሆን፤ በተያያዥነትም የአፍሪካ፣ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የዓለም ጉዳዮች ተዳሰዋል።
በውይይቱ ላይ ከስዊድን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የዓለም አቀፍ ምክትል ፀሐፊ የሆኑት ክላስ ኑርድማርክ ተገኝተው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ፣ በተለይም የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እስር አስመልክቶ በግላቸውም ሆነ ፓርቲያቸው ጉዳዩን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመለከተው ገልጸዋል። ፀሐፊው ለፕ/ር መስፍን ያላቸውን አድናቆትና ክብር አጋጣሚውን በመጠቀም ገልጸዋል።
በአቶ ማትያስ ከተማና በአቶ ራስወርቅ መንገሻ በየመሀሉ የተለያዩ ግጥሞች የተነበቡ ሲሆን፣ በተለይም አቶ ማትያስ “የፈና ጅራ፣ የፈና ጅርቱ” በሚል ርዕስ ያቀረበውና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ኢኮኖሚ ምን እንደሚመስል ያሳየበት ግጥም ብዙዎችን ያስፈገገ፣ ያሳዘነና ያዝናና ነበር። (ከግራ ወደ ቀኝ) አቶ መላኩ፣ ፕ/ር መስፍን፣ አቶ ራስወርቅ እና አቶ ማትያስ ከተማ
በዝግጅቱ ላይ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን፣ ለወ/ት ብርቱካን ቤተሰቦች (እናትና ልጅ) መርጃ ተሰብሳቢው ከ5 ሺህ የስዊድን ክሮነር በላይ አዋጥቷል። ከዚህም ሌላ የወ/ት ብርቱካን ምስል ያለበትና ከእስር እንድትለቀቅ የሚጠይቅ ቲሸርት ሲሸጥ ነበር። ውይይቱን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ሪፖርት በድምጽ ወይንም በጽሑፍ ለማቅረብ እንሞክራለን። ከዚህም ሌላ ባለፈው ማርች 26 ቀን በስቶክሆልም ከተማ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ተገኝተው ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡበትንና ያስተማሩበትን በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ የተደረገውን ሴሚናር በቪዲዮ ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን።