አንድነት ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው
በቅርቡም ህዝባዊ ሰልፍ እንደሚጠራ ታወቀ
Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. March 25, 2009)፦ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 20 ቀን 2001 ዓ.ም. ታላቅ የህዝብዊ ስብሰባ እንደሚጠራና ከህዝብ ጋር የሕግ የበላይነት መከበርን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት በኢምፔሪያል ሆቴል እንደሚያካሂድ ከአዲስ አበባ የደረሰን መረጃ ጠቆመ።
ፓርቲው በሚያካሂደው ውይይት ላይ አራት ምሁራንና የፖለቲካ ሰዎች የመወያያ ጽሁፎችን አዘጋጅተው እንደሚቀርቡ የታወቀ ሲሆን፣ ከጽሁፍ አቅራቢዎቹ ውስጥም ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ ዶ/ር መራራ ጉዲናና አቶ ስዬ አብርሃ እንደሚገኙበት ለማወቅ ችለናል።
መጋቢት 20 ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ወደ እስር የተጣለችበት ሶስተኛ ወር በመሆኑ በየወሩ የሚካሄደው የሻማ መብራት ስነሥርዓት በዕለቱ የሚካሄድ መሆኑ ከመገለጹም በላይ፤ በውይይቱ የወ/ቷ የእስር ሂደትና በየክልሉ ያሉ የፓርቲው አባላትና ጽ/ቤቶች ላይ የሚደረገውን ከፍተኛ ተጽእኖና እስር በሚመለከት ከውይይቱ ርእስ ጋር በተገናኘ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል።
ስብሰባውን በሚመለከት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል ማስታወቃቸውን የገለጹት የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ ቅዳሜ መጋቢት ሃያ ከሚደረገው ሲምፖዚየም በኋላ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለመጥራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሰልፉ መቼ ሊደረግ እንደሚችል ገና እንዳልተወሰነ፤ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ድርጅቱ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ ከወዲሁ አስታውቀዋል።



