የማረሚያ ቤቶችና የወ/ት ብርቱካን ጠበቃ ሙሉ የፍርድ ቤት ሙግት

W/t Birtukan MideksaEthiopia Zare (እሁድ መጋቢት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. April 5, 2009)፦ ልደታ አካባቢ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘጠነኛ ፍትሐብሔር ችሎት መግቢያ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ተጨናንቋል። ከዚህ ቀደም በዚህ ችሎት ሁለትና ሦስት ሆነው ከሚመጡ ባለጉዳዮች ውጭ እንዲህ ቁጥሩ በርከት ያለ ታዳሚ ታይቶ አይታወቅም። ከችሎቱ መግቢያ ፊት ለፊት ላይ ሰዎች ሦስትና አራት ሆነው በመሰባሰብ የየራሳቸውን ውይይት ይዘዋል። የወ/ት ብርቱካን እናት ነጠላቸውን ተከናንበው ከአንዱ ጥግ ተቀምጠው የሚሆነውን ይጠባበቃሉ። ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ አቶ አክሉ ግርግሬ፣ አቶ አስራት ጣሴና ሌሎች የአንድነት ፓርቲ ሰዎችም ተገኝተዋል።

 

የችሎት ተራ አስከባሪው ”የፌደራል ማረሚያ ቤቶችና ወ/ት ብርቱካን” ሲል ኀሙስ መጋቢት 26 ቀን ከጧቱ ሦስት ሰዓት ላይ ጥሪ አሰማ። የወ/ት ብርቱካን ጠበቃ ተጣድፈው ወደ ችሎት ገቡ፤ ማረሚያ ቤቶች ግን በሰዓቱ አልቀረበም ነበር።እንደ ፍትሐብሔር ሕግ ሥነሥርዓት ተከሳሽ መጥሪያ ደርሶት ካልቀረበ በሌለበት ውሳኔ ይሰጣል፤ ነገር ግን ዳኛው ያንን ማድረግ አልፈቀደም መሰል ተከሳሾቹ እስኪመጡ ለመጠበቅ ወሰነ።

 

ተከሳሹ እስከ አራት ሰዓት ብቅ አላሉም፤ ችሎቱ ሌላ ውሳኔ አስተላለፈ ጠበቃው መጥሪያ ማድረሳቸውን በቃለ መሐላ እንዲያረጋግጡ ጠየቀ። ብዙም ሳይቆይ ተራ አስከባሪው ”የፌደራል ማረሚያ ቤቶችና ወ/ት ብርቱካን” ሲል በድጋሚ ተጣራ ሁሉም ሰው ጠበቃውን ተከትሎ ወደ ችሎቱ ገባ።

 

በችሎቱ ውስጥ ታዳሚ የሚቀመጥበት አንድ አግዳሚ ብቻ ያለ ሲሆን፣ ሌሎች በርካታ ችሎት ተከታታዮች ለመቆም ተገደዋል። መዝገቡ ለዕለቱ የተቀጠረው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ”የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን” ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚነካ አኳኋን አለበቂና ሕጋዊ ምክንያት ለብቻቸው እንዲታሰሩ ማድረጉን፣ በሌሎች ላይ ባላደረገው ሁኔታ በተለይም በከሳሽ ላይ ልዩነት በሚፈጥር አኳኋን ከልጅና እናታቸው በስተቀር እህታቸው፣ ወንድማቸው፣ ሌሎች የቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና የሕግ አማካሪዎቻቸው እንዳይጎበኟቸው ክልከላ ማድረጉን፤ በተለይም የተሰጣቸው ይቅርታ የተነሳበትን ሁኔታ ሕጋዊነት በተመለከተ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ለማቅረብ ቢያስቡም ከሕግ አማካሪያቸው (ጠበቃቸው) ጋር ለመገናኘት እና ለመነጋገር ባለመቻላቸው ችግር እንደገጠማቸው በመግለጽ በመሰረታዊ መብታቸው ላይ የተቃጣው ክልከላ እዲወገድ፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የሚደረግባቸው ልዩነት እንዲቆምና ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቅ አኳኋን እንዲያዙ ሲል ፍርድ ቤቱ በተፋጠነ ሥነሥርዓት እንዲወስንላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት ላቀረቡት ክስ፣ ኮሚሽኑ የሚሰጠውን መልስ ለመቀበል ነበር።

 

ከአንድ ሰዓት በላይ አርፍደው የተገኙት የተከሳሽ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተወካይ ሱፐር ኢንተንደንት እናቴነሽ መኮንን መልሳቸውን በጽሑፍ ይዘው የቀረቡ ቢሆንም፤ ክሱን ከመቃወም በቀር ስለ ወ/ት ብርቱካን አያያዝ ሁኔታ ለቀረበባቸው ክስ ምንም ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

 

ለክሱ ስድስት መቃወሚያዎችን ያቀረቡ ሲሆን አንደኛ፦ “ክሱን ያቀረቡት ጠበቃ አቶ ተስፋዬ ደረሰ ናቸው። አንድ ጠበቃ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ከመከራከሩ በፊት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አዋጅ 467/97 መሰረት የጽሑፍ ውክልና ከውልና ማስረጃ ሊኖረው ይገባል። በፌደራል ጠበቆች ሥነ ምግባር ደንብ 57/92 መሰረት የጥብቅና አገልግሎት ውል በጽሑፍ ሊኖረው ይገባል። እንዲሁም በፍርድ ቤቶች መመሪያ መሰረት ይኸው መያያዝ ይኖርበታል። ነገር ግን ጠበቃ ተስፋዬ ደረሰ ውክልናም ሆነ የጥብቅና አገልግሎት ውል የሌላቸው በመሆኑ ያቀረቡት ክስ ውድቅ ተደርጎ መዝገቡ ተዘግቶ እንሰናበት።” ሲሉ ጠይቀዋል።

 

ሁለተኛ፦ በሕገመንግሥታችን የሥልጣን ክፍፍል ተደንግጓል። አስፈጻሚ አካላት በተሰጣቸው ሥልጣን ክልል ውስጥ እንዲሠሩና ውሳኔ እንዲሰጡ ተደንግጓል። ፍርድ ቤቶች በዚህ የአፈጻጸም አካላት ሥልጣን ላይ ያላግባብ መግባት የለባቸውም። በዚህ ጉዳይ የእስረኛን አያያዝ አስመልቶ አስፈላጊውን በማድረግ እንዲጠብቅ ለማረሚያ ቤት ሥልጣን የተሰጠ በመሆኑ የአያያዙን ሁኔታ አስመልክቶ በፍርድ ቤት ጣልቃ ሊገባበት አይገባም። ስለሆነም ክቡር ፍርድ ቤቱ ይህን አስተዳደራዊ ጉዳይ የማየት ሥልጣን ስለሌለው መዝገቡን እንዲዘጋልን እንጠይቃለን።

 

ሦስተኛ፦ ከሳሽ ክስ ያቀረቡት በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ላይ ነው። ነገር ግን መስሪያ ቤቱ የሚያስተዳድራቸው ብዛት ያላቸው ማረሚያ ቤቶች አሉት። እያንዳንዱ ማረሚያ ቤት የሚላኩትን ታራሚዎች አያያዝ ሁኔታ በመወሰን በጥንቃቄ ያስተዳድራል።

 

ፌደራል ማረሚያ ቤቶች አጠቃላይ በጀትና አጠቃላይ የአስተዳደራቸውን ሁኔታ ይቆጣጠራል። ከአባል ሠራተኞችም ሆነ ከታራሚዎች ደረጃውን ጠብቆ የሚቀርብ ቅሬታ ካለ አመራርና መፍትሔ ይሰጣል። በዚህ ጉዳይ ቅሬታ እስካሁን አልቀረበልንም። ቅሬታ ሲቀርብ በታራሚው፣ በደበዳቤ ወይም በቤተሰቡ፣ ወይም በአግባቡ በተወከለ ጠበቃ ከቅሬታውና ከማስረጃው ጋር ይቀርብልናል። ጉዳዩን አጣርተንም ተገቢ ውሳኔ እንሰጣለን።

 

በያዝነው ጉዳይ ግን የቀረበልን ቅሬታ የለም። ከቀረበው ክስ በመነሳትም በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የቀረበ ቅሬታ እንዳለም ለማረጋገጥ ሞክረን ምንም የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩን አረጋግጠናል።

 

ስለሆነም አንደ ቅሬታ ያለው ታራሚ አስቀድሞና ደረጃውን ጠብቆ ላለበት ክፍል ኃላፊዎች፣ በመጨረሻም ለማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ፣ በመቀጠልም ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የመጨረሻ ውሳኔ ቅሬታውን ማቅረብ ይጠበቅበታል። ወ/ት ብርቱካን ግን ይህን አላደረጉም። ይህ ደግሞ የአስተዳደር ውሳኔዎችን ፍርድ ቤቶች እንዲከልሱ የሚፈቅድላቸው ከሆነ አስቀድሞ ቅሬታውን በአስተዳደሩ ለመፍታት ጥያቄ መቅረቡንና የመጨረሻ ውሳኔ በአስተዳደር መስሪያ ቤቱ የተሰጠ መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይላል።

 

(Exhaustion of local remedies) የሚጠቅመው ፍርድ ቤቶች ያላግባብ በአስተዳደር ሊፈታ ይችል የነበረን ጥያቄ በመመልከት ጊዜ እንዳያጠፉ፣ አስተዳደር መስሪያ ቤቱም በተሰጠው ሥልጣን የሚሠራውን ሥራ ሠርቶ ሳይጨርስ በሥልጣኑ ጣልቃ እንዳይገባበት ለመከላከል ነው። ስለሆነም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም ሆነ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ቅሬታ ያላቀረቡና ተከሳሽ የመጨረሻ ውሳኔ ባልሰጠበት ሁኔታ ይህ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማየት ስለማይገባው መዝገቡን ዘግቶ እንዲያሰናብተን እንጠይቃለን።

 

አራተኛ፦ በተፋጠነ ሥነሥርዓት የሚቀርቡ ጉዳዮች በጣም የተወሰኑ በልዩ ሁኔታ ተዘርዝረው የተመለከቱ ብቻ ናቸው። ከነዚህ ውጭ በተፋጠነ ሥነሥርዓት ሊቀርቡ አይገባም። ከሳሽ ነኝ ያሉት ጠበቃ ያቀረቡት ጉዳይ በተፋጠነ ሥነሥርዓት የሚወድቅ አይደለም። የፍ/ሥ/ሕ/ቁ 314 ግልጽ አንቀጽ ነው። የሚገዛቸውም ጉዳዮች በአንድ መዝገብ ወይም በመንግሥት መዝገብ (እንደ ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ) በክብር መዝገብ አልመዘግብም ተብሎ ሲከለከል፤ ይህን ለማስወገድ የሚቀርብ ብቻ እንጂ ፍርደኛ መጠየቅ ተከለከልኩ፣ ለብቻ ታሰሩብኝ የሚል ጥያቄ በተፋጠነ ሥነሥርዓት ሊቀርብ የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ ክቡር ፍርድ ቤቱ ይህን በተፋጠነ ሥነሥርዓት የተከፈተ መዝገብ እንዲዘጋልን እንጠይቃለን።

 

አምስተኛ፦ የቀረበው ማመልከቻ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 302/1/ለ/ መሰረት በመሀላ ቃል ተደግፎ ያልቀረበ በመሆኑ የተፋጠነ ሥነሥርዓት ጥያቄ መዝገብ እንዲዘጋልን እንጠይቃለን። ከዚህም በላይ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ/ 92 መሰረት እንኳን በአግባቡ ያልተረጋገጠ ነው። ከሳሽ ነኝ ባይ ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ እውነት መሆኑን አረጋግጠው ማቅረብ ሲገባቸው የማያውቁትን ያላረጋገጡትን ነገር ”እስከማውቀው በክሱ የተገለጸው እውነት ነው” በማለት ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።

 

ስድስተኛ፦ ኮሚሽኑ በዚህ የመጨረሻ መቃወሚያው፤ ጉዳዩ የተፋጠነ ሥነሥርዓት ውስጥ አይወድቅም እንጂ ክቡር ፍርድ ቤቱ ይወድቃል እንኳ ቢል፣ ከሳሽ ለክሱ መነሻ የሆናቸው ጉዳይ ተፈጠረ የሚሉት ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ (ከወራት በላይ) እንደመሆኑ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 301/1 መሠረት በ15 ቀናት ውስጥ ጥያቄ ካላቸው ጥያቄያቸውን ማቅረብ ነበረባቸው። የመብት ክልከላን የሚሉት ከተፈጠረ ከ15 ቀን በላይ ያለፈ በመሆኑ ያቀረቡት ክስ ውድቅ እንዲደረግልን እንጠይቃለን።

 

ከዚህም ባሻገር ክቡር ፍርድ ቤቱ ባለፉት 15 ቀናት የተፈጸመ ክልከላ ካለ ይህንኑ አካተው ክሳቸውን እንዲያሻሽሉ የፈቀደው ከፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 208 መሰረት የቀድሞውን ትዕዛዝ በማረም በማመልከቻው ባለፉት 15 ቀናት የተፈጸመ ክልከላ ገልጸው ባለማቅረባቸው መዝገቡ ሊዘጋ ይገባል በማለት እንዲታረምልን እጠይቃለን።

 

አሁንም ተሻሽሎ የቀረበው ክስ ክልከላው ተፈጠረ ከሚሉት (ከእስሩ ወራት በኋላ) የቀረበ በመሆኑ መዝገቡ ይዘጋልን ያልነው እንደተጠበቀ ሆኖ የተሻሻለው ክስ የቀረበው መጋቢት 2 ቀን 2001 ዓ.ም. እንደመሆኑ ከዚህ ኋላ 15 ቀን ጀምሮ ማለትም ከመጋቢት 18 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ያለ ጥያቄ ባለማቅረባቸው መዝገቡ ይዘጋልን ሲሉ ክሱን ተቃውመዋል።

 

ፍርድ ቤቱ በጽሑፍ የተቀበለውን መቃወሚያ ከተመለከተ በኋላ፤ ክሱ በተፋጠነ ሥነሥርዓት የቀረበ በመሆኑ የመልስ መልስ ለመቀበል ቀጠሮ ስለማንሰጥ በዕለቱ በቀረበው መቃወሚያ ላይ ጠበቃው አቶ ተስፋዬ ምላሽ እንዲሰጡ አዟል።

 

አቶ ተስፋዬ ለመቃወሚያው ተራ በተራ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ ውክልናና ውል የላቸውም የሚለውን በተመለከተ ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሕጋዊ ወኪል ወ/ት እየሩሳሌም ይልማ ሕጋዊ ውክልና መቀበላቸውንና ውክልናና ውሉን ለፍርድ ቤቱ ከመዝገቡ ጋር ማያያዛቸውን ገልጸው፤ እንዲህ ያለው ሰነድ ደግሞ ለፍርድ ቤት እንጂ ለተከሳሽ የመስጠት ግዴታ እንደሌለባቸው ከገለጹ በኋላ፤ ነገር ግን አስፈላጊ ከሆነ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ በማስረዳት ችሎቱ ፊት ቅጂውን ለኮሚሽኑ ወኪል ሰጥተዋል።

 

በተጨማሪም በአምስተኛ መቃወሚያቸው ላይ ቃለ መሐላ አልተፈጸመም ላሉት፤ በእርግጥ አንድ ጉዳይ በተፋጠነ ሥነሥርዓት ይታይ ሲባል በቃለ መሐላ መደገፍ እንዳለበት ሕጉ ያዛል፤ እኛም ሕጉን ስለምናውቅ ቃለመሐላችንን ከመዝገቡ ጋር አያይዘናል ብለዋል።

 

በሁለተኛ መቃወሚያነት የቀረበው የማረሚያ ቤቱን ሥልጣን ፍርድ ቤቱ ሊጋፋ አይገባም ለሚለው መልስ ሲሰጡ፤ በሕገመንግሥቱ መሠረት የተቋቋሙ ሦስት የመንግሥት አካላት አሉ። እነሱም ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ እንደሆኑ ይታወቃል። በዚህ ሥልጣናቸውም አንዳቸው አንዳቸውን የመቆጣጠር ሥራ ይሠራሉ። እኛ ክስ ያቀረብንበት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፤ በአዋጅ ቁጥር 365/95 መሠረት መክሰስና መከሰስ የሚችል ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው አካል ነው። ሊከሰስባቸው የሚችልባቸው ተግባራት ደግሞ ከሚፈጽማቸው ተግባራት ሊመነጩ የሚችሉ ናቸው። ከተግባሮቹ የሚመነጩትንና ክስ የሚቀርቡበትን ጉዳዮች ደግሞ ሕግ የመተርጎም ሥልጣን ካለው ”ፍርድ ቤት” ውጪ ሌላ ዳኝነት ሊሰጥ የሚችል አካል የለም። የከሳሽ የወ/ት ብርቱካን ጥያቄ በሕገመንግሥቱ መሠረት የተረጋገጠው መብት በሕግ ይጠበቅልኝ የሚል ሲሆን፤ እነዚህ አካላት ደግሞ መብቶች በሕገመንግሥቱ መሰረት መረጋገጣቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለባቸው ናቸው። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ክሱን የማየት ሥልጣን አለው ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

 

በመስሪያ ቤታችን ያለውን የቅሬታ ማቅረቢያ በሙሉ አሟጠው ሳይጠቀሙ ያቀረቡት ክስ ነው በሚል በሦስተኛ ደረጃ ለቀረበው መቃወሚያ የጠበቃው ምላሽ፤ (Exhaustion of local remedies) የሚባለው የተለያዩ የመንግሥት አስፈጻሚ አካለት ለምሳሌ ሀገር ውስጥ ገቢ፣ ጡረታ ሚኒስቴር የመሳሰሉት ይኖሩና በሥራቸው ያቋቋሟቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይኖራሉ። እነዚህ አስፈጻሚ አካላት ዳኝነት የሚመስል ሥልጣን ይኖራቸውና በሥራቸው ባሉ ተቋማት የሚቀርቡ ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ ይሰጣሉ። ቅሬታውን በየደረጃው አቅርቦ ውጤት ያላገኘ ካለ ውሳኔው እንደገና እንዲታይለት ለፍርድ ቤት አቤት ይላል። እኛ ይዘን የቀረብነው ከዚህ የተለየ ነው፤ ማንም አካል በወ/ት ብርቱኳን ጉዳይ ክልከላ አደረገ እንጂ በጽሑፍ ውሳኔ አልሰጠም። ያቀረብነው ክስ ”የመብት ይከበርልን” ጥያቄ ነው። ይህን ጥያቄ ከፍርድ ቤት ውጪ ማንም ሊመልሰው አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ መብቴ አልተከበረልኝም ስትል አቤቱታ ያቀረበች አንዲት በጥበቃ ስር ያለች ግለሰብ ያቀረበችው ክስ ለኮሚሽኑ ከደረሰው 15 ቀናት ሆኖታል። መጀመሪያ ”አልሰማሁም ነበር” አለ፤ ከሰማ በኋላስ ምን መፍትሔ አመጣ? በክሱ ላይ የተገለጸው የመብት ጥሰት ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም? ብሎ ለማጣራት የሞከረው ነገር አለ? አሁንስ ቢሆን ከመቃወሚያ ውጭ ስለ ዋናው ጥያቄ ለምን መልስ አልሰጠም? ይሄ የሚያሳየው በድርጊቱ ማመኑን ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይስጠን ሲሉ ጠይቀዋል።

 

በአራተኛነት ለቀረበው በተፋጠነ ሥነሥርዓት ክሱ ሊቀርብ አይገባም፣ ለሚለው መቃወሚያ፦ ከፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 300 ጀምሮ በተፋጠነ ሥነሥርዓት ሊታዩ የሚገባቸው ነገሮች ምን አይነት እንደሆኑ ይዘረዝርና በተለይ 314 ላይ ሲደርስ ለአብነት ያህል ምን ምን አይነት ጉዳዮች በዚህ ችሎት እንደሚታዩ ዘርዝሮ፤ በአጠቃላይ ግን ”ክልከላ እንዲወገድ” የሚጠይቅ አንቀጽ ነው። ”ክልከላ እንዲወገድ” ማለት ከመብት ጋር የተያያዙ ማንኛውም ጥያቄዎች የሚቀርቡበት ሥርዓት እንደሆነ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ ክሳችንን በዚህ ሥርዓት ማቅረባችን ትክክል ነው ብለዋል።

 

ከሳሽ ነኝ ባይ ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ እውነት መሆኑን አረጋግጠው ማቅረብ ሲገባቸው የማያውቁትን ያላረጋገጡትን ነገር ”እስከማውቀው በክሱ የተገለጸው እውነት ነው” በማለት ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል የሚለውን መቃወሚያ በተመለከተ፣ አቶ ተስፋዬ ምላሽ ሲሰጡ፤ ማንኛውም ክስ ሲቀርብ ጠበቃው ከደንበኞቹ የተነገረውን ሐቅ “እስከሚያውቀው” ድረስ ብቻ ነው ማቅረብ የሚችለው፣ ለእኔ እውቀት ማረጋገጫ ላቀርብ አልችል፤ በክሱ ላይ የቀረቡት ነገሮች እውነት ናቸው? እውነት አይደሉም? የሚለውን በተመለከተ ማረጋገጥ የሚቻለው በምስክሮች ብቻ ነው ብለዋል።

 

ቀኑ ስላለፈ በይርጋ እንዲታለፍ የተጠየቀውን የማረሚያ ቤቶች መቃወሚያ በሚመለከት፤ የመጀመሪያውን ክስ ያቀረብነው የካቲት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. ነው በዕለቱ ፍርድ ቤቱ ክልከላው የተደረጉበትን ቀናት ምስክሮቹ በሚያስረዱት ጭብጥ ዝርዝር ውስጥ እንጂ በክሱ ላይ አካተን ያላቀረብን ስለሆነ ቀናቱን አካተን ክሱን እንድናሻሽል ፍርድ ቤቱ ብይን ሠጠ። በብይኑ መሠረት መጋቢት 2 ቀን 2001 ዓ.ም. ክሳችንን አሻሽለን አቀረብን መቆጠር ያለበትም ክሳችንን ፍርድ ቤት ካቀረብንበት ቀን ጀምሮ ነው። ምክንያቱም ሕጉ የሚለው ድርጊቱ ከተፈጸመ ከ15 ቀናት በፊት ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ነው ለፍርድ ቤት አቅርበናል። በዚህ መሰረት ክልከላ ተፈጸመብን ያልነው የካቲት14፣ 15፤ 17፣ 18፣ 21፣ 22 በመሆኑ ፈጽሞ ክሱ ቀን አልፎበታል ሊባል አይችልም ሲሉ ተከራክረዋል። በመጨረሻም ተከሳሽ የቀረበውን ክስ ከፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 285 መሰረት በግልጽ መካድ ወይም ማመን አለበት በዚህ መሰረት በግልጽ የቀረበ ነገር ባለመኖሩ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ አቶ ተስፋዬ ተሟግተዋል።

 

ፍርድ ቤቱም ለተከሳሽ ወኪል ”በፍሬ ነገሩ ላይ ለምን መልስ አትሰጡም?” በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ፤ ”ጉዳዩን በማጣራት ላይ ስለሆንን በዛሬው ዕለት መልስ አንሰጥም፤ ባቀረብነው መቃወሚያ ላይ ብይን ይሰጠን” ብለዋል።

 

ከክርክሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ በሰጠው ትዕዛዝ፤ የተከሳሽ ጠበቃ ክስ ማቅረብ ይችላል? አይችልም?፣ ፍርድ ቤቱ ሥልጣን አለው የለውም?፣ ከሳሽ በተከሳሹ መሥሪያ ቤት በየደረጃው ያለውን የቅሬታ ማቅረቢያ ተጠቅሟል አልተጠቀመም? ያልተጠቀመ ከሆነ ክሱ ይቀጥል አይቀጥል? ክሱ በተፋጠነ ሥነሥርዓት መታየት ይችላል አይችልም? የሚሉትን ጥያቄዎች መርምሮ ሚያዝያ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ