Ethiopia Zare (ሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2001 ዓ.ም. April 6, 2009)፦ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባላትና የአጋር ፓርቲ መሪዎች “ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰሩበት የሕግ አግባብ ትክክል አይደለም” በሚል የፊታችን ሐሙስ ሚያዝያ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ሠላማዊ ሰልፍ ሊያካሂዱ መሆኑን ፓርቲው ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

 

ፓርቲው ዓርብ ዕለት በጽ/ት ቤቱ በሰጠው በዚሁ መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው ለአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ለወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ቀደም ሲል የተሰጠው ይቅርታ መነሳት የሕግ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ይቅርታው እንዲፀናና ወ/ሪት ብርቱካን ከእስር እንዲፈቱ ከዲፕሎማሲያዊው ጫና በተጨማሪ መንግሥት ላይ “ጫና ለመፍጠር” ታስቦ የሚደረግ ሠላማዊ ሰልፍ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል።

 

የፓርቲው ም/ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ እንደተናገሩት፤ በሰልፉ ላይ ለመሳተፍ በርካቶች ፍላጎት ቢኖራቸውም “ሠላማዊ ሰልፉን ለመቆጣጠር እንችላለን ወይ?” የሚለው ጥያቄ በቀላሉ መልስ የሚያገኝ ባለመሆኑ 250 የሚደርሱ በየደረጃው ያሉ የፓርቲው አመራር አባላት ብቻ በሰልፉ እንዲሳተፉ መወሰኑን ተናግረዋል።

 

የሠላማዊ ሰልፉ መነሻ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 18 የቤት ቁጥር 045 በተምዶ ባምቢስ ድልድይ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ሲሆን፣ መድረሻው ደግሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ነው።

 

ሰልፉ ፍቃድ አግኝቶ የሚደረግ ከሆነ ሠላማዊ ሰልፈኞቹ ከአንድነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተነስተው ከጠዋቱ 4 ሰዓት ፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ይደርሳሉ። ከዚያም ከቀኑ 5፡30 ሰዓት ላይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያመራሉ። ከፕሬዝዳንቱና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ከተሰማም በኋላ ሠላማዊ ሰልፈኛው በመጣበት ሰልፍ ሳይሆን በአመቸው ሁኔታ ወዲያው ወደ ፓርቲው ጽሕፈት ቤት ይመለሳል። በጽሕፈት ቤቱም ውስጥ የሠላማዊ ሰልፍ ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ይካሄዳል።

 

ፓርቲው ሠላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን፤ ፍቃድ የማያገኝ ከሆነ ሰልፉ ላይደረግ እንደሚችል ታውቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ