ወ/ት ብርቱካን የመጎብኘት መብቷ በፍርድ ቤት ተረጋገጠ
ማረሚያ ቤቱ እስረኛዋን ለብቻዋ ማሰር ይችላል ተብሏል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. April 15, 2009)፦ ለሦስት ወራት ከ17 ቀን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በታጣቂዎች ታፍና ወደ ቃሊቲ እስር ቤት የተጣለችው ብቸኛዋ የሴት የፖለቲካ መሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በጠበቃዋ፣ በሐኪሟ፣ በኃይማኖት አባቷ፣ በቤተሰቦቿ፣ በወዳጅ ዘመዶቿና በጓደኞቿ የመጎባኘት መብቷ የተረጋገጠ መሆኑን ዛሬ በአዲስ አበባ የተሰየመው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ መስጠቱ ታወቀ።
በወ/ሪቷ ጠበቃ በኩል ክስ ቀርቦ ”ፌደራል ማረሚያ ቤቶችና ወ/ት ብርቱካን” በሚል መዝገብ በፍርድ ቤት ሲታይ የቆየው ይሄው ክስ ዛሬ ውሳኔ ያገኘ ሲሆን፣ የውሳኔው ግልባጭ በ30 ደቂቃ ውስጥ ደርሶ ለግራ ቀኙ (ከሳሽና ተከሳሽ) እንዲደርስ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ማረሚያ ቤቱ ያቀረበው ስድስት ነጥቦች የያዙትን መከራከሪያዎች ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎ፤ ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ እስረኛዋን ለብቻዋ ማሰር ይችላል ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።
የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል የድርጅቱ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በፍርድ ቤቱ ዙሪያ እንደነበሩ ምንጮቻችን ገልጸው፤ የወ/ት ብርቱካን እናት ወ/ሮ አልማዝ በውሳኔው ተደስተው መታየታቸውን ለማረጋገጥ ችለናል።
የፍርድ ቤቱን ሂደት በሚመለከት ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ አገዛዙን በማናቸውም መልኩ በራሱ ሜዳ ማሳጣት ለወደፊቷ ሀገራችን የፍትህ ግንባታ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስረኛዋ ከእስር እንድትፈታ የሚደረገው ጥረት በየአቅጣጫው መቀጠል እንደሚኖርበትና በእንደዚህ አይነት ውሳኔዎች እንቅስቃሴዎች መገታት እንደማይኖርባቸው ጠቁመዋል።
የውሳኔ ዝርዝሩን ሙሉ ቃል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!



