Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. April 16, 2009)፦ በእስር ላይ ያሉት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ብቻዬን በመታሰሬ የሰብዓዊ ክብሬ ተገፏል ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉን ትናንት መዘገባችን አይዘነጋም። ማረሚያ ቤቱ ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገናኙ አድርጎ ብቻቸውን የማሰር ሥልጣን አለው ሲል የፌደራል የመጀመሪ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘጠነኛ ችሎት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፤ ለሁለተኛው ክስ "በቅርብ ጓደኞቻቸው፣ ዘመዶቻቸው እንዲሁም በሐኪማቸው፣ የሕግ ባለሙያ እና በኃይማኖት አባት የመጎብኘት መብት ባለቤት መሆናቸው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 21 እና በሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 13 ላይ ስለተረጋገጠ ተከሳሽ ለሌሎች እስረኞች ይህንን በሚያከብርላቸው መልክ የከሳሽንም እነዚህ መብቶችን እንዲያከብርና በከሳሽ ላይ የጣለው ክልከላ እንዲነሳ ተወስኗል" በማለት መዝገቡን ዘግቷል። የውሳኔውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

የኮ/መ/ቁ 140618

ቀን፦ 7//8/2001 ዓ.ም.

 

ዳኛ፦ ታገል ጌታሁን

ከሣሽ፦ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጠበቃ ተስፋዬ ደረሰ

ተከሳሽ፦ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሱፐርኢንቴንደንት እናቴነሽ መኮንን

 

መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሽ በ24/7/2001 ጽፎ ባቀረበው መልስ ላይ ያነሳቸው መቃወሚያዎች ላይ ብይን ለመስጠት ነው። በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክር መርምረን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሐ/ቁ. 245 መሠረት የሚከተለውን ብይን ፍርድ ቤቱ ሰጥቷል።

 

ብይን

 1/ ክሡ

ከሳሽ በጠበቃቸው አቶ ተስፋዬ በኩል በ2/7/2001 ዓ.ም. ጽፈው ባቀረቡት የተሻሻለ ክስ ተከሳሽ በከሳሽ ላይ የተሰጠን ቅጣት ለማስፈጸም በሚል ከሳሽ በተከሳሽ ጥበቃ ስር እንዲሆኑ ተደርጓል። ተከሳሽ ከሳሽን ለብቻቸው በማሰር የሰብዓዊ ክብራቸው እንዲነካ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ከሳሽ ከእናታቸውና ከልጃቸው በቀር በሌላ ዘመድ፣ ወዳጅና የሕግ ባለሙያ እንዳይጎበኙ ተከሳሽ የክልከላ ድርጊት ፈጽመዋል። ይህ ክልከላ እንዲነሳ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይስጥልኝ በማለት አመልክተዋል።

 

 2/ መልሱ

ክሱ ለተከሳሽ እንዲደርስና መልስ እዲያቀርብ ታዞ፣ ተከሳሹ በ24/07/2001 ዓ.ም. በተጻፈ ጹሑፉ በሱፐርኢንቴንደንት እናቴነሽ መኮንን በኩል ባቀረበው መልስ የሚከተለውን መቃወሚያዎች አቅርቧል።

 

ሀ/ አቶ ተስፋዬ ደረሰ ከከሳሽ የተሰጠው ውክልና ስለሌለ እንደከሳሽ ጠበቃ ሆኖ ክስ ማቅረብ አይችልም።

 

ለ/ የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ ውሳኔ የሚሰጠው ተከሳሽ ነው። ፍርድ ቤቱ በዚህ የተከሳሽ ሥልጣን ውስጥ ጣልቃ ገብተው ከሳሽ ያቀረቡትን ክስ ለማስተናገድ የሚችሉበት ሥልጣን የላቸውም።

 

ሐ/ ከሳሽ አለኝ የሚሉትን ቅሬታ መጀመሪያ ማቅረብ የነበረባቸው ለታሰሩበት ክፍል ኃላፊ ነበር። ከዚሁ በመቀጠል ደግሞ ከሳሽ ለሚገኙበት ማረሚያ ቤት ኃላፊ ነው። በዚህም ውጤት ካላገኙ ነው የመጨረሻ ውሳኔ ለማግኘት ለተከሳሽ ማቅረብ የነበረባቸው። ከሳሽ ይህንን የአስተዳራዊ መዋቅር ሰንሰለት ሳይከተሉና ተከሳሽ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ውሳኔ ሳያቀርቡ ነው ተከሳሽን በፍርድ ቤት የከሰሱት። ከሳሽ ከፍርድ ቤቱ ውጪ ያሉትን ቅሬታ ማቅረቢያ ዕድሎች ሳይጠቀሙ ያቀረቡት ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል።

 

መ/ ክሱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 314 ላይ በተቀመጠው መሰረት በተፋጠነ ሥነሥርዓት መታየት የሚችል አይደለም።

 

ሠ/ ከሳሽ በተፋጠነ ሥነሥርዓት እንዲታይ ክሱን ማቅረብ አይችሉም እንጂ ይችላሉ ቢባል እንኳን ተፈጸመብኝ የሚሉት ክልከላ ተደርጓል ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ይህ ክስ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ ያለው ጊዜ ሲታሰብ 15 ቀን ስላለፈው ክሱን ማቅረብ አይችሉም ብሎ ተቃውሟል።

 

 3/ ትንታኔ

 

3.1/ መቃወሚያ ቁጥር “ሀ” ላይ

 

ከሳሽ ወ/ት እየሩሳሌም ይልማ ገ/እግዚአብሔር ለተባሉ ግለሰብ በ18/1/98 ዓ.ም. በቁጥር 3150/98 የተጻፈ ውክልና ሰጥተዋል። በዚህ መሰረት የተከሳሽ ወኪል የሆኑት ወ/ት እየሩሳሌም ይልማ ገ/እግዚአብሔር የውክልና ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በ2/6/01 ዓ.ም. የተጻፈ የጥብቅና ውክልና ለአቶ ተስፋዬ ደረሰ ዘውዴ ሠጥተዋል። በዚህ የውክልና ሰነድ ላይ አቶ ተስፋዬ ደረሰ ዘውዴ ከሳሽን ወክለው ክስ ማቅረብ እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል።

 

ይህ ለጠበቃው የተሰጠው የውክልና ሰነድ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 467/97 መሠረት በጽሑፍ ተደርጎ በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ማኅተም የተረጋገጠ ነው። እንዲሁም የከሳሽ ጠበቃ በ24/06/01 ዓ.ም. የተደረገ የጥብቅና አገልግሎት ውል የከሳሽ ወኪል ከሆኑት ወ/ት እየሩሳሌም ይልማ ጋር ሁለት ምስክሮች በተገኙበት ውል ፈጽመው የዚህ ውል ኮፒ በማስረጃት ከዚህ መዝገብ ጋር ተያይዞ ይገኛል። ስለሆነም ከሳሽ በወኪላቸው አማካኝት አቶ ተስፋዬ ደረሰን በጠበቃነት የወከሉ መሆኑን የውልና ሰነዱንና የጥብቅና ውሉ ስለሚያስረዳ አቶ ተስፋዬ ደረሰ ከሳሽን ወክለው ክስ ለማቅረብ የሚችሉበት ውክልና የላቸውም ብሎ ተከሳሽ ያቀረበው መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል።

 

3.2/ መቃወሚያ ቁጥር “ለ” ላይ

 

ተከሳሽ ያቀረበው ሁለተኛ መቃወሚያ የእስረኞችን አያያዝ አስመልክቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው ተከሳሽ ነው። የእስረኞች አያያዝ አስመልቶ ተከሳሽ በፍርድ ቤት አይከሰስም ፍርድ ቤቶችም ጉዳዩን ካዩት ለተከሳሽ በሕግ የተሰጠ ሥልጣን ውስጥ ጣልቀ እንደገቡ ይታያል፤ ስለሆነም ክሱ ውድቅ ሊደረግ ይገባል የሚል ነው።

 

የከሳሽ ጠበቃ በዚህ የተከሳሽ መቃወሚያ ላይ በቃል ለችሎቱ በሰጡት አስተያየት መቃወሚያው በመንግሥት አካላት መካከል ያለውን የሥልጣን ክፍፍል ጽንሰ ሃሳብ የሚጥስ ስለሆነ ውድቅ ይደረግልኝ ብለዋል።

 

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግሥት የፌደራል መንግሥቱ ሲቋቋም ሦስት ቅርንጫፎች ተከፋፍሏል። እነዚህም ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ ናቸው። የመንግሥት አካላት በዚህ መልክ የተከፋሉትን ሕግን ማውጣት መፈጸምና መተርጎም በአንድ አካል ብቻ ቢሠራ (ቡህተ.ሥልጣን) ስለሚፈጥር ይህ አካል ሕገመንግሥቱን አክብሮ በህዝብ የተሰጠውን አደራ መወጣቱን ለመቆጣጠር ስለማያመች ነው። ሥልጣን በአንድ አካል ላይ ቢከማች ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት ሲባል የመንግሥት ሥልጣን በሦስት እንዲከፈል ተደርጓል። እነዚህ ሦስት የመንግሥት አካላት የራሳቸው የሥራ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም፤ እያንዳንዱ አካል የተሰጠውን ሥራ ለመሥራቱ አካላቱ እርስ በርሳቸው ይፈታተሻሉ።

 

ለምሳሌ የሕግ አውጭው አካል ያወጣቸው ሕጎች በትክክል ስለመፈጸማወቸው ለማረጋገጥ የአስፈጻሚው ኃላፊዎች በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 55/17 እና 18 መሰረት እየቀረቡ ሪፖርት እንዲያርጉና አስፈላጊ የመሰለውን ትዕዛዝ ለመስጠት የሕግ አውጪው አካል ሥልጣን ተሰጥቶታል። እንዲሁም ይህ የሕግ አውጪው አካል የሕግ አስፈጻሚውንና ተርጓሚውን አካል ከላይ በተባለው መልክ የሚቆጣጠር ሲሆን፣ የሕግ ተርጓሚው አካል ደግሞ የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 37 በሚፈቅድለት መሰረት በፍርድ ቤቱ መታየት የሚችሉ ጉዳዮችን ለመዳኘት ይችላል። በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 78/1/ ላይ የዳኝነት አካል ነፃ እንዲሆን ተደንግጓል። እንዲሁም በአንቀጽ 79/1/ ላይ ክርክሮች ላይ ዳኝነት የመስጠት ኃላፊነት የፍርድ ቤት መሆኑ ተደንግጓል። ተከሳሽ አንድ የመንግሥት አካል እንደመሆኑ ሕገመንግሥትን ማክበርና ማስከበር አለበት። ተከሳሽ ሕገመንግሥቱን አክብሯል ሊባል የሚችለው ሕገመንግሥቱን መሰረት አድርገው የወጡ ሕጎችንም አክብሮ ሲሠራ ነው።

 

ከሳሽ ያቀረቡት ክስ የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 21 እና የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/99 ላይ የተቀመጡ መብቶችን መሰረት ያደረገ ነው። ተከሳሽ እነዚህ የእስረኞች መብቶች እንዲያስከብር በአዋጅ ቁጥ 365/95 ላይ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ተከሳሽ እንደማንኛውም የመንግሥት አካል ሥራውን ግልጽነትና ተጠያቂነት በተሞላት መልክ ሊሠራ እንደሚገባ የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 12 ይደነግጋል። በእርግጥ የእስረኞችን መብት የማስከበር ሥራ የተከሳሽ ቢሆንም፤ ተከሳሽ ይህንን ሥራው በአግባቡ ከውኗል ወይ? የሚለውን ግን በሕግ አውጪውና በሕግ ተርጓሚው መፈተሽ ይችላል። በአጠቃላይ ስላለው የእስረኞች አያያዝ ለሀገሪቱ ሕግ አውጪ የተከሳሽ ኃላፊዎች ሪፖርት ማቅረብ አለባቸው። አንድ ታሳሪ ደግሞ በተናጠል መብቴ ይከበርልኝ የሚል ከሆነ የሕግ ተርጓሚ ለሆነው ፍርድ ቤት መክሰስ ይችላል። ምክንያቱም ተከሳሽ ተጠያቂነት ስላለበት ነው።

 

ነፃ የሆነ ፍርድ ቤት የተቋቋመበት ዓላማ ሁለት ነው። አንደኛው ግለሰቦች በመንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል የዕለት ተዕለት ሥራ ውስጥ ጣልቃ እየገቡ ሥራ አላሠራም እንዳይሉ ለመከላከል ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በሕገመንግሥቱ ላይ የተረጋገጡ የዜጎች መብቶች በማንም (ተከሳሽን ጨምሮ) እንዳይጣሱና ከተጣሱ እንደዲከበሩ ለማድረግ ነው። በሀገራችን ሕገመንግሥት አንቀጽ 8 ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸው ተረጋግጧል።

 

ይህ ማለት ትልቁ የሥልጣን ባለቤት ተከሳሽ ሳይሆን ህዝቡ ነው ማለት ነው።የህዝቡ ሉዓላዊነት የሚገለጸው ደግሞ በሕገመንግሥቱ ነው። በሀገሪቱ ሕጎች ላይ የተቀመጡ መብቶች ስለመከበራቸው ፍርድ ቤቱ ዘብ ስለሆነ ቅሬታዎችን ማስተናድ አለበት። ተከሳሽ የነበረው በሀገሪቱ ያለው ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ህዝቡ እንጂ ተከሳሹ ባለመሆኑ ተከሳሽ ሌሎች የመንግሥት አካላት እንደሚከሰሱት ሁሉ እርሱም በፍርድ ቤት ሊከሰስ ይችላል። ይህ ደግሞ ሕገመንግሥቱ በከሳሽ ላይ የጣለው የተጠያቂነት መርኅ መገለጫ ነው። ህዝብ ለተከሳሽ የሰጠውን ኃላፊነት የዳኝነት አካል የሆነው ፍርድ ቤት የመቆጣጠር ሥልጣን አለው። ተከሳሽ እንዳለው በፍርድ ቤት የማይከሰስ ቢሆን ኖሮ የሕግ የበላይነት መከበርና የሥልጣን ክፍፍል ዓላማ ጥያቄ ውስጥ ይወድቁ ነበር። ይህ ፍርድ ቤት ህዝብ የጣለበትን ሐቅን፣ ምክንያትንና ፍትህን የማስፈን አደራውን መወጣት የሚችለው፤ መብቴ ተጣሰ የሚል ግለሰብን ቅሬታ አዳምጦ ለፍትህ ጥያቄው ምላሽ ሲሰጥ ነው። ስለሆነም በሕገመንግሥቱ፣ በአዋጆችና በደንቦች ላይ የሰፈሩ መብቶችን መከበርና የተመለከቱ ክሶች በተከሳሹ ላይ ሲቀርቡ ሀገሪቱ የሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ባለቤት እንደመሆኗ መጠን አንዱ የሕገመንግሥታዊ ሥርዓት መገለጫ ተከሳሽ በፍርድ ቤት መከሰስ መቻሉ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ ማየት መቻል አለበት።

 

በልዩ ሕጎች ሥልጣኑ የፍርድ ቤቶች አይደለም ተብሎ ለሌላ አካል እስካልተሰጠ ድረስ እንደተከሳሽ ያሉት የሕግ አስፈጻሚ አካላት ሲከሰሱ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት ይችላል። ይህ ፍርድ ቤት የንብረት መብቶችን ለማስከበር በመንግሥት አካላት ላይ ክስ ሲቀርብ እንደሚመለከተው ሁሉ፤ ከሳሽ ያቀረቡትን ከንብረት መብት የተሻለ ዋጋ ያለውን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር የሚቀርብ ክስን ማየት መቻል ይኖርበታል።

 

ተከሳሽ የሕግ አስፈጻሚው አካል እንደመሆኑ በሕግ የተሰጡትን ሥልጣንና ኃላፊነት ያለማንም ጣልቃገብ ሊሠራ ይገባል። ተከሳሽ በፍርድ ቤቱ ሥራ ጣልቃ እንደማይገባው ሁሉ ፍርድ ቤቱም በተከሳሽ የውስጥ ሥራ ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችልም። ተከሳሽ ባቀረበው መቃወሚያ ላይ ፍርድ ቤቱ በእኔ ሥልጣን ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችልም ብሏል። ጣልቃ መግባት ከቃሉ እንደምንረዳው አንድ አካል በሌላ አካል ሥራ ውስጥ ገብቶ ሲገኝ የሚሰጥ ስያሜ ነው። ፍርድ ቤቱ በዚህ መዝገብ ውስጥ እየሠራ ያለው ግን በሕገመንግሥቱ የተሰጠውን የዳኝነት ሥራ ነው። ፍርድ ቤቱ ይሄን ተግባሩን ሲወጣ ለተከሳሽ የተተዉ በፍርድ ቤቱ መታየት የማይችሉ (non-justiciable) ጉዳዮችን ማየት ይችላል ማለት አይደለም።

 

ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ተከሳሽ በየዕለቱ እኔ የምፈልገው የምግብ አይነት እየሠራ ሊሰጠኝ ይገባል የሚል ቅንጦት አዘል ይዘት ኖሮት ለእስረኞች በየዕለቱ የሚቀርቡ ምግቦችን ምንነት መወሰን ያለበት ተከሳሹ ስለሆነ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት የሚችል አይሆንም። ነገር ግን ክሱ ተከሳሽ በሕግ ላይ ምግብ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎበት ሳለ ሙሉ በሙሉ ምግብ ከለከለኝ የሚል ቢሆን ተከሳሽ ምግብ ለእስረኛ የማቅረብ ግዴታ በሕጉ ላይ ስለተጣለበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት የሚችል (justiciable matter) ይሆናል። ከዚህ አንጻር ከሳሽ በዚህ መዝገብ ያቀረቡትን ክስ ስናየው የሰብዓዊ ክብሬ ተጣሰ፣ የመጎብኘት መብቴ ተነካ የሚል ስለሆነና እነዚህ መብቶች ደግሞ በሕገመንግሥቱና በሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ላይ ስለተቀመጡ የከሳሽ ክስ በፍርድ ቤት መታየት የሚችል (justiciable matter) ይሆናል። በመሆኑም ለፍርድ ቤቱ የቀረበለት ክስ (justiciable matter) በመሆኑ ይህን ለመመልከት የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 37 ስለሚፈቅድለት ፍርድ ቤቱ በተካሽ ሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብቷል ሊባል አይችልም።

 

በአዋጅ ቁጥር 365/95 እና በደንብ ቁጥር 135/99 ላይ ተከሳሽ ስለእስረኞች አስተዳደር መመሪያ ማውጣት እንደሚችል ተደንግጓል። በዚህ መሰረት ተከሳሽ ያወጣቸው መመሪያዎች ካሉት እነዚህ መመሪያዎች አክብሮ ሥራውን እየሠራ መሆኑን ፍርድ ቤቱ መቆጣጠር ይችላል። ይህም ብቻ ሳይሆን ይህ መመሪያ ከእናት አዋጁና ደንቡ ጋር የሚቃረን መሆን አይችልም፤ የሚቃረን ከሆነ የበላይነት ያለው አዋጁና ደንቡ ስለሆነ መመሪያውን ፍርድ ቤቱ ሥራ ላይ ላያውለው ይችላል። በመሆኑም ተከሳሽ ፍርድ ቤቱ የእስረኞችን አያያዝ የሚመለከት ክስ የማየት ሥልጣን የለውም ብሎ ያቀረበው መቃወሚያ ከላይ ባብራራነው መሰረት ውድቅ ተደርጓል።

 

3.3/ መቃወሚያ ቁጥር ”ሐ” ላይ

 

ተከሳሽ ያቀረበው ሦስተኛ መቃወሚያ “ክሱ የአስተዳደር ውሳኔ ክለሳን (administrative review) የሚመለከት እንደመሆኑ ከሳሽ ወደ ፍርድ ቤት ክስ ከማቅረባቸው በፊት ከፍርድ ቤት ውጪ ያሉት ቅሬታ ማቅረቢያ መንገዶች ተጠቅመው ጉዳዩን ለተከሳሽ ስላላቀረቡ ይህ ዕድል ተሟጦ ሳያልቅ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ማየት አይችልም።” የሚል ነው። ለዚህ መቃወሚያ የከሳሽ ጠበቃ በችሎት በሰጡት አስተያየት ከሳሽ የሚገኙት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ ነው። ይህ ማረሚያ ቤት በተከሳሽ ስር የሚተዳደር ተቋም ነው። ከሳሽ ላይ እስር ቤቱ የፈጸመባት ክልከላና የመብት ጥሰት በተመለከተ ኃላፊነቱ የእስር ቤቱ የበላይ ተከሳሽ ነው። ስለሆነም ቃሊቲ ያለው እስር ቤት የራሱ የሕግ ሰውነት ስለሌለው የሚከሰሰው ተከሳሽ ነው። በሕግ የተቀመጠ የቅሬታ ማቅረቢያ መድረክ በተከሳሽ መስሪያ ቤቱ ውስጥ ስለሌለ በቀጥታ ተከሳሽን በፍርድ ቤት መክሰስ እንችላለን፤ ተከሳሽም ቢሆን በከሳሽ ላይ ሰብዓዊ መብት በደል የተፈጸመ መሆኑን ክሱን ከመጥሪያ ጋር ስንሰጠው አውቋል። ክሱ ከደረሰው ጊዜ ጀምሮ 14 ቀናት አልፈዋል። በመሆኑም በዚህ ጊዜ ውስጥ ተገቢው ማጣራት አድርጎ ስለጉዳዩ ተገቢውን ነገር ማድረግ ይችል ነበር። ይህንን ያላደረገው ስለሆነም ክርክሩ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። የተከሳሽ ወኪል ሱፐርኢንተንደንት እናቴነሽ መኮንን በዚህ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ስለጉዳዩ የምናውቀው ነገር የለም፤ እያጣራን ነው፤ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትን ጠይቀን ምላሽ አልሰጠንም ብለዋል።

 

በከሳሽ የቀረበው ክስ የተከሳሽ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲከልስ የሚጠይቅ ነው።የአስተዳደር ውሳኔ ክለሳ (administrative review) ክስ መቅረብ የሚችለው ከፍርድ ቤቱ ውጪ ያሉ የቅሬታ ማቅረቢያ ዕድሎችን ከሳሽ አሟጦ ከተጠቀመ በኋላ ነው፤ በሀገራችን ሕጎች ውስጥ አንድ እስረኛ ተፈጸመብኝ የሚለውን በደል ማቅረብ የሚችልበት ከፍርድ ቤት ውጪ ያለ የዳኝነት ሰጪ አካል የለም። ተከሳሽን ባቋቋመው አ/ቁ 365/95 ላይም እስረኞች ቅሬታ የሚያቀርቡበት ልዩ የዳኝነት አካል የለም። ፍርድ ቤት የሚቀርቡለትን ክሶች በሌላ አካል መታየት ያለባቸው ናቸው ብሎ መመለስ የሚችለው በሕግ በሌላ የዳኝነት አካል የተሰጠን ጉዳይ ነው። ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ለመለየት የተቋቋመ የዳኝነት አካል የለም። እንዲሁም የተከሳሽ ወኪል በችሎት ቀርበው ስለጉዳዩ አናውቅም ነበር ቢሉም ክሱ ደርሷቸው መልስ እስኪሰጡ ድረስ 14 ቀናት ጊዜ ነበራቸው። ይህ ግዜ ደግሞ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘውን የከሳሽን የአስተሳሰር ሁኔታ ለማጣራትና የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቂ ግዜ ነው። ተከሳሽ ግን እነዚህን 14 ቀናት በዝምታ አልፎታል። ይህ ማለት በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ በዝምታ እንደተሰጠ ያስቆጥረዋል። በመሆኑም ከላይ በተብራሩት ምክንያቶች ተከሳሽ ያቀረበው ሦስተኛ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።

 

3.4/ መቃወሚያ ቁጥር “መ” ላይ

 

ተከሳሽ ያቀረበው አራተኛ መቃወሚያ ክሱ በተፋጠነ ሥነሥርዓት መታየት አይችልም፤ ከሳሽ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ.302 መሠረት ቃለመሃላ አላቀረቡም የሚል ነው። ከሳሽ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ.302 መሠረት ቃለመሃላ አቅርበው በመዝገቡ ውስጥ ይገኛል፤ ስለሆነም ቃለመሃላ አልተደረገም ብሎ ተከሳሽ ያቀረበው መቃወሚያ ታልፏል።

 

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ. 314 መሠረት በተፋጠነ ሥነሥርዓት እንዲታዩ የሚቀርቡት ጉዳዮች የመንግሥት አካላት ክልከላ የሚፈጽሙባቸው ጉዳዮች ናቸው። በዚህ አንቀጽ ላይ ከተዘረዘሩት ክልከላዎች ውስጥ ጋብቻ ከማድረግ መከልከል አንዱ ነው። ይህ አንቀጽ የክልከላ አይነቶችን ዘርዝሮ ጨርሶ አይዘጋም (open ended) ነው፤ ጋብቻን ከማድረግ ሲከላከል የሚነካበት ጋብቻው የሚፈጽም የተፈጥሮ መብት አለ። በመሆኑም በዚህ አንቀጽ መሠረት መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ክልከላዎች ይቀርባሉ ማለት ነው። ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ከመብት ጋር በተያያዘ ክልከላ ተፈጸመብኝ የሚል ነው። መብት ላይ የተደረገ ክልከላ ከሆነ ደግሞ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ. 314 መሰረት በተፋጠነ ሥነሥርዓት መቅረብ ስለሚችል የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል።

 

3.5/ መቃወሚያ ቁጥር “ሠ” ላይ

 

ተከሳሽ ያቀረበው የመጨረሻ መቃወሚያ ክሱ ክልከላ ተፈጸመበት ከተባለበት ዕለት 15 ቀን በላይ ስለቀረበ ክስ ማቅረቢያው ጊዜ አልፏል የሚል ነው።

 

ከሳሽ በፍርድ ቤቱ አሻሽለው እንዲያቀርቡ በታዘዙት መሰረት በ2/7/01 ዓ.ም. የተጻፈ ከስ አቅርቧል። በዚህ ክስ ላይ ክልከላው የካቲት 22 ድረስ እንደተፈጸመ ገልጸዋል። ከሳሽ ይህንን መዝገብ የከፈቱት ደግሞ በ27/6/01 ዓ.ም. ነው። ከዚህ ቀን ወደኋላ 15 ቀናት ሲቆጠሩ ከሳሽ ከ13/6/01 ጀምሮ ተፈጸመብኝ የሚሉትን ክልከላ መሰረት አድርገው ክሱን ማቅረብ ይችላሉ። በሌላ አነጋገር ከሳሽ በ22/6/01 ዓ.ም. ተፈጸመብኝ የሚሉትን ክልከላ እስከ 06/07/01 ድረስ ክስ ሊያቀርቡበት ይችላሉ። ክሱን ደግሞ ከ6/7/01 በፊት ነው ያቀረቡት። በመሆኑም ከሳሽ ክልከላ ተፈጸመብኝ ካሉት ቀን በኋላ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ክሱን ስላቀረቡ 15 ቀናት አልፈዋል ብሎ ተከሳሽ ያቀረበውን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።

 

 ፍርድ

 

የከሳሽ ክስ ለብቻዬ እንድታሰር ተደርጌ የሰብዓዊ ክብሬ ተነካ እና በቅርብ ወዳጆቼ እና ጠበቃዬ የመጎብኘት መብቴን ተከልክያለሁ፤ እንዲከበሩ ውሳኔ ይሰጥልኝ የሚል ነው።

 

ተከሳሽ በሰጠው መልስ ላይ ከሳሽ በክሱ ላይ የተዘረዘሩትን ድርጊት አልፈጸምኩም ብሎ አልካደም። በ/ፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ. 234 መሠረት ተከሳሽ መልስ ሲሰጥ በግልጽ ካልካደ በክሱ ላይ የተዘረዘረውን ነገር እንዳመነ ያስቆጥርበታል። ተከሳሽ በሰጠው መልስ ከሳሽ ከእናቷና ከልጇ ውጪ ባሉ ዘመዶቿ ለምን መጎብኘት እንደሌለባት ምክንያቱን አቅርቦ አልተከራከረም እስረኞቹ ምንም እንኳን በፍርድ የተመሰከረላቸው የህዝቡ ጠላቶች (judicially certified enemies of the public) ቢሆኑም የመሰረታዊ መብቶች ባለቤቶች ናቸው። የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 21 እና የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 13 እስረኞች በቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻው እንዲሁም ሐኪም የሕግ ባለሙያና የኃይማኖት አባት የመጎብኘት እንዲሁም ከሌሎች እስረኞች ጋር በእኩል የመታየት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ይህ የሆነው የእስር ቅጣት ዓላማ እስረኞች ማረም ማነጽ መሆኑ ነው። ከሳሽ በክሳቸው ላይ ከእናታቸውና ከልጃቸው ውጭ ሌላ ሰው እንዳይጎበኛቸው ክልከላ ተደርጎባቸዋል። ተከሳሽም ይህንን ክዶ ባለመከራከሩ የክሱ ይዘት እውነት እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ ወስዷል። ተከሳሽ ከከሳሽ በቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው የማይጎበኙበት ምክንያት መኖሩን ተከሳሽ ስለተከራከረና ከሳሽ በእነዚህ ሰዎች የመጎብኘት መብት ስላላቸው ተከሳሽ በከሳሽ የመጎብኘት መብት ላይ የጣለው ክልከላ ሊያነሳ ይገባል።

 

በሌላ በኩል ከሳሽ ለብቻዬ መታሰሬ ሰብዓዊ ክብሬን ይነካል፤ ከሌሎች እስረኞች ጋር አብሬ ልታሰር ይደረግልኝ ብለው የጠየቁ ቢሆንም፤ አንድ እስረኛ ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቅሎ የመታሰር መብት በሕግ አልተረጋገጠለትም።

 

ተከሳሽ እስረኞች ሲያስተዳድር የተጣለበትን አንዱን ግዴታ እስረኞች እንዳያመልጡ መጠበቅ ነው። ተከሳሽ ከሳሽን ለብቻዋ ማሰሬ ለጥበቃ ያስፈልገኛል ብሎ ካመነ ይህንን ከማድረግ የሚከለክለው ነገር ስለሌለ ከሳሽ ብቻዬን መታሬ ሰብዓዊ ክብሬ ተነካ ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።

 

 ውሳኔ

 

1. ተከሳሽ ከሳሽን ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገናኙ አድርጎ ብቻቸውን የማሰር ሥልጣን አለው። ከሳሽ ብቻዬን በመታሰሬ የሰብዓዊ ክብሬ ተገፏል ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል።

 

2. ከሳሽ በቅርብ ጓደኞቻቸው ዘመዶቻቸው እንዲሁም በሐኪማቸው የሕግ ባለሙያ እና በኃይማኖት አባት የመጎብኘት መብት ባለቤት መሆናቸው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገመንግሥት አንቀጽ 21 እና በሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 13 ላይ ስለተረጋገጠ ተከሳሽ ለሌሎች እስረኞች ይህንን በሚያከብርላቸው መልክ የከሳሽንም እነዚህን መብቶች እንዲያከብርና በከሳሽ ላይ የጣለው ክልከላ እንዲነሳ ተወስኗል። መዝገቡም ተዘግቷል።

 

(የዳኛ ፊርማ)

 

ታገል ጌታሁን

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ