የአንድነት ፓርቲ ሠላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው
'ታጋይን በማሰር ትግልን ማቆም አይቻልም!' ሰልፈኞች
ህዝብ በየቦታው ቆሞ እየተከታተለ ነው
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. April 16, 2009)፦ ዛሬ ጠዋት የጀመረው የአንድነት ፓርቲ ሠላማዊ ሰልፍ ብዛት ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በቅርበት እየተከታተሉት ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ሰዓት በቤተመንግሥት አካባቢ በከፍተኛ ድምፅ መፈክሮችን እያሰሙ መሆኑን በስፍራው የሚገኙ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
"ታጋይን ማሰር ትግልን አያቆምም!፣ ፍትህን በዜጎች ህሊና ውስጥ ማፈን አይቻልም!፣ ወ/ት ብርቱካን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትፈታ!፣ ..." የሚሉና በርካታ መፈክሮችን የሚያሰሙት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የአዲስ አበባ ቢሮዎች ኃላፊዎች ቁጥራቸው ከሦስት መቶ በላይ መሆናቸው ታውቋል።
አራት የድርጅቱ አመራሮች ደብዳቤያቸውን ለማስገባት ወደ ቤተመንግሥት የገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሰልፈኞች በቤተመንግሥቱ መግቢያ ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። የሰልፉን ጠቅላላ ሪፖርት ይዘን እንቀርባለን።



