የቴዲ አፍሮ ዘፈኖች በኢግዝቢሽን ማዕከል እንዳይዘፈኑ ተከለከለ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. April 16, 2009)፦ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ዘፈኖች በኤግዝቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ባለው "የአዲስ ፋሲካ የንግድ ትርዒት" ዝግጅት ላይ እንዳይዘፈኑ ተከለከለ።
የክልከላው ትዕዛዝ የተላለፈው የንግድ ትርዒቱ ከመከፈቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሲሆን፤ ይኸው ትዕዛዝ ትርዒቱ ከተከፈተበት ከመጋቢት 30 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።
የአዲስ ፋሲካ 2001 የንግድ ትርዒት ቅዳሜ ሚያዝያ 10 ቀን 2001 የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ በንግድ ትርዒቱ የሙዚቃ ዝግጅት ለሚያቀርቡት የአፍሮ እና የድሪም.ቲ. የሙዚቃ ባንድ ኃላፊዎች ትዕዛዙን ያስተላለፈው የመንግሥት አካል፤ በባንዱ ስር ያሉ ሙዚቀኞች (ድምጻዊያን) የቴዲ አፍሮን ዘፈን መዝፈን አይችሉም። ይህም ትዕዛዝ ተፈፃሚ መሆን አለበት” ማለቱን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ወገኖች ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
እንደምንጮች ዘገባ ከሆነ የቴዲን "ዳህላክ፣ ጃ-ያስተሰርያል፣ እቴጌ እና ላምባዲና፣ …" የተሰኙትን ዘፈኖች በኤግዝቢሽን ማዕከል መዝፈን፤ እየተካሄደ ያለውን አዲስ ፋሲካ 2001 የንግድ ትርዒት ያውካል፣ ስኬታማም እንዳይሆን ያደርጋል። በተያያዘ ዜና በምሽት ክበባት የቴዎድሮስን ሙዚቃ የሚጫወቱ አንዳንድ ወጣት ሙዚቀኞች ከሥርዓቱ አፍቃሪዎች ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሳቸው መሆኑ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለግንቦት 19 ቀን 2001 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የቴዲ ክስ ጉዳይ፣ በሰበር ሰሚ ችሎት በኩል የፊታችን ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. እንደሚታይ ጠበቆቹ አቶ አምሃ በድሉና አቶ ሚሊዮን አሰፋ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።



