ወ/ት ብርቱካን እንዲፈቱ የሚጠይቀው ሰልፍ ያለውጤት ተመለሰ

Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. April 16, 2009)፦ ከምርጫ 97 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈቀደውን ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የአንድነት አመራሮች ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ነበር በአንድነት ቢሮ መሰባሰብ የጀመሩት።

የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ፎቶ የተለጠፈበትና ከመታሰሯ በፊት “ቃሌ” በሚል ርዕስ ስር ጽፋ ካሰራጨችው ውስጥ “እኔ ሁሌም የምኖርለት፣ የምቆምለት፣ አንዳንዴም የምታሰርለትና የምፈታለት ታላቅ ቁምነገር ነው። የሕግ የበላይነት ወይም ሕገመንግሥታዊነት” የተወሰደውን ጽሑፍ በትልቁ ፖስተር ተሰርቶለት ከመፈክሮቹ ጎን ለጎን ተይዟል።

ሰልፈኞቹ ከጽሕፈት ቤታቸው ሲነሱ አንዳንድ ወጣቶች ለመቀላቀል ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ከፓርቲው ፍቃድ ባለማግኘታቸው ወደኋላ ተመልሰዋል። በአብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) አድርጎ ወደ አራት ኪሎ ያቀናው ሰልፈኛ፤ “ወ/ት ብርቱካን ዛሬውኑ ትፈታ፣ ወ/ት ብርቱካንን በማሰር አንድነትን ማዳከም አይቻልም፣ ወ/ት ብርቱካን የህሊና እስረኛ እንጂ ወንጀለኛ አይደለችም፣ …” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን እያሰሙ ወደ አራት ኪሉ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ወዳሉበት ቤተመንግሥት አቅንተዋል።

ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ እና አቶ አስራት ጣሴ አንድ ላይ በመሆን ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ ቤተመንግሥት ገብተው ምላሽ ይዘው እስኪወጡ ሰልፈኞቹ እንዲጠብቃቸው ተናግረው፤ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ወደሚኖሩበት ቤመንግሥት ገቡ። የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤትም የመልዕክተኞቹን ደብዳቤ አልቀበልም በማለት መልሷቸዋል።

አመራሮቹ እስኪመጡለት መፈክር እያሰማ ሲጠብቅ የነበረው ሰልፈኛ፣ አንገታቸውን ደፍተው ያለውጤት የተመሱትን መልዕክቱን ይዘው የሄዱት ሦስቱ አመራሮች የሰጡትን ቀጣይ መመሪያ ተከትለው አራት ኪሎ ወደሚገኘው ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት አምርተዋል። በመንገድ ላይ አንዳንድ ሰዎች ድጋፋቸውን ሲሰጧቸው ተስተውሏል።

በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት መግቢያ ላይ ሰልፈኞቹ ጮክ ብለው ድምፃቸውን በማሰማት መፈክር ማሰማታቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ አሁንም ሦስቱ አመራሮች ወ/ት ብርቱካን በአስቸኳይ እንድትፈታ የሚጠይቀውን ደብዳቤ ይዘው ገብተዋል።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ የተመለሰው ይሄ ቡድን ጠቅላይ ሚንስትሩ በተወካያቸው አማካኝነት የሰጧቸውን ምላሽ ይዘው በመምጣት ለሰልፈኛው በንባብ አሰምተዋል።

መንግሥት የሰጠው መልስ ይዘትም “… ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ይቅርታ አልጠየኩም በማለት በአደባባይ የሰጡትን መግለጫ እንዲያስተባብሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ቢጠይቃቸውም ግለሰቧ ፈቃደኛ የተሰጠው ይቅርታ በማጭበርበር የተገኘ በመሆኑ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለማስከበር ተገዷል። በመሆኑም የእሳቸው ፍርድ እንዲፈጸም ከማድረግ ውጭ መንግሥት ምንም አማራጭ አይኖረውም። ይህ የመንግሥት የፀና አቋም መሆኑን እናስታውቃለን …” የሚል ነው።

ይህ ምላሽ የተነበበለት ሰልፈኛ በኀዘን ስሜት ወደየመጣበት የተመለሰ ሲሆን፣ “ትግላችንን እንቀጥላለን!” የሚለው የአመራሮቹ ተጨማሪ መፈክርም በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ፊት ለፊት ተስተጋብቶ ተሰምቷል።





