የቴዲ አፍሮና የዓቃቤ ሕግ የሰበር አቤቱታ ለችሎት መቅረብ አለመቅረቡን ለመወሰን ለግንቦት 14 ተቀጠረ
ዓቃቤ ሕግ የስድስት ዓመቱ ቅጣት እንዲፀናበት ጠይቋል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. April 22, 2009)፦ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መግቢያ በር ላይ የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እናት ወ/ሮ ጥላዩ አራጌ (ራዬ)ን ጨምሮ በርካቶች የከሰዓት በኋላውን የፍርድ ቤቱ የውጭ በር መግቢያ መከፈትን መጠባበቅ የጀመሩት ገና በጊዜ ነበር።
ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት ተኩል ሲሆን የግቢው በር ተከፍቶ ወደ ውስጥ ቢዘለቅም የችሎቱ በር እስኪከፈት በችሎቱ መግቢያ በር ላይ ፀሐይ እየጠጡ ለሰላሳ ደቂቃ መቆም ግድ ነበር። ችሎቱ ከተከፈተ በኋላም ዳኞች እስኪሰየሙ ለአንድ ሰዓት ያህል በትዕግስት ከጠበቅን በኋላ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን የመሐል ዳኛ መስፍን ዕቁበዮናስ፣ የቀኝ ዳኛ ተሻገር ገ/ሥላሴ እና የግራ ዳኛ አብዱራሂም አህመድ ተሰየሙ። ነግር ግን ሌሎች መዝገቦችን እያነሱ በመጥራት ውሳኔዎችን በመስጠት የቴዲን ጉዳይ ለመመልከት በችሎት የተገኘውን ሰው ልብ አንጠልጥለው ቆዩ።
በግምት ወደ 10 የሚሆኑ መዝገቦችን ጉዳይ ከተመለከቱ በኋላ፤ “ቴዎድሮስ ካሳሁን” ሲሉ ተጣሩ። ችሎት ታዳሚው የቴዲን መምጣት ቢጠባበቅም በዚህ ችሎት የሚቀርብበት ሥነሥርዓት ባለመኖሩ ጠበቆቹ አቶ ሚሊዮን አሰፋና አቶ አምሃ በድሉ ቀረቡ። ክሱን ከስር ፍርድ ቤት ጀምሮ የሚሞግተው ዓቃቤ ሕግ ፍቃዱ ፀጋም በችሎት መገኘቱን አስመዘገበ።
መዝገቡ የተቀጠረው ሁለቱም ወገኖች የሰበር አቤቱታ በማቅረባቸው መጋቢት 24 በተቀጠረው መሰረት ለጉዳዩ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲያመች ሁለቱን በአንድ ቀን ለማየት በመሆኑ፤ እንደ አቤቱታ አቀራረባቸው ቅደም ተከተል ዓቃቤ ሕግ ቀድሞ እንዲያቀርብ ተፈቀደለት።
ዓቃቤ ሕግ በሦስት ዳኞች ለተሰየመው የሰበር ቅሬታ ሰሚ ችሎት ሲያቀርብ፤ “በከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ በስድስት ዓመት ጽኑ እስራት እና በ18 ሺህ ብር የተቀጣው ተከሳሹ ቴዎድሮስ ካሳሁን ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ “ጥፋተኛ ልባል አይገባም” እንጂ፤ “የተሰጠው ቅጣት ይቅለልልኝ” የሚል አይደለም፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ በራሱ የቅጣት ማቅለያ አቅርቦ ቅጣቱን ሊቀል አይገባም።
“ቅጣቱን እንዲቀልለት የጠቀሰው የቅጣት ማቅለያ ሃሳብ ሟች መጀመሪያውኑ መሃል መንገድ ላይ ወድቆ ለግጭቱ አስተዋጾ አድርጓል የሚል ነው፤ ይህ ደግሞ የክሳችን ዋና ጭብጥ ነው። ይህ እንደምክንያት ቢወሰድ እንኳን ሟች የወደቀው ከካሳንችስ ወደ አራት ኪሎ የሚወስደው መንገድ ላይ ሲሆን፣ ተከሳሽ የገጨው ደግሞ ከአራት ኪሎ ወደ ካሳንችስ በሚወስደው መንገድ ከዋናው መንገድ 50 ሳንቲ ሜትር ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ነው።
“ክሳችን የሚለውም ሆነ በማስረጃ ያስረዳነው ተከሳሽ መኪና ለማሽከርከር የሚያስችል መንጃ ፍቃድና ሞያ ሳይኖረው መኪና በማሽከርከር ሰው ከገጨ በኋላ የገጨውን ሰው ሳይረዳና በመጨለሙ ምክንያት ሌላ ሰው ሊረዳው እንደማይችል እያወቀ የጭካኔ ተግባር ፈጽሟል የሚል ነው። ይህን በቸልተኝነት የተፈጸመ ተግባር ፍርድ ቤቱ እንደ ቅጣት ማቅለያ ሊያየው አይገባም” ሲል ዓቃቤ ሕግ ተከራክሯል።
ዓቃቤ ሕግ “ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ባልተጠየቀበት ሁኔታ መዝገቡን ሲመረምር የቅጣት ማቅለያ ባገኘ ጊዜም ሊመረምር የሚገባው የቅጣት ማቅለያውንም ማክበጃውንም ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ይህን አላደረገም። ይልቁንም የፍትህ ሥርዓቱን ተገማች ሊያደርግ በሚችል ሁኔታ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ክስና የድርጊት አፈጻጸም የስር ፍርድ ቤቱ ሰባት ዓመት የወሰነውን ስድስት ዓመት በመወሰን ቅጣት አቅልሏል። ነገር ግን በዚህ መዝገብ በተለየ ሁኔታ ከስድስት ዓመት ወደ ሁለት ቀንሶ ከፍተኛ የሕግ ስህተት ፈጽሟል። ቅጣት እንዲቀል ባልተጠየቀበት ሁኔታ ቅጣቱን ማቅለል ቢፈልግ እንኳን ለሁለቱም ተከራካሪ ወገኞች በሚጠቅም መልኩ መጀመሪያ ቅጣቱን አክብዶ ከዛ ወደ ማቅለል ይሄዳል እንጂ፤ ከቅጣት መነሻው ዝቅ ብሎ ሊወስን አይገባም ነበር። ይህን ባለማድረጉ በዚህ አቤቱታ ፍርድ ቤቱን የምንጠይቀው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅጣቱን የቀነሰው አላግባብ ነው ተብሎ ቅጣቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በወሰነው በስድስት ዓመት እስርና በ18 ሺህ ብር ይጽናልን” ሲል ጠይቋል።
ቀጣዩን የሰበር ቅሬታ ያቀረበው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ሲሆን፤ የሰበር ቅሬታ ለማቅረብ ያበቃቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የካቲት 11 ቀን 2001 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ እንደሆነ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ፈጽሟል ያላቸውን የሕግ ስህተቶች በዝርዝር አቅርቧል።
በአንደኝነት ያቀረበው፤
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረብነውን ይግባኝ ያየው እንደ ይግባኝ ሰሚ ችሎትነቱ በአመልካች የቀረቡትን የይግባኝ ቅሬታ ነጥቦች በዝምታ በማለፍ የድጋሚ ዳኝነት (re-trial) አቤቱታን ተቀብሎ እንደሚመለከት ወይም እንደመጀመሪያ ፍርድ ቤት በመሆን የሰጠው የጥፋተኝት ውሳኔ የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 20/6፣ የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 181፣ 185 እና 195 ድንጋጌዎች በግልጽ የሚቃረን መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞብናል ብሏል።
ሁለተኛው የቅሬታ ምክንያት፤
የስር ፍርድ ቤት የመጀመሪያው ፍርድ ቤት ሟች የሞተበት ቀን በ23/2/99 ዓ.ም. በማለት የደረሰበትን መደምደሚያ የፍርድ ቤት ማስረጃ እንዲሆን ብይን ያልተሰጠበትን ቁጥር 4777/44/2000 በሆነው ማስረጃ ላይ ተመስርቶ፣ ሕጋዊውና በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 124 እና 142 መሠረት የቀረበውን ቁጥር 856/44/99 የሐኪም ማስረጃ እንዳልቀረበ በማለፍ ለሐኪም ማስረጃው ሁለት መለኪያ (double standard) በመጠቀም፣ በአመልካች የመከላከያ ምስክርነት ቀርበው ቁጥር 477/44/2000 የሆነው ማስረጃ የተሳሳተ ማስረጃ መሆኑንና ማንኛውም ሰው የሞተበትን ቀን እና ለሞት ያበቃውን ምክንያት በሣይንሳዊ ትንተና ላይ በተመሠረተ የአስክሬን ምርመራ ባለሙያ የሚረጋገጥ መሆኑን፤ አስክሬን ያልመረመረ ባለሙያ ሟች የሞተበትን ቀንም ሆነ ለሞት ያበቃው ምክንያት በተመለከተ የሙያ ምስክርነት መስጠት አይቻልም በማለት የሰጡትን የሙያ ምስክርነት በማለፍ በቁጥር 856/44/99 የሐኪም ማስረጃ ላይ የተገለጸው ሟች ሕይወቱ ያለፈበት ቀን 22/2/99 ዓ.ም. ነው የሚለው ምስርነት የሐኪም ማስረጃውን የሰጠው ሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ዋና መዝገብ ትክክለኛ ግልባጭ መሆኑን የሚያረጋግጠው ግዙፍ የሰነድ ማስረጃ በማለፍ፤ በሐኪም ማስረጃው በግልጽና በማያሻማ አኳኋን የተገለጸውን ሟች የሞተበት ቀን የሚለውን ፍሬ ነገር የሟች አስክሬን ወደ ሆስፒታል የመጣበት ቀን ወደሚል የሐኪም ማስረጃው ላይ የትም ቦታ ወዳልተገለጸ ፍሬነገር በመቀየር እና አመልች ባቀረባቸው በዚህ የይግባኝ የቅሬታ ነጥቦች ላይ የይግባኝ ሰሚ ዳኝነት ሳይሰጥ ጉዳዩን በመጀመሪያ የዳኝት ሥልጣን ተመልክቶ ሟች ደጉ ይበልጣል ሕይወቱ ያለፈው በ23/2/99 ዓ.ም. ነው ማለቱ የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 20/6፣ የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 181፣ 185 እና 195 ድንጋጌዎች በግልጽ የሚቃረን መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞብናል ሲል መከራከሪያው አቶ ሚሊዮን አቅርቧል።
ሦስተኛው የቅሬታ አቤቱታ
እንደጠበቃው አነጋገር፤ ምልባትም በኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ እና ወሳኝ የሆነ የመብት መዛባት የፈጠረ ውሳኔ ያለው ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የሰነድም ሆነ የሰው ምስክር ተከሳሹን ቴዎድሮስ ካሳሁንን መኪናውን እያሽከረከረ ሲገጭ አየነው ተብሎ ባልተመሰከረበት ሁኔታ፤ “… በአደጋው ጊዜ ሌላ ሰው ያሽከረክር እንደነበር አቅርቦ ያልተከላከለ በመሆኑ አደጋውን ያደረሰው እሱ ነው …” በማለት ያልተመሰከረበትን ፍሬ ነገር አልተከራከረም ብሎ የገጨነው ብሎ መወሰን በወንጀል ፍትህ ሥርዓት ጸንቶ የቆየውን “ተከሳሾች ከሳሻቸው በማስረጃ ያላረጋጠባቸውን ፍሬ ነገር የመከላከል ግዴታ የለባቸውም የሚለውን መርኅ እና የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 20/3 ድንጋጌን በግልጽ የሚቃረን መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ብሏል።
አራተኛው ቅሬታም፤
ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤት አቅርቦ ያስመሰከራቸው ሁለት ፖሊሶችም ሆነ በጣቢያ የሰጠው ነው ተብሎ ከመዝገቡ ጋር የተያያዘው የአንድ ፖሊስ ቃል የሚለው አደጋውን ያደረሰውን መኪና ታርጋማየታቸው ሲሆን፣ ራሱ ፖሊስ ደንበኛዬን ባሰረበት ወቅት በ24/2/99 ለፍርድ ቤት ያቀረበው የጊዜ መጠየቂ የሚለው ፖሊሶቹ የአደጋ አድራጊን መኪና ያላዩና አንድ ታክሲ ተከታትሎ ታርጋ እንዲያመጣላቸው ሲጠይቁት ተከታሎ ሄዶ ታርጋ ብቻ ሰጥቷቸው አድራሻውን ሳይሰጣቸው ስለሄደ ባለታክሲውን እስኪያገኙ ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀበትን እነሱ ለፍርድ ቤት ያቀረቡትን የሰነድ ማስረጃ ፍርድ ቤቱ ያለአንዳች ምክንያት ውድቅ ማድረጉ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ነው ብለው እንደሚያምኑ ዘርዝሯል።
የአደጋውን አፈጻጸምና ቦታም በተመለከተ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች አንደኛው ሟች በወደቀበት መኪናው ጨፍልቆ ገደለው ሲል፣ አንደኛው ደግሞ ሟች ከጓደኛው ጋር እየተጓተቱ ሲሄዱ ወደቀና የመኪናው አፍንጫ መታው የሚሉ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ምስክርነቶች ተቀባይነት ማግነታቸው አግባብ አለመሆኑን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ስናቀርብ፤ ጥያቄውን በማለፉ የሕግ ስህተት ተሰርቷል እንደሚሉ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ እነኚህን ሁሉ መከራከሪዎች ተመልክቶ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንን በነፃ እንዲያሰናብትላቸው፤ ይህ ቢታለፍ ደግሞ ፍርድ ያሉትን የቅጣት ማቅለያ ተጠቅሞ እስካሁን የታሰረው በቂ ነው ብሎ እንዲያሰናብታቸው ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም ለሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች የማጣሪያ ጥያቄ ካቀረበ በኋላ መዝገቡ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም የሚለውን ለመወሰን ለግንቦት 14 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል።
“ያስቀርባል” ካለ ሁለቱም ወገኖች ቀርበው ይከራከሩና ውሳኔ ይሰጣል። “አያስቀርብም” ከተባለ ግን ከዚህ በኋላ ምንም ክርክር አይኖርም። ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ፀንቶ ከአራት ወራት በኋላ ቴዲ ይፈታል።



