ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ አስከሬኑን ተሰናበተ

በኢትዮጵያ የቀብር ታሪክ ከፍተኛው ህዝብ የተገኘበት ነበር

የክቡር ዶ//ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሥርዓተ ቀብር፣ ሚያዝያ 15 ቀን 2001 ዓ.ም.

Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. April 23, 2009)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በተለምዶ ፒኮክ በሚባለው ቦታ በሚገኘው የዝነኛው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ መኖሪያ ቤት ገና ከጠዋቱ በሰው ተጨናንቋል። “ቤተል” የተባለው የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት የቀብር ሥነሥርዓቱ ያማረ እንዲሆን ሽርጉድ ይዘዋል። ከቀኑ አምስት ሰዓት ተኩል ሲሆን አስክሬኑን ከቤቱ አጅቦ ለማውጣት በተፈጠረው የሰው ብዛት ምክንያት እጅግ አስቸጋሪ ነበር። (ከላይ ያለው ፎቶግራፍ ላይ በግራ በኩል ተደግፈውና አጎንብሰው የሚያለቅሱት የክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ የቀድሞ ባለቤቱና የሁለት ልጆቹ እናት ወ/ሮ ማርታ ናቸው)

 

 

The funeral of Tilahun Gessese, 20090423

አስክሬኑን ወደ መስቀል አደባባይ መውሰድ የግድ በመሆኑ፤ ጥቁሩን የአስክሬን መኪና ለማጀብ የተዘጋጁ፣ ጥቁር በጥቁር የለበሱ አርቲስቶችና ክንዳቸው ላይ ጥቁር ሪቫን ያሰሩ አድናቂዎችና ዘመድ ወዳጆች በኢትዮጵያ ባንዲራ የተሸፈነ ፎቶግራፉን ይዘው ከፊት እና ከኋላ አስክሬኑንን ሲያጅቡ ቁጥሩን ለመገመት የሚያስቸግር ህዝብ ከፊት ከኋላና ከግራና ከቀኝ በመሆን ይከተል ነበር።

 

በዚህ ሁኔታ እየተጓዘ የመጣው አስክሬን ከቦሌ ወደ አብዮት አደባባይ እየቀረበ ሲመጣ እጅግ ለዓይን በሚማርክ ሁኔታ የተሰለፈው ማርሽ ባንድ አስክሬኑን በአጀብ ተቀብሎ መስቀል አደባባይ ወደ ተዘጋጀለት የክብር ስፍራ አደረሰው።

 

የክቡር ዶ//ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሥርዓተ ቀብር፣ ሚያዝያ 15 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

በመስቀል አደባባይ አስክሬኑን ለመሰናበት የወጣውን ሰው ሚያዝያ 30 ለቅንጅት ሰልፍ የወጣው ሰው 3 ሚሊዮን ከመገመቱ ጋር ንጽጽር ውስጥ ቢገባ ቁጥሩ ወደ 500 ሺህ (ግማሽ ሚሊዮን) ሊጠጋ የሚችል ነው።

 

The funeral of Tilahun Gessese, 20090423የክቡር ዶ//ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሥርዓተ ቀብር፣ ሚያዝያ 15 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

አስክሬኑ በቤተሰቦቹ ታጅቦ ወደ መድረኩ በሚወሰድበት ወቅትም የተሰበሰበው ህዝብ በለቅሶና በዜማ በማጀብ ኀዘኑን ገልጿል። በመስቀል አደባባይም ቤተሰቦቹ፣ አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ ሼክ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲን የተገኙ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመካነ መቃብሩ ላይ በተወካዮቻቸው አማካይነት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

 

 

The funeral of Tilahun Gessese, 20090423
 

 

በመስቀል አደባባይ የሕይወት ታሪኩ ከተነበበና ጥላሁን አዲስ በሚያስቀርጸው አልበም ውስጥ ሊያካትተው አዘጋጅቶት የነበረውን “ምስጋና” የተሰኘ አዲስ መዝሙር አርቲስት በመሐሙድ አህመድ፣ በአርቲስት ንዋይ ደበበ እና በልጁ ዳንኤል ጥላሁን አቀንቃኝነት በአበጋዙ ሺፈታ አቀናባሪነት አዘጋጅተውት እንዲሰማ አድርገዋል።

 

 

የክቡር ዶ//ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሥርዓተ ቀብር፣ ሚያዝያ 15 ቀን 2001 ዓ.ም.
 

 

በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለአርቲስቱ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ኀዘን በተወካያቸው አማካይነት ገልጸዋል። በኀዘን መግለጫው ላይ እንዳሉት አርቲስቱ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ በሕይወት ዘመኑ ባበረከተው አስተዋጽኦ ሀገራችን ከምትኮራባቸው ስመጥር ሰዎች መካከል እንደሚገኝ፣ አርቲስቱ በሀገራችን ሙዚቃ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል።

 

The funeral of Tilahun Gessese, 20090423

ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው በክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሞት የተሰማቸውን ኀዘን ለቤተሰቦቹ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል።

 

 

የክቡር ዶ//ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሥርዓተ ቀብር፣ ሚያዝያ 15 ቀን 2001 ዓ.ም.
 

 

የአርቲስቱ አስከሬን በኢትዮጵያ ባንዲራ ተሸፍኖ ከመስቀል አደባባይ ደርሶ ህዝቡን ከተሰናበተው በኋላ በሠረገላ ሆኖ ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማምራት በስፍራው ደርሶ ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል። የታዋቂው የሙዚቃ ንጉሥ የአርቲስት ጥላሁን ሥርዓተ ቀብር በኢትዮጵያ ታሪክ በቀባሪ ህዝብ ብዛትም ሆነ ባገኘው የሚዲያ ሽፋን በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅና በታሪክ ማስታወሻ የሚቀመጥ ሆኖ አልፏል። (የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል የአርቲስቱን ሥርዓተ ቀብር ዝርዝርና ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሚዲያዎች ያገኘውን ሽፋን ከነይዘቱ በቀጣይ ለማስነበብ እንሞክራለን)

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ