ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳአንድ ዘመዷና ሹፌሯ ብቻ ተፈቅዶላቸዋል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሚያዝያ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. April 25, 2009)፦ ለሦስት ወራት ከ17 ቀን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በታጣቂዎች ታፍና ወደ ቃሊቲ እስር ቤት የተጣለችው ብቸኛዋ የሴት የፖለቲካ መሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በጠበቃዋ፣ በሐኪሟ፣ በኃይማኖት አባቷ፣ በቤተሰቦቿ፣ በወዳጅ ዘመዶቿና በጓደኞቿ የመጎብኘት መብቷ የተረጋገጠ ቢሆንም የምትገኝበት ቃሊቲ የሚገኘው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ዛሬም ጠያቂዎቿን ማስገባት ከለከለ። የአክስቷ ልጅ እና ሹፌሯ ብቻ ተፈቅዶላቸዋል።

 

ክልክላ እንዲነሳ በጠበቃዋ አማካኝነት ክስ የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘጠነኛ ፍትሐብሔር ችሎት ሚያዝያ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፤ ወ/ት ብርቱካን በጠበቃዋ፣ በሐኪሟ፣ በኃይማኖት አባቷ፣ በቤተሰቦቿ፣ በወዳጅ ዘመዶቿና በጓደኞቿ የመጎብኘት መብቷ እንዲረጋጥ ከወሰነ በኋላ የውሳኔው ግልባጭ በ30 ደቂቃ ውስጥ ለግራ ቀኙ (ከሳሽና ተከሳሽ) እንዲደርስ ትዕዛዝ የሰጠና እንደተባለውም ትዕዛዙን ሁለቱም ወገኖች የወሰዱ ቢሆንም፤ ባለፈው ሣምንት ቅዳሜ ሚያዝያ 10 ቀንና እሁድ ሚያዝያ 11 ቀን ሊጠይቋት ከሄዱት በርካታ ሰዎች መካከል ሁለት ሰዎች ብቻ ፈቅደው ለሌሎቹ ውሳኔ አልደረሰንም በማለት ሳይፈቅዱ ቀርተዋል።

 

ክልከላውን በቅን ልቦና የተመለከቱ ጠያቂዎች ትዕዛዙ የተሰጠበትን የጊዜ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት “እውነትነም ማረሚያ ቤቱ አልደረሰው ይሆናል” የሚል ግምት ወስደው የነበረ ቢሆንም፤ ከአንድ ሣምንት በኋላም በዛሬው ዕለት (ሚያዝያ 17 ቀን 2001 ዓ.ም.) ከእናቷና ከልጇ በተጨማሪ የአክስቷ ልጅ እና ሹፌሯ ብቻ ተፈቅዶላቸው ገብተው ጠይቀዋታል።

 

የወ/ት ብርቱካን ጠበቃ አቶ ተስፋዬ ደረሰ ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አልደረሰው ይሆናል በሚል ለማድረስ አስበው ግልባጩን ፍርድ ቤት ሲጠይቁ፤ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ነገረ ፈጅ ሚያዝያ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. እንደወሰዱ እንደተገለጸላቸው ጠቁመው፤ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የማይፈጸም ከሆነ በቀጣይ የአፈጻጸም መዝገብ እንደሚከፍቱ ተናግረዋል። በዛሬው ዕለት ገብተው የጠየቋት የወ/ት ብርቱካን ቤተሰቦች ጤንነቷ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ምንም አይነት የተስፋ መቁረጥ ስሜት በፊቷ ላይ እንደማይነበብ ገልጸዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ