የስዊድን የአንድነት ድጋፍ ማኅበር ለዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ የመታሰቢያ ዝግጅት አደረገ
በወዛደሮች ቀን ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትፈታ በኢትዮጵያውያን ሰልፍ ይደረጋል
By Matias Ketema (Sweden)
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. April 28, 2009)፦ የስዊድን የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር ቅዳሜ ሚያዝያ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. (አፕሪል 25 ቀን 2009) ቀን ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠን በማሰብ ዝግጅት አደረገ።
በዕለቱ የድጋፍ ማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ የራስወርቅ መንገሻ ዶ/ር ጥላሁን የህዝብ ልጅ የሀገሪቷም አብረቅራቂ ኮከብ እንደነበር፣ ሥራውም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ዘለዓለም ተቀርጾ እንደሚቀመጥና የህዝብ አዕምሮም ምንጊዜም እንደማይዘነጋው ገልጸው፤ ፀሎት እንዲደረግለት ባሳሰቡት መሰረት በተሰብሳቢው የህሊና ፀሎት ተደርጎለታል።
ከዚህ በተጨማሪ አቶ አበበ ኃይሉ የስዊድን የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባልና የስቶክሆልም ከተማ አስተዳደር አባል በቦታው በመገኘት በመጪው ዓርብ ሜይ 1 ቀን 2009 (ሚያዝያ 25 ቀን 2001 ዓ.ም.) በሚከበረው የዓለም ወዛደሮች ቀን ላይ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትፈታ የሚጠይቁ የአንድነት ፓርቲ አባላት፣ ደጋፊዎች እና ሀገር ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጭምር እንዲገኙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ይህ ሰልፍ እንዲደረግ እንዴት እንደተፈቀደ ለአቶ አበበ ኃይሉ ከኢትዮጵያ ዛሬ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ሰልፉ ላይ ኢትዮጵያውያን እንዲወጡ የተፈቀደው በእሳቸውና በኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ኮሚቴ አሳሳቢነት እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚሁ ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያውያኑ የወ/ሪት ብርቱካን ምስል ያለበትን ካኒተራ በመልበስ፣ መፈክሮችንና የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ በመያዝ እንደሚወጡ ታውቋል።
አቶ አበበ ኃይሉ በማያያዝም ሰልፈኛው 12፡00 ሰዓት (ስድስት ሰዓት - በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር) በሰገርቶርየት ይገናኛል። ከዚያም ወደ ሁመልስጎርደር ያቀናል። በመቀጠልም ከሁመልስጎርደር ወደ ኖርባንቶርየት አደባባይ እንደሚጓዝና በቦታውም ላይ የሠራተኛው ማኅበር ሊቀመንበር ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን ንግግር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የፓርላማ አባልና የውጭ ጉዳይ ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ካሪና ሄግ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ወቅት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ለመጠየቅ ያደረጉት ሙከራ በባለሥልጣኖች ተጽዕኖ ሊሳካ አለመቻሉን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ያዩትን የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉድለቶች ለሁሉም የፓርላማ አባላት በማስረዳት ከፓርቲዎቹ የተውጣጣ የወ/ሪት ብርቱካንን ጉዳይ የሚከታተልና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትፈታ የሚንቀሳቀስ ኮሚቴ አቋቁመዋል።
በተጨማሪ በኢትዮጵያ የታዘቡትንና የተመለከቱትን ሁሉ በደብዳቤ በማስፈር ለስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ለካርል ቢልት ማቅረባቸውን ለመረዳት ችለናል።
ወ/ሮ ካሪና ሄግ ምንም እንኳን ወ/ሪት ብርቱካንን ለማግኘት ባይችሉም እስር ቤት ድረስ በመሄድ መልዕክት እንደተዉና እናትየዋን ወ/ሮ አልማዝ ገ/እግዚአብሔርን እንዳነጋገሩ መዘገባችን አይዘነጋም።



