ማረሚያ ቤቶች በወ/ት ብርቱካን መብት ላይ የተሰጠውን ውሳኔ እንዲፈፀም መጥሪያ ተላከለት
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም. May 9, 2009)፦ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሚያዝያ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍትሐብሔር ችሎት እንደማንኛውም እስረኛ እንዲጉበኙ ያስተላለፈው ውሳኔ ሳይከበር 23 ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ጠበቃው አቶ ተስፋዬ ደረሰ ይህን በማስመልከት ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሐብሔር ችሎት ውሳኔው ይፈፀም ሲሉ አቤት በማለታቸው፤ ተከሳሹ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ውሳኔውን ፈፅሞ እንዲቀርብና የማይፈፀምበት ምክንያት ካለም ቀርቦ እንዲያስረዳ መጥሪያ ተልኮለታል።
ወ/ት ብርቱካን ከእናታቸውና ከልጃቸው ውጪ ማንም እንዳይጎበኛቸው መከልከሉ፤ አግባብ አለመሆኑን በመግለፅ በጠበቃቸው አማካኝነት ቀርበው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ ፍርድ ቤቱ፤ በቤተሰቦቻቸው፣ በጓደኞቻቸው፣ በጠበቆቻቸው፣ በኃይማኖት አባታቸው በአጠቃላይ በወዳጅ ዘመዶቻቸው መጎብኘት ማንም ሊነካባቸው የማይችል መብታቸው እንደሆነ በመግለፅ ወስኖላቸዋል።
ወ/ት ብርቱካን ለብቻቸው መታሰራቸው አግባብ አለመሆኑን ያቀረቡትን ክስ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረጉ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን፣ በመብታቸው ላይ የተፈፀመውን ጥሰት አስመልክቶ ባቀረቡት ክስ ላይ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ባለመፈፀሙ እንዲፈፀምላቸው መዝገብ ከፍተዋል።
የአፈፃፀም መዝገቡ የደረሰው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፤ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ወ/ት ብርቱካን በተፈቀደላቸው መሰረት በወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲጎበኙ እንዲያደርግና ይህን ውሳኔ ካላስፈፀመም ያላስፈፀመበትንም ምክንያት እንዲያስረዳ ለግንቦት 18 ቀን 2001 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቶታል።



