Teddy AfroEthiopia Zare (ማክሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2001 ዓ.ም. May 12, 2009)፦ አቶ አዲስ ገብሩ የተባሉ ሠዓሊ፣ ሥዕሎቼ ያለ ፈቃዴ በሰለሜ ክሊፕ ውስጥ ተካተውብኛል በሚል ባቀረቡት አቤቱታ፣ በፌደራል ዓቃቤ ሕግ አማካኝነት በአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንና በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤት ላይ የቀረበውን ክስ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተመልክቶ በነፃ ቢያሰናብተውም፤ በይግባኝ የቀረበለት ፍርድ ቤት እንዲከላከል ወስኖ፣ መዝገቡን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመልሶ የነበረ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት (ማክሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2001 ዓ.ም.) ሁለቱም ተከሳሶች በነፃ ተሰናበቱ።

 

ዛሬ ጧት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ወንጀል ችሎት በክርክሩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ሲሰየም፣ ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ለቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ጠበቃ ቴዎድሮስ ሞሲሳ (ድምፃዊው) ደግሞ ለኤሌክትራ ሙዚቃ ባለቤት ለሆኑት ለአቶ ተሾመ የቀረቡ ሲሆን፤ ዳኛ ብርሃነመስቀል ዋግሬ ሁለቱንም ተከሳሾች በነፃ የሚያሰናብት ውሳኔ ሰጥተዋል።

 

ተከሳሾች አቶ ቴዎድሮስ እና አቶ ተሾመን የስር ፍርድ ቤቱ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ይሰናበቱ ብሎ ውሳኔ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ውሳኔ በመስጠቱ ፍርድ ቤቱ የሚመረምረው ተከላክለዋል ወይም አልተከላከሉም የሚለውን ጭብጥ እንደሆነ ዳኛው ገልፀዋል።

 

በዚህ መሰረት ተከሳሾቹ ባቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ አንደኛው ምስክር ሠዓሊው አቶ አዲስ ገብሩ ሲሆኑ፤ “ሥዕሎቼ ያለ ፈቃዴ በሰለሜ ክሊፕ ውስጥ ተካተውብኛል” በሚል ክስ ያቀረቡባቸው ሥዕሎች፣ ከፎቶ ላይም ሆነ ከሞዴል ላይ ያላነሱት የራሳቸው የፈጠራ ውጤቶች መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2003 ባወጣው ካላንደር ላይ አሳትሞ እንዲያወጣውና፣ በአንዳንድ ምርቶቹም ላይ አትሞ እንዲያወጣው ፈቅደው የተዋዋሉ መሆናቸውን፣ አየር መንገዱም ካላንደሩን በነፃ ለህዝብ ማሠራጨቱን፣ በዋናው የሥዕል ሥራው ላይ ፊርማቸው እንዳለና በክሊፑ ላይ ሆን ተብሎ እንደተቆረጠባቸው በመጥቀስ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

 

አቶ ታምራት ኪዳነማርያም የተባሉ የሕግ ባለሞያና፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዕምሮአዊ ንብረት ሕግ ላይ የሠሩት ሁለተኛው ምስክር የሙያ ምስክርነት የሰጡ ሲሆን፣ ምስክሩም ስለ ቅጂና አጎራባች መብቶች ምንነት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

ሦስተኛው ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ሲሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ባቀረበው የማጣሪያ ጥያቄ በሥዕል ሙያ ያላቸውን እውቀት ተጠይቀው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥነ-ጥበብ ት/ቤት መማራቸው፣ በውጭ ሀገር ለሰባት ዓመታት፣ በሥዕል ሞያ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለ23 ዓመታት በኃላፊነት ማገልገላቸውን፣ በአዲስ አበባ ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት መምህር ሆነው ማገልገላቸውንና በአሁኑ ሰዓት የኢንላይትመንት አርት አካዳሚ መምህር መሆናቸውን አስረድተዋል።

 

በሰጡት ሞያዊ ምስክርነትም ሥዕል የፈጠራ ሥራ ነው የሚባለው፤ አንደኛ፦ ከራሱ ሃሳብ አመንጭቶ እንደ ማንኛውም የጥበብ ሥራ ሲሠራ፣ ሁለተኛ፦ ሞዴል የሆነ ሰው አስቀምጦ ተፈጥሮን ተመርኩዞ ሲሠራ፣ ሦስተኛ፦ ከሱ ካነሳው ፎቶግራፍ ላይ የሠራው እንደሆነ ብቻ ነው ብለዋል። ከዚያ ውጪ የራሱ ካልሆነ ነገር ሌላ መነሻ አድርጎ የተሠራና፣ በሌላ ሰው ካሜራ የተነሳን ፎቶ ከገለበጠ፣ የራሱ የፈጠራ ሥራ ሊሆን አይችልም ሲሉ ሞያዊ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

 

ለሁለተኛው ተከሳሽ አቶ ተሾመ የመከላከያ ምስክር የሆነው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ በሰጠው ምስክርነትም “ሰለሜ” የተሰኘው ክሊፕ የተቀረፀው፣ አሜሪካን ሀገር አቶ ሱራፌል በተባለ ፕሮዲዩሰርና ዲጄ መንጌ በተባለ አቀናባሪ መሆኑን ገልጾ፣ ክሊፑ ከተሠራ በኋላ ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ካሠራጫቸው ሌሎች አምስት ክሊፖች ጋር ተቀላቅሎ እንደወጣ መስክሯል።

 

አቶ ጥላሁን ወ/ጊዮርጊስ የተባለው ሁለተኛ ምስክር “ሰለሜ” የተባለው ክሊፕ በዋሽንግተን ሲቀረፅ በቦታው የነበረ መሆኑንና፣ በቀረፃው ወቅት ዲጄ መንጌ ከካሜራ ባለሙያው አቶ ሱራፌል ጋር ሲነጋገሩ በመመልከቱ፣ ክሊፑን ያቀናበሩት እነሱ ይሆናሉ የሚል ግምት መውሰዱን መስክሯል።

 

በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት የውል ጉዳዮች አስፈፃሚና፣ የሂሳብ ባለሞያ ሆኖ ለሰባት ዓመታት መሥራቱን ጠቅሶ፣ በዚህ ሥራ ሂደት ውስጥ ከአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ጋር የተደረገውን የሥራ ውል እንዳስፈፀመ ገልጿል። ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ከአርቲስቱ ጋር በገባው ውል “መርጠን ለምናሠራቸው” ክሊፖች የሚል በመሆኑ፣ ከዘፈን አልበሙ ላይ ላምባዲና፣ ሰሚ ለሌለው አፌ፣ ንገሪኝ ካልሽማ እና አላምን አለ የሚሉትን ዘፈኖች መርጠው የክሊፕ ቀረፃ ካደረጉ በኋላ፣ ዲጄ መንጌ ከአሜሪካ ደውሎ፣ “ሰለሜ” የሚለውን ክሊፕ አብረው አሳትመው እንዲያሠራጩለት ትብብር በመጠየቁ ያለ ምንም ክፍያ እንዳሠራጩለት በመግለጽ፣ ለአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንም የፈፀሙት ክፍያ መርጠው ለሠሯቸው አራት ክሊፖች መሆኑን መስክረዋል።

 

ፍርድ ቤቱም ይህን ማስረጃ ሲመዝነው፤ ምስሎቹ በክሊፑ ላይ የሚታዩት ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ እንዳቀረበው አምስት ሳይሆኑ ሁለት መሆናቸው፣ ክሊፑን ያቀናበሩት ተከሳሾቹ ሳይሆኑ ዲጄ መንጌ መሆኑን፣ ከክሊፑ ስርጭት ከያንዳንዱ አንድ ብር አገኝ ነበር የተባለው ከተራ ምኞት የማያልፍ መሆኑንን፤ ምክንያቱም ሥዕሎቹ ክሊፑ ላይ ለአራት ሰከንድ ታይተው የሚጠፉና ማንም ሰው ክሊፑን እንጂ ሥዕሎቹን እንደማይገዛ፣ ሥዕሎቹ ለአየር መንገድ ተሸጠው በካሌንደርና በፖስተር መልክ ያለ ሠዓሊው ለህዝብ የተበተኑ በመሆናቸው፣ በአጠቃላይ ባለመብት ነኝ ያሉት አቶ አዲስ ገብሩ (ሠዓሊ) የጠየቁት ገንዘብ ይገባኛል ውድቅ መደረጉን፣ በአዕምሮዬ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል ያሉት ምንም የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን፣ በመግለጽ በዛሬው ዕለት ከፍርድ ቤት በነፃ ተሰናብቷል።

 

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ውሳኔው ከተነበበና በነፃ መሰናበቱ ከተረጋጋጠለት በኋላ በደስታ ቤተሰቦቹን ስሞ ወደቃሊቲ ወደሚወስደው መኪና ያመራ ሲሆን፤ ውጭ ተሰብስበው ሲጠብቁ ለነበሩ አድናዎቹ ሞቅ ያለ ሠላምታ ሰጥቶ ወደ መቆያ ስፍራው አምርቷል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ