Playwright, writer & journalist Dawit Issak ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅማትያስ ከተማ ከስቶክሆልም

Ethiopia Zare (ዓርብ የካቲት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. March 5, 2010)፦ ከተመሰረተ ከመቶ ዓመት ዕድሜ በላይ ያስቆጠረውና ብዙ እውቅ ደራስያንና ጋዜጠኞችን በላቀ የሥራ ውጤታቸው ሲሸልም የቆየው የኖርዌይ ደራስያን ማኅበር፤ የ2009 (እ.ኤ.አ.) ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ሽልማቱን ስዊዲሽ-ኤርትራዊ ለሆነውና በኤርትራ በእስር ላይ ለሚገኘው ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅ ሰጠ።

 

ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ፀሐፊ ተውኔት ዳዊት ይስኃቅ በአምባገነኑ ኢሣያስ አፈወርቂ መንግሥት ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከስድስት ወር በእስር ቤት እንደቆየ በመግለጽ፤ ለሽልማት ውድድሩ ዕጩ ሆኖ እንዲቀርብ ያደረጉት ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ መሆናቸው ታውቋል። ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ካሁን በፊትም ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅንን በዕጩነት አቅርበው ለሽልማት ማብቃታቸው ይታወሳል።

 

ደራሲ አበራ ለማ የኖርዌይ የፈጠራ ስነጽሑፍና የኢ-ልቦለድ ደራስያን ማኅበራት አባል ከመሆናቸውም ባሻገር፤ የኖርዌጅያን ፔን እና የስነጽሑፍ ማዕከል አባል ናቸው። ደራሲ አበራ፣ ለውድድሩ አስራ ሦስት ዕጩዎች እንደቀረቡና ዕጩዎቹን አቅራቢዎቹም የተሰጣቸውን ሙሉ ኃላፊነት (Mandate) በመጠቀም የማኅበሩን ሕግና ደንብ ተከትለው በዓለም አቀፍ ኮሚቴው አማካኝነት ተግባራቸውን እንዳከናወኑ ገልጸዋል።

 

አብዛኛዎቹ ዕጩዎች ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ እጅግ ጠንካራ የተወዳዳሪነት ብቃት ያላቸውና በዚሁ ሥራቸው በዓለማችን ተጠቃሽ የሆኑ ባለሙያዎች እንደነበሩ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የገለጹት ደራሲ አበራ፤ ዓለም አቀፍ ኮሚቴው የአቅራቢዎቻቸውን ብርቱ ማስረጃ መነሻ በማድረግ በላቀ አሸናፊነት ጋዜጠኛና ደራሲ ዳዊት ይስኃቅን መምረጡን አስታውቀዋል።

 

ይኼንኑ የሽልማት ውሳኔ የማኅበሩ ላዕላዊ አካል የሆነው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ አጽድቆ ለአሸናፊው የተመደበውን ሁለት መቶ ሺ የኖርዌይ ክሮነር (ወደ 34 ሺህ የአሜሪካ ዶላር / ወደ 25 ሺህ ዩሮ የሚጠጋ) እና ዲፕሎማ ከነሙሉ ክብሩ እንደሚሸልም ታውቋል። በተጨማሪ ይህ የሽልማት ገንዘብ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን በ2005 ዓ.ም. ከተሸለሙት በእጥፍ ማደጉን ለመረዳት ችለናል።

 

በኢሣያስ አፈወርቂ ስውር እስር ቤት ከ2001 እ.ኤ.አ. ጀምሮ የሚማቅቀው ዳዊት ይስኃቅ ይህንን ሽልማት ለመቀበል ባለመታደሉ፤ ማኅበሩ የፊታችን ማርች 13 እና 14 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. (መጋቢት 4 እና 5 ቀን 2002 ዓ.ም.) ኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ በሚገኘው ክላርዮን ሮያል ክርስቲያንያ ሆቴል ኦስሎ በሚያደርገው መደበኛ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ባለቤቱና ልጆቹ ተገኝተው ሽልማቱን እንደሚቀበሉ ታውቋል።

 

የኖርዌይ ደራስያን ማኅበር ለጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅ ነፃነት በተለያየ መንገድ ሲያካሂድ የቆየ ትግሉን ወደፊትም እንደሚቀጥል የገለፁት ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ፤ ይህ ሽልማት በአምባገነኑ የኢሣያስ አፈወርቂ መንግሥት ላይ ዓለም አቀፍ ጫናንም እንደሚያስከትል አክለው ገልፀዋል።

 

ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅ ከባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድኅን ቀጥሎ ሁለተኛው ባለሙሉ አፍሪካዊ ተሸላሚ ሲሆን፤ ከሴፕቴምበር 23 ቀን 2001 እ.ኤ.አ. (ከመስከረም 13 ቀን 1993 ዓ.ም.) ጀምሮ እስር ቤት ውስጥ ከደረሰበት የጤና እክል ጋር እየታገለ ያለፍርድ ታስሮ እንደሚገኝ ይታወቃል።

 

ጋዜጠኛ ዳዊት ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ሲሆን፣ ቤተሰቡ ነዋሪነታቸው በስዊድን ሀገር ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ