ለሕክምና ወደ ውጭ ሄደዋል ተባለ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. June 30, 2009)፦ ከአዲስ ብሮድካስቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያለቀረጥ የገቡ የሕትመት መሣሪያዎችን አላግባብ መጠቀም በሚል ክስ ተጠርጥረው ታስረው በዋስ የተለቀቁት እውቁ የሕግ ባለሙያ አቶ አበበ ወርቄ በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ቢወጣባቸውም፤ ዛሬ በዋለው የፍርድ ቤት ውሎ በሕመም ምክንያት ወደ ውጭ ሀገር በመሄዳቸው ሊቀርቡ አለመቻላቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

ኩባንያው ጋር በተያያዘ የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ መለስካቸው አምሃን ጨምሮ ወይዘሮ ዓመለወርቅ ታደሰ፣ አቶ እውነቱ እንደዋጋው፣ አቶ ዳዊት ገ/እየሱስ እና አቶ ደመቀ ጌጡ ያለቀረጥ የገባ መሣሪያን ያለአግባብ መጠቀምና ለመሸጥ መሞከር በሚል ክስ የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፤ አቶ አበበ ወርቄ ባለመቅረባቸው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ 8ኛ ወንጀል ችሎት በፖሊስ ታስረው ለዛሬ ሰኔ 23 ቀን እንዲቀርቡ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

 

በዛሬው ችሎት አቶ አበበ ወርቄ በሕመም ምክንያት ከሀገር ውጭ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከሰባት ሰዓት ተኩል እስከ አስር ሰዓት በቆየው የፍርድ ቤት ውሎ ግራ ቀኙን ሲያዳምጥ ውሏል። ዓቃቢ ሕግ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በኤግዚቢትነት የያዛቸውን የሕትመት መሣሪያዎች መለያ (ሲሪያል) ቁጥር ለፍርድ ቤቱ እንዲነግር ተጠይቆ ዓቃቢ ሕጉ ቁጥሮቹን የማያውቃቸው መሆኑን በመግለጹና የክሱን ሂደት ለመበየን እንዲያስችል የመሣሪያዎቹን መለያ (ሲሪያል) ቁጥር ዓቃቢ ሕግ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ለሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ