የቪኦኤው ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ ነፃ ተሰናበተ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. July 15, 2009)፦ ያለቀረጥ የገቡ የህትመት መሣሪያዎችን አላግባብ መጠቀምና ለመሸጥ መሞከር በሚል ክስ የቀረበባቸው የአዲስ ብሮድካስቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤቶችና ዕቃውን ለማሻሻጥ ሞክረዋል የተባሉ ደላሎች ክሳቸው ሲታይ ውሎ የቪኦኤው ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ በነፃ የተሰናበተ ሲሆን፣ ሌሎቹ መከላከያቸውን እንዲያቀርቡ ዛሬ የዋለው ችሎት ብይን ሰጠ።
ዛሬ የዋለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ 8ኛ ወንጀል ችሎት አቶ አበበ ወርቄ በሌሉበት፣ ወይዘሮ ዓለመወርቅ ታደሰና ሌሎች ተከሳሾች መከላከያቸውን እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
የህትመት መሣሪያዎችንና የስቱዲዮ ቁሳቁሶችን ለማሻሻጥ ደላላ ሆነዋል የተባሉት ግለሰብ ዛሬ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ተይዘው እንዲቀርቡ ለፖሊስ ትዕዛዝ መስጠቱን ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።
እውቁ የሕግ ባለሙያ አቶ አበበ ወርቄ ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር የሄዱ መሆናቸው የተገለጸ ከመሆኑም በላይ፤ ከአዲስ ብሮድካስቲንግ ባለቤቶች ውስጥ አንዱ ናቸው። በአዲስ ብሮድካስቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በባለቤትነት ከተመዘገቡት ከ30 በላይ እውቅ ሰዎች ውስጥ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ብርሃነ መዋ፣ ዶ/ር ሻውል ኃይሉ፣ ዶ/ር በፍቃዱ ደግፌና አቶ አለማየሁ ፈንቱ እንደሚገኙበት ይታወቃል።



