ታዋቂው ጠበቃ አበበ ወርቄ የአንድ ዓመት እስራት ተፈረደባቸው
ፍርዱ ከአሜሪካን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለሱ ለማድረግ እንደሆነ ተጠቁሟል
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሐምሌ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. August 6, 2009)፦ ለሕክምና በአሜሪካ ሀገር በሚገኙት ታዋቂው ጠበቃ አበበ ወርቄ ላይ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ከኤቢሲ ብሮድካስቲን ጋር በተያያዘ የአንድ ዓመት እስራትና የገንዘብ ቅጣት ወሰነባቸው። ቅጣቱ አቶ አበበን ወደ ሀገር ቤት እንዳይመለሱ ለማድረግ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለፁ።
የአዲስ ብሮድካስቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር (ኤቢሲ ብሮድካስቲንግ) ንብረቶች ከሰባት ዓመት በኋላ በኢህአዴግ የድል በዓል ቀን ግንቦት 20 ቀን 2001 ዓ.ም. “በሕገ-ወጥ መንገድ የገቡ ናቸው” በሚል በታጣቂዎች መወረሳቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም “ያለቀረጥ ነፃ የገቡ ንብረቶችን አላግባብ በመጠቀምና ለመሸጥ መሞከር” በሚል በስድስት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቶባቸው ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ታዋቂው ጠበቃ አበበ ወርቄ በሌሉበት በአንድ ዓመት እስራትና በገንዘብ፤ ሥራ አስኪያጅዋ ወ/ሮ አለመወርቅ ታደሰ ደግሞ የስድስት ወር እስራትና የ250 ሺህ ብር ቅጣት እንዲቀጡ የፌደራሉ አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው ዕለት (ሐምሌ 30 ቀን 2001 ዓ.ም.) ወስኖባቸዋል።
የአዲስ ብሮድካስቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበርን ቦርድ የሚመሩት ጠበቃ አበበ ወርቄ በፖሊዝ ተይዘው እንዲቀርቡ ወስኖ የነበረው ይኸው ፍርድ ቤት፤ አቶ አበበ በሕክምና ምክንያት በአሜሪካን ሀገር እንደሚገኙ የቀረበለትን ማስረጃ ውድቅ በማድረግ በሌሉበት ነው የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ እና የኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ) ሊቀመንበር የነበሩት ታዋቂው ጠበቃ አበበ ወርቄ ኢህአዴግ በዓይነ ቁራኛ ከሚከታተላቸውና በጠላትነት ከሚፈርጃቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ መሆናቸውን የጠቀሱት የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች፤ “ኢህአዴግ እንዲህ ያሉ ሰዎችን ከማሰር ይልቅ በውጭ ሀገር ስደተኛ ሆነው ከሀገር እንዲርቁለት ይፈልጋል። ጠበቃ አበበ ወርቄ ላይ ዛሬ ፍርድ ቤቱ የጣለው ቅጣት፤ አቶ አበበን ከሀገር ለማራቅና ስደተኛ ለማድረግ ነው” ሲሉ ገልፀዋል።
“ያለቀረጥ ነፃ የገቡ ንብረቶችን አላግባብ በመጠቀምና ለመሸጥ መሞከር” በሚል ክስ ጠበቃ አበበ ወርቄን ጨምሮ ተከስሰው ከነበሩት ስድስት ሰዎች ውስጥ በዛሬው ዕለት ጥፋተኛ የተባሉት ሁለተኛዋ ተከሳሽ የኤቢሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አመለወርቅ ታደሰ የስድስት ወሩን እስራት አምስት ሺህ ብር ዋስትና ካስያዙ በገደብ ሊለቀቁ እንደሚችሉ ታውቋል።
ክስ ተመስርቶበት የነበረው የአዲስ ብሮድካስቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበርንም እንዲሁ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ በማለት የገንዘብ ቅጣት ጥሎበታል።
ኩባንያው ጋር በተያያዘ ተከስሰው የነበሩት ቀሪዎቹ አራት ተከሳሾች የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ፣ አቶ እውነቱ እንደዋጋው፣ አቶ ዳዊት ገ/እየሱስ እና አቶ ደመቀ ጌጡ በነፃ መሰናበታቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።
የአዲስ ብሮድካስቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር በባለቤትነት ከተመዘገቡት ከ30 በላይ እውቅ ሰዎች ውስጥ እውቁ ጠበቃ አበበ ወርቄ፣ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶ/ር ብርሃኑ፣ ዶ/ር በፍቃዱ ደግፌ፣ ዶ/ር ሽመልስ ተ/ፃዲቅ፣ አቶ ብርሃነ መዋ፣ ዶ/ር ሻውል ኃይሉ እ አቶ አለማየሁ ፈንቱ ይገኙበታል። ኩባንያው በባለአክሲዮኖቹ ተቋቁሞ ለ7 ዓመታት የሚዲያ ፍቃድ ሳይሰጠው ቆይቷል። ድርጅቱን በአደራ ይመራው የነበረው የቪኦኤ ዘጋቢ መለስካቸው አምሃ ሲሆን፣ ሥልጣኑን በቅርቡ ለወ/ሮ አመለወርቅ ታደሰ አሳልፎ ነበር።



