ለነፃነት ታገል - በአንድነትህ ፅና!

ወለላዬ - ከስዊድን፤ ሐምሌ 2009 ዓ.ም. This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

(Read on PDF)

ኩታበር ዙሪያውን ኮምቦልቻ - ከሚሴ፣

ማጨው - ላሊበላ፣ ሐይቅና ደሴ፣

ወልድያና ባቲ፣ ቦሩ - ወረባቦ፣

ሳይንትም ያለኸው ወረየሉ - ቆቦ፣

ወረመኑ፣ አንባሰል፣ መርሳና ቦረና፣

ድፍን ወሎ ያለህ የጁ፣ ወገል ጤና፣

ወያኔ ያለህን ባህልና ታሪክ፣

ሊያጠፋብህ ዘምቷል እንዳትፍረከረክ።

በጦሳ ተራራ ምለህ በቦርከና፣

ለነፃነት ታገል - በአንድነትህ ጽና።

 

አሰገደች ዓሊ፣ ስንቅነሽ መሐመድ፣

ሽፈራሁ ኑር ሁሴን፣ ገብረመስቀል ሰይድ፣

አቡበከር ሰይፉ፣ ዘይነባ ፈለቀ፣

ሁሴን አስፋወሰን፣ አብደላ ዘለቀ፣

ተብለህ ተጠርተህ እንዲህ በመዋሃድ፣

በጋራ ያነጽከው ቤተ እግዚአብሔር መስጅድ፣

እደሴ ከተማ በአርሴማ ቅድስት፣

የደረሰብህን ሰምተናል በቁጭት።

እፊትም በጅማ በኋላም በጎንደር፣

ሳይሰምር ቀረ እንጂ ፍጹም ይሄ ነገር፣

ህዝብን ለማጫረስ ተሞክሮ ነበር።

 

ይሄንን መሰሪ ተግባሩን ተረዳ፣

ለሚፈጥረው ተንኮል እንዳትሆን እንግዳ፣

ባንድነትህ አብር ተጠናከር ይበልጥ፣

እርቃኑን አስቀረው ወያኔ እንዲጋለጥ

የጁና ቦረና ኩታበር ዙሪያውን፣

የተወለዱብህ ነብዩ ሼክ ሁሴን፣

ይበቃሃል በለው በአንድነት ተነሳ

ሐይቅ፣ ወገል ጤና፣ ወረኢሉ መርሳ።

ይሄንን እያየህ አትተኛ ሳይንት፣

በደል ያንገፍግፍህ ይናፍቅህ ነፃነት፣

በበደሉህ ቁጥር ባሳዩህ ጭካኔ፣

ማይጨው፣ ላሊበላ አይለይህ ወኔ

ካልበረታህ በቀር፣ ፈሪ አይለቅም ጥሎ፣

ወረመኑ፣ አምባሰል ይሄን እውቅ ወሎ

ብዙ ነው ቁጥራችን ለትግል የቆምነው፣

አይዞህ ወረባቦ ድላችን ቅርብ ነው።

እንግዲህ በቃኝ በል የግፍ ቀንበር አውልቅ፣

ሙስሊም ክርስቲያኑ አንድነትክን አጥብቅ።

 

በጎሣ፣ በእምነት፣ ህዝብን አበጣብጦ፣

ሊቀመጥ አስቧል ኢህአዲግ አላግጦ

ነገም በባሌ ህዝብ በሙስሊም፣ በክርስቲያን፣

ይሄ ነገር ደርሶ እንደሚዘልቅ እመን

በትግራይ፣ በሐረር፣ በአርሲ፣ ሲዳሞ፣

በዚሁ ሁኔታ ይቀጥላል ደግሞ

ሆኖም ፀብ ቢጭሩም ተንኮል ቢያራግቡ፣

ሊለያይ አይችልም ሸሩን አውቋል ህዝቡ።

 

ስለዚህ ኩታበር፣ ኮምቦልቻ - ከሚሴ፣

ማጨው - ላሊበላ፣ ሐይቅና ደሴ፣

ወልዲያና ባቲ፣ ቦሩ - ወረባቦ፣

ሳይንትም ያለኸው ወረኢሉ - ቆቦ፣

ወረመኑ - አምባሰል፣ መርሳና ቦረና፣

ድፍን ወሎ፣ ያለህ የጁ፣ ወገል ጤና፣

ሠላምን ተላብሰህ እንድትኖር በጤና፣

ለነፃነት ታገል - በአንድነትህ ፅና።


 

ወለላዬ - ከስዊድን፤ ሐምሌ 2009 ዓ.ም. This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!