“ቃለ ዓዋዲው ይዳኛችሁ” ጠ/ሚ መለስ

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. July 4, 2009)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በፓትርያሪኩና በአቡነ ሳሙኤል መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት መባባሱንና ባለፈው ማክሰኞ ስብሰባ የቤተክህነት ውዝግብ መቀጠሉ ተገለጸ።

 

በቤተ-ክርስቲያኒቱ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ሳሙኤል የተመራ ስብሰባ በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ባለፈው ማክሰኞ ለግማሽ ቀን ተከናውኖ የነበረ ሲሆን በተመሳሳይ በማግስቱ ፓትርያርኩ ደጋፊዎቻቸውን ስብሰባ ጠርተው እነደነበር ተጠቁሟል።

 

አቡነ ሣሙኤል በመሩት ስብሰባ የቤተክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ ምክትል ሊቀናመናብርት፣ ዋና ፀሐፊዎችና የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮች ተገኝተዋል። በእለቱ አቡነ ሣሙኤል በቤተክርስቲያኗ ሕገ ቤተክርስቲያን መጣሱን፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ምዕመናንን ቤተክርስቲያኗ ማጣቷን፣ በየመንገዱ ስዕል አንጥፈው ለቤተክርስቲያን የሚለምኑት፣ በመልካም በአስተዳደራዊ ሥርዓት ማጣት ሥራ ያላገኙ ምዕመናን መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

በብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ከሥራ የታገዱት አቡነ ሣሙኤል እግዱን እንደማይቀበሉ ሲናገሩ “የሾመኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፣ የሚያወርደኝም ሲኖዶሱ ነው” ብለዋል። የአቡነ ሣሙኤልን ንግግር ደግፈው የተናገሩት የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች “ሙስናን ስለታገሉ፣ ቤተክርስቲያኒቱ እንድታድግና እንድትስፋፋ ስለጣሩ፣ ዘረኝነትን ስለተዋጉ እንዴት ይታገዳሉ?” በማለት የፓትርያርኩን ውሳኔ ተቃውመዋል።

 

ተሰብሳቢዎቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራበት ቃለ ዓዋዲ /ሕገ ቤተክርስቲያን/ በመጣሱ ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድላቸው፤ በቤተክርስቲያንና በግለሰቦች ላይ የሚፃፉ መጻሕፍትንና መጣጥፎችን በሚበትኑ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ እርምጃ እንዲወስድ በመጠየቅ እና በአቡነ ሣሙኤል ላይ የተወሰደውን የእግድ እርምጃ ሲኖዶሱ እንዲያነሳላቸው በመጥቀስ ለሀገሪቱ ፕሬዝዳነት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት ጽ/ቤት፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ለፌዴራል ፖሊስ ደብዳቤ ልከዋል።

 

በእለቱ የሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ በፌዴራል ፖሊስ እየተጠበቀ የነበረ ሲሆን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባ ጢሞቲዎስ፤ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥርዓት ተላልፈዋል፣ ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራበትን ቃለ አዋዲ ጥሰዋል፣ ሕገ ቤተክርስቲያንንም ለመሻር ተንቀሳቅሰዋል” በማለት የፌዴራል ፖሊስ እንዲመደብላቸው ለዋና ዳይሬክተር ወርቅነህ ገበየሁ ደብዳቤ ጽፈውም ነበር።

 

ረቡዕ ዕለት የተሰበሰቡት የፓትራያርኩ ወገኖች ስብሰባ ግን ለጋዜጠኞች ክፍት ባለመሆኑ የተላለፈውን ውሳኔ ለማወቅ አልተቻለም። ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማነጋር የሄዱት ሁለቱም ወገኖች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ምላሽ “በጉዳዩ አልገባበትም፣ ቃለ አዋዲውን አክብሩ፣ ቃለ አዋዲው ይዳኛችሁ!” የሚል እንደነበር ተገልጿል።

 

በግንቦት ወር መጨረሻ ተቋቁሞ የነበረውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ብፁዕ አቡነ ጵውሎስ ከሰኔ 18 ቀን ጀምሮ አግጀዋለሁ…. ያሉ ሲሆን የታገዱት ሰባት ጳጳሳት መሆናቸው ታውቋል። ከሰባቱ አንዱ አቡነ ሳሙኤል መሆናቸው ይታወሳል። ሌላው ደግሞ አቡነ ጢሞቲዎስ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!