አንድ ጳጳስ በለሊት ደህንነት ቢሮ ተወሰዱ

የጳጳሳት መኖሪያ ቤት በምሽት ተደብድቧል

ፓትርያርኩ ሕገ ቤተክርስቲያን አላውቅም አሉ

(ልዩ ሪፖርታዥ)

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2001 ዓ.ም. July 18, 2009)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርኩ በሥራ አስፈጻሚው ላይ የጣሉትን እግድ እንዲያነሱ ውሳኔ አሳለፈ።

 

መነሻ

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የሚያስተዳድሩት ቤተክርስቲያን ሙስና ተንሰራፍቶበታል፣ ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራው ጉዳዩ በማይመለከታቸው ሹማምንትና፣ ቀደም ሲል የአርቲስት መሐሙድ አህመድ ባለቤት የነበሩት፣ ከደርግ ዘመን ጀምሮ ስማቸው አንድም ግዜ በበጎ የማይነሳውና በአሁኑ ግዜ የፓትርያርኩ የቅርብ አማካሪ በሆኑት ወ/ሮ እጅጋየሁ በተባሉ ግለሰብ ነው፣ ፓትርያርኩ ያልወደዱት ወይም ያልተደሰቱበት ጳጳስ ወይ የቤተክርስቲያን አገልጋይ በእኚህ ሴት አማካኝነት ስሙ እንዲጠፋ፣ እንዲወገዝና በቅጥረኞች ማስፈራሪያ እንዲደርሰው ይደረጋል።

 

በተጨማሪም ቤተክርስቲያኒቱ በፓትርያርኩ ዘመዶች የተሞላና የእነሱ ጥቅም ማስፈጸሚያ ሆኗል በሚል የሲኖዶሱ አባላት በተደጋሚ ምሬታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ።

 

ይህንንም በስብሰባ ላይ የተናገረ ጳጳስ በግልም ሆነ በቡድን ማስፈራት የሚደርስበት ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት የሆኑ ጳጳሳት የቻሉትን እየሞከሩ በትዕግስት ቆይተዋል።

 

የአቡነ ሳሙኤል መምጣትና ለውጡ

 

አቡነ ሳሙኤል በዋልድባ ገዳም ውስጥ መነኩሴ የነበሩ ሲሆን፣ አዲስ አበባ በመምጣት ቤተክርስቲያኒቱን እያገለገሉ የቀለም ትምህርታቸውን ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በመማር ራሳቸውን ካሻሻሉ በኋላ ያሳዩት ለውጥና ችሎታቸው ታይቶ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ፀሐፊ ሆነው ይሾማሉ። በዚህ የሹመት ግዜ ፓትርያርኩ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ከተባረሩት አምስት ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ፓትርያርኩ ሥልጣን ላይ ከወጡም በኋላ አብረው በመሥራት ቤተክርስቲያኒቱ እንድትለወጥ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

 

ፓትርያርኩ መንበረ ሥልጣናቸውን እየተለማመዱ ሲመጡና ዘመዶቻቸውን ወደቤተክርስቲያኒቱ በማምጣት የግልንና የቤተሰብ ጥቅም ማስጠበቅ ሲጀምሩ፤ እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ሥራ እየተበላሸ ሲመጣ አቡነ ሳሙኤል ሙግት ጀመሩ። ሙግቱ ያልተስማማቸው አቡነ ጳውሎስ አባ ሳሙኤልን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅት አንስተው የብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው። ውሳኔውን ያልተቀበሉት አቡነ ሳሙኤልም በዛው ሣምንት ወደ አሜሪካ ሀገር በማቅናት ለአስር ዓመታት ራሳቸውን በትምህርት ሲያደራጁ ቆይተው የተለያዩ ትምህርቶችን ከተማሩ በኋላ ወደ ሀገራቸው በመመለስ ተመልሰው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነዋል። በሥራ አስኪያጅነታቸው ያሳዩት የሥራ ተግባር በሲኖዶሱ ተደንቆላቸው የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ሆነውም ተሹመዋል።

 

የአቡነ ሳሙኤልና የፓትርያርኩ የፀብ መነሻ

 

ቅዱስ ሲኖዶሱ ቋሚ ሲኖዶስና ሙሉ ሲኖዶስ ተብሎ በሁለት ይከፈላል። ቋሚ ሲኖዶሱ ሦስት ጳጳሳት ያሉት ሲሆን፣ 51 የሀገረ ስብከት ሊቀጳጳሳት ያሉት ሙሉ ሲኖዶሱ በስብሰባ ያሳለፈውን ውሳኔ ተቀብሎ የሚሠራ ሲኖዶስ ነው። ሙሉ ሲኖዶሱ በየሦስት ወሩ ወይም አስቸኳይ ስብሰባ ሲጠራ የሚሰበበሰብ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምትመራውም ይህ ሲኖዶስ ሕገ-ቤተክርስቲያኑን መሠረት በማድረግ ለሚያሳልፈው ውሳኔ ተገዢ በመሆን ነው።

 

ነገር ግን ፓትርያርኩ በራሳቸው መንገድ የሚያሳልፉትን ውሳኔ በተለያየ መንገድ ተፈጻሚ በማድረግ ሲኖዶሱን ሲያዋርዱና ሲዘልፉ ጳጳሳቱን ሲሻቸው በገንዘብ እየደለሉ፣ አሊያም በማስፈራራት ወይም በማገድ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ነገር ግን አቡነ ሳሙኤል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ከሆኑ በኋላ ገጥሟቸው የማያውቅ የማይገዳደሩት ጠላት እንደመጣባቸው በማመን በአባ ሳሙኤል ላይ ወታደሮቻቸውን አሰማሩባቸው። በከፍተኛ ደረጃም የአሉባልታ ዘመቻ አወረዱባቸው።

 

የኢትዮጵያ ሚሊኒየም (2000)

 

ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያውያንን ሚሌኒየም እንዴት ታክብር በሚለው ሃሳብ ላይ ሲኖዶስ ከተስማማ በኋላ ኮሚቴ ይቋቋማል። የኮሚቴው ሰብሳቢም አቡነ ሳሙኤል ሆነው ይሾማሉ። ይህ ያላስደሰታቸው አቡነ ጳውሎስ እንደለመዱት ወታደሮቻውን በአቡነ ሳሙኤል ላይ ያሰማሩባቸዋል። በወቅቱም አቡነ ሳሙኤል ለ15 ቀናት ስብሰባ እስራኤል ሀገር ሄደው በነበሩበት ወቅት ፎቷቸው በታተመበት በራሪ ወረቀት ላይ “የሚሊኒየሙ አባት” የሚል ጽሑፍ በመጻፍ ልክ አቡነ ሳሙኤል በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት የበተኑት አስመስለው ፀብ ይቀሰቅሳሉ። ሚሊኒየሙን ለማክበር የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ ምንም ሳይሠሩ የራሳቸውን ፎቶ አትመው “የሚሊኒየሙ አባት” በሚል ጽሑፍ በተኑ ሲሉ አብጠለጠሏቸው። ኮሚቴው መፍረስ አለበት ብለው በመወሰን ኮሚቴውን አግደው ወ/ሮ እጅጋየሁ ከነግብርአበሮቻቸው ያሉበት ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደረገ።

 

ይህ ኮሚቴም በአባ ሳሙኤል ከሚተዳደሩት የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ደብራት እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ብር በማውጣት የፓትርያርኩን ፎቶ አሠርተው እንዲለጥፉ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ሐመር መኪና ተገዝቶ ሽልማት እንዲሰጣቸውም አስገዳጅ መዋጮ ጠየቀ። አባ ሳሙኤልም በዚህ ጉዳይ ላይ እሺ አላሉም፤ በየገጠሩ ስንት የተጎሳቆሉ ቤተክርስቲያናት ባሉበትና የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት በወደቀበት በዚህ ሁኔታ እንዲህ ያለ መዋጮም አይደረግም፣ የፓትርያኩ ፎቶ በየደብሩ እንዲሰቀልም ሕገ ቤተክርስቲያ አትፈቅድም ሲሉ ክልከላ አደረጉ። በዚህ ውሳኔያቸውም ጥርስ ውስጥ ገቡ።

 

የፀቡ መፋፋም

 

ቅዱስ ሲኖዶሱ የፓትርያኩ አምባገነንት ሲበዛበት፣ የቤተክርስቲያኒቱ ምዝበራ ሲፋፋም፣ ዕድገቷ ተቋርጦ ቤቱ ሙስና የሰፈነበትና ተቆጣጣሪ የሌለው የዘመድ ቤት ሲሆን፤ አንድ ውሳኔ አሳላፈ። ፓትያርኩ በማንኛውም አስተዳደራዊ ሥራ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ የሚከለክልና አስተዳራዊ ሥራን የሚሠራ ከሲኖዶሱ ጳጳሳት ውስጥ ሰባት አባቶች ያሉበት አንድ ኮሚቴ ከግንቦት 6 ቀን እስከ ግንቦት 13 ቀን አድርጎት በነበረው ስብሰባ አቋቋመ።

 

የመንፈሣዊ ኮሌጁ ዲን አቡነ ጢሞቲዎስ የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ሳሙኤል ፀሐፊ እንዲሁም፤ የሐዋሳ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል፣ የጅማ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የአዳማ ሀረገ ስብከት ጳጳስ አቡነ ጎርጎሪዮስ፣ የደሴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ አትናቲዮስ እና የከንባታና ሀዲያ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ መልከጸዲቅ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባላት ሆነው ተሾሙ።

 

ኮሚቴው ሥራውን እንደጀመረ የተከፈተበትን የአሉባልታ ዘመቻ ወደጎን በመተው ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን፣ ፀቡ አደባባይ እንዲወጣ መነሻ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንድ ውሳኔ አሳለፈ። ውሳኔው ፓትርያርኩ ከሲኖዶሱ እውቅና ውጪ ጉዳዩ የማይለከታቸውን የቤተክርስቲያን ሹማምንት ሰብስበው ወደጣሊያን ጉዞ አደረጉ። በዚህ ጉዞ ወቅትም በኋላ ላይ ማስተባበያ ቢሰጡም በኢትዮጵያ “ታቦተ ጽላት ይታያል” ብለው መግለጫ ሰጡ፤ ይህንኑ የውጭ ሚዲያዎች አስተጋቡ።

 

ፓትርያርኩ ከጉዞ ሲመለሱ ስለአካሄዳቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ከኮሚቴው ተጠየቁ። እንዴት እጠየቃለሁ ሲሉም ዘራፍ አሉ። በመሃሉ አቡነ ሳሙኤል ጽዮን ግርማ ከተባለች የአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዘጋጅ ጋራ ቅዳሜ ግንቦት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. በወጣው ጋዜጣ ላይ ሰፋ ያለ ቃለምልልስ ሰጡ። በቃለምልልሱም ወቅትም ለአንድ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ቤተክርስቲያን ከቴክኖሎጂው ጋር እኩል በመራመድ ወጣት ምዕመናንን መሳብ አለብን ከሚለው መነሻ ሃሳብ ተነስተው በኢንተርኔት ስርዓተ ቅዳሴን መከታተል ይቻላል የሚል መልዕክት አዘል ቃለ ምልልስ ሰጡ። በጉዳዩ ላይ በሣምንቱ ማብራሪያ ሰጡ። ይህ ያልተዋጠላቸውና በአጋጣሚው አቡነ ሳሙኤልን አውግዘው ከሥልጣን ማውረድ የሚፈልጉ አሉባልታውን ተያያዙት።

 

ወ/ሮ እጅጋየሁም በሌላት የቤተክርስቲያን እውቀት አቡነ ሳሙኤልን አብጠልጥላ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ጻፈች። በዚህ የተበሳጩ ሌሎች ግለሰቦችም በጉዳዩ ላይ ወ/ሮ እጅጋየሁ ሌላ ሰው አጽፈው በስማቸው ያወጡትን ጽሑፍ ተቃውመው ተጨማሪ አስተያየቶችን ሰጡ። ጉዳዩን በሚመለከትም ምንም አይነት አስተያየት እንደማያስተናግዱ በመግለጽ ዘጉት።

 

አቡነ ጳውሎስ በዚህ የተናደዱ ይመስላል ጋዜጠኞችን ሰብስበው “አባ ሳሙኤል በኢንተርኔት ማስቀደስ ይቻላል ብለው ቤተክርስቲያኒቱን አዋርደዋል” በማለት አብጠለጠሏቸው። ማምሻውንም ሲኖዶሱ ላቋቋመው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ለአባ ሳሙኤል የእግድ ደብዳቤ አስተላለፉ።

 

የሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ

 

አቡነ ሳሙኤል ደብዳቤው እንደደረሳቸው በሕገ ቤተክርስቲያን መሰረት የሾማቸው ሲኖዶሱ በመሆኑ ሊያግዳቸውም የሚችለውም ሲኖዶሱ መሆኑን በመጥቀስ እግዱን እንደማይቀበሉት ገልጸው ደብዳቤ ጻፉ። ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱም በአስቸኳይ ተጠራ። አቡነ ጳውሎስ ሲኖዶሱን እኔ አልጠራሁም በማለት ለማንገራገር ቢሞክሩም ጳጳሳቱ የማይሰበስቡን ከሆነ እኛ ራሳችን እንሰበሰባለን በማለታቸው ፍርሃት ስላደረባቸው ሲኖዶሱን ሰብስበውታል።

 

ማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

የተጠራው ሙሉ ሲኖዶስ ለስብሰባው በቤተክህነት ቅጥር ግቢ ባለው መሰብሰቢያ አዳራሽ ከጠዋት ጀምሮ ቢሰባሰብም ከመካረር ውጭ ምንም መፍትሔ ሳያበጅ፤ አቡነ ጳውሎስም እግዱን በሚመለከት የቀረቡትን መወያያ አጀንዳዎች አልቀበልም በማለታቸው ያለምንም ውጤት ተበትኗል።

 

ረቡዕ ሐምሌ 1 ቀን 20001 ዓ.ም.

 

በዚህ ዕለት ጳጳሳቱ እጅግ ተቆጥተው ፓትርያርኩ ኮሚቴውንም ሆነ አባ ሳሙኤልን ያገዱት ከሕገ ቤተክርስቲያን ውጭ ሆነው ነው። የእሳቸው ተጠሪነት ለሲኖዶሱ ነው፤ ጳጳሳት መሾምም ሆነ ማገድ የሚችለው ሲኖዶሱ እንጂ እሳቸው አለመሆናቸውን በመጥቀስ ስህተት መሥራቸውን አምነው ይቅርታ እንዲጠይቁና እግዱን እንዲያነሱ ይጠይቋቸዋል።

 

“ይህን በፍጹም አልቀበልም እንደውም እንዲህ ያለ ሕገወጥ ስብሰባ አልመራም” በማለታቸው፤ ”ስብሰባውን የማይመሩ ከሆነ አዳራሹን ለቀው ይውጡልን” በማለት ጳጳሳቱ ቢጠይቋቸውም “አልወጣም የምትሉትን እዚሁ ቁጭ ብዬ እሰማለሁ” በማለታቸው 41 የሚሆኑ ጳጳሳት ስብሰባውን ረግጠው በመውጣት ለብቻቸው በሌላ አዳራሽ ተሰባስበዋል።

 

ለብቻው ተሰብስበው በደረሱበት ድምዳሜም ፓትርያርኩ ያሳለፉት የዕግድ ውሳኔ ሕገ ቤተክርስቲያንን የተከተለ ባለመሆኑ እግዱ እንዲነሳ፤ እሳቸውን በተመለከተ የአስተዳደር ሥራውን ጨርሶ መሥራት ስላልቻሉና ቤተክርስቲያኒቱን ወዳልተፈለገና ፍጹም ወደተበላሸ አቅጣጫ እየወሰዷት በመሆኑ ከፀሎት ውጭ በማንኛውም አስተዳደር ሥራ እንዳይገቡ እንደራሴ ሊሾምባቸው ይገባል በሚል ውሳኔ ላይ ደርሰው ይህን ውሳኔ ለማጽናት ለአዳሪ ቀጥረው ተለያይተዋል።

 

ሐሙስ ሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አቡነ ሳሙኤልን ወደ ቢሮአቸው ከዛም ወደ ሲኖዶሱ ስብሰባ ሊወስዳቸው የመጣው ሹፌራቸው ቁልፍ ተቀምቶ አቡነ ሳሙኤል ከሚኖሩበት የመንፈሣዊ ኮሌጁ ግቢ መኖሪያቸው እንዳይወጡ በሦስት ሲቪል በለበሱ ወጣቶች ታግተው ዋሉ። ቀኑን ሙሉ ማንም ወደሳቸው ግቢ አይገባም፤ ማንም እንዲወጣ አልተፈቀደለትም። ፓትርያርኩ በተመሳሳይ ሁኔታ አይታገዱ እንጂ እሳቸውም ወደሲኖዶሱ ስብሰባ እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም። ይህ የተደረገውም ሲኖዶሱ ነፃ ሆኖ ውሳኔውን እንዲያሳልፍ ታስቦ እንደሆነ ተገልጾላቸው በማግስቱ እገታው ተነስቶ ሁለቱም ስብሰባ እንዲገቡ ተደረገ።

 

አርብ ሐምሌ 3 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

ስብሰባው የተመራው እንደወትሮ በፓትርያርኩ ሳይሆን በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን አባይ ፀሐዬ ነበር። እንዲሁም ኮሚሽነር ወርቅነህ ገበየሁ እና ሌሎች ሁለት ባለሥልጣናት ስብሰባውን አጅበውት ውለዋል።

 

መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው በመግለጽም ቤተክርስቲያኒቷን ወደ ሠላም ለማጣት ሕገቤተክርስቲያኒቷንና የሲኖዶሱን ውሳኔ አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ሲኖዶሱም ተሰብስቦ ይበጃል ያለውን ውሳኔ እንዲያሳልፍ መክረው ስብሰባው በተረጋጋ መንፈሥ ሰኞ ዕለት እንዲቀጥልና ይበጃል ያለውን ውሳኔ እንዲያሳልፍ አሳስበው ተለያይተዋል።

 

ሰኞ ሐምሌ 6 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

ጳጳሳቱ አርብ ዕለት በተሰጣቸው ተስፋ ስብሰባው በተረጋጋ መንፈሥ ይቀጥላል የሚል ስሜት የነበራቸው ቢሆንም፤ ፓትርያርኩ ምንም የተለየ መሻሻል ሳያሳዩ በአቋማቸው በመጽናት በቀዳሚነት አጀንዳ ተይዞ የነበረውን የሥራ አስፈጻሚውን እግድ አላነሳም በማለት አሻፈረኝ አሉ።

 

ሲኖዶሱ የሾማቸውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከሕገ ቤተክርስቲያን ሕገ ደንብ ውጪ ለምን ታገዱ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቡነ ጳውሎስ፤ ኮሚቴው የተሰየመው መተዳደሪያ ደንብ አቅርቦ ከሐምሌ 5 ቀን 2001 ዓ.ም. በኋላ ለሲኖዶሱ እንዲያቀርቡ እንጂ ከዛ ውጭ እየተሰበሰቡ የፈለጉትን ውሳኔ ለማሳለፍ ባለመሆኑ መተዳደሪያ ደንቡን አዘጋጅተው ሳያቀርቡ በሱ ጉዳይ ላይ በስብሰባው መነጋገር እንደማይፈልጉ ፓትርያርኩ በመናገር ምላሽ መስጠታቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

 

ሊቃነ ጳጳሳቱ መተዳደሪያ ደንቡን አዘጋጅተው መጨረሳቸውን ኮሚቴው በስብሰባው ላይ ሲገልጹ፤ ፓትርያርኩም ቀበል ብለው ሥራችሁን ስለጨረሳችሁ መተዳሪያ ደንቡ ወደ ሕግ ክፍሉ ተመርቶ ይመርመር ይላሉ። ጳጳሳቱም ሲኖዶሱ ከላይ መተዳደሪያ ደንብ አውጥቶ ያስተዳራል እንጂ ወደታች ልኮ ሕግ አያጸድቅም፤ መተዳደሪያ ደንቡ ተመርምሮ መታየት ካለበትም ገለልተኛ የሆነ የውጭ ኮሚቴ እንዲያየው መደረግ እንዳለበት በመግለጽ ተከራክረዋቸዋል።

 

ዋናው ጉዳይ መተዳደሪያ ደንቡ ሳይሆን መጀመሪያ ከሲኖዶሱ እውቅና ውጭ የተደረጉ እግዶች ይነሱ የሚለው ነው በሚል ጠንካራ መከራከሪያ በማቅረብ ቢሞግቷቸውም ፓትርያርኩ በጀ የሚሉ ሆነው አልተገኙም።

 

ሲኖዶሱም እንደሌሎች ስብሰባዎች ውሳኔን የሚያሳልፈው በድምፅ ብልጫ በመወሰን ሳይሆን ሁሉም በመተማመን ውሳኔ በመሆኑ ሊስማሙ ባለመቻላቸው በዕለቱ ተሰብስበው ከነበሩት 39 ጳጳሳት 26ቱ እንግዲያው ስብሰባው ስናደርግ ከመንግሥት ታዛቢ ይኑርልን በማለት ለማግስቱ ቀጠሮ በመያዝ ስብሰባውን ጥለው ወጥተዋል።

 

በማግስቱ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ “የመንግሥት ባለሥልጣናት በሰጡት ማሳሰቢያ መሠረት፣ 39 የሲኖዶስ አባላት ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 6 ቀን 2001 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ የስብሰባ አዳራሽ ተሰብስበው የነበረ ቢሆንም፣ በማግስቱ፣ ትናንት በተነሳ ነጥብ ባለመስማማታቸው፣ 13 ሊቃነ ጳጳሳት ስብሰባውን አቋርጠው መውጣታቸውንና ጉዳዩ በጠረጴዛ ዙሪያ ሊፈታ ባለመቻሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁን ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ።” በማለት ጥለው የወጡትን ጳጳሳት ቁጥር ወደ 13 ዝቅ በማድረግ ፍጹም የተሳሳተ ዘገባ ይዞ ወጣ።

 

ረቡዕ ሐምሌ 7 ቀን 2000 ዓ.ም.

 

ከፌደራል ጉዳዮች ሚንስትር የመንግሥት ተወካይ የተላከለት ሲኖዶሱ በታዛቢ ፊት ስብሰባው የተከናወነ ሲሆን፣ ለዕለቱም ተይዞ የነበረው አጀንዳ ፓትርያርኩ ሥራ አስፈጻሚው ላይ የሰጡት የእግድ እርምጃ ይነሳ የሚል ነበር። እንደሰሞኑ ሁሉ በዕለቱ ፓትርያርኩ ግትር ሆነው የቆዩ ሲሆን፣ ጳጳሳቱ በአንድ ድምፅ እየለመኑ፣ እያግባቡና እየተቆጡ ለማሳመን ቢሞክሩም አሻፈረኝ ብለው ቆዩ።

 

በኋላ ማምሻውን ከመንግሥት ተወካይና ከጳጳሳቱ ሕገቤተክርስቲያን እንዲያከብሩ ሲጠየቁ “እንደውም ሕገ ቤተክርስቲያን የሚባል ነገር አላውቅም” በማለት ለሲኖዶሱ አስደንጋጭ ንግግር ተናግረዋል።

 

በዚህ ወቅት አንድ ጳጳስ “እኔ እየገባኝ እንዳለው እኚህ ሰውዬ ሕገ ቤተክርስቲያኑ የማወቅ ያለማወቅ ጉዳይ አይደለም። እዚህ ብንጨቃጨቅ ዋጋ የለውም። አሟቸው ሊሆን ስለሚችል ሆስፒታል እንውሰዳቸው።” ብለዋል።

 

ሌሎቹም ጳጳሳት ሕገቤተክርስቲያን የማያውቁ ከሆነ ፕትርክናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እንዲለቁ በማለት ጠንካራ ወቀሳ ሲሰነዝሩባቸውና እንዳውም ለዚህ አባባላቸው ተንበርክከው ይቅርታ ካልጠየቁ ሲኖዶሱ የሚያሳልፈው ውሳኔ ከባድ እንደሆነ በመግለጽ ገስጸዋቸዋል። በዚህ ግዜም እንደተባሉት ሳይንበረከኩ ወንበራቸው ላይ እንደተቀመጡ ሕገ ቤተክርስቲያንን አከብራለሁ እግዱን አንስቻለሁ በማለት እግዱን አንስተዋል። በማግስቱም አቡነ ሳሙኤል ላይ የሰጡትን እግድ እንዲያነሱ በሚጠይቀው አጀንዳ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ሰጥተው ተለያይተዋል።

 

ረቡዕ ሐምሌ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. ከምሽቱ አራት ሰዓት

 

ለስብሰባም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ጳጳሳቱ ከየሀገረ ስብከታቸው ሲመጡ የሚያርፉበት ቤት የሚገኘው አምስት ኪሎ ባለው የጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ውስጥ ባለ ሕንጻ ውስጥ ነው።

 

በዕለቱ አካባቢው የመብራት ተረኛ በመሆኑ መብራት አልነበረም፤ ጀነሬተሩም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ጠፍቷል። ልክ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ በህንፃው ላይ የሚገኙት የከምባታና ሃዲያ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ ሳዊሮስ፣ የአቡነ ኢጲፋኒዮስ፣ የአቡነ ሉቃስ፣ የመንፈሣዊ ኮሌጁ ዲን አቡነ ጢሞቲዎስ፣ የሰሜን ወሎ ሀገረስብከት ጳጳስ የአቡነ ቄርሎስ በር እኩል መደብደብ ይጀምራል በኃይለቃል ድምፅም እንዲከፍቱ ይጠየቃሉ። ሁኔታው ያላማራቸውና ጭለማው ፍርሃት የፈጠረባቸው ጳጳሳት ለፖሊስ ስልክ ይደውላሉ ግን የደረሰላቸው አልነበረም። በር ላይ ላሉት ጥበቃዎች በመደወል ድረሱልን በራችን እየተደበደበ ነው የሚል ጥሪ ያሰማሉ፤ መጣን ከማለት ውጭ የሚመጣላቸው ያጣሉ። ቤታቸው አጠገብ ላጠገብ ቢሆንም ደፍሮ የሚወጣ አልተገኘም። እርስ በርሳቸው ባደረጉት የስልክ ልውውጥ ከሳሎኖቻው ወጥተው መኝታ ክፍላቸው ለመግባት ተመካክረው ወደየመኝታ ክፍላቸው ይገባሉ። የሌሎቹ ጳጳሳት በር አልከፈት ሲል የሰሜን ወሎው ሀገረስብከት ጳጳስ የአቡነ ቄርሎስ በር ግን ተሰበረ። አቡነቄርሎስ መኝታ ክፍላቸው ገብተው የሚመጣውን ሲጠባበቁ፤ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች የመኝታ ቤቱን በር እየደበደቡ “ትከፍታለህ ክፈት” በማለት ስድብና ዘለፋን በመሰንዘር የመኝታ ቤታቸውን በር መደብደብ ይጀምራሉ፤ በመጨረሻም ያሰማራቸው ሰው እንዲመለሱ ትዕዛዝ ያስተላለፈላቸው በሚመስል ሁኔታ ጥለዋቸው ሄደዋል።

 

ሁኔታውን ለማመልከት በማግስቱ ስልክ ወደደወሉበት ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ለምን እንዳልደረሱላቸው ሲጠይቁ ፖሊሶቹ መምጣታቸውን፤ ነገር ግን በሩ ላይ ያሉት ጥበቃዎች ሠላም ነው ብለው እንደመለሱላቸው ገልጸዋል።

 

ከግቢው ውጭ ቃሊቲ በሚገኘው ቤተሰቦቻቸው ቤት አድረው የነበሩት የሐዋሳው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ ፋኑኤል ቤትም ሲደበደብ ያደረ ሲሆን፣ በሩ የብረት በመሆኑና አልከፍትም በማለታቸው ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ቀርቷል። የከምባታና ሃዲያ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ መልከጸዲቅ ላፍቶ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መጥተው በራቸው ለደበደቡት ሰዎች በመክፈታቸው ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ከቤታቸው ይዘዋቸው ጴጥሮስ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ባለ የደህንነት ቢሮ ወስደዋቸው በስብሰባው ላይ አክርረው የሚሰጡትን አስተያየት እንዲቀንሱ የሚያሳስብ ማስጠንቀቂያ ለሦስት ሰዓት ያህል ከተሰጣቸው በኋላ ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

 

ጳጳሳቱ በዚህ ሁኔታ ስብሰባ ተሰብስቦ ውሳኔ ማሳለፍ ለሕይወታቸው አስጊ በመሆኑ መንግሥት ለደህነታችን ጥበቃ ካደረገ አንሰበሰብም በማለታቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወርቅነህ ገበየሁ ሰብስቧቸው ምንም ስጋት እንዳይገባቸው ቃል በመግባት ተሰብስበው ውሳኔ እንዲያሳልፉ አዟቸው ሲኖዶሱ ለአርብ ተቀጥሮ ተለያይተዋል።

 

በትናንትናው ዕለትም ሲኖዶሱ ተሰብስቦ ለቤተክርስቲያኒቱ ሠላምና ለጳጳሳቱ ደህንነት ሲባል የአባ ሳሙኤል እገዳ ማንሳትን በሚመለከት የተያዘው አጀንዳ ለጥቅምት ወር እንዲተላለፍ ተወስኗል።

 

እስከዛው አቡነ ሳሙኤል በሥራ አስፈጻሚው ፀሐፊነታቸው እየሠሩ እንዲቀጥሉ፣ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ ፓትርያርኩ የሾሟቸው ግለሰብ ተነስተው ሲኖዶሱ የራሱን ሥራ አስኪያጅ እንዲሾም፤ ሥራ አስኪያጁም ተጠሪነቱ ለሲኖዶስ እንዲሆን በማለት ውሳኔ አስተላፈው በጥቅምት ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ተለያየተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!