የመንግሥት ባለሥልጣኖች በታዛቢነት ታድመዋል

Ethiopia Zare (አርብ ሐምሌ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. July 10, 2009)፦ እየተካረረ የመጣውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ውዝግብ ለመፍታት በማሰብ የተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ፤ ዛሬ አርብ ሐምሌ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. የመንግሥት ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በተገኙበት ማለዳ ላይ በቅዱስ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

 

ከማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. እስከ ሐሙስ ሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም. ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ጉባዔ፤ በአባላት አለመሟላት፣ “እኔ ጉባዔውን አልጠራሁም፣ ልሳተፍበትም ፈቃደኛ አይደለሁም፣ …” በማለት አቡነ ጳውሎስ ተቃውሞ በማቅረባቸው፤ እንደዚሁም የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ያቀረቧቸውንና እሳቸውን ወቃሽ ሃሳቦች “አልቀበልም! ... አቡነ ሳሙኤልን ማገዴ ጥፋት ቢሆንም፤ እሱ የአዲስ አበባ ሀገር ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ሆኖ እንዲቀጥል ፍላጎት የለኝም …” የሚል መከራከሪያ እና የልዩነት ሃሳብ በማቅረባቸው የሲኖዶሱ ቀዳማይ ጉባዔ 5 ለ30 በሆነ ልዩነት ሊስተጓጎል መቻሉ ታውቋል።

 

ይሄም መነሻ ሆኖ ከአቡነ ጳውሎስ በአቋምና በሲኖዶሳዊ አመለካከት የተለዩት 30 ሊቃነ-ጳጳሳት ረቡዕ እና ሐሙስ ዕለት በፓትሪያርኩ የፀሎት ሥርዓት ማካሄጃ ክፍል ውስጥ ስብሰባ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

 

የዛሬው - አርብ ጉባዔ የተጠራው በቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ኃላፊ በአቡነ ማቴዎስ እና በዋግ ዕምራ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ በአባ ቄርሎስ አስተባባሪነትና ሸምጋይነት መሆኑን የጠቆሙ የቤተክህነት ምንጮች፤ በዛሬው አርብ ሐምሌ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. ጉባዔ አቡነ ጳውሎስ እንደተወቃሽነታቸው በአድማጭነት ተሳትፎ የሚያደርጉበትም ነው ተብሏል።

 

በትላንትናው ዕለት ምሽት አቡነ ጢሞቲዎስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ አቡነ ሳሙኤል የመኪናቸውን ቁልፍ ተነጥቀው ከሀገር እንዳይወጡ (እንዳይንቀሳቀሱ) እግድ ተጥሎባቸዋል መባሉ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል።

 

ላለፉት 17 ዓመታትም የቅድስት ቤተክርስቲያኗ መንፈሣዊ አመራር በአቡነ ጳውሎስ ግለሰባዊ አምባገነንነት ሥር ወድቋል። የሲኖዶሱም የወሳኝነት ሚና ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። በዛሬው ዕለት ጉባዔን የጠሩትና የመንግሥትን ሰዎች በታዛቢነት የጋበዙት እነ አቡነ ቄርሎስ፤ የቤተክርስቲያኒቱን እና የሲኖዶሱን መንፈሳዊ ሥርዓትና ሕግጋት በመጣስ እግዚአብሔርንና ምዕመናንን አስቀይ መዋል በሚሏቸው አባ ጳውሎስ ላይ በማስረጃ የተደገፈ ክስና ወቀሳ ያቀረባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!