Special report on Coronavirus in Ethiopia

ከመጋቢት 7 - 13 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

ከኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች (ልዩ ጥንክር)

ኢዛ (ከየካቲት መጋቢት 7 - 13 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ የዓለምም የኢትዮጵያም ወቅታዊ አጀንዳ የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ያለው ጥፋት ነው። በኢትዮጵያም ይህ የአገር ሥጋት እየኾነ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ለመገደብ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ መኾናቸውን የሚያመላክተው በዚህም ሳምንት የመገናኛ ብዙኀን ቀዳሚ ዜና የመንግሥትም ተከታታይ መረጃዎች የኮሮና ቫይረስን የተመለከተ ነው።

ወትሮ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲጋጋሉ የነበሩ የፖለቲካ ወሬዎች ሁሉ ጥግ ይዘው የኮሮና ጉዳይ በሁሉም ስፍራ ቀዳሚ ኾነ።

ባሳለፍነው ሳምንት በእያንዳንዱ ዕለት ኮሮናን የተመለከቱ ዜናዎች ተደጋግመው የሚሰሙበት በመኾኑ ሌሎች ፖለቲካም ኾነ ከዚሁ ጋር ተያያዥ የኾኑ ጉዳዮች ጋብ ብለው ታይተዋል። በአጭሩ ወሬው ሁሉ ይኸው የወቅቱ የዓለማችን ወረርሽኝ ነው።

ጉዳዩ የዓለም ነውና በየዕለቱ በጣልያን ይህንን ያህል ሰው ሞተ፤ በአሜሪካ ተጠቂዎች ይህንን ያህል ሰው ደረሰ ከሚሉ ጋር የተገናኙ ናቸው።

ኢትዮጵያ ዛሬም ካሳለፍነው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ከዚሁ ጋር በተያያዙት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል። ይህንን ዘገባ በድረገጻችን ለንባብ ባበቃንበት ደቂቃ በዓለም ላይ 15 ሺህ 303 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ 349 ሺህ 676 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ መዳን የቻሉት ቁጥር ደግሞ 100 ሺህ 340 ነበር።

የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱ ይፋ የኾነው መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር። ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት ይፋዊ መረጃዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው አስራ አንድ መድረሱን ነው። የሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ዕለት መጋቢት 13 ቀን ነበር ይህ ቁጥር ይፋ የተደረገው። (ኢዛ)

ኮሮናና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ6 ቢሊዮን ብር ኪሳራ

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ ምናልባትም ብዙዎች በመልካም ያዩት ውሳኔ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ30 በላይ የሚኾኑ በረራዎችን እንዲያቆም መወሰኑ ነው።

ከ75 በላይ አገሮች በረራዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በእነኝህ አገራት ወደ 123 ከተሞች ዓለም አቀፍ በረራዎችን የሚያደርግ ሲሆን፣ አገር ውስጥ በሚያደርገው በረራ ደግሞ 22 መዳረሻ ከተሞች እንዳሉት ይታወቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ውጭ አገራት የሚያደርገውን በረራ ያቁም የሚለው ውትወታ የሰነባበተ ቢሆንም፤ አሁን የተወሰደውና ወደ 30 ከተሞች የሚያደርገውን በረራ የማቋረጥ እርምጃው በመልካም ታይቷል።

ይሁንና እነዚህ በረራዎች የአንዳንዶቹ ቀድሞም ቢሆን ይበርባቸው የነሩ አገሮች ውሳኔ የተላለፈበት እንደነበር ለመረዳት ይቻላል። ይህ በረራ የተቋረጠው በጊዜያዊነት ሲሆን፤ እየታየም በሌሎች በረራዎችም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ይፋ የኾነ መረጃ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 195 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደገጠመው ነው።

የአየር መንገዱ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንዳመለከቱት፤ ባለፉት ወራት የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በዓለም ደረጃ እስካሁን ባልታየ ሁኔታ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም የዚሁ ሰለባ በመኾን 195 ሚሊዮን ዶላር ከስሯል። አሁን ባለ የምንዛሪ ዋጋ ይህ የኪሳራ መጠን ወደ ስድስት ቢሊየን ብር ገደማ መኾኑን ያመለክታል።

ይህ ኪሳራ ከፍተኛ ሲሆን፤ እንዴት ሊቀጥል ይችላል የሚለውም ነገር ማሳሰቡ አልቀረም። (ኢዛ)

ኮሮና ቫይረስና የተረበሸው ገበያ

በኢትዮጵያ ከቫይረሱ መከሰት በኋላ በተለየ የታየው ነገር ገበያ ውስጥ ያለው ትርምስ ነው። ጥቂት የማይባሉ የንግድ ድርጅቶች ዋጋ ለመጨመር ጊዜ አልወሰዱም። በተለይ ለቫይረሱ መከላከያ የሚባሉ እንደ የአፍ ማክስ፣ ጓንት፣ አልኮልና ሌሎች የንጽሕና ዕቃዎች ፈጽሞ የማይጠበቅ ዋጋ ይዘው ብቅ አሉ። በሚገርም ሁኔታ የአፍ ማክስ 500 ብር ለመሸጥ ማስታወቂያ ያወጣ ጭምር ነበር። ነገር ግን የአፍ ማስክን 200 ብር ለመሸጥ ገዥም ተስማምቶ ለመግዛት እስከመደራደር ተደርሶ ነበር። ይህ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ከቫይረሱ መከላከያ ጋር ብቻ የተወሰኑ አልነበረም። 30 - 32 ብር ኪሎው ሲሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ጤፍ 40 ብር ድረስ ለመሸጥ ገበያ ወጣ፣ ሌሎች ምርቶችም በተለየ መጠን ጨምረው መሸጥ ተጀምሮ ነበር።

በዚህ ሳምንት ግን ከሞላ ጐደል ይህ የዋጋ ንረት ጋብ ብሏል። በአዲስ አበባና በሁሉም ክልሎች የዋጋ እድገት እንዳይኖር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ቁጥጥር ተገብቷል። እስከ ዓርብ ድረስ ያሉ መረጃዎች በአማራ ክልል ከአንድ ሺሕ በላይ፣ በአዲስ አበባ ከ760 በላይ፣ በደቡብ ከ216 በላይ የንግድ ድርጅቶች ታሽገዋል። በተለይ በአዲስ አበባ ከ70 በላይ የሚኾኑ የበርበሬ መሸጫ መደብሮች ታሽገዋል። ወፍጮ ቤቶችና ፋርማሲዎች ታሽገዋል። እነዚህ ሁሉ የታሸጉት ከመደበኛ ዋጋ በላይ በመሸጥና ያለአግባብ ምርት በማከማቸት ጭምር ነው።

ያለንግድ ፈቃድ ሲሠሩ ነበሩ የተባሉም በሰሞኑ የቁጥጥር ሥራ ንግድ ቤታቸው ታሽጓል። በዚህ ሳምንት በተደረገ ቁጥጥር መደብሮችን ከማሸግ ባለፈ ንብረታቸው ተወርሷል። የተወረሰው ምርትም በሸማቾች ማኅበራት በኩል ወደ ሸማቹ እንዲሠራጭ እየተደረገ ነው ተብሏል። እነዚህ ሕገወጥ ተግባር ፈጸሙ የተባሉ የንግድ ድርጅቶችም በሕግ እንደሚጠየቁ ተገልጿል። (ኢዛ)

የቫይረሱ ተጠቂዎች ማንነትና ያልተገባው ተግባር

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የቫይረሱ ተጠቂዎች ማንነት ለየት ያለ መስሏል። ይህም በኢትዮጵያ ቫይረሱ ተገኘበት ከተባለው የመጀመሪያውን ጃፓናዊ ጨምሮ ከአሥራ አንዱ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ስድስቱ የውጭ ዜጐች መኾናቸው ነው። በጤና ጥበቃ የእስካሁን ሪፖርት የሚያመላክተው ሦስቱ ጃፓናውያን አንድ አውስትራሊያዊ፣ አንድ እንግሊዛዊ ናቸው። ይህም ብልጫ ያለው የቫይረሱ ተጠቂዎች የውጭ አገር ዜጎች መኾናቸውን ያሳያል። ይህ ሁኔታ ግን ሌላ መዘዝ ይዞ መጥቷል። መዘዙ ደግሞ አደጋ ያለው መኾኑንም የሚጠቁም ነው። በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ነጮችን ወይም የውጭ ዜግነት ያላቸውን ሰዎች ማግለል ያስከተለ እንዲያውም ጥቃት እንዲሰነዘርባቸው ስለማድረጉ ተነግሯል።

ይህ ጉዳይ ግን በንግግር ብቻ የተተወ አይደለም፤ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደገው የአሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ እንዲያወጣ አስገድዷል። መግለጫውም የኮሮና ቫይረስ እናንተ ናችሁ ያመጣችሁብን በማለት የውጭ ዜጐች ላይ ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ፤ ሁኔታው እንዳሳሰበው ጭምር በማከል፤ የውጭ ዜጐች እንዲህ ዐይነት አደጋ እንዳይደርስባቸው ማስጠንቀቂያ እስከመሥጠት ደርሷል።

ይህ መግለጫ እንደተሰማ ግን በመንግሥትም ኾነ ኃላፊነት በሚሰማቸው የሚዲያ አካላት ድርጊቱ ተፈጽሞ ከኾነ፤ ፈጽሞ የማይገባ መኾኑን በማስረገጥ አውግዘዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን ከሰነዘሩት ውስጥ አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆኑ፤ በጽሕፈት ቤታቸው በኩል፤ “ቫይረሱን የመከላከል ጥረታችን ሰብአዊነታችንን የሚጋርድና ርኅራሄን የሚያስጥል መኾን አይኖርበትም። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካል እንደመኾናችን መጠን አንዳችን የአንዳችን ጠባቂዎች በመኾን ቫይረሱን መከላከል ይገባል። ከዚህ ባለፈም የበሽታ ፍርሐት ሰብአዊነታችንን እንዲነጥቀን አንፍቀድ” በማለት ይህንን ጉዳይ አውግዘዋል። አሁንም ግን ሕብረተሰቡ በዚህ አንፃር አመለካከቱ ማስተካከያ ግድ ይለዋል።

የቫይረሱ መተላለፊያ መንገድ ንክኪ መኾኑ እየታወቀ ሕብረተሰቡ በእንዲህ ያሉ ሰልፎች መታየቱ አደገኛ እስከመባል ደርሷል።

ቫይረሱን ለመከላከል አልኮል ለመግዛት የተሰለፈው ሸማች በሌላ አገላለጽ እግረ መንገዱን ቫይረሱ ያለበት ሰው ካለ ቫይረሱንም ሸምቶ ይገባል ተብሎ የተሠጠ አስተያየት ለመቀበል ያልፈለጉ ሸማቾች፤ በዚህ ሳምንት በተለያዩ የከነማ ፋርማሲዎች ታይተዋል። ብዙዎች ከቫይረሱ ይሰውራችሁ በማለት አለፉት እንጂ የኾነውን ማወቅ አይቻልም።

ይህ ሁኔታ በዚሁ መቀጠል እንደሌለበት ታምኖ፤ በቂ አልኮልና የጽዳት ዕቃዎች እየተመረቱ በመኾኑ፤ በከነማ ፋርማሲ የሚደረገውን ሽያጭ እንዲቆም ተደርጓል።

እነዚህ ምርቶች በሸማቾችና በሕብረት ሥራ ማኅበራት መደብሮች በኩል እንዲታደል ተደርጓል። (ኢዛ)

ከመልካም ተግባሮች በጥቂቱ

የቫይረሱ ሥርጭትን ለመከላከል አንዱ መላ ደጋግሞ እጅን መታጠብ ነው። ይህንን ከቤት ውጭ ለመተግበር የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ደጃፋቸው ላይ ሰዎች እጃቸውን ታጥበው እንዲገቡና እንዲወጡ እያደረጉ ነው።

በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በጐ አድራጊ ወጣቶች የእጅ ማስታጠቢያ በማዘጋጀት ሰዎች ሲያልፉና ሲያገድሙ እንዲታጠቡ እያደጉ ይገኛሉ።

የሕዝብ ማመላለሻዎች በተለይ ታክሲዎች ትርፍ ሰው እንዳይጭኑ የሚደረገው ቁጥጥርም፤ መልካም ቢኾንም አሁንም አንዳንዶች ይህንን እየጣሱ ከልክ በላይ እየጫኑ እየተመለከትን ነው። ተጠቃሚውም ይህንን ለመከላከል ያለመቻሉ ግን ለአደጋ ማጋለጡ አልቀረም።

የከተማ ባቡር ንጽሕናው እንዲጠበቅ በፀረ ተዋስያን እየታጠበ ሲሆን፤ መነሻና መድረሻ ላይ የሚደረገው የእጅ ማስታጠብ ተግባር እንደ መልካም የሚታይ በጐ ተግባር ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ከንቲባው እንዲህ ያሉ በጐ ተግባራትን በማበረታታትና በተለይ የጽዳት ዕቃዎችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያደርጉት ድርጊት አሁንም መቀጠል ስላለበት የሚደገፍም ነው።

የኢትዮ ቴሌኮም የስብሰባ ጥሪ ድምፆችን ቫይረሱን በተመለከተ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚያሳስብ እንዲኾን ማድረጉ ሌላው የተመለከትነው ጥሩ ነገር ሲሆን፤ ይህንን መልእክት በተለያዩ ቋንቋዎች ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም አሳውቋል።

ንግድ ባንክ ደንበኞቹ ወደየ ቅርንጫፎች ሲመጡ የእጅ መታጠቢያ ማዘጋጀቱ መልካም ሲሆን፤ ሌሎችም ሊከተሉት የሚገባው ነው። ዳሸን ባንክና ሕብረት ባንክ በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ደንበኞች በኤትኤም እንደሚጠቀሙና በቀን ማውጣት የሚገባቸውን ወጪ ከፍ ማድረጉ አንዱ ሲሆን፤ ለዚህ የሚያስከፍለውን የአገልግሎት ክፍያ ነፃ አድርጓል። በሌሎችም አምስት አገልግሎቶቹ ላይ የዋጋ ቅናሽና በነፃ እንዲኾን መወሰኑን አስታውቋል። (ኢዛ)

ኮሮናና ኢኮኖሚ

የኮሮና ቫይረስ በመጀመሪያ በቻይና መገኘቱ ከተሰማና ወረርሽኙ እየሰፋ ሲመጣ፤ በቻይና ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ሳይታለም የተፈታ ነበር። ችግሩ ግን የዓለም ሁለተኛዋ ኢኮኖሚ የኾነችውን ቻይናን በመፈተን ብቻ የሚገታ ያለመኾኑን ኢኮኖሚ ባለሙያ ትንተናን የሚጠይቅ ስላለመኾኑም ግልጽ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የዓለም ኢኮኖሚ ከቻይና ጋር ያለው ትስስር እጅግ ከፍተኛ በመኾኑ ነው። ውሎ አድሮ ቀውሱ የዓለም እየኾነ መምጣቱን በግልጽ ያሳየው የዓለም የኢኮኖሚ መለኪያ ተደርጐ የሚወሰደው የነዳጅ ዋጋ በእጅጉ ማሽቆልቆል ነው። የነዳጅ ዋጋ እንዲህ ባለ ሁኔታ ሲያሽቆለቁል የዓለም ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ መግባቱን እንደሚያመለክት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያሰምሩበታል።

ዛሬ የኮሮና ቫይረስ ዓለምን እየደቆሰ ሲሆን፤ በአንፃሩ በቻይና የቫይረሱ አዙሪት ጋብ ብሎ በቫይረሱ የሚጠቃ ሰው ሳይመዘገብ የሚውልበት ቀን ተፈጥሯል። ይህ መልካም እድል ቢኾንም፤ አሁንም የዓለምን ኢኮኖሚ ወደነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ስላለመኾኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሳይጠቁሙ አያልፉም። ምክንያቱ ደግሞ በቻይና የቱንም ያህል ቫይረሱ ቢረጋጋ፤ ከእርሷ ላይ ምርቶችን ይገዙ የነበሩ አገሮች ለሸመታ የሚኾናቸውን ገንዘብ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ እየዋሉ መኾኑ አንዱ ችግር ሊሆን ይችላል። በአንፃሩ ግን ቻይና ለዚህ ቫይረስ መከላከል ለሌሎች ዓለሞች ተርፋ ኢኮኖሚውን ከፍ ለማድረግ እድል ያለመኾኑን ሳይገልጹ አላለፉም። ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ግን አሁንም ብዙ የሚያልፉ መኾኑን ነው። ይህ ለቫይረሱ ፈውስ የሚኾን መድሃኒት ማግኘትን ጭምር ያካትታል። አሁን ባለው ደረጃ እየፈጠረ ያለው ቀውስ ግን የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል። ኢትዮጵያም የዚሁ አካል ኾናለች።

ለሌሎች ተግባራት ሊወጣ የሚችል በጀት ይህንን ቫይረስ በመከላከል ለሚደረግ ጥረት እንደሚውል ከወዲሁ እየታየ ነው። እየተዛባ የመጣውን የአገር ውስጥ ገበያ ለመደገፍ በድጐማ ጭምር ለሕብረተሰቡ ሊቀርቡ የሚችሉ ምርቶችን ለመግዛት ተጨማሪ በጀት የሚሻ ስለኾነ የዶ/ር ዐቢይን መንግሥት መፈተኑ አይቀርም። አገርን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ይረዳሉ የተባሉ የኢኮኖሚ ፕሮግራሞችን ወደተግባር ለመቀየር ሊከብድ እንደሚችል ይጠቁማል።

የወጪ ንግድ የሚያዳክም በመኾኑ በቂ የውጭ ምንዛሪ አለማግኘት ብቻ ሳይሆን፤ የአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከማስከተሉም በላይ፤ የአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የኾነው ሬሚታንስ ገቢ በእጅጉ ይጐዳል። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለየዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ በያሉበት አገር ያለው የኢኮኖሚ ድቀት ሰለባ ስለሚኾኑ ወደ አገር ውስጥ (ኢትዮጵያ) የሚልኩት ገንዘብ ያጥራል፤ ይህም ሌላ ተጨማሪ ጉዳት ነው።

በአገር ውስጥም ቢኾን የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ መዳከም ተቋማት ሠራተኞች ወደመቀነስ የሚገቡ መኾኑን የሚያመለክት ኾኗል። ምክንያቱም በውጭ ምንዛሪ በሚገባ የጥሬ ዕቃዎች የተመሠረተው የአገሪቱ የማምረቻ ተቋማት በቂ አቅርቦት ስለማይኖራቸው በሙሉ ኃይል ሊሠሩ አይችሉም።

ገና ከወዲሁ አንዳንድ ድርጅቶች ሠራተኞች የዓመት ፍቃድ እንዲወጡ እያደረጉና በሁለት ሺፍት የሚሠሩ ወደ አንድ እየወረዱ ነው። ይህ ደግሞ ሌላ ቀውስ ነው። ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ይህ ወቅት እጅግ ፈታኝ ነው። መንግሥት ቢያንስ ይህንን ችግር ለመወጣት የአጭር ጊዜ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መቅረጽ ግድ ሊለው ይችላል። በተለይ የቫይረሱ ሥርጭትን አሁን እየተወሰዱ ባሉት እርምጃዎች ማርገብ ካልተቻለ፤ ጠንከር ያሉ እርምጀዎች ያሻሉ። ለዚህ ደግሞ ያገባናል የሚሉ ወገኖችን ባሳተፈ መልኩ ሁነኛ ሥራ መሠራት ይጠበቅበታል።

ሕዝቡም ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመረዳት በመንግሥት ሊቀርቡ የሚችሉ የተሻሉ አማራጮችን በመረዳት ለተግባራዊነቱ መተባበር አለበት። እንዲህ ባለወቅት ያለ ትብብር አስቸጋሪ ጊዜን ለብቻ ተጋፍጦ ማለፍ የማይችል ነው።

እንደ ብዙዎች እምነትም ችግሩን እንደ ችግር በመቀበል ለመፍትሔው ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ዛሬ ቫይረሱን ለመከላከል ተጨማሪ ውሳኔዎች ተወስደዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች በ30 መዳረሻዎች መቀነስ፣ የምሽት ክበቦች መዘጋት፣ አንዳንድ ተቋማት አገልግሎት ቆጠብ እንዲል መደረጉ፤ በተለይ የአገልግሎት ዘርፍ ሊያመነጭ የሚችለውን ሀብት በእጅጉ ይጐዳል። እንደምሳሌ በአየር መንገዱ የ30 መዳረሻዎችን በረራ ማቆም አገሪቱን ሚሊዮን ዶላሮች ያሳጣታል። እስካሁንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አየር መንገዱ 195 ሚሊዮን ዶላር ማጣቱንም ልብ ይሏል።

ከእነዚህ በረራዎች መቋረጥ ጋር ተያይዞ ዛሬ አዲስ አበባን የሚያደምቁ ሆቴሎች የገቢ ምንጭ ከሚታሰበው በላይ ይቀንሳል ወይም ገቢ ይታጣል። አዲስ አበባ የምትታወቅበት የኮንፈረንስ ቱሪዝም በእጅጉ ይጎዳል፤ ይመታል ተብሎ ይጠበቃል። በተከታታይ ሦስትና አራት ወራት አዲስ አበባ ላይ ይስተናገዳሉ የተባሉ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም፣ የፊፋ ጉባዔ፣ የተመድ የተለያዩ ፕሮግራሞች ስብሰባዎች እና ሌሎች ትላልቅ ስብሰባዎች አይካሔዱም ተብሏል። ይህ በአገሪቱ ገቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራልና ይህንን ሁሉ ክፍተት ለመድፈን ብዙ መሠራት አለበት። እነዚህ የተዘረዘሩ የኢኮኖሚ ጉዳቶች ሁሉም ላይ የሚታዩና ሁሉንም የሚጎዱ መኾኑ አይቀርምና፤ ቫይረሱን ከመከላከል ጐን ለጐን በብዙ ምክንያት ሊጐዳ የሚችለውን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ፖሊሲ ያሻል የሚባለውም ለዚህ ነው። (ኢዛ)

ኮሮናን ለመከላከል ከመንግሥት የተላለፈው ሁለተኛው ውሳኔ

በዚህ ሳምንት ኮሮናን በተመለከተ የተሠጠው ተጨማሪ መረጃና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድም የሠጡት መግለጫ ነበር።

ኮሮናን ለመከላከል የተቋቋመ ብሔራዊ ኮሚቴው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠጡት መግለጫ ተያያዥነት ነበራቸው። ብሔራዊ ኮሚቴው መጀመሪያ ትምህርት ቤቶችና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ለ15 ቀን እንዲዘጉ፤ እንዲሁም ሌሎች ውሳኔዎችንም ያሳለፈ መኾኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሳምንትም መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ተጨማሪ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ይፋ ያደረገበት ነው።

ከእነዚህ ውሳኔዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሰላሳ መዳረሻዎች የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ ማድረግ ነው። ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀን በራሳቸው ወጪ በሆቴሎች ራሳቸውን ለይተው ያቆዩ መባላቸውም አዲስ ውሳኔ ሲሆን፤ ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የኾነው ዘመናዊው ስካይላይት ሆቴል ለዚሁ ማቆያ አገልግሎት እንዲውል ተወስኗል። ግዮን ሆቴልም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሠጣል ተብሎ ይጠበቃል።

መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የተሠጠው ሌላው አዲስ ውሳኔ፤ ታራሚዎችን እስር ቤት ሔዶ መጠየቅ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ተወስኗል። ከዚህ ጐን ለጐን የተመረጡ አንዳንድ የሕግ ታራሚዎች ከእስር እንደሚለቀቁ ተገልጿል። ከእስር ይለቃቃሉ ተብለው የሚጠበቁት የእርምት ጊዜያቸው ወይም ለመፍታት የተወሰነ ጊዜ የቀራቸው፣ በቀላል ጥፋት ማረሚያ ቤት የሚገኙ እንዲፈቱ ይደረጋል። ሕፃናት የያዙ ታራሚዎችም የዚህ እድል ተጠቃሚ ይኾናሉ ተብሏል። ከዚህ በተለየ ማረሚያ ቤቶች ጊዜያዊ ማቆያዎችን እና ሌሎች ስፍራዎችን በመጠቀም መተፋፈግን እንዲያስቀሩ የተወሰነ ሲሆን፤ ወደማረሚያ ቤት የሚገቡ አዲስ ታራሚዎች ካሉ ከኮሮና ነፃ መኾናቸው ምርመራ እንዲያካሒድላቸው ሁሉ ውሳኔ ተላልፏል። ከዚህ ውሳኔ ጐን ለጐን አዲሷ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የቃሊቲ ማረሚያ ቤትን ጐብኝተዋል።

ኮሮናን ለመከላከል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ከሰሞኑ ያስተላለፈው ሌላው ውሳኔ፤ የጭፈራ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች ለጊዜው ሥራ እንዲያቆሙ ነው። ከዚህ ውሳኔ በኋላ በተለይ ቅዳሜ መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎት እየሠጡ የነበሩ ጭፈራ ቤቶችና ትላልቅ መጠጥ ቤቶች የጸጥታ ኃይሉ እንዲዘጉ እያደረገ ነበር። ይህ የመንግሥት ውሳኔ በትክክል እየተተገበረ ያለመኾኑ ቅዳሜ ምሽት ላይ ታይቷል።

የብሔራዊ ኮሚቴው ሌላ ውሳኔ ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን የመቆጣጠሩን ሥራ አጠንክሮ የሚቀጥል መኾኑን ማሳወቁ ነው። ብሔራዊ ኮሚቴው ውሳኔ የሠጠበትና ለሕብረተሰቡ ያሳሰበበት ሌላው ነጥብ፤ ከውጭ ዜጐች ጥቃት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ሥጋት ነው። ይህ ድርጊት አግባብ አለመኾኑን ያወገዘው ብሔራዊ ኮሚቴው፤ “የውጭ ዜጐችን መተንኮስ ተቀባይነት የሌለውና ኢትዮጵያዊ ያልኾነ ጥፋት ነው። ሕዝቡ ቫይረሱ ዘርና ዜግነትን የማይለይ መኾኑን ተገንዝቦ፤ የውጭ ዜጐች ላይ ጣት ከመቀሰር እና ከማግለል ይልቅ ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሠረት ቫይረሱን የመከላከል እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል” ብሏል። ከሰሞኑ ችግር ጋር በበጐ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትንም አመስግኗል። (ኢዛ)

ምርጫ 2012 እና ኮሮና

በመጪው ነኀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አገሪቱ ምርጫ ታደርጋለች ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ወትሮም ብዙ ጥያቄዎች ሲቀርቡበት የነበረው የዘንድሮ ምርጫ 2012፤ አሁን ደግሞ ሌላ ችግር ያንዣበበት መስሏል። ይህም የቫይረሱ ሥርጭት የሚሰፋና የሚያሰጋ ከኾነ፤ ምርጫውን ማካሔድ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ነው።

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሠጡት መግለጫ፤ ጉዳዩን የምርጫ ቦርድ እየተመለከተው እና ውሳኔ የሚሠጥበት መኾኑን ነው። ኾኖም ቫይረሱ ሥርጭት እና ሊያስከትል የሚችለው ማኅበራዊ ቀውስና ኢኮኖሚያዊ ችግር በርካታ አገራዊ ጉዳቶች ሊኖረው ይችላል የሚለው የብዙዎች ሥጋት ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ ምርጫ ነው። የምርጫው ጊዜም ሲታይ ጥቂት ወራት ብቻ የቀረው በመኾኑ፤ እስከ ምርጫው ጊዜ ድረስ ቀድሞ የሚተገበሩ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም።

በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው መሠረት የምርጫ ሒደቶችን ሊያሳኩ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ኾኑ የምርጫ ቦርድ ሥራዎች ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ በመኾኑ፤ የምርጫ ቦርድን መፈተኑ አይቀርም ተብሎ ተሰግቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው ሳምንት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ዓለም አቀፍ ችግር የኾነው የኮሮና ቫይረስ ሥጋት፤ በምርጫ ኦፕሬሽን ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ እንዲሁም ሊወሰዱ ስለሚችሉ አማራጭ እርምጃዎች ውይይት አከናውኗል። የገዥው ፓርቲን ጨምሮ 45 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁለት የተለያየ ዙር በዚህ ጉዳይ ላይ በተደረገው ውይይት የተሳተፉ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ያለው አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ለጥቂት ሳምንታት እንኳን ከቀጠለ በቀጣይ በዋናነት መፈጸም በሚገባቸው የመራጮች ትምህርት፣ የአስፈጻሚዎች ሥልጠና፣ የቁሳቁስ ሥርጭት ከፍተኛ የሰው ዝውውርን የሚያሳትፉ በመኾናቸው የመራጮች ምዝገባ ዝግጅት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አቅርቧል።

ከዚህ በተጨማሪ ወረርሽኙ በዚህ መልኩ ከቀጠለ፤ ምርጫው ዝርዝር አፈጻጸም እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተፅዕኖዎችን እና ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ግምገማ ከፓርቲዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በተከታታይ እንደሚያደርግ አሳውቋል። ፖለቲካ ፓርቲዎችም በበኩላቸው ይህንን አገራዊ እና ዓለም አቀፍ ችግር በምርጫ ሒደት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ እንደሚገነዘቡ ገልጸው፤ መደረግ አለባቸው ያሏቸውን ሐሳቦች ያጋሩ ሲሆን፤ ከሁኔታዎች በፍጥነት ተለዋዋጭነት አንጻርም ቦርዱ እነዚህን ሁኔታዎች እያገናዘበ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት የተደረገባቸው ውሳኔዎችን እየወሰነ መሔድ እንዳለበት አስተያየታቸውን ሠጥተዋል። ቦርዱም የዚህ ዐይነት ተከታታይ ውይይቶችን እንደሚያከናውን አሳውቋል። (ኢዛ)

የእምነት ተቋማት ማሳሰቢያ

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሃይማኖታዊ ክንውኖችን ለተወሰነ ጊዜ መገደብ አስፈላጊ በመኾኑ፤ የሃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ የሃይማኖታዊ ጉዞዎች ለጊዜው እንዲቋረጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያሳሰበች ሲሆን፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትም ማንኛውም ሙስሊም በሽታው አስጊ በኾነበት ሁኔታ ጁምአና ከጁምአ መቅረት በሸሪአ የተፈቀደ ሲሆን፤ በየቤቱ መስገድ ይችላል ብሏል። ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የተለያዩ ተቋማት አንዳንድ አገልግሎታቸውን እያቋረጡ ቢሆንም፤ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ብዙ ሕዝብ የተገኘበት ስብሰባ እየተካሔደ መኾኑ አሳሳቢ ኾኗል። በተለይ የብልጽግና ፓርቲ ያዘጋጃቸው ናቸው የተባሉ ስብሰባዎች ከአንድ ሳምንት በፊት የተወሰነውን የመንግሥትን ውሳኔ የተጻረረ ነው በሚል እየተተቸ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ