Prosperity Party

ብልጽግና ፓርቲ

ፓርቲው በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ያስገኘውን ሀብትና ንብረትና ዕዳ የሚያሳይ የሒሳብ ሪፖርት ለቦርዱ እንዲያቀርብ ቦርዱ ወስኗል

ኢዛ (ዓርብ ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 27, 2019)፦ ሦስቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶችና በአጋርነት ሲገለጹ የነበሩት አምስት ፓርቲዎች ራሳቸውን በማክሰም ብልጽግና ፓርቲን በመመሥረት እውቅና እንዲሠጣቸው ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል።

አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ቦርዱ ጥያቄውን ከመረመረ በኋላ እውቅናውን መሥጠቱን የሚያረጋግጥ ውሳኔ አሳልፏል።

ምርጫ ቦርድ የእውቅና ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ ተጨማሪ መሟላት ያለባቸውን ሰነዶች ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲያሟሉ መጠየቁንና ታኅሣሥ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የጥያቄዎቹ ምላሾችና ማብራሪያዎች ተሟልተው መቅረባቸውን በማረጋገጡ፤ ብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሠጠው መወሰኑም ታውቋል።

ስምንቱ ፓርቲዎች በየፊናቸው በጠቅላላ ገባዔያቸው ውሳኔ መሠረት አድርገው ውሕደቱን ለመቀላቀልና ፓርቲያቸውን ለማክሰም የወሰኗቸው ውሳኔዎች፤ እንዲሁም ውሕደቱን ለመመሥረት ያደረጉትን ስምምነት በሙሉ ሕጉን ተከትሎ የተፈጸመ በመኾኑ፤ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ተሰርዘው ብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሠጠው ውሳኔ ላይ መደረሱን ይኸው የምርጫ ቦርድ መረጃ ያስረዳል።

በመኾኑም ውሕዱ ፓርቲ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 92/2 መሠረት በተመዘገበ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ውሕደቱ ያስገኘውን ሀብት፣ ንብረትና ዕዳ የሚያሳይ የሒሳብ ሪፖርት ለቦርዱ እንዲያቀርብም ቦርዱ መወሰኑ ታውቋል።

ይህ ውሳኔ ኢሕአዴግ የሚለው መጠሪያ ቀርቶ ብልጽግና ፓርቲ እውን መኾኑን ያሳየ ኾኗል። በዚህ ውሕድ ፓርቲ ውስጥ ሕወሓት ያልተካተተ እንደኾነ ይታወቃል።

ብልጽግና ፓርቲን ተዋሕደው የመሠረቱት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ፓርቲ (ጋሕአዴን) እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ) ናቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ