የ2012 ዓ.ም. 33ኛ ሳምንት አንኳር ወሬዎች
ከሚያዝያ 12 -18 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ
የዓመቱ ሠላሳ ሦስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች
ኢዛ (ከሚያዝያ 12 - 18 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዜናዎች ባሻገር ሌሎች ክንውኖች የሚመለከቱ የተለያዩ ዜናዎች ብቅ ያሉበት ነው ማለት ይቻላል። ከእነዚህ ውስጥ በዓባይ ተፋሰስ አገሮች አወዛጋቢ የኾነው የህዳሴ የውኃ ሙሌት መርኀ ግብርን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአቋሟ መጽናትዋን ያረጋገጠችበትን የውኃ ሙሌት ሥራውን ለማድረግ ዝግጅት መጀመሯንና የግድቡ ሥራ ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ ያሳወቀችበት መረጃ ተጠቃሽ ነው። በመጪው ክረምት አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደውንም ከግብ ለማድረስ እየተሠራ መኾኑንና ለዚሁ የሚኾነውን ችግኝ ልማት ያለበትን ሁኔታን የሚያሳይ የመስክ ጉብኝት መደረጉም ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው።
ከኮሮና ቫይረስ መከሰትና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ቀዝቀዝ ያሉ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት በአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች ብዙ ያስባለ ጉዳይ ተከስቷል። ይህም በታላቁ ቤተ መንግሥት መግቢያ ላይ የሁለት ፒኮክ ቅርጾች መገንባታቸውና ለዕይታ ይፋ መኾንን ተከትሎ እንዴት በቤተ መንግሥት ደጃፍ ላይ ይህ ይሠራል የሚል ተቃውሞ እያቀረቡ ነው።
በዚህ ጉዳይ የተለያዩ አመለካከቶች እየተንሸራሸሩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ በአንበሳ ምልክት የሚታወቀው መለያችን ተነካብን የሚሉ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አንበሳ ወይም ፒኮክ መኾኑ ሳይሆን ይህ ምልክት በቤተመንግሥቱ መግቢያ ላይ መሠራቱ ለምን? እያሉ እየጠየቁ ነው። ይህ ቢደረግ ምን ችግር አለው ብለው የሚሞግቱም ለመቃወም ሲባል የሚደረጉ ነገሮችን በመፈለግ አጀንዳ ማድረግን ሲኮንኑ ተሰምቷል። ስለሁኔታው ታዋቂ ሰዎችም ሰሞናዊውን ትኩሳት ያላቸውን ሐሳብ እንዲሰነዝሩም አድርጓል።
በይበልጥ ግን ይህንን ጉዳይ አጀንዳ ማድረግ በተለይ ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ስንት ችግር ባለበት አገር ይህ ጉዳይ እንዲራገብ ያዘኑም አሉ። ከሁሉ በተለየ ደግሞ ባልደራስ በመባል የሚታወቀው ፓርቲ አንበሳ ኢትዮጵያን የሚገልጽ ምልክት ነውና በፒኮክ መቀየር የለበትም በሚል ተቃውሞውን አሰምቷል። ተቃውሞውንም ፊርማ በማሰባሰብ ለመግለጽ ተነስቻለሁ ማለቱ ጋብ ያለውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የቻለም ተደርጐ ተወስዷል።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ እንደ መልካም የሚታዩ የተለያዩ ክንውኖች ስለመኾናቸው የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ሰንብተዋል። በተለይ በሳምንቱ ውስጥ በ24 ሰዓት ከአንድ ሺሕ በላይ የኮሮና ቫይረስ የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉ አንዱ ሲሆን፤ በቀጣይ ሳምንት የመመርመር አቅምን እስከ አምስት ሺሕ ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም በመልካምነት የሚታይ ነው። ከዚህ ሌላ እስከ ትናንት ሚያዚያ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች 41 የሚኾኑ ማገገማቸው ነው። ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ ወረርሽኙን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው “ትምህርት በቤቴ” በሚል በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ እንደ ዋትስአፕና ቤሌግራም የሞባይል አፕሊኬሽኖች ትምህርት መጀመሩ ነው። ከተፈጥሮ አደጋ ጋር በተያያዘ ጐርፍ የሚያጠቃት ድሬዳዋ በዚህም ሳምንት በደረሰ ጐርፍ አራት ነዋሪዎቿን አሳጥቷታል።
ከቢዝነስ ዜናዎች የኦጋዴንን የተፈጥሮ ጋዝ አውጥቶ ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ከቻይና ኩባንያ ጋር መደረጉ የሚጠቀስ ነው። ከዚህም ሌላ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ያሉ ላኪዎች ወደ ወደብ በሚደረግ የባቡር ጉዞ በነፃ ዕቃቸውን እንዲጭኑ መወሰኑና በሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች ላይ እስከ 73 በመቶ ቅናሽ እንዲደረግላቸው ውሳኔ የተላለፈውም ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነው። እንዲህ ካሉት የሳምንቱ ዜናዎች የተወሰኑትን የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አቀናብሮ አቅርቧል። መልካም ንባብ!
ትምህርት በቤቴ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመማር ማስተማር ሒደቱን ካስተጓጐለ ከወር በላይ ኾኖታል። ተማሪዎች ከቤት ውለዋል። ይህ ጉዳይ በቀጣይም ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ ለወላጆችም ለመንግሥትና ለትምህርት ተቋማትና ማኅበረሰቡ ግራ ያጋባ ኾኗል። ከሰሞኑ ግን እንዲህ ሆኖ ከመቀጠል ተማሪዎች ቤት ኹነው ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት ሥርዓት መዘርጋቱን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ገልጿል።
እንደ አዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ መረጃ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ በማሰብ የሚተገበር ነው። ይህም በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ እና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በመታገዝ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች እንዲተላለፉ እየተደረገ ነው።
ሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮም በአፍሪ ሄልዝ ቲቪ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርት ሙሉ በሙሉ መሠጠት መጀመሩንም አሳውቋል።
ከዚህም ሌላ በኤፍ ኤም 97.7 እና ቴሌግራም እና ዋትስአፕ በመሳሰሉት ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በሁሉም የትምህርት ክፍሎች የተለያዩ የትምህርት ዐይነቶችን ቀጥታ የማስተማር ሥራ እየተካሔደ መኾኑንና ከአማርኛ እና ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ በአፋን ኦሮሞ ትምህርቱ በመሠራጨት ላይ ስለመኾኑም የአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ገልጿል። ትምህርት በቤቴ በሚል የጀመረው መርኀ ግብር ምን ያህል ተማሪዎች እየተጠቀሙበት እንደኾነ ግን አልተገለጸም። (ኢዛ)
ጐርፍ የማያጣት ድሬ
በሳምንቱ ከተሰሙት አሳዛኝ ዜናዎች ውስጥ ወቅት እየጠበቀ ጐርፍ የሚያጠቃት ድሬዳዋ ሰሞኑንም የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉ መገለጹ ነው።
ሐሙስ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የመኖሪያ ቤቶችን ማፈራረሱንም የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል። በጎርፉ በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩ የአራት ዓመት ሕፃን እና የሁለት ወር ጨቅላ ሕይወታቸው ማለፉን የሚያመለክተው የፖሊስ መረጃ፤ የ19 ዓመት ወጣት እና 45 ዓመት ጎልማሳ በጎርፍ ተወስደው ሕይወታቸው አልፏል።
ከዚህም ቤት 3 ባጃጆችና የፎርስ ተሽከርካሪዎችም አሸዋ ውስጥ ተቀብረው መገኘታቸውንም የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ እና የመኖሪያና የመሥሪያ ቤት አጥሮችን በማፍረስም አፍርሷል ተብሏል። (ኢዛ)
የኮሮና ለይቶ ማቆያ ጉብኝትና የሕክምና ባለሙያዎች ጥያቄ
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ በኤካ ኮተቤ የኮቪድ 19 ለይቶ ማቆያና የሕክምና መስጫ ማዕከል የመስክ ምልከታ አድርጓል። የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበትን ጨምሮ ሌሎች አባላትን የያዘው ቡድን የጉብኝት ዋና ዓላማ ከሆስፒታሉ ሥራ ጋር በተያያዘ በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ሥራውን ከሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመወያየት አሉ የተባሉ ችግሮችም መፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ነው።
በዚህም ጉብኝት ወቅት በሆስፒታሉ ኃላፊዎች ቫይረሱ በአገሪቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እያከናወነ ባለው ተግባር እና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ለቦርዱ አባላት ማብራሪያ ስለመሠጠቱ የሚያመለክተው መረጃ አሉ የተባሉ ችግሮችም ያስረዱበት ነው።
ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ 450 በቫይረሱ የተያዙና የተጠረጠሩ ታካሚዎች ወደ ማዕከሉ ገብተው የወጡ መኾኑ የገለጸ ቢሆንም፤ ጉብኝቱ እስከተከሰተበት ዕለት ድረስ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ 73 ታካሚዎች በሕክምና ላይ እንደሚገኙም ተገልጾላቸዋል። ባለሙያዎቹም መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ ለመወጣት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መኾናቸውን በመጥቀስ፤ በሦስት ፈረቃ የ24 ሰዓት የሕክምና አገልግሎት በመሥጠት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ይሁንና በጉብኝቱ ወቅት እንደ ተግዳሮት የተነሱ ጉዳዮች ነበሩ። በመንግሥትና በጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ለባለሙያዎች የመኝታ ክፍሎችና የመከላከያ ቁሳቁሶች እየተሟሉ ቢሆንም፤ አሁንም የውኃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርት እጥረት እና የላቦራቶሪ ውጤት መዘግየት ችግሮች መኖራቸውን የሆስፒታሉ ኃላፊዎች ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ የሕክምና ባለሙያዎች መንግሥት ባለው አቅም ራሳቸውን አግልለው አገልግሎቱን ለመሥጠት የሚችሉባቸው ክፍሎችና ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያሟላም በጉብኝቱ ወቅት ጥያቄ መቅረቡ ተዘግቧል። (ኢዛ)
የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ስምምነት ስድስት ቢሊዮን ዶላር የማግኘት ውጥን
በዚህ ሳምንት ከተሰሙ በዝነስና ኢኮኖሚ ነክ ዜናዎች ውስጥ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ተፋሰስ የለማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል የተፈጥሮ ጋዝ የንግድ ስምምነት ስለመፈረሙ መገለጹ ነው። የተፈጥሮ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ አሁን በተደረሰው ስምመነት በ20 ዓመት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ይገኛል።
በኦጋዴን አካባቢ ስምንት ትሪሊየን ጫማ የሚገመት የተፈጥሮ ጋዝና መጠኑ እየተለየ ያለ ፈሳሽ ነዳጅ መገኘቱን ተከትሎ፤ ከቻይና ኩባንያ ጋር በተደረገው ስምምነት ወደ ልማት እንዲገባ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ሚኒስቴሩ ገልጾ፤ ይህም ልማት ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ የተፈጥሮ ጋዙን ማቅረብ ያስችላል።
በኦጋዴን በዚህም በአካባቢው ያለውን ካሉብ፣ ሂላላ እና ሽላቦ የተባሉ የተፈጥሮ ጋዝ መስኮችን ለማልማት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በስምምነቱን የተፈራረሙት ከቻይናው ፖሊ ጂ ሲ ኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ኩባንያ ጋር ነው። ይህም ስምምነት የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ ስምምነት ሲሆን፤ ስምምነቱ የተፈጥሮ ጋዝ ልማቱ በተካሔደባቸው የካሉብና ሂላላ እንዲሁም ሽላቦ የተፈጥሮ ጋዝ መስኮች ላይ የለማውን ክምችት በቧንቧ መስመር በማስተላለፍ ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ነው።
እንደ መረጃው ከእነዚህ የተፈጥሮ መስኮች በቀን 190 ሚሊዮን ኪዩብ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ በአገር ውስጥ ለሚገነባ የማዳበሪያ ፋብሪካና ለሌሎች የአገር ውስጥ ፍላጎቶች እየታየ አቅርቦቱ የሚወሰን መኾኑን ነው።
የተፈጥሮ ጋዙን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጭምር የታቀደ በመኾኑ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በሚዘረጋው የቧንቧ መስመር ጅቡቲ ወደብ ላይ በሚገነባው ወደ ፈሳሽ መቀየሪያ የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሚቀርብ ይኾናል ተብሏል።
በዚሁ ጉዳይ የተሠጠው መረጃ እንደሚያመለክተው በጅቡቲ የሚገነባው ማቀነነባበሪያ ፋብሪካው በቀን 215 ሚሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ፈሳሽ ጋዝ የመቀየር አቅም ይኖረዋል። ይህም በዓመት 1.5 ሜትሪክ ቶን ፈሳሽ ጋዝ ማቅረብ ያስችላል የሚል ነው።
በዚህ ፕሮጀክት ሌሎች ግኝቶችን ሳይጨምር በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንደሚያስችል በጥናት መረጋገጡንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው። (ኢዛ)
ዘንድሮም አምስት ቢሊዮን ችግኝ
ባሳለፍነው ሳምንት ለየት ብሎ ሊገለጽ የሚችለው ከአንድ ወር ተኩል በላይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ውጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በኦሮሚያ ክልል ሶደሬ አካባቢ የሚገኘውን ችግኝ ማፍላት ሥራውን ከክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመኾን መጐብኘታቸው ተጠቃሽ ነው።
በመጪው ክረምት አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም የሚኾን ችግኝ የማዘጋጀት ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ በ38 ሺሕ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እየተካሔደ መኾኑንም ከጉብኝቱ በኋላ ገልጸዋል።
የተፈሉት አብዛኞቹ ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ እንደ አቦካዶ እና ማንጎ ያሉ የፍራፍሬ ስለመኾናቸው እና የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን መግታት ከተቻለ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ችግኞቹን መትከል እንደሚጀመርም ገልጿል።
በፊታችን ክረምት የሚተከሉትን ችግኞች ጨምሮ በቀጣይ አራት ዓመታት እስከ 20 ቢሊዮን ችግኞችን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል እየተሠራ መኾኑንም ዶ/ር ዐብይ ተናግረዋል። አያይዘውም ባለፈው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከለው አራት ቢሊዮን ችግኝ የዝናብ ሁኔታው ጥሩ ስለነበርና እንክብካቤ በመደረጉ አብዛኛው ችግኞችም ስለመጽደቃቸው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሠጡት መረጃ ገልጸዋል። (ኢዛ)
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ አቋሟን አጽንታ ቀጥላለች
ባሳለፍነው ሳምንት የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ይፋ የተደረገው መረጃ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባሻገር ትኩረት ያገኘ ዐቢይ ዜና ነበር። በዚህ መረጃ መሠረት የግድቡ የብረታ ብረት ፍሬም ሥራ መቶ በመቶ የተጠናቀቀ ስለመኾኑ ተገልጿል። የሲቪል ሥራው 87 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ደግሞ 46 በመቶ መጠናቀቁን የህዳሴው ግድብ ሥራ የሥራ ኃላፊዎች አመልክተዋል።
ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የኮሮና በዓለም ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጥላውን ያጠላበት ወቅት ቢሆንም፤ የህዳሴው ግድብ ሥራ በነበረው ግለት እንደቀጠለ መኾኑን የግድቡ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂንየር ክፍሌ ሆሮ ተናግረዋል። አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 73 በመቶ መድረሱንም ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ፤ ግድቡ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ ኃይል ማመንጨት እንዲችል በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የሚጠቁም መረጃ ሠጥተዋል። ከዚህ ፕሮጀክት ሥራ ጋር በተያያዘ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ይፋ የተደረገው መረጃ፤ የግድቡ የውኃ ሙሌቱ በሚቀጥለው የክረምት ወር እንደሚጀምር የገለጸ ነው። ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ግድብን ውኃ ለመሙላት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተካሔደ መኾኑም ተመልክቷል።
በመጀመሪያው የግድቡ ውኃ ሙሌት ሥራ የሚሞላው የውኃ መጠን 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ሲሆን፤ ይህም የግድቡን ሁለት ተርባይኖች ማንቀሳቀስ የሚያስችል እንደኾነም ሰሞኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ በተመለከተ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን የተሠራጩ መረጃዎች አመልክተዋል።
በተመሳሳይ 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ውኃ እንደሚሞላ የታቀደ ሲሆን፤ ይህም ግድቡ 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ውኃ የሚይዝ በመኾኑ ሁሉንም የግድቡን ተርባይኖች ለማንቀሳቀስ እንደሚያስችል ተመልክቷል።
እንዲህ ያሉ ሰሞናዊ መረጃዎች ኢትዮጵያ የግድቡን ሥራ በቶሎ ለማጠናቀቅ ያላትን ፍላጐት በእቅዷ ልክ እያከናወነች ስለመኾኑ ማሳያ ነው ተብሏል።
ግብጽ የህዳሴው ግድብ የውኃ ሙሌት ሥራ በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያም በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንድትለቅና ተያያዥ የኾኑ ጥያቄዎችን አቅርባ የነበረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዚህ ባለመስማማት በራስዋ መንገድ ሥራውን አስቀጥላለች።
እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ የወንዙ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ግድቡን ውኃ ለመሙላት ሥራውን የምታከናውን መኾኑንም አሳውቃለች። አሁን ላይ ደግሞ የግድቡን የውኃ የሙላት ሥራ ከሁለት ወር በኋላ ለመሙላት እየተዘጋጀች መኾኑንም ለእነዚህ ተፋሰስ አገሮች ስታሳውቅ ቆይታለች። (ኢዛ)
ንግድ ሚኒስቴርና ወቅታዊ ገበያ
አምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በማሳደግ የኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ችግር ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ተጽዕኖ ምክንያት በማድረግ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሠራተኛ እንዳያሰናብቱ፣ ምርት እንዳይቀንሱ፣ እንዲሁም ፋብሪካ እንዳይዘጉ ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል። የኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ችግር ለመፍታት የሚያስፈልጉ ምርቶችን ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በማሻሻል በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሩ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ሳምንት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የሳሙናና ዲተርጀንት ፋብሪካዎች ያለባቸውን የጥሬ ዕቃ ችግር በመፍታት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአገራችንን ፍላጎት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገር ውስጥ ምርት ለማሟላት 100 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ የሚያስፈልጋቸውን ጥሬ ዕቃ እንዲያስገቡ እየተደረገ መኾኑንም ይኸው መረጃ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በበቂ ሁኔታ ስለሚያቀርብ የአቅርቦት ችግር እንደማይኖር ሚኒስቴሩ የገለጹ ሲሆን፤ ወረርሽኙ በዓለም የምጣኔ ሀብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚሁም ሳቢያ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በርካታ አገራት ላይ የምርት እንቅስቃሴ እንዲገታ፣ ኢንዱስትሪዎች ምርት እንዲያቆሙ፣ የፋይናንስ ተቋማት እክል እንዲገጥማቸው እና አልፎ አልፎም ሕገወጥ ድርጊት እንዲከሰት ምክንያት መኾኑን ገልጾ፤ በኢትዮጵያም ይህ ሁኔታ አደጋ እንዳይኾን እየተሠራ ነው ተብሏል።
ከእነዚህም እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ለዜጎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ማቅረብ ሲሆን፤ ስንዴ 650 ሺሕ ኩንታል፣ ስኳር 615 ሺሕ ኩንታል፣ ዘይት 40 ሚሊዮን ሊትር፣ እንዲሁም ነዳጅ 399 ሚሊዮን ሊትር በየወሩ በመንግሥት በኩል እየቀረበ ስለመኾኑም ተነግሯል። (ኢዛ)
ለላኪዎች ባቡርን በነፃ እንዲጠቀሙና ሌሎች አገልግሎቶች እስከ 73 በመቶ ቅናሽ ተደርጐላቸዋል
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በመንግሥት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ሲሆን፤ በሳምንቱ መጨረሻ ላይም በውጪ ንግድ ትራንስፖርት ላይ የተለያዩ ዋጋ ቅናሽ ተደርገዋል። ከትራንስፖርት ሚኒስቴር የወጣው መረጃ በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ይቻል ዘንድ በመንግሥት በኩል የተለያዩ እርምጃዎች የተወሰዱ እንደሆነ በማስታወስ፤ ከዚህ አንፃር በተጨማሪነት መወሰድ ከሚገባቸው እርምጃዎች አንዱና ዋነኛው በአገር ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ የተሰማሩ አምራቾች ለውጭ አገር ገበያዎች የሚያቀርቧቸውን ምርቶች ከማቅረብ አንፃር እያጋጠማቸው ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ ውሳኔ ተላልፏል ብሏል።
ይህንን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ለመወጣት እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረግላቸው በመንግሥት የተወሰነ ሲሆን፤ ከእነዚህ ድጋፎች አንዱ በትራንስፖርት እና በሎጂስቲክ ዘርፍ የደረቅ ወደብ አገልግሎትን ማዕከል በማድረግ የሚሰጥ እንዲሆን ተወስኗል።
በውሳኔው መሠረትም ከተደረጉት ለውጦች መካከል የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር፤ ከሚያዚያ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ከሜይ 1 ቀን 2020) ጀምሮ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚወጡትን የኤክስፖርት ምርቶችን እስከ ጅቡቲ ለሦስት ወራት በነፃ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ መወሰኑ አንዱ ነው። ይህ ውሳኔ እንደ ሁኔታው ታይቶ እስከ አምስት ወር ሊራዘም እንደሚችል የትራንፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጸንቶ ለሚቆይበት ጊዜ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኤክስፖርት የሚቆይ እገዛ ለማድረግ በሞጆ ወደብ ላይ በባቡር ለሚጫኑ፤ እንዲሁም ከርቀት አንፃር በባቡር ለማጓጓዝ አመቺ ካልኾኑ ቦታዎች ለሚጫኑ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ወጪ ዕቃዎች የወደብ እና የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ቅናሽ መደረጉንም ገልጿል።
በዚሁ መሠረት የተደረገውን ቅናሽ በተመለከተ ሚኒስቴሩ፤ የደረቅ ወደብ አገልግሎት ክፍያ በየትኛውም የጭነት ዐይነት በ50 በመቶ እንዲቀንስ መወሰኑን አመልክቷል።
ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሞጆ ደረቅ ወደብ በኩል በባቡር ለሚጓጓዙ ጭነቶች ደግሞ ከሐዋሳ እስከ ሞጆ ደረቅ ወደብ ድረስ ማጓጓዣ ቀድሞ ከነበረው ዋጋ በ50 በመቶ ቅናሽ መደረጉን አስታውቋል።
ከጅቡቲ ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚላኩ የኤክስፖርት ምርቶች የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚጠቀሙ ላኪ ደንበኞች በሙሉ ከገበያ ዋጋ እስከ 73 በመቶ ቅናሽ እንዲያደርግ መወሰኑንም ትራንስፖርት ሚኒስቴር ቅዳሜ ምሽት ላይ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል። (ኢዛ)
ኮሮና ቫይረስና የሚያገግሙ ሰዎች 41 መድረስ
ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መረጃ እስከ ትናንት ሚያዝያ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 123 ደርሷል። በዚህ ሳምንት ከሌሎች ጊዜ በተለየ በየዕለቱ የተመርማሪዎች ቁጥር ማሳደግ የተቻለበትም ነበር። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከ900 በላይ ምርመራ በተደረገበት አንድ ዕለት ምንም በቫይረሱ ያልተያዘ ሰው መገኘቱም እንደ መልካም የታየ ቢሆንም፤ ይህ መዘናጋትን የሚፈጥር መኾን እንደሌለበት የተወሳበት ነው።
ከሁሉም በላይ ግን እስካሁን 123 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሪፖርት የተደረገ መኾኑን ያህል፤ በለይቶ ማቆያ ሕክምና ላይ ያሉ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 41 መድረሱ ጥሩ ዜና ኾኖ ተወስዷል።
ከዚህ ባሻገር አሁን ባለው የምርመራ አቅም በአማካይ በቀን ወደ 900 የሚኾነውን የመመርመር አቅም ለማሳደግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች፤ በቀጣይ አንድና ሁለት ሳምንታት ውስጥ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በቀን የመመርመር አቅምን ከአራት ሺሕ በላይ ማድረስ እንደሚቻል መገለጹ ነው። (ኢዛ)
ጋብ ያለውን ፖለቲካዊ ሙቀት ያስነሱት ፒኮኮች እና ግልጽ ያልኾኑ ምልከታዎች
የኮሮና ቫይረስ መከሰት ብዙ ነገሮችን ቀያይሯል። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን አቀዛቅዟል። ፅንፍ በሚይዙና በረባ ባልረባው ጉዳዮች የፖለቲካ ትኩሳትን ሲያግሉ የነበረው ጉዳዮችም እንደ ቀድሞ አይስተዋሉም። ሰሞኑን ግን ቤተመንግሥት አካባቢ የተሠሩ የሁለቱ ፒኮኮች ቅርጾች አንዳንድ አክቲቪስቶችና ጥቂት የፖለቲካ ድርጅት አባላትን ወደ ቀደመው የቃላት ጦርነት እየመለሰ ነው ማለት ይቻላል።
እነዚህ በቤተ መንግሥቱ የአንደኛው መግቢያ በር ላይ የቆሙትን የሁለት ፒኮኮች ቅርጾች በተመለከተ በቅድሚያ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ መረጃ ገጻቸው ላይ ካሰፈሩት መካከል አቶ ጁዋር መሐመድ ነው። ነገሩን የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ በማኅበራዊ ገጾች ላይ መነጋገሪያ እንዲሆን በማድረግ ደግሞ በአቶ እስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ ይጠቀሳል።
በቤተመንግሥቱ መግቢያ ላይ ምስላቸው የተቀመጡት ፒኮኮች የቤተመንግሥትን የማደስና የማስዋብ አንድ አካል ነው። ተመሳሳይ የአንዲት ፒኮክ ቅርፅ ምስል በቤተመንግሥት ውስጥ ባማረ አረንጓዴ ስፍራ ላይ ቢኖርም እስካሁን ምንም የተባለ ነገር አልነበረም። አሁን በቤተመንግሥቱ መግቢያ በር ላይ በጉልህ በመሠራታቸው ተቃውሞ የተነሳበትም ምክንያት በተለየ መንገድ እንዲገለጽ ኾኗል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ዘመቻ ስለመከፈቱ ለማሳወቅ ድርጊቱን የተቃወመው ባልደራስ፤ በአዲስ አበባ የተቃውሞ ፊርማ ሊያሰባስብ ስለመኾኑም ገልጿል። እንደባልደራስ እምነት የእነዚህ ፒኮኮች በቤተመንግሥት መግቢያ ላይ መሠራት አግባብ ያለመኾኑ ነው። “ትውፊቶቻችንን፣ ቅርሶቻችንንና እሴቶቻችንን እንጠብቅ! ሁሉም አገራት የየራሳቸው ምልክቶች አሏቸው።” በማለትም አሜሪካ ንስር፣ ታላቁ ብሪታንያ አንበሳ፣ ቻይና ፓንዳ ወዘተ .. ኢትዮጵያ አገራችን ደግሞ ከጥንት ጀምሮ ስትንከባከበው የኖረችው የጥንካሬ፣ የጥረት፣ የውበት፣ የኃይል ምልክቱ አንበሳ ነው በማለት ይሞግታሉ። አሁን ግን የአንበሳ ምልክታችን በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተደፍሯል፤ በማለትም ጉዳዩ እንደ ትልቅ አጀንዳ መታየት አለበት ብሏል።
ባልደራስ ፒኮኮቹ ይሠሩ እንጂ በቤተ መንግሥቱ ግቢ ውስጥ ሁለት ከተፈጥሮ በጣም ያነሱና ከፒኮክ እግር ስር የተቀመጡ አንበሶችን ስለመቀረፁ ይገልጻል። ይህም አምበሶቹ ያሉ መኾኑን ቢያመለክትም አንበሶቹ መጉላት ነበረባቸው የሚል አቋም የያዘ ይመስላል።
በስተመጨረሻ ይህንን ቤተመንግሥት በር ላይና ግቢ ውስጥ ያለውን ፒኮክ እንዲፈርስና በአንበሳ እንዲተካ ኢትዮጵያዊያን መጠየቅ አለብን በማለት አስታውቋል። በእነዚህ ፒኮኮች ላይ ሌላው አስተያየቱን የሰጠው አክቲቪስት ጃዋር ደግሞ፤ ይህንን ፒኮክ ያየሁ ጊዜ ወፏ ስለምታምር ለጌጥ የተደረገ መስሎኝ ነበር። የአገሪቷን አዕዋፍ ለማስተዋወቅ ለአፍሪካ ኢንደሚክ የኾነውን እና ለአገራችንም የቱሪስት መስህብ የኾነውን ሰጎን ቢያደርጉት አይሻልም ወይ ብዬ ነበር ይላል። አያይዞም ለካ ዓላማው ሌላ ነው በማለት አስተያየቱን ቀጥሎ “ለማንኛውም በአገራዊ ተቋማት ላይ እየተደረጉ ያሉ ነገሮች ችግር እንዳያባብሱ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል” የሚል አክሏል። ሴኩላሪስም እና ፌደራሊስም ለጋራ አገር ግንባታ እና ሰላማዊ ማኅበረሰባዊ አብሮነታችን ዋስትና ስላልኾኑ ከምናፈርሳቸው ብንጠግናቸው የተሻለ ይመስለኛል በማለት ያለውን አስተያየት አስፍሯል።
እንዲህ ያሉ አስተያየቶች ከተሰነዘሩ በኋላ በጉዳዩ ላይ አዎንታዊ ሐሳባቸውን ያሰፈሩት ደግሞ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው። “በጥንታዊ የኢትዮጵያ ትርጓሜና ሥነ ሥዕል የታወቀች ወፍ ናት” ይላሉ። ሥዕሏን ከ6ኛው መክዘ ጀምሮ በብራና መጻሕፍት ላይ እናገኛታለን። በተይም ከ15ኛው መክዘ ወዲህ በአውሳብዮስ ጦማር ዙሪያ በብዛት ሥዕሏ ይገኛል። በጣና ገዳማት ደግሞ ሥርዓተ ኑባሬ በተሰኘው ሥዕል ዙሪያ ትሳላለች በማለት ከገለጹ በኋላ፤ በጥንታዊ የኢትዮጵያ ጣዎስ በየሶራው በየሱቲው ትሳላለች፤ ትጠለፋለች። የሶራ ላይ ወፍ ተብላ በየዘፈኑ የምትነሣው ጣዎስ (ፒኮክ) መኾኗን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይናገራሉ በማለትም ያክላሉ።
የሶራ ላይ ወፌ የሶራ ላይ
ላይ ላዩን ነይ
በቀደምት ሰዎች እምነት ጣዎስ ሥጋዋ አይፈርስም አይበሰብስም ተብሎ ስለሚታመን የዘለዓለማዊነት፣ የትንሣኤና የህዳሴ ምሳሌ ናት በማለትም ስለ ፒኮክ ምንነት ሐሳባቸውን ታሪክ በማጣቀስ አመልክተዋል። የአራት ኪሎው ቤተ መንግሥት በመብራቱ በኩል ያለው በር ፊት ለፊት ሁለት ጣዎሶች መቆማቸውን በመጥቀስም “የኢትዮጵያን ትንሣኤ፣ ዘለዓለማዊነቷንም እንዲያሳዩ ሳይሆን ይቀራል” በሚል ሐሳባቸውን ያስቀምጣሉ። ለዚህም በምስል የተደገፈ መረጃም ከዚህ ጽሑፋቸው ጋር አያይዘው ያቀርባሉ።
የእነዚህ ፒኮኮች እንደ አገር አጀንዳ መነሳታቸው አግባብ አይደለም የሚሉ ወገኖች ደግሞ፤ በሁኔታው ስለማዘናቸው ይገልጻሉ። ሁሉም በመሰለው የራሱን ዓላማ ለማራመድ እየሞከረ መኾኑንም በመገንዘብ ጉዳዩን ለፖለቲካ ዓላማ መዋሉን ይተቻሉ።
ይህንን ሰሞናዊ ሙቀት ተንተርሶ ጉዳዩ ሁለት አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ አመለካከቶች የሚፈነዳው ነው ይላሉ። በዚሁ ላይ ተንተርሰው ባሰፈሩት ጽሑፍ በሁለታችሁም መንገድ መሔድ አያዋጣም ይላሉ። ኢትዮጵያ ብዙ ባህልና አስተሳሰብ አላት። አንድ ወጥ ልትሆን አትችልም። ኢትዮጵያውያን ብዙ የሚጋሩት እሴት አለ። ድንበር ሊገድባቸው አይችልም። በቀጣይ አብረው የሚያኖሩን አዳዲስ ድልድዮች ካልገነባን በስተቀር የሁለቱም ወገኖች አቋራጭ ፈርሷል። አልታይ አለው እንጂ …ሁለቱም ወገን ተሸንፏል በሚል ገልጸዋል። እርስ በርስ ሊጠፋፉ አይችሉም። ሁለቱንም የሚያጠፋ ዓለማቀፋዊ ባህል፣ ቋንቋና ችግር በደጅ ላይ ነው። የሚቀራረቡበትን መንገድ ካልፈለጉና ካልፈቀዱ ሁለቱም ወይ በምዕራባዊው ወይ በምሥራቃዊው ጎርፍ ተጠርገው ይወሰዳሉ ብለው ገልጸዋል።
“የሰሞኗ የ“ፒኮክ” ልፊያ አዲስ አይደለችም” በሚል ያሰፈሩት ፀሐፊው (መሐመድ ሐሰን)፤ በሁለቱ ካምፖች መካከል ለነበረው ውጊያ እንደ ሜዳ ከማገልገል በቀር በራሷ የሁለቱም ሐሳብ ተሸካሚ አልነበረችም ይሉና፤ አስተያየታቸውን በመቀጠል በቤተመንግሥቱ የሌላ ምስል ቢቀመጥም እነዚህ በሁለት ጐራ ያሉ ወገኖች የሚሉት እንደማያጡም ገልጸዋል።
ይህንንም አመለካከታቸውን “ፒኮክ” እባብ ብትኾንም፣ አይጥ ብትኾንም፣ ነብር ብትኾንም፣ ዋልያ ብትኾንም፣ አንበሳ ብትኾንም፤ እነዚህ ለትግል ያሰፈሰፉ ኃይሎች ወደኾነ ቦታ እየጠመዘዙ መታገያ ከማድረግ አይመለሱም በማለት ሁለቱንም ወገኖች ይወቅሳሉ።
“ባለፈው ታሪካችን መግባባት የግድ አይደለም! ቢያንስ የምንግባባበት አዲስ ታሪክ መጻፍ ግን ግድ ነው።” በማለትም አሁን በፒኮኮች ዙሪያ የተነሳው ውዝግብ አጀንዳነትን ያጣጥላሉ። ይህም ቢሆን ግን ለምን እንዲህ እንደኾነ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፤ በዚህ ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶች ቀጥለዋል። (ኢዛ)



