Ethiopia Zare's weekly news digest, week 37th, 2012 Ethiopian calendar

ከግንቦት 10 - 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሠላሳ ስድስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከግንቦት 10 - 16 ቀን 2012 ዓ.ም.) ካሳለፍነው ሳምንት ቀዳሚ ዜናዎች ውስጥ በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ትርጓሜን በተመለከተ የተደረገው ውይይትና ወደ ድምዳሜ የተደረሰበት ሐሳብ መገለጹና በዚሁ መድረክ የቀረቡ አብዛኞቹ ሐሳቦች ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ይቻላል የሚሉ ኾነው መገኘታቸው ነው። ከዚህ ዜና ባሻገር ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብጽ እስከተባበሩት መንግሥት ድርጅት ድረስ ለአቤቱታ የቀረበችበትና ኢትዮጵያ ከወትሮ የተለየ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ያደረገችበት ጊዜ ቢኖር ይህ ሳምንት ነው።

ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ፤ ግብጽ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቀረበችውን አቤቱታም ተከትሎ የሰጠችው ምላሽ፤ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ልዩነት አስፍቶ ወደ ባሰ ያለመግባባት ውስጥ ይገባሉ ተብሎም ነበር። በተለይ ኢትዮጵያ የግድብ ጉዳይ በሦስቱ አገራት ውይይት የሚፈታ መኾኑን በሰሞኑን በተከታታይ ባደረገቻቸው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዋ ስታንጸባርቅ ቆይታለች። ከእንዲህ ያሉ ክንውኖች በኋላ ግን፤ ግብጽ ወደ ሦስትዮሹ ድርድር እንደምትመለስ ማስታወቋ ያልተጠበቀ ዜና ተደርጐ ታይቷል።

እንደ ቀደሙት ሳምንታት ሁሉ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት አስጊ ወደሚባል ደረጃ ላይ ስለመድረሱ እየታየ ነው። ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በአንድ ቀን 61 የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙበት ሳምንት ኾነ በተባለ ማግስት፤ በአንድ ቀን 88 ሰዎች መገኘታቸው የሁኔታውን አሳሳቢነት መሠረት በማድረግ፤ በተመረጡ አካባቢዎች የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲደረግ እስከማሳሰብ ደርሷል።

ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞዎች መካሔዳቸውም ሌላው የሳምንቱ ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የ12 አባላቱን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ከሳምንቱ ዜናዎቹ አንዱ ነው።

በ2012 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት እንደሚመድብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ማሳለፉ፣ እስካሁንም በበጀት ዓመቱ የተጠየቀው ተጨማሪ በጀት ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገልጿል። የአዲስ አበባ አስተዳደር የታክስ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔ ላይ መድረሱን ያሳወቀውም በዚህ ሳምንት ነው።

ከባንኮች የሚወጣው የገንዘብ መጠን ገደብ እንዲጣልበት መወሰኑና ይህም ውሳኔ ከሳምንቱ መጀመሪያ ላይ መተግበር ጀምሯል። የሲዳማ ዞን በቅርቡ ወደ ክልል እንደሚያደራጅ ተገልጿል። እንዲህ ያሉና ሌሎች ክንውኖችን ያስተናገደው ካሳለፍነው ሳምንት ዜናዎች ውስጥ በተመረጡ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ የተጠናከረው ሪፖርት እንደሚከተለው ቀርቧል።

የአጣሪ ኮምሽኑና የሕገ መንግሥት ትርጉም መድረክ ድምዳሜ

የሳምንቱ ዐበይት ዜና ኾኖ የሚጠቀሰውና በኢትዮጵያ ከተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የፌዴራሉ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለሦስት ቀናት ሲያካሒድ ከነበረው የውይይት መድረኮች ምን ተገኘ የሚለው ጉዳይ ነው።

ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው በግልጽ በተጠቀሱ ሦስት አንቀጾች ላይ የውሳኔ ሐሳብ እንዲሰጥባቸው፤ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መመራታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ አጣሪ ጉባዔው ለውሳኔ እንዲያግዘው የተዘጋጁት መድረኮች ላይ በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል።

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው፣ ጉዳዩን ለማየት የተከተለበት ሒደት አንደኛው ባለሙያዎች እና የተቋማት ሙያዊ አስተያየት ማሰማት እንደነበር ተገልጾ፤ በዚህም ሳምንት ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ተቋማት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በሦስተኛው የውይይት መድረክ ሙያዊ አስተያየት የሰጡት ደግሞ የጤና ሚኒስቴር እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ናቸው።

የእነዚህ ሦስት መድረኮች መጠናቀቅ በኋላ፤ ባለሙያዎች እና ተቋማት አስተያየት የሰጡባቸው ሲሆን፤ በተለይ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች ላይ ጥናት ያደረጉ፣ በዳኝነት ወይም በጥብቅና የሠሩ ባለሙያዎች፤ በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ በጽሑፍ የሕግ ትንታኔ እንዲሰጡ የተደረገበት ከመኾኑም በላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

የሰሞኑ መድረኮች በቡድን የተዘጋጁት ጽሑፍ ጨምሮ 22 የጽሑፍ አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን፣ አብዛኛው አስተያየቶች ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜዎች የሚወስዱ መኾናቸውን የአጣሪ ኮምሽኑ ቦርድ ሊቀመንበርና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፤ የሦስቱን መድረኮች መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል። እንደሳቸው አባባል አነስ ያሉት አስተያየቶች ደግሞ ወደተለየ ድምዳሜ የሚያሳዩ ኾነው ስለመገኘታቸውም አስረድተዋል።

ይህም በአብዛኛው የቀረቡ የጽሑፍ አስተያየቶች፤ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ትንተና ውስጥ ኾነው፤ ነገር ግን ጥቂት አስተያየቶች ጉባዔው ሥልጣን የለውም የሚል አስተያየት የተሰጠበት ስለመኾኑ የሚያመላክት ነው። የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያሰጡ ጥያቄዎች አልቀረቡም የሚል መኾኑን የሚጠቁም ሲሆን፤ እነዚህ ጥያቄዎችን እና የቀረቡ ትንተናዎችን ተከትሎ አጣሪ ጉባዔው ወደፊት መልስ የሚሰጥበት ይኾናል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ሳምንት በሦስተኛው መድረክ ላይ አስተያየት ከሰጡት መካከል የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ አምስት ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አስታውሰው፤ ከ329 ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚተላለፍበት ዋነኛው መንገድም በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው መኾኑን በመግለጽም፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ምልክቱን ማሳየት ከመጀመራቸው በፊት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ የሚችሉ በመኾኑ፤ ሥርጭቱ አስቸጋሪ መኾኑን በመግለጽ ሞያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅና አካላዊ ንክኪን ማስቀረት አስፈላጊ መኾኑን በመጥቀስ፤ ይህንን እና ሌሎችን የቫይረሱን መከላከያዎች ለመፈጸም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እስካሁን ትምህርት ቤቶችን መዝጋት፣ የሥራ ቦታ እና የትራንስፖርት ላይ መጨናነቅን መቀነስ፣ ከውጭ የሚገቡትን ወደ ለይቶ ማቆያ ማስገባትን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅን ጨምሮ፤ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ብርቱካን ሚደቅሳም ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማካሔድ ያልቻሉበትን ዝርዝር ጉዳዮች አቅርበዋል። እንዲህ ያሉ ሙያዊ አስተያየቶችን አጣሪ ኮሚሽኑ በማደራጀት፤ ለውሳኔ አሰጣጡ ይጠቀምበታል ተብሏል። (ኢዛ)

ግብጽን እጅ ያሰጠው የኢትዮጵያ ሰሞናዊ ቆራጥ ትግል

እንደ ብዙዎች ምልከታ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀምና በህደሴ ግድብ ዙሪያ ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችን ካደረገችባቸው ጊዜያት ውስጥ ከሰሞኑ እየተወሰዱ ያሉ አጠቃላይ እርምጃዎች በተለየ የሚታይ ነው።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የውኃ ሙሌት ከአንድ ወር በኋላ ለመጀመር በዝግጅት ላይ በምትገኝበት ጊዜ፤ ግብጽ ይህንን ለማሰናከል እና መዘናጋትን ለመፍጠር ደብዳቤ ይዛ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ብትቀርብም፤ ኢትዮጵያ ለዚህ የግብጽ አዲስ እንቅስቃሴ “አይሰማም” የሚል ምላሽ ከመስጠት ባለፈ፤ ዓለም ስለጉዳዩ እንዲያውቅ በብርቱ የሠራችበት ሳምንት ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ለመከላከያ ሠራዊት ግንዛቤ ተሰጥቷል። ዜጐች በያሉበት ዲፕሎማሲያዊ ትግል አድርገዋል።

ግብጽ ለተመድ ያመለከተችው የውኃ ሙሌቱ እንዲዘገይ መኾኑ በመታወቁም፤ የኢትዮጵያን አቋም ለማስቀጠል እስከዛሬ ብዙም ያልተሠራበት ሁሉን አቀፍ ትግል የተደረገበት ነው ማለት ይቻላል። በተለይ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የኾኑ ዲፕሎማቶችን በመሰብሰብ፤ የኢትዮጵያ “አቋሜ ይኼ ነው” ብላ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቃለች።

የኢትዮጵያ ሰሞናዊ ጥረትም ወደ ውጤት ማምራቱን የሚያመለክተው፤ ትላልቅ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ሰሞናዊ ዲፕሎማሲያዊ ትግል፤ ግብረ መልስ መስጠታቸው ጭምር ነው።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ግድቡን በውኃ ለመሙላት የግብጽን ፈቃድ እንድትጠይቅ በሕግ የማትገደድ ስለመኾኗ በመግለጽ ለግብጽ ደብዳቤ ምላሽ ሰጥተዋል።

የግብጽን ማመልከቻ ተከትሎ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ በሰጠችው ምላሽም፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፤ ግብጽ እንደምትለው የደኅንነትና የጸጥታ ሥጋት ሳይሆን፤ ግድቡ ለታችኛው የተፋሰሱ አገራት የጋራ ጥቅም የሚያረጋግጥ ስለመኾኑ አስረድታለች። የውኃ ሙሌቱንም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንደምታካሒድ አሳውቃለች።

በሰሞናዊ የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ያላት ፍላጐት ለዲፓሎማቶች ከማሳወቋም በላይ ብዙ ግንዛቤ እንዲወሰድ ያደረገችበት ነው። በተለይ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ፤ አጠቃላዩን ሒደት ያስታወቁበት፤ ዝርዝር ጉዳዮችን በመተንተን ጉዳዩን ዓለም እንዲያውቅ ጊዜ ሰጥተው በተለያዩ መድረኮች ለአምባሳደሮች አስረድተዋል። እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ እየተደረገ ባለበት ሳምንት ላይም፤ ከወደ ግብጽ የመጣ አንድ መረጃ፤ ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል ሒደት ላይ ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ድርድር ለመቀጠል ስለመስማማቷ ተደምጧል። የግብጽ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ “ፍትሐዊ፣ ሚዛናዊ እና አጠቃላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ፤ በመጪዎቹ ጊዜያት በሚደረጉ ድርድሮች እና ውይይቶች ለመሳተፍ ግብጽ ሁልጊዜም ዝግጁ ነች” በማለት ሲሸሽ የነበረውን ውይይት ለመቀላቀል ተስማምተዋል።

ግብጽ እንዲህ ያለውን መረጃ ያወጣችው፤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በቪዲዮ ውይይት አድርገው፤ “የቴክኒክ ውይይቶችን ለመቀጠል” መስማማታቸውን ካሳወቁ በኋላ ነበር። የተባበሩት መንግሥታትና የአውሮፓ ሕብረትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። ለኢትዮጵያ ያደላ መልእክት የታየበት ነው ማለት ይቻላል። ይህም ከኾነ በኋላ የአፍሪካ ሕብረትም የሦስትዮሽ የቴክኒክ ውይይታቸውን ለመቀጠል በመስማማታቸው፤ የአፍሪካ ሕብረት ምስጋና አቅርቧል። ኮምሽኑ በሊቀመንበሩ በኩል ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በውኃ ሚኒስትሮቻቸው አማካኝነት የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ውይይታቸውን ለመቀጠልና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ስምምነት ላይ ለመድረስ መስማማታቸውን ተከትሎ የተሰጠ መግለጫ ነው። ኢትዮጵያ ጉዳዩ በሦስቱ ወገኖች፤ ገፋ ካለም በአፍሪካውያን ይፈታ በሚለው አቋሟ በመፅናት፤ በቀጣይ የሚደረጉ ድርድሮችም ከዚሁ በዚሁ መንፈስ እንደሚካሔዱ አሳይቷል። (ኢዛ)

ኮሮና አደገኛ እየኾነ ነው

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ወዲህ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ የጨመረው ባለፉት ሦስት ሳምንታት ነው።

በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት በአንድ ቀን 61 ሰዎች የተሰማበት ባለፈው ቅዳሜ ግንባት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ቢሆንም፤ በማግስቱ ግንባት 16 የተሰማው ዜና ግን ነገሮች አስከፊ እየኾኑ ስለመምጣታቸው የሚጠቁም ኾኖ ተገኝቷል።

ይህም እስከእሁድ ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በአንድ ቀን 88 ሰዎች መገኘታቸው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች ቁጥር 582 አድርሶታል።

ከሰሞኑ የጤና ሚኒስቴር ተከታታይ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው፤ የቫይረሱ ሥርጭት ከአንድ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች መከሰቱንና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ መምጣቱን ነው።

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የቫይረሱ ሥርጭት ጐልቶ የታየበት ከመኾኑም በላይ፤ እስካሁን በአገሪቱ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ውስጥ ከ64 በመቶ በላይ ከአዲስ አበባ በመኾናቸው፤ በከተማይቱ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ጐልቶ በታየባቸው አካባቢዎች የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል እንደሚችል አመላክቷል። በአንድ ቀን 88 በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች መገኘታቸው ሲገለጽም፤ 73 የሚኾኑት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። የጤና ሚኒስትሯ ቅዳሜ ግንባት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቁት፤ በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ጐልቶ በሚታይባቸው ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ላይ የእንቅስቃሴው ገደብ ሊጣል እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃ የሰጠው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮም፤ ችግሩ ከፍቶ በታየባቸው የከተማ ክፍት የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጣል መታሰቡንና ገደቡ ለመጣልም የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መኾኑን አስታውቋል። ከዚህም በኋላ የተሰጡ አስተያየቶች፤ ገደቡ መደረግ ያለበት መኾኑ ነው።

እስከ ሳምንቱ ማብቂያ እሁድ ግንቦት 16 ቀን፤ በአዲስ አበባ ከተማ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች፤ በአጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ ከተጠቁት 582 ሰዎች ውስጥ 377 ደርሰዋል። (ኢዛ)

የትግራይ ሕዝባዊ ንቅናቄ

ከአንድ ዓመት በፊት የሕወሓት ከፍተኛ የአመራር አባላት ደጋግመው ሲገልጹት ከነበሩት ጉዳዮች መካከል፤ “ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ ሰላም ያለው በትግራይ ብቻ ነው” የሚል ነበር።

በተለይ አቶ አስመላሽና ዶክተር ደብረጽዮን ይህንን በተለያየ ማዕዘን ተናግረዋል። በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያለውን ያለመረጋጋት፤ አሁን ባለው የፌዴራል መንግሥት ላይ በማሳሰብ፤ ሕወሓት በክልሉ - ለክልሉ እየሠራ በመኾኑ ሰላም የሰፈነበት ሊሆን መቻሉን የሚያመላክቱ አስተያየቶችን ሲሰጡ ነበር። አሁን ላይ ግን የትግራይ ክልል የተለየ ገጽታ እየታየበት ነው።

ሰሞኑን በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የተቃውሞ ድምፆች እየተሰሙ ነው። ይህ መኾን ከጀመረ ሳምንት የተቆጠረ ቢሆንም፤ እሁድ ዕለት ግን በአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ “ፈንቅል” በሚል የትግል ስያሜ ሰፋ ያለ ተቃውሞ እንዲይዝ እየተደረገ መኾኑን በጉዳዩ ላይ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

በክልሉ ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች አደባባይ ጭምር ተቃውሟቸውን ማሰማት ከጀመሩ ድፍን አንድ ሳምንት የኾናቸው ሲሆን፤ እሁድ ግንቦትት 16 ቀን ግን ለየት ባለመልኩ ተቃውሞው የተካሔደበት ነበር። በክልሉ የተፈጠረውን የተቃውሞ ጐልቶ እንዲታይ ያደረገው ደግሞ “ፈንቅል” በሚል መጠሪያ የተቃውሞ እንቅስቃሴው እንዲካሔድ ጥሪ መደረጉ ነው።

በትግራይ ክልል ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ እየሰፋ ያለው የተቃውሞ ድምፅን ተከትሎ፤ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም፤ ይህንን ተቃውሞ በተመለከተ እያሰፈሩዋቸው ያሉት መረጃዎች፤ በየአካባቢው የተነሳው ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች እየሰፋ መኾኑን ያትታሉ።

ሕወሓት ትግል የጀመረበት ደደቢት ሳይቀር ሕወሓትን የሚቃወም ትእይንት መካሔዱን የሚጠቁሙት መረጃዎች ያሳያሉ። በሽሬ ማይሐንስ፣ ደደቢት፣ ኂዋነ እና በሌሎች ከተሞች እየተሰማ ያለው ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም መንገድ በመዝጋት ጭምር የተካሔደ ነበር።

የሕወሓትና የክልሉ መንግሥት በአንድ በኩል፤ የፌዴራል መንግሥቱን ከሚቆጣጠረውና በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከሚመራው የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል። በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ልዩነቶችና መከፋፈሎች እንዳሉ እየተነገረ ነው። ኾኖም ሕወሓት በውስጡ ካሉ መከፋፈሎችና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ካለው ችግር በባሰ ሁኔታ ግን፤ ለሕልውናው ትልቅ አደጋ እየፈጠረበት ያለው በትግራይ የተነሳው መጠነ ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ናቸው።

“በተፈቀደ የወረዳነት ጥያቄ፤ ሕዝብ መሐል ገብታችሁ ልዩነት ለመፍጠርና ወደኋላ ለመመለስ እያካሔዳችሁ ያላችሁትን ተንኮል አቁሙ!” የሚል ተቃውሞ የተስተናገደበትም ነው።

ከሰሞኑ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በመቀሌና ማይጨው መካከል በምትገኘዋ ሂዋነ ከተማም፤ ነዋሪዎቹ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች አስጠርተው፤ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል። የክልል አመራሮች መጥተው እንዲያነጋግሩዋቸው፤ ላቀረቡት የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡም ስለመጠየቃቸው ዘገባዎቹ ያመለክታሉ። ይህ ካልሆነ ግን ፍትሕ የተጠማው ሕዝብ ወደሚቀጥለው ደረጃ እንደሚንቀሳቀስም አስጠንቅቀዋል ተብሏል።

በሽሬ፣ ማይሐንስ፣ ደደቢት ደግሞ፤ ሕዝቡ መንገዶችን በመዝጋት ጭምር ተቃውሞውን ማሰማቱ ተነግሯል። “የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ፣ ፍላጎትና መፃኢ እድል ተመሳሳይ ነው የምንለው በበቂ ምክንያት ነው” በማለት፤ ስለሰሞኑ እንቅስቃሴ ሐሳባቸውን በመረጃ ገጻቸው ያሰፈሩት የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል፤ “የሕወሓት ትጥቅ ትግል የተጀመረበት ማይሓንስ-ደደቢትም ሳይቀር 7 ቀን ያስቆጠረ የሕዝብ እንቢቱኝነት እየተካሔደ ይገኛል። ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ እናቶችና አዛውንቶች ሳይቀሩ እየተሳተፉበት የሚገኙ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በሰፊው እንደታየው ስር የሰደዱና ሕዝብን ከመጠን በላይ ያማረሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በማንገብ፤ መንገድ በመዝጋትና ሰላማዊ ሰልፍ በማካሔድ እየተገለጸ ይገኛል” በማለት ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሒዋነና በጨርጨር ከተሞችም ተመሳሳይ የሕዝብ ጥያቄዎች ያነገበ ሕዝብ፤ እንቢተኝነቱ እየገለጸ ስለመኾኑ ባወሱበት በዚህ ጽሑፋቸው፤ ይህ ሁሉ ሲሆን የክልሉ መንግሥት የጥቅሙና የአፈናው መረብ በዘረጋበት በመቐለና በመቐለ ዙሪያ ብቻ ተወስኖ ወይ መልስ መስጠት ወይም እንቢተኝነቱ ማስቆም አቅቶት፤ መላ ያጣና ተስፋ የቆረጠ ተመልካች ብቻ ኾኖ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“አዎ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ፣ ፍላጎትና መፃኢ እድል ድሮም አሁንም በመጪውም ተመሳሳይ ነው።” ለዚህ ነው የሕወሓት ትግል የተጀመረበት አካባቢ ሳይቀር በመላ የአገራችን ክፍል የታየው ዐይነት የሕዝብ እምቢተኝነት እየተካሔድ የሚገኘው በማለት አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሲሆን፤ እንቅስቃሴውን በቅርብ እየተከታተሉ መኾኑንም ገልጸዋል። (ኢዛ)

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ስብሰባና ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው አባላቱ

12 የክልሉን ምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት የተነሳበት የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ጉባዔው የተደረገው በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ነበር። የክልሉ ምክር ቤት ባካሔደው መደበኛ ጉባዔ፤ 12 የምክር ቤቱን አባላት ያለመከሰስ መብት ያነሳው ጉባዔውን ረግጠው በመውጣታቸው ነው። ምክር ቤቱ ጉባዔውን ለማስቀጠል የሚያስችለው አባላት በመቅረታቸው፤ ስብሰባውን በመቀጠል የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ታውቋል።

በሌላ በኩል ግን ስብሰባውን ረግጠው ከወጡ ወገኖች እንደተነገረው፤ ምክር ቤቱ ስብሰባውን ለማስቀጠል የሚያስችለው ተሰብሳቢ አልነበረውም በማለት ሞግተዋል። የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ግን፤ ስብሰባውን ለማስቀጠል የሚያስችል አባላት ስለነበሩ፤ ስብሰባው እንዲቀጥልና የተለያዩ ውሳኔዎች መወሰናቸውን ገልጿል።

በዕለቱ ምክር ቤቱ ካሳለፉአቸው ውሳኔዎች መካከል፤ የአስራ ሁለት አባላት ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የሚል ይገኝበታል።

ከዚህ ውሳኔው ባሻገር፤ ምክር ቤቱ አዳዲስ ሹመቶችን በመስጠት ስብሰባውን ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በዚሁ መሠረት ዶ/ር ሁሴን አብዱላሂ ቃሲም (የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ)፣ አቶ አሊ በደን አደን ማህመድ (ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ)፣ አቶ አብዱቃድር ረሽድ (የፐብሊክ ሰርቪስ ኃላፊ)፣ አቶ አብዲ መሕመድ (የማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ) በመኾን ተሹመዋል።

ምክር ቤቱ ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል የተባሉትንና ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ውሳኔ ያሳለፈባቸው አባላቱ ላይ ባካሔደው ግምገማ፤ በሙስና፣ በማኅበረሰቡ መካከል ኹከት በመፍጠርና ሥርዓት አልበኝነት እንዲሁም በሌሎች ወንጀሎች የሚጠረጠሩ መኾኑን አስታውቋል። (ኢዛ)

የአዲስ አበባ ካቢኔ ውሳኔ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ሰሞኑን በመሰብሰብ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን፤ ውሳኔው በዋናነት ያተኮረው በታክስ ዕዳ ማቅለያ እና ገቢ ማሻሻያ አጀንዳዎች ላይ ነው። በዚሁ ውሳኔ መሠረት ከ1997 – 2007 ግብር ዘመን ውዝፍ ዕዳ ለነበረባቸው ግብር ከፋዮች ዕዳው በምሕረት ቀሪ እንዲኾን፤ ከ2008 – 2011 ግብር ዘመን ዕዳ ላለባቸው ግብር ከፋዮች፤ ቅጣትና ወለድ ተነስቶ ፍሬ ግብር ብቻ እንዲከፍሉ መወሰኑ ታውቋል።

ቤታቸው ለተቀመጡ ሠራተኞች ደምወዝ ለሚከፍሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም ለተከራዮቻቸው የኪራይ ቅናሽ ላደረጉ አከራዮች የታክስ ጫና ማቃለያ የሚኾኑ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ታውቋል።

የከተማዋን ገቢ ለማሻሻል ሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ያላቸውን አቅም በዝርዝር ፈትሸው፤ ለከተማዋ ገቢ እድገት በቅንጅት መሥራት በሚቻልበት ዙሪያና አፈፃፀሙንም የቅርብ ክትትል የሚደረግበት መንገድ ላይ እንደተወያየ ከከተማዋ መስተዳደር የወጣው መረጃ ገልጿል።

በተለይም ማዘጋጃ ቤታዊ እና የከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅምና የአሠራር በተሻለ መልክ በማደራጀት የ2013 ዓ.ም. በጀት በመካከለኛ ገቢ ምጣኔ መሠረት ተዘጋጅቶ ለውይይት እንዲቀርብ ወስኗል ተብሏል። (ኢዛ)

የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ገደብና አንደምታው
ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ከባንክ ውጭ ነው

በዚህ ሳምንት በጉልህ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ውስጥ የኢትዮጵያ ባንኮች ለግለሰቦችም ኾነ ለኩባንያዎች በዕለት በጥሬ ሊሰጡ የሚገባቸው የገንዘብ መጠን እንዲገደብ መደረጉ ነው።

ከኢትዮጵያ ባንኮች በየዕለቱ የሚወጣ ገንዘብ ገደብ የሌለው ኾኖ መቆየቱ ሕገወጥ ገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲሰፋ እያደረገ ሲሆን፣ ዘመናዊ የገንዘብ ዝውውር ላይ ጫና ማድረሱም ይገለጻል። ይህም በመኾኑ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ ማንኛውም ባንክ ለግለሰቦች በጥሬ ገንዘብ በቀን ከ200 ሺሕ ብር በላይ፤ በወር ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ መስጠት እንደማይችሉ የሚደነግግ ሕግ ሥራ ላይ ውሏል። በዚህ መመሪያ መሠረት ከግለሰብ ሌላ ኩባንያዎች በቀን ማውጣት የሚችሉት ጥሬ ገንዘብ 300 ሺሕ ብር ብቻ ሲሆን፤ በወር ማውጣት የሚችሉት ደግሞ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያልበለጠ እንዲኾን ተወስኗል።

በዚህ መመሪያ ላይ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ፤ ይህ መመሪያ የወጣበትን በርካታ ምክንያቶች ያስቀመጡ ሲሆን፤ በተለይ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ንገድ ባንክ በተደራጀና በተጭበረበረ መንገድ 60 ሚሊዮን ብር ሊወጣ ሲል መያዙን ነው። ከዚህም ሌላ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል በአንድ የዳያስፖራ አካውንት ከተቀመጠ 350 ሚሊዮን ብር በላይ ውስጥ 55 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ለማውጣት የተደረገው ሙከራ፤ ይህንን መመሪያ በቶሎ ለማውጣት ማስገደዱን ገልጸዋል።

ገደብ የሌለው ጥሬ ገንዘብ ማውጣቱ እንደ አገር ጉዳት እያመጣ ከመኾኑም በላይ፤ ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የጦር መሣሪያ ግዥ ጭምር የሚውል በመኾኑ፤ ይህንን ለመገደብ መመሪያው አስፈላጊ ነው ተብሏል።

ይህ ማለት ግን ኩባንያዎችም ኾኑ ግለሰቦች በቀን ከሚያወጡት የጥሬ የገንዘብ መጠን በላይ መጠቀም ከፈለጉ፤ ገንዘባቸውን ከአካውንት ወደ አካውንት፣ በቼክና በሲፒኦ ማስተላለፊ መንገዶችን እንዲጠቀሙ እንጂ፤ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ አይችሉም ማለት እንዳልኾነ ተነግሯል።

ይህ መመሪያ በባንኮች ጭምር የተደገፈ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር አባላት እንደገለጹትም መመሪያው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ነው። በተለይ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ፤ የዚህ መመሪያ መጠን ከባንክ ውጭ ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ ለማምጣት ያግዛል። ባንኮች ቅርንጫፍ ባስፋፉ ቁጥር ወደ ባንክ የሚመጣው የገንዘብ መጠን ይጨምራል ቢባልም፤ አለመጨመሩ ችግሩን ያሳያል ብለዋል።

እንደ አቶ አቤ ገለጻ በ2016 (እ.ኤ.አ) በኢትዮጵያ ከባንክ ውጭ ያለው ገንዘብ 61 ቢሊዮን ብር አካባቢ ሲሆን፣ አሁን ግን ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቁመዋል። ይህ ገንዘብ ወደ ባንክ መምጣት ያለበት ሲሆን፤ ይህ አለመኾኑ ችግር ተደርጐ መታየት እንዳለበት ገልጸዋል። (ኢዛ)

የሲዳማ ዞን ክልል ምሥረታ

የሲዳማ ዞን በቅርቡ በተሰጠው የሕዝበ ውሳኔ መሠረት የክልል ምሥረታውን በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

የዞኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ሰሞኑን እንደገለጹት ሲዳማ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሕዝቡ በራሱ ድምፅ በሕዝበ ውሳኔ ያረጋገጠና ክልሉን ለመመሥረት የሚያስችል ድምፅ ያዥ በመኾኑ፤ በዚሁ መሠረት ቀጣይ የሚኾነው ሥራ፤ ክልል መኾኑን ማወጅ ነው ብለዋል። ይህም በተያዘው ዕቅድ መሠረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግም አመልክተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ