20210302 adwa

Ethiopia Zare's weekly news digest, week 38th, 2012 Ethiopian calendar

ከግንቦት 17 - 23 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሠላሳ ስምንተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከግንቦት 17 - 23 ቀን 2012 ዓ.ም.) ባሳለፍነው ሳምንት ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ በኾነው ግንቦት 20ን በተመለከተ በተለያዩ ወገኖች የወጡ መግለጫዎች ይጠቀሳሉ። በተለይ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው መግለጫ አንዱ ነው። ይህ መግለጫ ከለውጡ በኋላ ያለውን የለውጥ ሒደት በእጅጉ የኮነነበት ነበር። ባልተለመደ ሁኔታ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የክልሉን መግለጫ በኮነነ መልኩ ምላሽ የሰጠበት ኾኖ መገኘቱ አነጋጋሪ ነበር ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ እየሰፋ ስለመምጣቱ ጐልቶ የታየው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር ማለት ይቻላል። በአንድ ቀን ከ100 በላይ የሚኾኑ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙበት ሲሆን፤ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ከአንድ ሺሕ በላይ መኾኑ የተነገረበት ሳምንት ነበር።

ከዚህም ሌላ ከሳምንቱ ቀዳሚ ወሬዎች ውስጥ በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በተነሳ ጦርነት ደረሰ የተባለው ጉዳት ነው። በዚህ ዜና የሱዳን መንግሥት መግለጫ የሰጠበት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ስለሁኔታው መከሰት ኀዘኗን የገለጸችበት መግለጫ የተሰጠው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነው።

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኾኑ ወዲህ፤ የመጀመሪያ ነው የተባለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ ተጠቃሽ ነው። ይህ መግለጫ ባልተለመደ ሁኔታ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ላይ ተፈጸመ የተባለውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያተተበት ነው። ይህ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ ግን ሚዛናዊነት የጐደለው መኾኑን በመግለጽ የአማራና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት ተቃውመዋል። ኾን ተብሎ የተደረገ ስለመሆኑና ከመንግሥት ወገን ምንም ዐይነት አተያይ የሌለበት ነው ተብሏል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ የልማት ባንክ ካፒታል ከ7.5 ቢሊዮን ብር ወደ 28.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ የወሰነ ሲሆን፤ ይህ ውሳኔ ከመጽደቁ በፊት ግን መመርመር አለበት ብሎ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቃውሞውን ያሰማው በዚሁ ሳምንት ነው። በ2012 ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅ ውሳኔ የተሰጠውም ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ነው።

ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ አዳዲስ የሕግ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ መታሰቡ የተገለጸበትም ሳምንት ነው።

በኦሮሚያ ክልል ያልተገባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የገለጸው የክልሉ መንግሥት፤ ይህ እንቅስቃሴ ግን ሕገወጥ በመኾኑ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የተጠናከረውን ቅኝት እነሆ!

በግንቦት 20 መግለጫ ላይ የመቀሌና የአዲስ አበባ የቃላት ጦርነት

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ግንቦት 20ን በማስመልከት ያወጣው መግለጫና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለክልሉ መግለጫ የተሰጠው ምላሽ በሳምንቱ አነጋጋሪ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ነበር። እንዲህ ባለ ሁኔታ አንዱ ለሌላው ምላሽ የሰጡበት አጋጣሚ ብዙም ያልተለመደ ስለነበር፤ ጉዳዩ ትኩረት መሳቡ አልቀረም። ከመቀሌ የወጣው መግለጫና ከአዲስ አበባ የተሰጠው ምላሽ ይዘት ደግሞ የተካረረ ሁኔታ እንዳለ፤ መደማመጥም ያልተቻለ መኾኑን አመላካች ነበር።

ሁለቱም ወገኖች ግንቦት ሃያን ተንተርሰው የሰጡት መግለጫ፤ የየቅል አመለካከታቸው የተንፀባረቀበት ነው። የትግራይ ክልል ግንቦት 20ን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ በጥቅል ሲታይ፤ ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ስለመግባቷ የሚያትት እና ማዕከላዊ መንግሥቱን በእጅጉ በሚኮንኑ ቃላቶች የታጀለ ነው።

“ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ በብዙ ሁኔታ ወደኋላ ቀርታለች” የሚል አንደምታ ያለው መኾኑንም ከመግለጫው መገንዘብ ይቻላል። ጭራሽ ማዕከላዊ መንግሥቱን ከደርግ ሥርዓት ጋር በማመሳሰል ጭምር የገለጸበት ነው።

በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ታይቷል የተባለው ችግር በሰፊው የተዘረዘረበት የክልሉ መግለጫ፤ በጥቅል ድምዳሜው የማዕከላዊ መንግሥት ወቅታዊ አቋም የደከመ ነው፤ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው ሥርዓት ይሻል ነበር የሚል ትርጉም ያዘለ ነው።

ይህንን የክልሉን መግለጫ ግን የማዕከላዊው መንግሥት በዝምታ ያለፈው አልኾነም። መግለጫውን ተንተርሰው ለመገናኛ ብዙኀን ማብራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ የሕወሓት መግለጫ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በእጅጉ የራቀና ከብስጭት የመነጨ ነው በማለት፤ ውኃ የማያነሳ መኾኑንም አክለዋል።

እንደ አቶ ንጉሡ ገለጻ፤ የትግራይ ክልልን የሚመራው ሕወሓት ብዙ መግለጫዎችን አውጥቷል። የሚወጡት መግለጫዎች መልእክቶቹ ቁጣና ብስጭት የተሞላባቸው ናቸው። በጣም የተቆጣና የተበሳጨ አካል ደግሞ የሚሰነዝሯቸው ቃላትና የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ስሜት የተቀላቀለባቸው ስለሚኾኑ፤ የተረጋጉና የሰከኑ አለመኾናቸውን አስረድተዋል። ምናልባትም ከጊዜ በኋላ ከስሜት ሲወጡ፤ እንዲህ ብለን ነበር ወይ? ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው የሚችልም ነው ብለዋል።

በክልሉ መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታ እስርና እንግልት የሚፈጸምበት ነው ማለቱንም በተመለከተ አቶ ንጉሡ በበኩላቸው፤ አሰቃቂና የከፋ ግፍና እስር ይፈጸም የነበረው ከለውጡ በፊት በነበረው የሕወሓት ጊዜ ነበር የሚል አንደምታ ያለውን ሐሳብ ሰንዝረዋል። አሁን ያለው የለውጡ መገለጫ እስር ቤቶች በመዝጋት፣ ማፈኛና ማሰቃያ ቦታዎች ለታሪክ እንዲኾኑ ማድረግ ነው እንጂ፤ እንደተባለው ያለመኾኑንም አመልክተዋል። ይህም በመኾኑ፤ አሁን ያ ግፍ ቀርቷል በማለት፤ በኢትዮጵያ ግፍ ይፈጸም የነበረው፣ አሁን መግለጫውን ባወጣው ቡድን እንደነበርም አጠንክረው ተናግረዋል። ምን ዐይነት በደል እንደደረሰ ተነግሮ ይቅርታ ተጠይቋል። አሁን ለመጣው ለውጥ ምክንያቱ፤ ከዚያ በፊት ይፈጸም የነበረው ግፍ መኾኑን ያስታወሱት አቶ ንጉሡ፤ ክልሉን የሚመራው ቡድን እንዲህ ያለ በቁጣ የተሞላ መግለጫ ለማውጣቱ ምክንያትም፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ እየተነሳ ያለውን የሕዝብ ጥያቄ አቅጣጫ ለማስለወጥ የታለመ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

አሁን ሕወሓት ይህንን ማለቱ በተለይ ደግሞ በግፉ ጊዜ በደል የደረሰባቸው፣ የተሰቃዩ ሰዎችና ቤተሰቦች ዘንድም ትዝብት ውስጥ የሚጥለው እንደኾነ በመግለጽ፤ የሰብአዊ መብት ረገጣ ከሁለት ዓመት በፊት እንጂ፤ አሁን በክልሉ መግለጫ በተገለጸው መልክ አለመኾኑንም አብራርተዋል። በአጠቃላይ በለውጡ ሒደት ችግሮች አይኖሩም ባይባልም፤ በሕወሓት ጊዜ ሁኔታው በአጠቃላይ ሲፈተሽ፤ የዜጐች ማሰቃያና ግፍ መፈጸሚያ ቦታዎች ላይ በስፋት ሰው መድቦና አደራጅቶ የሚያሰቃይ የነበረው ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበርም ገልጸዋል። ዋነኛው አስኳል በዜጐች ላይ ይደርስ የነበረው ግፍና በደል ሞልቶ በመፍሰሱና ስቃያቸው በመብዛቱ፤ ዜጐች መብቶቻቸውን በመጠየቃቸው፤ ከሁለት ዓመት በፊት ሊወገድ መቻሉንና አሁን እንዲህ ያለ መግለጫ ማውጣትም ትዝብት ላይ የሚጥለው መኾኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ያለውን የፌዴራል መንግሥቱን ከደርግ ጋር ማነፃፀሩን በተመለከተም አቶ ንጉሡ በሰጡት ምላሽ፤ እንዲያውም አሁን በትግራይ ክልል ከውስጥም ወጣቶች፣ እናቶችና ምሁራን የሚያነሱትን ጥያቄ በተመለመደ መልኩ ለማስቀየስና ለሕዝብ ሥጋት ፈጥሮ ጠላት ለመፍጠር፣ ለማዘናጋትና ለማደናገር ካልኾነ በቀር፤ ምንም እውነትነት እንደሌለው አመልክተዋል። “በዚህ በለውጥ ሒደቱ ውስጥ ያለው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፤ የዜጐች መብትና የሚል ተግባራዊነቱ ቀን ከሌሊት መትጋት - መሥራት ደርግ ካሰኘ፤ ከውስጥ ከትግራይ የሚነሳውን የሕዝብ ጥያቄ በተለመደው መልኩ ለማስቀየስና ለሕዝቡ ሥጋት ፈጥሮ ጠላት ለመፍጠር ለማዘናጋትና ለማደናገር ካልሆነ በስተቀር ይህንን እነሱ ያውቁታል። የደርግንና የሕወሓትን፣ የሕወሓትና የለውጡን አመራር ምንነትና ማንነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይለያል በማለት የሕወሓትን መግለጫ አጣጥለዋል።

አቶ ንጉሡ ሰው ሲያሰቃይ የነበረው ሥርዓት ከሁለት ዓመት ተወግዷልም በማለት ተናግረዋል። እንዲያው አገሩን ሳይቀር ካጥላላነውና ካስጠላነው አይቀር እስከመጨረሻው አምባገነንነት እስኪገለጽበት ድረስ እንውሰደው በሚል የወጣ መግለጫም ነው ብለውታል። ይህ ግን የሕዝብ ልብ የሚገዛ እና ውኃ የሚቋጥር አለመኾኑንም ጠቁመዋል።

ግንቦት 20 በርካቶች ዋጋ የከፈሉበት ስለመኾኑም ያስታወሱት አቶ ንጉሡ፤ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የታገሉለት ብዙዎች የሞቱላት ጥያቄ ይዘው በረሃ የገቡለት፤ ዛሬ የተኮላሸበት ነው ብለውታል። አሁን ያለው የለውጥ ሒደት ግን ይህንን የተጓደለ ነገር ለማሟላት የመጣ ነው በማለት ተናግረዋል። (ኢዛ)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ተጨማሪ የሕግ ማሻሻያዎች

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ሥጋት እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል። ይህንን እየሰፋ የሔደውን ችግር የበለጠ እንዳይሰፋ በመንግሥት ዘንድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ፤ የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ የተለገጸው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

የኮሮና ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር፣ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስተባባሪ ሴክሬተሪያትና የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ ለሚኒስትሮች ኮሚቴ እንዳስታወቁት፤ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መምጣቱንና አዲዲስ ባሕርያትም እየተስተዋሉ ነው። በተለይ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ንክኪ ያላደረጉ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ መምጣቱ አሳሳቢ መኾኑን ለመገንዘብ በመቻሉ፤ የሕግ ማሻሻያዎችን በማድረግ ቁጥጥር ማድረጉ ተገቢ መኾኑን አመልክተዋል።

አገሪቱ በምትወስንባቸው በድንበር አካባቢዎች የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን በማዘጋጀት፤ በተለይ በመተማ በኩል አቋርጠው የሚገቡ ዜጎችን ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን የማጠናከርና የቁጥጥር ሒደቱን ለማጥበቅ ስለመታቀዱ ይኸው የወይዘሮ ሙፈሪያት ማብራሪያ ያስረዳል።

የሚኒስትሯ ጥቅል ማብራሪያ የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት እየጨመረ በመምጣቱ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ በቀጣይ ቀናትም የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች የሚደረጉ ስለመኾኑ የሚያመላክት ነው። (ኢዛ)

የሱዳንና የኢትዮጵያ ግጭት

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ በሁለቱ አገሮች ታጣቂዎች መካከል ጦርነት መከሰቱ መገለጹ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ላይ ተፈጥሮ በነበረው ክስተት በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ኀዘን የገለጸበትን መግለጫ እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አውጥቷል።

ሚኒስቴሩ እሁድ ባወጣው መግለጫ፤ ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሰተው ግጭት የተሰማውን ኀዘን ገልጾ፤ በአደጋው ሰለባ ለኾኑ ቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለሁ ብሏል።

እንዲሁም ሚኒስቴሩ ሁለቱ አገራት የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ እና በጋራ ለማጣራት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ አስታውቆ፤ በአጎራባች የአካባቢ እና የክልል አስተዳደሮች መካከል የተቀናጀ ትብብር ቀጣይነት እንዲኖረው ጥሪውን አስተላልፏል። ችግሮቹ በተሻለ ሁኔታ መፍትሔ የሚያገኙት በሁለቱ አገራት መካከል ባለው መልካም፣ ወዳጃዊ እና ሰላማዊ ግንኙነት ላይ በመመርኮዝ እንደኾነም መግለጫው አመልክቷል።

በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ይህ ክስተት እንደማይወክልም እናምናለን ብሏል። በሁለቱ አገራት መካከል መልካም ግንኙነትን እና መግባባትን መሠረት ያደረገ የረጅም ጊዜ ግንኙነቶችን የሚያንፀባርቅ ጠንካራና ወዳጃዊ አካባቢን የበለጠ ማጎልበት አስፈላጊ መኾኑም በመግለጽ፤ ለተፈጠረው ግጭት ምላሽ ሰጥቷል። (ኢዛ)

የአምነስቲ መግለጫና የክልሎች ተቃውሞ

ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣ ሪፖርት ቢኖር ከሰሞኑ የወጣው ነው። ይህ ሪፖርት በተለይ በኦሮሚያ አካባቢ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚጠቁም ነው። እነዚህ ተደረጉ የተባሉ የመብት ጥሰቶች በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ስለመፈጸማቸውም የአምነስቲ ሰሞናዊ ሪፖርት ገልጿል። ይህ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ ግን የተሳሳተና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሲያስታውቅ፤ የአማራ ክልላዊ መንግሥትም በተመሳሳይ መግለጫውን ኮንኗል።

መንግሥት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመንግሥት የጸጥታ አካላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በማለት ያወጣውን መግለጫ ተንተርሶ መግለጫውን የሰጡት የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ሲሆኑ፤ ሪፖርቱ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ እና ሊታረም የሚገባው ነው በማለት የአምነስቲን መግለጫ አጣጥለውታል።

አምነስቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብት ጥሰትን እየተከታተለ ይፋ የሚያደርግ ኾኖ ሳለ፤ የመንግሥትን ምላሽ ባላካተተ መልኩ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ብቻ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን አስተያየት በመቀበል ያወጣው መረጃ መኾኑንም የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል።

እንደ ቢሮው ኃላፊ መግለጫ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ከዚህ ቀደም ሲፈጸሙ በነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ዝምታን ይመርጥ እንደነበር ተናግረዋል። በተለይም ነፍጥ ያነገቡ ታጣቂዎች በተለያዩ አካባቢዎች በሕዝብና የመንግሥት ኃይሎች ላይ የሚፈጽሙትን ወንጀል የካደ እና የተጎጂዎችን ድምፅ ያላሰማ፤ ይልቁንስ የአንድን ወገን ፍላጎት ለማጉላት ጥረት ያደረገ በመኾኑ የአሁኑም መግለጫ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ያወጣውን ሪፖርት ሚዛናዊነቱን በጠበቀ መልኩ ዳግም ማስተካከል የሚፈልግ ከኾነ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።

ይህ እንዲህ እንዳለ የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ይህንን የአምነስቲ ኢንተናሽናልን መግለጫ በመቃወም ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቷል። ይህንን ሪፖርትም የክልሉ መንግሥት እንደማይቀበለው አስታውቋል። የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ፤ እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያቀረበው ሪፖርት ኢ-ምክንያታዊና ኢ-ፍትሐዊ በማለት ገልጸውታል።

መስከረምና ጥቅምት ወራት አካባቢዎች በጎንደርና አካባቢዋ ግጭቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ የግጭቱ መነሻም በጽንፈኝነት በሚንቀሳቀስ ቡድን በተሠራ ሥራ መኾኑን አስታውሰዋል። በግጭቱም ንጹኃን ሰዎችም፣ የጸጥታ ኃይል አባላትም የሕይወትና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሀብትና ንብረት ወድሟል፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል። ይህን ጉዳይም “የክልሉ መንግሥት አውግዟል፤ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታትም ጥረት በማድረጉ ሰላማዊ መንገድ ፈጥሯል” ብለዋል።

“ሪፖርቱ አድሏዊነት ያለው፣ የተፈጸመን ድርጊት በሚገባ ያልገለጸ፣ ያልተነተነና በይፋ ያላወጣ ነው” ብለዋል። ሪፖርቱ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ላይ ብቻ ማተኮሩም ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ መኾኑን አንስተዋል።

“ሪፖርቱ ምክንያታዊ ያልኾነና ፍትሐዊነት የጎደለው ነው፤ የክልሉ መግለጫ የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ችግሩን ለመፍታት የሄድበትን መንገድ ያልዳሰሰ ነው” በማለትም ሪፖርቱን ኮንኗል። (ኢዛ)

የኦሮሚያ ክልል ማስጠንቀቂያ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ኹከትና ብጥብጥ ሊፈጥሩ ያቀዱ አካላት ስለመኖራቸውና ሕዝቡም ይህንን በንቃት ይጠብቅ ሲሉ የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በሠጡት መግለጫ አስጠነቀቁ። በዚሁ መግለጫም አሁን ላይ በክልሉ በተለያየ መልኩ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ የሚጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ ተቀባይነት የሌለው መኾኑን አስታውቀዋል።

ከአራት ሰዎች በላይ መሰብሰብ የማይቻልበት በአሁኑ ወቅት ሕብረተሰቡን ለችግር ለማጋለጥ የሚደረገውን ጥረት፤ ሕዝቡ ተረድቶ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ጥሪውን የሚያቀርቡ ሰዎች የሽግግር መንግሥት ይመሥረት የሚሉ አካላትና በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ኃይሎች መኾናቸውንና እነዚህም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አቶ ጌታቸው ባልቻ ተናግረዋል። ከምንጊዜውም በላይ እንደሚሠራም አመልክተዋል።

“አንዳንድ አካላት ክልሉን የኹከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ እየሠሩ በመኾኑ ሕዝቡ ነቅቶ ሊጠብቅ ይገባል” ብለዋል። የክልሉ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም ኃይል የሚያበረታታና የሚደግፍ መኾኑን ጠቅሰው፤ በሕገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ይኸው የክልሉ መረጃ አመልክቷል። (ኢዛ)

የልማት ባንክ ጉዳይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቃውሞ ቀረበበት

በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ተጨማሪ ካፒታል እንዲመደብለት የተሰጠው ውሳኔ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቃውሞ አሰምቷል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጉዳይ ሳይመረመር ይህንን የካፒታል ማሳደግ ጥያቄ መቀበል ተገቢ አይደለም በማለት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቃውሞውን አሰምቷል። ችግር ውስጥ ለሚገኘው ልማት ባንክ ይህንን ማድረጉ ተገቢ ባለመኾኑ ነገሩ በደንብ መታየት እንደሚኖርበትም የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል።

በተለይ አንድ የምክር ቤቱ አባል፤ መርጦ የወከላቸው ሕዝብ ባለበት ወረዳ 22 የሚደርሱ ባለሀብቶች የእርሻ መሬት ተረክበው፤ ከባንኩ እስከ 10 ሚሊዮን ብር ብድር ወስደው፤ 10 ዓመት ሙሉ ምንም ሳይሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። እነዚህ የባንኩን ገንዘብ በቡድን የተከፋፈሉ ግለሰቦች፤ “ሐመር መኪና ይነዳሉ፤ ዱባይ ይዝናናሉ፤ መሬቱም ጦሙን አድሯል፤ የሕዝብ ገንዘብም ባክኗል” በማለት አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ባንኩን በተመለከተ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ የተመራለት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ጉዳዩን በትኩረት እንዲያየው አሳስበዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የልማት ባንክ ካፒታል ከ7.5 ቢሊዮን ብር ወደ 28.5 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ወስኖ እንደነበር አይዘነጋም። ከዚህ ሌላ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽንን ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅንና የጂኦተርማል ማሻሻያ አዋጅን ያጸደቀውም በዚህ ሳምንት ነው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ካውንስል ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት የተዘጋጀውንም ረቂቅ፤ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ አድርጓል። (ኢዛ)

የጉባዔው ምላሽ

ከሳምንቱ ዐበይት ዜናዎች ውስጥ ሌላው ተጠቃሽ ሊሆን የሚችለው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ፤ ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ምርጫን በወቅቱ ማካሔድ ባለመቻሉ፤ እንዲሁም የምክር ቤቶቹንና የአስፈፃሚ አካላት የሥራ ዘመን አስመልክቶ የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ምላሽ መሰጠቱ ነው።

ጉባዔው ከምክር ቤቱ ጥያቄው ከቀረበለት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አንፃር መመርመሩን የሚያመለክትና ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሐሳብ ከመስጠቱ በፊት በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 9 መሠረት የፈጸማቸውን ተግባራት በማብራራት ምላሽ ሰጥቷል።

በሕገ መንግሥት የትምህርት ዘርፍ የተሰማሩና ልምዱ ያላቸውን ባለሙያዎች ማወያየቱንና ሐሳብ እንዲሰጡ ማድረጉን ጠቅሷል። ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅ ሒደት በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ ያላቸውን ግለሰቦች፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ተቋማት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን ሐሳብ ለሕብረተሰቡ ግልጽ በኾነ መንገድ ስለመቅረቡም አስታውቋል። በተለያዩ ሚዲያዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት በማስተላለፈ፤ በጉባዔውም ኾነ በአገሪቱ ደረጃ የመጀመሪያ የኾነውን የመስማት ሒደት ማከናወኑን ነው ጭምር አስረድቷል።

ከመስማት ሒደቱ ጎን ለጎን ጉባዔው ባደረገው ጥሪ መሠረት፤ በጽሑፍ የቀረቡ በርካታ ሐሳቦችን እንደተመለከተ እና ከዚህም ሌላ ሐሳብ ለማጎልበት የሚረዱ ጥናቶችን በጉባዔው ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎች ያስጠና ሲሆን፣ እነዚህን መሠረት አድርጎ ጉባዔው ባስቀመጣቸው ዋና ዋና ጭብጦች ላይ ለሁለት ሳምንታት ያህል ተከታታይና ጥልቅ የኾነ ውይይት በማድረግ ምላሽ በማዘጋጀት የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን ገልጿል። (ኢዛ)

ተጨማሪ በጀት ማጽደቅ

ኢኮኖሚያዊ ከኾኑ የሳምንቱ ዐበይት ጉዳዮች ውስጥ የኮሮና ወረርሽኝን ለመቋቋምና ለማለፍ ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅ ውሳኔ መተላለፉ ነው። ወረርሽኙ እያስከተለ ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ለመቋቋም የሚያግዝ ነው የተባለው ተጨማሪ በጀት በጸደቀበት ወቅት እንደተነገረው፤ ወረርሽኙ በጤና፣ በማኅበራዊና በምጣኔ ሀብት ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ በመኾኑ፤ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ነው።

መንግሥት እስካሁን ችግሩን ለመቋቋም በ2012 በጀት ዓመት ከተፈቀደው ውስጥ፤ ከ12 እስከ 15 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ እየዋለ ቢኾንም፤ ይህ ብቻ በቂ ባለመኾኑ ተጨማሪ 48 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማስፈለጉን በሚመለከት የተጨማሪ በጀቱ ጥያቄ ቀርቦ ጸድቋል።

ይህንን ወጪ ለመሸፈንም ከልማት አጋሮች በበጀት ድጋፍ መልክ 28 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እርዳታና ብድር ስለመገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፤ የተቀረው 20 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታደቀዱ፤ በጀቱን ለማጸደቅ በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ተገልጿል።

በዚሁ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የኮሮና ወረርሽኝን የኢኮኖሚ ጫናን ለመቋቋም ከውጭ አገር በሚገኝ 28 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እና ከአገር ውስጥ ምንጮች በሚገኝ 20 ቢሊዮን ብር ለመቋቋም መታቀዱንና ይህ ገንዘብ በቅርቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!