ሕወሓትና የብልጽግ

የሕወሓትና የብልጽግና የ29ኛው የግንቦት 20 በዓል መግለጫዎች

29ኛውን በዓል የቀድሞው ኢሕአዴግ ለሁለት ተከፍሎ ያሳልፋል

ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 27, 2020)፦ ላለፉት 27 ዓመታት በአደባባይ ጭምር ሲከበር የነበረው የግንቦት ሃያ በዓል ለሁለተኛ ጊዜ በቀድሞ መልክ መከበር ያቆመ ሲሆን፤ ቀኑን ለማስታወስ ግን መግለጫ መውጣቱን አልቀረም። 29ኛውን በዓል የቀድሞው ኢሕአዴግ ለሁለት ጎራ ተከፍሎ ያሳልፋል።

በዛሬው ዕለትም (ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግንቦት 20ን አስመልክተው አጭር መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ የትግራይ ክልል መንግሥት ደግሞ “ኢትዮጵያ ዳግም የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ፈጽሞ አትኾንም!” በማለት ረዥም መግለጫ አውጥቷል። መግለጫዎቹን እነኾ! (ኢዛ)

እንኳን ለግንቦት ሃያ የድል መታሰቢያ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ! ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ግንቦት ሃያ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ከቀየሩ ዕለታት መካከል አንዱ ነው። ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ለማድረግ አያሌ ታጋዮች እጅግ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ነፍስ ሠውተዋል። የግንቦት ሃያ ታጋዮች የነፍስ ዋጋ የከፈሉለት ዓላማ ግፍና ጭቆና፣ አድሎና ወገንተኝነት ቆሞ፤ እኩልነት ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ነው።

ግንቦት ሃያን ማክበር ያለብን እነዚህን ዓላማዎች እያሰብን መሆን አለበት። ቀኑን የምናስበው በግንቦት ሃያ ላይ ተቸክለን ሳይሆን ወደፊት እየሄድን የኋላውን እየገመገምን መሆን አለበት። ግንቦት ሃያን ያመጡ ታጋዮች ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ግንቦት ሃያ ሁለት መውሰድ እንጂ ወደ ግንቦት አሥራ ዘጠኝ መመለስ አልነበረም። አገራቸው በሁሉም መመዘኛ ግንቦት ሃያን አልፋ፣ ግንቦት ሃያ አንድንም ተሻግራ፣ ወደ ግንቦት 22 መድረስ ነበር።

የግንቦት ሃያ ታጋዮችን ዓላማ የምናሳካው በሁለመናዋ ከግንቦት 19 የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ከቻልን ብቻ ነው። የብልጽግና ጎዳናችን ዓላማ ግንቦት ሃያ ላይ ቆሞ ግንቦት አሥራ ዘጠኝን እያሰቡ መኩራራት ሳይሆን አገራችን ወደ ግንቦት 22 ማስፈንጠር ነው። ይህ ማለትም አገራችን ከነበረችበት አስከፊ ሁኔታ ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን መድረስ ወደነበረባት የላቀ ደረጃ ማድረስ ነው። የግንቦት ሃያ የድል መታሰቢያ በዓልን ሰናከብር በተባበረ ክንድ ከግንቦት ሃያ የሚልቅ፣ ወደ ግንቦት 19 እንዳንመለስ የሚያደረግ ምጡቅ ሥርዓት ለመገንባት ቃላችን የምናድስበት እና ወደ ላቅ ውጤት ለመቀየር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምንገባበት መሆን ይገባዋል።

ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ በአጥንትና ደማቸው ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ላቆዩ ሰማዕታት!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ግንቦት 19/ 2012 ዓ.ም.

* በአካል ተራርቀን፤ ንጽሕና ጠብቀን፣ እርስ በርስ ተረዳድተን- ኢትዮጵያን ከኮሮና እንታደግ *
* Qaamaan gargar fagaannee, qulqullina eegnee, waliikeenya walgargaarree, Itoophiyaa Koroonaa irraa haa baraarru! *

29ኛው ዓመት፣ የግንቦት 20፣ የድል ቀን በማስመልከት፣ ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ዳግም የብሔርና ብሔረሰቦች እስርቤት ፈፅሞ አትሆንም!! ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በማንም ምድራዊ ሐይል አይነጠቅም!!

ከሁሉ አስቀድሞ፣ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ እንኳን ለ29ኛው ዓመት፣ የግንቦት 20፣ የድል ቀን፣ በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን! የሚል መልእክት፣ በትግራይ ሕዝብ ስም ሲያስተላልፍ፣ እንደ ትላንቱ ሁሉ፣ ዛሬም የጋራ ክንዳችን አፈርጥመን፣ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን አንኮታክተው፣ አገራችንን ብተና አፋፍ ላይ ያደረሱትን የጥፋት ኃይሎች፣ አደብ እንዲገዙ ሁላችን ተባብረን እንደምንንቀሳቀስ ተስፋ በማድረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ግንቦት 20 በየዓመቱ እያከበሩ ዓመታት የዘለቁት፣ በዋነኛነት ብሔራዊ ክብራቸውና ማንነታቸው በጉልበት ተደፍቆ፣ በገዛ አገራቸው፣ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተደርገው የሚቆጠሩበት፣ በአጭሩ ገዢዎቹ እግር ተወርች አስረው ባደረሱባቸው፣ ምህረት የለሽ ብዝበዛና ጭቆና ለችግር፣ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ እንግልት ስደትና ሞት፣ የዳረጉዋቸውን፣ ዘውዳዊ የመሳፍንትና የወታደራዊ ፋሽሽታዊ ደርግ አፋኝ ስርዓቶች፣ በዋነኛነት በቀድሞ ኢሕአዴግ እየተመሩ፣ በገጠርና በከተማ በዋጀው ደማቸውና በተከሰከሰ አጥንታቸው፣ የትምክህት ሓይሎች፣ ከመንበረ ስልጣናቸው አስወግደው፣ በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች፣ የአርነት ችቦ አውለብልበው፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብቸኛ የአገሪቱ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸውንና ቀጣይ የህዳሴ ጉዞ ያወጁበት ቀን በመሆኑ ሁሌም በጉጉት ይጠባበቁታል፡፡

በመሆኑ በቅድሚያ ለዘመናት ተንሰራፍተው በቆዩት ኋላቀር ስርዓቶች የተፈጠሩትንን የተዛቡ ግንኙነቶች ለማረም እና የችግሩ ምንጮች ከእነሰንከፋቸው በመቅበር፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማክበር፣ አንድ የፖለቲካና አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመገንባት እንዲቻል በወቅቱ ከነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ማለትም ከ19 ሚልዮን በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ የተሳተፈበት፣ በመጨረሻም መርጦ በላካቸው ተወካየቹ ሰፊ ውይይትና ክርክር ከተደረገ በኋላ፣ በዴሞክራሲያዊ አኳሃን፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፣ ህዳር 29/1987 ዓ.ም.፣ ፀድቆና የአገሪቱ የሁሉም ህጎች የበላይ ሕግ ሆኖ ሳይሸራረፍ 27 ዓመት ሙሉ ስራ ላይ ውሏል፡፡

በመሆኑም አገራችን ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ግልፅ ራእይ ተቀምጦ፣ በአገራችን ሰላም እንዲነግስ፣ ዲሞክራሲ ስር እንዲሰድ እና ዙሪያ መለስ ልማት ለማፋጠን የሚያስችሉ፣ የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት መሰረታዊ እምነቶችና ምሶሶዎች መነሻ ያደረጉ፣ አራት ዓበይት ግቦችን ለማሳካት ወደር የለሽ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡ ይኸውም ከሁሉም በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተጎናፅፈዋል፡፡

በመሆኑም ከ1983 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. በነበረው ሩብ ክፍለ-ዘመን፣ በየአመቱ በአማካይ ስምንት በመቶ፣ በ1993 ዓ.ም. የተካሄደውን ተሃድሶ ማግስት ጀምሮ በነበሩት 15 ዓመታት ደግሞ በየዓመቱ ባለሁለት አሃዝ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ፣ በ1980ዎቹ መጨረሻ በኢትዮጵያ ከድህነት በታች የነበረውን 48 ከመቶ ምጣኔ፣ በ2008 ዓ.ም. ወደ 23 ነጥብ ሰባት ከመቶ ወርዷል፡፡ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችም ከድህነት ተላቀዋል፡፡ በሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ባለሃብቶቾም ተፈጥረዋል፡፡ የነፍስ - ወከፍ ገቢም ወደ 790 ዩኤስ አሜሪካ ዶላር ከፍ ብሎ ነበር፡፡ 45 ዓመት የነበረው በህይወት የመኖር አማካይ የዕድሜ መጠንን ወደ 66 ከፍ ብሏል፡፡ በትምህርት መስክ ከሁለት ዩኒቨርስቲዎች ተነስታ አገራችን የ45 ዩኒቨርስቲዎች ባለቤት ሁናለች፡፡ ይህም ከ110 ሚሊዮን በላይ ከሚገመተው ሕዝቧ ሩብ ያህሉ ትምህርት ገበታ ላይ እንዲውል ሁነዋል፡፡

ባጠቃላይ አገራችን ኢትዮጵያ እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም. ድረስ በአለም በድህነት መዝገብ ሰፍረው ከነበሩት 10 አገራት አንዷ ነበረች፡፡ ሆኖም የደርግ ስርዓት ከተደመሰሰ ማግስት ጀምሮ በዋነኝነት ከግንቦት 20/1983 ዓ.ም. በኋላ ባስመዘገበችው የሚጨበጥ የልማት ግስጋሴ በፍጥነት እያደጉ ካሉት 10 የዐለም አገራት መካከል በመጀመሪያ ረድፍ እንድትቀመጥ አስችሏት ነበር፡፡ ይህ የህዳሴ ጉዞና የግንቦት 20 ቱሩፋቶች በኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ጥረት እና የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ሕዝባዊ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የአመራር ብቃት ውጤት በመሆኑ፣ ሁላችንም ልንኮራበትና አንገታችን ቀና አድርገን በየትኛውም ጊዜና ቦታ በድፍረት የምንናገረው መሬት ላይ ያለ እውነታ ነው፡፡

በመሆኑም ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን የመራው የቀድሞ ኢሕአዴግ፣ አልፋ-ኦሜጋ እምነት፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላዕላዊ የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጠው፣ በዋነኝነት ለተጋላጭነት የዳረገን ድህነትን የማስወገድ፣ ከየትኛውም የዓለም ጫፍ ሲዘነዘር የነበረውን የውጪ ጣልቃ ገብነት እና ተፅዕኖ ሳይንበረከክ፣ ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ የፖሊሲ ነፃነቱን ጠብቆ ተመፅዋትነት ለማስወገድ፣ ኢንቨስትመንትና ንግድ ለማስፋፋት የሚረዳ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ባጭሩ የኢትዮጵያን አገራዊ ጥቅም የሚያረጋግጥ ነፃነቷና ሉአላዊነቷ ክብሯ ከፍ የሚያደርግ ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያማትር ማለትም ድህነትን ደረጃ በደረጃ በመቀነስ ውስጣዊ አቅምን ለማጠናከር ምሰሶ የሆነውን የሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት ያደረገ የደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርፆ በመንቀሳቀሱ፣ ኢትዮጵያ፣ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አስችሏት ነበር፡፡ ይህ በመሆኑ ለአመታት የራሳችን ሃብት እንዳንጠቀም የነበሩትን መሰናክሎች ጥበብ በተሞላበት የዲፕሎማሲ አካሄድ፣ አመራርና ትግል በመበጣጠስ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በራስ አቅም ለመገንባት አስፈላጊውን ሁሉ ተደርጓል፡፡ ባጭሩ የአፍሪካ ሕብረት ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ ለማስነሳት የነበረው ሴራም በማክሸፍ አገራችን በታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ እየተወከለች የአፍሪካ ቃል አቀባይ በመሆን፣ ጂ-7፣ ጂ-20 የሚባሉት መድረኮች ጨምሮ በተለያዩ የዐለም አቀፍ መድረኮች አሳማኝ፣ የመፍትሄ ሐሳቦችን በማቅረብ የዐለም ጉፉአን ሕዝብ ጠበቃ መሆኗን በተግባር አሳይታ ነበር፡፡ በዋነኛነት ቀደም ሲል በታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ የተነደፈው የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ ለማሳካት በተለይ የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ዩኤስ አሜሪካን ጨምሮ የዐለም ኃያላን መንግሥታት በማሳመን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ለማስፈረም በታላቁ መሪያችን ታጋይ መለስ ዜናዊ የተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግልና የተመዘገበው ውጤት ታሪክ ለዘለዐለም ሲዘክረው የሚኖር ታላቅ ፍፃሜ ነው፡፡ ባጠቃላይ አገራችን የራሷ አቅምና ውስጣዊ ሰላሟ በማጠናከርዋ፣ እና የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የመጨረሻ ዋልታና ማገር የሆነውን ሕዝባዊ የመከላከያ ሰራዊት ገንብታ በዓለም ሰላም የማስከበር ተልእኮ ቁጥር አንድ ተመራጭ ሆና ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ የሚያስጎመጅ ግስጋሴና እድገት በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች አልቀጠለም፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል በህዳሴ ጉዞ የተፈጠረውን የጠያቂ ሕብረተሰብ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች በወቅቱ ባለመመለሳቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞ ኢሕአዴግ የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የፈጠራቸውን ችግሮች ተንሰራፍተው በመቀጠላቸው ነው፡፡ በወቅቱ እነዚህ ችግሮች የለየው የቀድሞ ኢሕአዴግ ዳግም ጥልቅ ተሃድሶ ለማካሄድ ወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሕወሓት በስተቀር የቀድሞዎቹ ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደኢህዴን፣ የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ ባለማካሄዳቸው እንዲሁም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በቀድሞ ኢሕአዴግ አባል የነበረው እና የፌደራል መንግሥት እያስተዳደረ ያለው አካል በ27 ዓመታቱ የትግል እና የድል ጉዞ ማለትም፣ በልማቱም በጥፋቱም መላ አካሉን ተነክሮበት የነበረውን ሂደት፣ አይኑን በጨው ዓጥቦ በመካድ ዓለም የመሰከረለትን እድገት ከል ከማልበስ ባሻገር ፣ የተጀመረው የህዳሴው ጉዞ ተንገራግጮ የኋሊዮሽ ለመመለስ በመፍጨርጨር ላይ ይገኛል፡፡

ፋሽሽታዊ ወታደራዊ ደርግ ሕዝቡ ታግሎ ያመጣውን ለውጥ በጉልበት በመቀማት “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም” ብሎ መንበረ ስልጣኑ በተቆጣጠረበት ማግስት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን በቀይ ሽብር በየአደባባዩ ረሽኖና ጨፍጭፎ አገሪቱ የደም እንባ እንድታነባ አደረጋት፡፡ ባጭሩ ደርግ ያደረሰው ግፍና ሰቆቃ በዋነኛነት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በተለይም አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ያለው የቀይ ሽብር ሰላባ የሰማእታት መታሰቢያ ሙዝየም ልብ ይሏል፡፡ አሁን የፌደራል ስልጣን ተቆጣጥሮ ያለው አካልም፣ “አካታችነት፣ ፍቅር፣ አብሮነት፣ አንድነት” ወዘተ በሚሉ ቃላት፣ ሕዝብን እያማለለ ሳይውል ሳያድር፣ ከሶስት ሚልዮን በላይ ሕዝብ ተፈናቀለ፣ በሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች በፖለቲካዊ እምነታቸውና በማንነታቸው ብቻ በየእስርቤቱ ታጎሩ፡፡ በዓለም ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ፣ የሰው ልጅ በድንጋይ ተወግሮ እንዲሁም በአደባባይ ተዘቅዝቆ የሞተበት አረሜናዊ ተግባርም ተፈፀመ፣ ብሔር ተኮር ጥቃት በሰፊው ተካሄደ፣ ዜጎች በጠራራ ፀሓይ እየታፈኑ የገቡበት የማይታወቅበት ሁኔታ ተፈጠረ፣ ሕዝብ ለሕዝብ እንዳይገናኝ አውራ መንገዶች ተዘጉ፣ ባጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈፀመው ግፍ ዐይነቱና ብዛቱ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባይሆንም ታሪክ መዝግቦታል እና እነዚህን አረሜናዊ የጭካኔ ተግበራት የመሩና በአስፈፃሚነት የተሰለፉ ሁሉም መሪ ተዋንያንም ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡

ባጭሩ የፌዴራል መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ ስልጣን ቀምቶ፣ ከትግራይ ክልል በስተቀር የሁሉንም የክልል መስተዳድሮች በጉልበት አፍርሶ የራሱን ምስለኔዎች ተክቶ አገራችን ሰላም ርቋት፣ የስርዓት አልበኛ፣ የጎቦዝ አለቆችና ጠመንጃ ነካሾች መፈንጫ ሆናለች፣ ቢባል ማጋነን ሳይሆን መሬት ላይ ያለው እውነታ መግለፅ ነው፡፡

የፌደራል መንግሥቱ ኢትዮጵያ ክብሯና ነፃነቷ በሚያዋርድ መልኩ የአገሪቱን የፖሊሲ ነፃነት አሽቀንጥሮ ጥሎ ሁሉም የአገሪቱ መግቢያ በሮች በርግዶ ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የልማት ምሶሶ የሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ አየር መንገድ፣ የስኳር ፋብሪካዎችን ጨምሮ በርካታ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ የልማት ተቋማት፣ እንደ ተራ ሸቀጥ እንዲቸበቸቡ ለሽያጭ አቅርቦአቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ሲባል የተጀመረ ነው፣ በቀጣይ አስር ዓመታትም አይጠናቀቅም፣ በማለት የኢትዮጵያን እድገት የሚወስነውና እያንዳንዱ የኢትዮጵያዊ ዜጋ አሸራ ያረፈበትን ይህንን ግድብም ዓይኑ ሳያሽ በማን አለብኝነት ለድርድር አቀረበው፡፡ ይህንን ክህደቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማይቀበለው በተገነዘበበት ሰዓት ደግሞ፣ ደሮን ሲያታልሏት እንደሚባለው የግድቡ ተቆርቋሪ መስሎ አዛኝ ቅቤ አንጓች ሆኖ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎቹ ነጋጠባ የአዞ እንባ ልፈፋውን ተያይዞታል፡፡ ይህንን እያደረገ ያለውም የተዘፈቀበትን ችግር ለመሸፋፈንና ኢትዮጵያውያን በየአቅጣጫው እያካሄዱትን ያለውን ትግል በማደብዘዝ አጀንዳ ለማስቀየስ የተጠነሰሰ ሴራ ነው፡፡ በአጠቃላይ የፌደራል መንግሥቱ ከቆዩት የአገራችን ኢትዮጵያ ወዳጅ የጎረቤት አገሮች ጋር አጋጭቶ፣ ከልማት አጋሮቻችንም አራርቆ የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት ከማይመኙት፣ የቅርብና የሩቅ አገራት ያልተቀደሰ ግንኙነት መስርቶ፣ አገራችን ባለፉት 27 ዓመታት የገነባችው አወንታዊ ገፅታና የነበራት ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ተሰሚነት ተሽመድምዶ ደብዛው እንዲጠፋ አድርጓል፡፡

ተጠቃልሎ ሲታይ ልማት ሳይሆን ተመፅዋችነትና ልመናን መርህ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ይህ አካል፣ የአገራችን ኢኮኖሚ መቀመቅ እያስገባው ይገኛል፡፡ ይኸውም በቀድሞ ኢሕአዴግ ዘመን ከፍተኛ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ሲጎርፍላት የነበረችው አገራችን ይህ ሓይል ወደ ስልጣን ከመጣበት ማግስት ጀምሮ ማለትም በአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ 17 ነጥብ ስድስት በመቶ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ቀንሷል፡፡ የገቢና የውጭ የንግድ ሚዛን በከፍተኛ ሁኔታ ከመዛባቱ ባሻገር ወደ ውጭ የምንልከው የምርት መጠንም 48 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ ቁጠባ ተዳክሞ ግብር የመሰብሰብ አቅምም ቁልቁል በመውረድ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገራችን 52 ነጥብ 3 ቢልዮን ዶላር የእዳ ቁልል አለባት፡፡ ይህም ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዓመታዊ ምርት 59 ከመቶ መሆኑ ነው፡፡ በሚያዝያ ወር 2012 ዓ.ም.፣ የአገሪቱ የዋጋ ንረትም 26 ከመቶ ደርሷል፡፡ የስራ አጥነት ቁጥሩ በመጨመር ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ያለው የስራ አጥ ቁጥር 19 በመቶ መድረሱ የኢኮኖሚ ሙሁራን በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡

ባጭሩ የፌደራል መንግሥቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በማንአለብኘት የአገራችን አገራዊ ክብርና ጥቅም በስውር እና በግላጭ ለባዕድ ሓይሎች አሳልፎ ከመስጠት ባሻገር የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ ስልጣን ቀምቶ አምባገነን መሆኑን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው አሳይቷል፡፡ ስለዚህ የፌዴራል መንግሥቱ በጀመረዉ አካሄድ ከቀጠለ የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ እንደሚሆን ንፁህ ህሊና ላለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም፡፡

የተከበርክ የትግራይ ሕዝብ!!

አፋኙ የደርግ ስርዓት ለማስወገድ፣ ታሪክ ለዘለአለም የሚዘክረውን አኩሪ ተግባር ፈፅመሃል፡፡ ባጭሩ የልብህ ስላደረግክ፣ የምታፍርበት ሳይሆን የምትኮራበት የድንቅ ገድል ባለቤት በመሆንህ ሁሌም ክብርና ሃሴት ሊሰማህ ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው ለከፈልከው ወደር የለሽ መስዋእትነትም ከማንም ካሳ አልጠየቅክም፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም የተለየ ጥቅም አላገኘህም፡፡ ሆኖም ከማንም በላይ ሰትመኘው የነበረው ሰላም፣ ደምህና አጥንትህን ገብረህ ባሰፈንክበት ማግስት፣ በጥረትህና በላብህ ብቻ የግንቦት 20 ፍሬዎች ተቋዳሽ ሆነሃል፡፡ በመሆኑም በግብርና የተሰማራው ሕዝባችን ከረሃብና እንግልት ደረጃ በደረጃ እየተላቀቀ የአቅሙን ያህል ሀብትና ንብረት ቋጥረዋል፡፡ በመቋጠርም ይገኛል፡፡ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ባሳየኸው ድንቅ ተግባር ለምድራችን ተምሳሌት በመሆን ዓለምአቀፍ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጀው ሕዝባችንም የልማቱ ተቋዳሽ ሆነዋል፡፡ ባጠቃላይ ሕዝባችን መንገድን ጨምሮ በመሰረተ ልማት ዘርፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ካስከፊ ድህነት ባለመላቀቃችን ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን ሊሰመርበት ይገባል፡፡

የትግራይ ሕዝብ በትጥቅ ትግሉም ይሁን ባለፉት 27 ዓመታት ላበረከትከው አስተዋፅኦ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ክዶ ጥላሸት ቀብቶ፣ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት እና ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ይጠበቅ፣ የህግ የበላይነት ይከበር ስላልክ ብቻ ብሔር ተኮር ጥቃት፤ እስራት፣ እንግልት፣ መድልዎ፣ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ፈጽሞብሃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሉአላውነትህ መገለጫ የሆነውን 6ኛው ዙር ምርጫ አካሂዳለሁ ስላልክ ብቻ ትጨፈለቃለህ፣ እናቶች ተጠንቀቁ ደም ይፈሳል በማለት አስፈራርቶሃል፡፡ ሆኖም የራስን የማስተዳደር ጉዳይ ለማንም አሳልፈህ እንደማትሰጥ፣ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ መሆኑ የትምክህት ሓይሎችም አበጥረው ያውቁታል፡፡

በአጭሩ የትምክህት ሓይሎች አሁንም ህልውናህንና ማንነትህን ለማጥፋት የማይፈነቅሉት ድንጋይና አለት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጎን ተሰልፈህ ያከሸፍካቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሴራዎች፣ አሁንም አንድነትህ እንደብረት አጠንክረህ እንደምትመክታቸው አያጠራጥርም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ኮረና ቫይረስ፣ የበረሃ አንበጣ እና የአሜሪካ ባርኖስ በመመከት ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ በግንቦት 20 የተጎናፀፍካቸውን ዘርፈ ብዙ ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ ባአጠቃላይ በተሰማራህበት የስራ መስክ በተለይም የ2012/13 ዓ.ም. የአዝመራና ሌሎች የክረምት ወቅት ስራዎችን ለማሳካት እንደምትረባረብ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ይተማመናል፡፡

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የፌደራሊስት ኃይሎች!

የማንነታችን መገለጫ የሆነው ሕገ-መንግሥታዊ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን በመፈራረስ ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ ወደ ባርነት የሚመልሰንን አሃዳዊ የግዛት አንድነት ከመቃብር አውጥቶ ዳግም ለመመለስ ሩጫው ተጧጥፏል፡፡ ነገር ግን ይህ እውን እንደማይሆን የጋራ ድምፃችን የምናሰማበት ወቅት አሁን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የፌዴራል መንግሥቱ የትግራይ ሕዝብና ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቱን፣ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ለማጋጨት የሸረበውን ሴራ እና ያሰራጨው ሓሰተኛ የበሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳ እንዲከሽፍ የበኩላቹሁን ድርሻ ስላበረከታቹሁ፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ስም ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የፖለቲካ ፓርቲ፣ መሪዎችና ሙሁራን!

አገራችን ኢትዮጵያ ገደል አፋፍ ላይ መድረሷ በገሃድ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የፌደራል መንግሥቱ፣ የኮሮና ቫይረስ ሰበብ አድርጎ፣ የስልጣን ዘመኑ ለማራዘም ላይ ታች በማለት ላይ ነው፡፡ በእርግጥ የኮሮና ቫይረስ አደገኛና ገዳይ በሽታ ነው፡፡ ለዚህም ነው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት አስቀድሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ኮረና ቫይረስን በመመከት ላይ ያለው፡፡ ስለዚህ ኮሮና ቫይረስን በጋራ እየመከትን ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በጋራ እንድንንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የተከበርክ የኤርትራ ሕዝብ!

በቅድሚያ ከ30 ዓመታት መራራ ትግል በኋላ ነፃነትህ ለተጎናጸፍክበት 29ኛው ዓመት ግንቦት 16፣ እንኳን በሰላም አደረሰህ! አደረሰን! እያልን፣ ተጀምሮ የነበረውንና በሁለቱ አገር መሪዎች ግልፅ ያልሆነ ግንኙነት ሳንካ የገጠመውን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩልህ አስተዋፅኦ እንድታደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ የዓለም-አቀፍ ማህበረሰብ!

በፈጣን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ የእድገት ምህዋር ገብታ የነበረችውና ተስፋ ተጥሎባት የነበረችው ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት አልባ የመሆን ዳር ላይ ደርሳለች፡፡ ኢትዮጵያ መበታተን ማለት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ እና የቀይ ባህር አካባቢ የትርምስ ቀጠና በማድረግ፣ ከ60 በመቶ በላይ የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ እንዲገታና ያሸባሪዎች መፈንጫ እንዲሆን መፍቀድ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ተረድታችሁ ለጋራ ጥቅም ሲባል የመፍትሔ አካል እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም ታሪክ ራሱ ይደግማል እንደሚባለው፣ የፌደራል መንግሥቱ እንደ ወታደራዊ ደርግ አምባገነን መሆኑ እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከአሁን በኋላ፣ ኢትዮጵያ ዳግም የብሔርና ብሔረሰቦች እስርቤት ፈፅሞ አትሆንም! ራስን በራስ የማስተዳደር መብትም በማንም ምድራዊ ሓይል እንደማይነጠቅ ወዳጅም ጠላትም ሊያውቅ ይገባል፡፡

አሁንም መስመራችንን አፅንተን እንመከታለን!!
ዘላላማዊ ክብር ለትግሉ ለወደቁ ታጋዮች!!
የግንቦት 20 ትሩፋቶች ወደላቀ ከፍታ እናሸጋግራለን!

የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መቐለ፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ