Ethiopia Zare's weekly news digest, week 39th, 2012 Ethiopian calendar

ከግንቦት 24 - 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሠላሳ ዘጠነኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከግንቦት 24 - 30 ቀን 2012 ዓ.ም.) ያሳለፍነውን ሳምንት በጨረፍታ የምናስቃኝበት በዛሬው የሳምንቱ ቅኝታችን አንኳር አንኳር ዜናዎች ውስጥ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በኦነግ ሸኔ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በሕወሓት የሚታገዙ ስለመኾኑ መገለጹ አንዱ ነው። ከወታደራዊ እገዛ ጋር በተያያዘ በይፋ የሕወሓት እጅ አለበት በሚል የገለጸበት ሰሞናዊ አነጋጋሪ ወሬ ነበር።

ባሳለፍነው ሳምንት ሌላው አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ ደቡብ ሱዳን ለግብጽ ለወታደራዊ ግልጋሎት የሚውል ቦታ ሰጠች የሚለው ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ደቡብ ሱዳን ከደሙ ንጹሕ ነኝ ብላ ዘገባውን አስተባብላለች። ዓለም በኮሮና ቫይረስ በምትታመስበት በዚህ ወቅት ጾታዊ እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች የመበራከታቸው ጉዳይ አሳዛኝ ኾኗል። በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ወራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። እንዲህ ያለው ዜና ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጐልተው የታዩበትና ቁጣን እየቀሰቀሰ ያለ ጉዳይ ኾኗል።

ኢትዮጵያ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም አምስት ቢሊዮን የሚደርሱ ችግኞችን ለመትከል በይፋ የችግኝ ተከላ መርኀ ግብሩ የተጀመረበት ሳምንት ነው። ይህ የችግኝ ተከላ መርኀ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዋሳ ተጀምሯል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች የበረከቱበት ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺሕ በላይ መድረሱ የተረጋገጠበት ኾኗል። የሟቾች ቁጥርም እየጨመረ በመምጣቱ፤ አሳሳቢ ከተባለ ደረጃ ላይ ተደርሷል። አዲስ አበባ ደግሞ ወረርሽኙ በብርቱ እያጠቃት ያለች ከተማ መኾንዋንም ቀጥላለች።

የህዳሴ ግድቡ አሁንም መነጋገሪያ ጉዳይ ነው። እንደ ግብጽ ሁሉ፤ ሱዳንም የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ሊፈጸሙ ይገባል ያለችውን በመጥቀስ ለተባበሩት መንግሥታት አቤት ማለቷ የተሰማው በዚህ ሳምንት ነው። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌቱን ለማስጀመር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሻለሁ በማለት አስታውቃለች።

ከሳምንቱ ዐበይት ኢኮኖሚያዊ ዜናዎች መካከል ኢትዮጵያ ለ2012 በጀት ዓመት የሚያስፈልጋትን አገራዊ ረቂቅ በጀት አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አግኝቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ነው።

በውሳኔው መሠረት ለ2012 በጀት 476 ቢሊዮን ብር እንዲኾን መወሰኑ ነው። ሌላው ቢዝነስ ነክ ዜና ደግሞ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ካሉ 16 ባንኮች እስካሁን ስምንቱ ሲገለገሉባቸው የነበሩ ዓርማዎቻቸውን በአዲስ መቀየራቸውን የሚመለከት ነው። በዚህ ሳምንት ሕብረት ባንክ ዓርማውን በመቀየር በአዲስ መለያ ብቅ በማለት ስምንተኛ ባንክ ኾኗል። በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የተጠናከሩት እንዲህ ያሉት የሳምንቱ አንኳር ዜናዎች በሚከተለው መልኩ ቀርበዋል። መልካም ንባብ!

አስነዋሪው አስገድዶ መድፈርና ወሲባዊ ጥቃት

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት በተለይ በዚህ ሳምንት ብዙዎችን አብዝቶ ያሳዘነ ጉዳይ ቢኖር በአስገድዶ መድፈርና ወሲባዊ ጥቃትን የሚመለከቱ ዘገባዎች በርከት ብሎ መሰማቱ ነው።

እንደ አንዳንድ መረጃዎች ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ቤት መቀመጥ፤ ወሲባዊ ጥቃት መጨመራቸውን ነው። ይህ ችግር በመላው ዓለም እየታየ ነው። ባለፉት ጥቂት ወራትም በኢትዮጵያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወሲባዊ ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፤ አባት ልጆቹን ስለመድፈሩ ጭምር የተዘገበበት ሳምንት ነው። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም ይህ ሁኔታ እያሳሰባቸው መኾኑን ጠቁመዋል። በተለይ ከአስገድዶ መድፈር ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ ከተዘገቡ ዜናዎች ውስጥ በትግራይ ክልል ኾነ የተባለው ይጠቀሳል።

በትግራይ ክልል በሦስት ወር ውስጥ 133 ሴቶች ዕድሜያቸው ከሦስት ዓመት ከዘጠኝ ወር እስከ 12 እና 13 ዓመት ዕድሜ የኾኑ ሴት ልጆች፤ በአባቶቻቸው፣ አጎቶቻቸውና ወንድሞቻቸው ተደፍረዋል ይላል። የዘንድሮው 133 ሕፃናት ሲደፈሩ ባለፈው ዓመት ደግሞ 560 ሴቶች በትግራይ ክልል መደፈራቸውን ያብራራል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በትግራይ ሓውዜን ከተማ አንዲት የስድስት ዓመት ታዳጊ በፖሊስ አባል አሰቃቂ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባት ገልጿል። ይህንን መረጃ የሰጡት የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል ናቸው።

በዚህ ዓመት መባቻም በላዕላይ አድያቦ ዓዲ-ዳዕሮ ከተማ አንድ የፖሊስ አመራር 50 ሴቶች በተለያየ ጊዜ ደፍሮ፤ ወንጀሉ በሕዝብ ሲጋለጥ፤ በስድስት ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቅ በመደረጉ፤ ትልቅ ሕዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሶ እንደነበር አቶ ነብዩ አስታውሰዋል።

አቶ ነብዩ አያይዘውም ሕዝባችን በክልሉ የበላይ አመራሮች አይዞህ ባይነት የወሲብ ጥቃት ጨምሮ፤ ሁሉም ዐይነት በደል በገዛ ሕዝባቸው ላይ የሚያደርሱ ኃላፊነት በማይሰማቸው የጸጥታ አባላትና አመራሮች አጥብቆ ሊታገላቸው እንደሚገባ ነው።

“የፌዴራል መንግሥትም፤ ይህ በትግራይ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግፍ የማስቆምና አጥፊዎቹን ለሕግ የማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱ መወጣቱን አጠናክሮ ይቀጥል” ያሉት አቶ ነብዩ፤ በሴት እኅቶቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጾታዊ ጥቃት አጥብቀን እንቃወማለን፤ አጥፊዎችም በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡም ብለዋል።

በሳምንቱ ከወሲብ ጥቃት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሴቶች መጠለያ ጥምረት ምክትል ሰብሳቢ የኾኑት ወ/ሮ ማኅሌት ኃይለማርያምም ለዋልታ ቴሌቪዥን እንደገለጹት፤ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶችና ሕፃናትን የሚቀበሉ መደበኛ መጠለያዎች፤ በኮሮና ምክንያት አዳዲስ ኬዞችን መቀበል በማቆማቸው በርካታ ዜጎች ተቸግረዋል።

አሁን ላይ አዳዲስ ኬዞችን ከሚቀበል ለስድስት ወር የሚቆይ መጠለያ በቅርቡ መዘጋጀቱን የገለጹት ወይዘሮ ማኅሌት፤ በመጠለያው እስከ አሁን 27 የሚደርሱ በጾታዊ ጥቃት፣ በአስገድዶ መድፈር፣ ልጅ በመካድና በባላቸው ጥቃት የተፈጸመባቸው ሚስቶች ተቀብሎ እያስተናገደ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በአባቶቻቸው የተደፈሩ የ14 እና የ17 ዓመት ሕፃናትን እንደምሳሌነት የጠቀሱት ምክትል ሰብሳቢዋ፤ ላላስፈላጊ ውርጃ ተጋልጠው ሽንታቸውን መቆጣጠር የማይችሉበት ደረጃ ደርሰው እንደነበር አመልክተዋል። በተለይ የ17 ዓመቷ ሕፃን፤ አባትየው የአደንዛዥ እፅ ጭምር እንድትጠቀም ማድረጉን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የጾታዊ ጥቃቶች ዐይነትና መልካቸውን እየቀየሩ መምጣታቸውንም በመግለጽ የሁኔታውን አሳሳቢነት አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ጾታዊ ጥቃት መበራከት አንዱ ምክንያት፤ የዚህ አስነዋሪ ተግባር ፈፃሚዎች ተመጣጣኝ የኾነ ፍርድ አለማግኘታቸው ነው። የእስር ቅጣቱ አነስተኛ መኾኑም ይጠቀሳል። ከሰሞኑ በአማራ ክልል ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ወሲባዊ ጥቃት የፈጸመ አባት፤ የተሰጠውም ፍርድ ይህንን ያመለክታል። ጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የተፈጸመ ወሲባዊ ጥቃት ነው። አባቴ ብላ አምና ከጎኑ የኾነችውን የ13 ዓመት የእንጀራ ልጁን፤ በሽጉጥ በማስፈራራት አስገድዶ እንደደፈራት ታውቆ የተመሠረተ ክስ፤ ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤት የ11 ዓመት እስራት ፈርዶበታል።

የድርጊቱን አስነዋሪነት በመግለጽ ጥፋተኛነቱን በማሳየት የዓቃቤ ሕግን አንድ ማክበጃ በመቀበል፤ ተከሳሽ የስምንት ልጆች አባት በመኾኑና ከአሁን በፊት ሪከርድ ባለመኖሩ፤ ሁለት ማቅለያዎችን ፍርድ ቤቱ በመያዝ የተሰጠ ፍርድ ነው ተብሏል። መረጃውን የሰጠው የጠገዴ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን፤ ወንጀሉ ተከሳሹንም ሆነ ሌሎችን ያስተምራል በሚል ተከሳሽ እጁ ከተያዘበት ጀምሮ የሚታሰብ የ11 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ግንቦት 21 ቀን 2012 ወስኗል ይላል። (ኢዛ)

ኦነግ ሸኔና የሕወሓት ጥምረት

ከሳምንቱ አነጋጋሪ ዜናዎች ውስጥ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ጸጥታና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ዙሪያ የተሰጠው መግለጫ ነው። መግለጫው በክልሉ በዝርፊያ በግድያና በተያያዥ ወንጀሎች የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የሚያመክት ቢኾንም፤ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ግን፤ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ ቡድኖች የሚፈጥሩት ውንብድና በሕወሓት የታገዘ ስለመኾኑ መጠቀሱ ነው።

የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮምሽነር ግርማ ገላን በግልጽ እንደተናገሩት በኦሮሚያ ክልል ኦነግ ሸኔ የሚፈጽማቸው ጥቃቶች፤ ከሕወሓት ጋር በመቀናጀትና በመተባበር የሚሠራ መኾኑን በመግለጽ፤ ከኦነግ ሸኔ ጀርባ ሕወሓት መኖሩን ጠቁመዋል። ለዚህም መረጃ ያለ መኾኑን የገለጹት ምክትል ኮምሽነሩ፤ በርከት ያሉ የሕወሓት ታጣቂዎች ከኦነግ ሸኔ ጋር ተደባልቀው እየተንቀሳቀሱ ስለመኾናቸው አመልክተዋል።

ለዚህም የሰጡት መረጃ፤ ከሥልጠና ቦታ ጠፍተው የመጡ ወጣቶችን ማን እንዳሠለጠናቸው እና ተልዕኮ እንደሰጣቸው በግልጽ የተናገሩ መኾናቸውን ነው። በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ላይ እጅግ በጣም በርከት ያሉ የሕወሓት ሠራዊቶች ከኦነግ ሸኔ ጋራ በመደባለቅ እንቅስቃሴ ላይ እንዳሉ ሙሉ መረጃ አለን ብለዋል ምክትል ኮሚሽነር ግርማ።

ፖሊስ ሕግን የማስከበር ሥራውን ሁሉንም በእኩል ዓይን በማየት እየሠራ መኾኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ “ፖሊስ ሕግን የማስከበር ሥራውን አንድም ቀን አቅቶት አያውቅም፤ አሁን መውሰድ የጀመርናቸው እርምጃዎች ከምንጊዜውም በላይ አጠናክረው ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲህ ያለውን መግለጫ በሰጡበት ወቅት በተለያዩ ግድያዎች የጠረጠራቸውን 48 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ገልጸዋል። እነዚህ ተጠርጣሪዎች ከኦነግ ሸኔና “አባ ቶርቤ” በሚል ራሱን ከሚጠራው ቡድን አባላት ጋር ግንኙነት ያላቸው ስለመኾኑ ተነግሯል። ይህ የክልሉ መግለጫ ከተሰጠ በኋላ ግን፤ ከሕወሓት የተሰጠው መግለጫ፤ የተባለው ነገር ሐሰት መኾኑን የሚገልጽ ነው።

እንደ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ፤ ከለውጡ በኋላ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች እና ጥቃቶች ከጀርባ ያሉ አካላት አሉ ተብሎ የሚነገረውን በይፋ ያወጣ ነው ብለዋል። (ኢዛ)

ደቡብ ሱዳን ለግብጽ ወታደራዊ ጣቢያ ሰጠች መባሉና ያስነሳው አቧራ

ከሰሞኑ አነጋጋሪ የነበረው ሌላው ዜና፤ ደቡብ ሱዳን ለካይሮ ወታደራዊ ጣቢያ ሰጠች በማለት በአንድ የደቡብ ሱዳን የመረጃ ምንጭ መገለጹ ነው። ይህ ዜና ከተናፈሰ በኋላ ብዙዎችን ያነጋገረ ሲሆን፣ የደቡብ ሱዳንን መንግሥት ከጁባ እና ከአዲስ አበባ ተከታታይ መግለጫ እንዲሰጥ ያስገደደም ነበር። መጀመሪያ ከጁባ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ የተናፈሰው ወሬ ፍጹም የተሳሳተ መኾኑን በመግለጽ ነው። ቁራጭ መሬትም አልሰጠሁም ብሎም አስታውቋል። አዲስ አበባ ያሉት አምባሳደርም ዜናውን አስቀያሚ ዓላማ የያዘ መኾኑን በመግለጽ፤ ከደሙ ንጹሕ ነን ብለዋል።

አምባሳደሩ ጄምስ ፒታ ሞርጋን ለተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፤ ደቡብ ሱዳን ለሌሎች አገራት መሬት አትሰጥም፤ በተለይም የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር እንደማትፈጽም በመናገር፤ ወሬው የተነዛው በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል ልዩነት ለመፍጠር በሚጥሩ አካላት ነው በማለት ሁኔታውን አስተባብለዋል። አያይዘውም እነዚህ ኃይሎች ደቡብ ሱዳን እንደዚህ ያሉ ነገሮች እንዲከሰቱ እንደማትፈቅድ ማወቅ ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ዐይነቱን ወሬ በቁም ነገር መውሰድ የለባቸውም በማለት፤ የመንግሥታቸውን አቋም የገለጹት አምባሳደሩ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትስስር ጠንካራ እንደኾነም አስታውቀዋል።

“ከዚህ የሐሰት ዜና በስተጀርባ ያለው ዓላማ ትኩረት በማግኘት፤ ድጋፍ ማሰባሰብ ነው” በማለት፤ በዚህ ዜና ኢትዮጵያ ሥጋት አይግባት ብለዋል። የደቡብ ሱዳን ይፋዊ መግለጫ ላይም ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ባለውለታ መኾኗን አውስቶ፤ እንዲህ አናደርግም የሚል መልእክት አስተላልፈዋል። (ኢዛ)

የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት የመጨረሻ ምዕራፍ

በመጪዎቹ የክረምት ወራት የህዳሴ ግድብ ውኃ መያዝ እንደሚጀምርና በመንግሥት የተሰጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ልዩ ልዩ የግንባታና የኃይድሮሊክ ስትራክቸር ሥራዎች ተገባደው፤ ለውኃ ሙሌት ሥራው ዝግጅት እየተደረገ ስለመኾኑ በሳምንቱ ዘገባዎች መካከል አንዱ ነው።

በመጪዎቹ የክረምት ወራት የውኃ ሙሌቱን ለማከናወን የግድቡ ግንባታ 560 ሜትር ላይ መድረስ ስለሚገባው፤ ይህንኑ የማከናወን ሥራ እየተገባደደ መኾኑን ያስታወቁት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሃሮ፤ የግድቡን ጎንና ጎን ወደ 572 ከፍታ ላይ ለማድረስ ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው። እነዚህ የግንባታ ሥራዎችም በአሁኑ ሰዓት እየተጠናቀቁ ሲሆን፤ ከውኃ ማስተላለፊያ ጋር የተገናኙ የብረታ ብረትና የአሸንዳ ሥራዎም በመፋጠን ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከክረምቱ በፊት የቅድመ ሥራዎችን በማከናወን ክረምቱ እንደገባ የውኃ ሙሌት ሥራውን ማከናወን የሚቻልበት ዝግጅት መደረጉን ያወሱት ሥራ አስኪያጁ፣ ኃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ግንባታው ላይ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠ በመኾኑ፤ ከመጀመሪያው ውኃ ማቆር ሥራ ጋር የተገናኙት የዩኒት 9 እና 10 ሥራዎች በከፍተኛ ትኩረት እየተሠሩ መኾናቸውን ነው።

ከዚህም ጎን ለጎን ከቅድመ ኃይል ማመንጫ ጋር የሚያያዘው የጄኔሬተር ተርባይን በኮንክሪት የመሙላት ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ የጄኔሬተር ገጠማ ሥራዎችም በመከናወን ላይ መኾኑን ከዚሁ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል። የውኃ ሙሌቱን ዝግጅት በተመለከተም፤ ግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ቡድን በህዳሴው ግድብ ላይ ተገኝቶ ጉብኝት አድርጓል። (ኢዛ)

በትግራይ እስራት ያስከተለው ተቃውሞ

በሳምንቱ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዜናዎች መካከል አንዱ በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ የተቃውሞ ድምፆች ሳቢያ፤ የክልሉ መንግሥት እየወሰደ ነው የተባለው እርምጃ ይገኝበታል። በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ እንዳመለከተው በሰሞኑ የተቃውሞ ሰልፎች ተሳትፋችኋል የተባሉ ታፍነው እየተወሰዱ ነው። በዚህም ፍራቻ ያደረባቸው ወጣቶች እየሸሹ ነውም ብሏል።

የትግራይ ሕዝብ ከገበሬ እስከተማረው፤ ፍትሕ ሲጎድልበት፣ ጭቆና ሲያይልበት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን መግለጽ መቀጠሉን ዓረና ገልጿል። ዓረና 11 ሺህ ሕዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን ባሰማባት ኦራሪት ወልቃይት አካባቢ፤ ምክትል አስተዳዳሪ ጨምሮ ተቃውሞውን መርተዋል፣ አስተባብረዋል የተባሉ 340 ሰዎች ስለመታሰራቸውም ይጠቅሳል። የዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የኾኑት አቶ አምዶም ገብረሥላሴ በተለይ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፤ የትግራይ ሕዝብ ምሬቱን እየገለጸ መኾኑን ተናግረዋል።

በዋጅራት፣ በማይሐንሰን፣ ኦራሪት ወልቃይት፣ በሌሎች አካባቢዎችም የተስተዋሉት ተቃውሞዎችና ቁጣዎች፤ የትግራይ ሕዝብ በደሉ ከሚሸከመው በላይ እንደኾነበት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። በተለይ በኦራሪት ወልቃይት፣ በርካታ ሰዎች ተደብድበዋል፣ ቆስለዋል፣ ሌሊት የመኖሪያ ቤታቸው በር እየተሰበረ እየተወሰዱ ነው ያሉ ሲሆን፤ ወጣቱ በፍራቻ ከመኖሪያ ቤቱ ሸሽቶ በረሃ ስለመኾኑም አቶ አምዶም ለዚሁ ሚዲያ የሰጡት ማብራሪያ ያስረዳል።

ዓረና ሕወሓት እንደሚለው ይሄን የተቃውሞ ሰልፍ ባይጠራም፤ የሕዝቡ ጥያቄ ጥያቄያችን ስለኾነ እስከመጨረሻው ከሕዝቡ ጎን ነን በማለት ገልጸዋል። ሕወሓት በምርጫ እንደማያሸንፈን ያውቀዋል ያሉት አቶ አምዶም፤ ለዛ ነው አሁን በኮሮና ግርግር ሕዝብ በነፃነት ወጥቶ በማይመርጥበት ሁኔታ አሸነፍኩ ለማለት ምርጫ ይደረግ እያለ ያለው ሲሉ ተናግረዋል። ሕዝቡ ሕወሓት ያውቀዋል ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው ያመለክታል።

ከዚህም ሌላ በክልሉ በተካሔዱ የተቃውሞ ሰልፎች ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ሰዎች ስለመታሰራቸው በተለያየ አቅጣጫ የተገለጸ ሲሆን፤ በአንዳንድ ዞኖች ሰዎች ስለመታሰራቸው የሚያረጋግጡ ቢሆንም፤ ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ ግን ከመግለጽ የተቆጠቡበትን መረጃዎች ማስተላለፋቸው ግን ታውቋል።

በሌላ በኩልም በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ቆራሪት በተባለች ከተማ ነዋሪዎች ተቃውሞ ሰልፍ በማካሔዳቸው፤ ሰዎች እየታሰሩ መኾኑን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት በሁለት ቀናት ውስጥ ከ150 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል። የከተማው አስተዳደር በበኩሉ ታስረዋል ተብሎ የተገለጸው ቁጥር የተጋነነ መኾኑን ገልጾ፤ የሕዝብ ሰላም ለማወክ የሚሠሩ ሰዎች በመለየት ሕጋዊ የእርምትና እርምጃ እየወሰድን ነው በማለት መግለጹ፤ በክልሉ እየተካሔደ ነው የተባለውን እስርና አፈና ያረጋገጠ ነው አስብሏል። (ኢዛ)

የአምስት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ጅማሮ

ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም. በጀት ዓመት አራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ አድርጋለች። በወቅቱ በ2012 በጀት ዓመትም አምስት ቢሊዮን ችግኝ እንደምትተክል ተገልጾ፤ በዚሁ መሠረት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። በዚህ ሳምንት ደግሞ የአምስት ቢሊዮን የችግኝ ተከላው መረኀ ግብር በሳምንቱ አጋማሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዋሳ በመገኘት አስጀምረዋል። አጋጣሚው የኮሮና ወረርሽኝ የተከሰተበት ወቅት ኾኖ ተከላው በጥንቃቄ እንዲከናወን ማሳሰቢያ የተሰጠበትም ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዛፍ በደጃፍ” በሚል መርኀ ግብር ዜጐች ተከላውን በግቢያቸው እና በአካባቢያቸው እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በዚሁ መልእክት መሠረት የ2012 የአረንጓዴ አሻራ በይፋ መጀመሩን ከአዋሳ መልስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለቤታቸው ከቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው እና ከልጆቻቸው ጋር በመኾን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የችግኝ ተከላ አካሒደዋል።

ወረርሽኙን መከላከል እንዲቻል ሕብረተሰቡ በ“ዛፍ በደጃፍ” መርኀ ግብር በመሳተፍ ችግኞቹን በግቢው እና በመንደሩ በመትከል እንዲሳተፍ ጥሪ አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት በተካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርኀ ግብር በሺዎች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል ችለዋል። ባለፈው ዓመት ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 84 በመቶው እንደጸደቁ ተገልጿል። (ኢዛ)

ለ2013 በጀት ዓመት የ476 ቢሊዮን ብር ረቂቅ ጸደቀ
በ89 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሔደው 84ኛ መደበኛ ስብሰባው የ2013 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት 476 ቢሊዮን ብር እንዲኾን ውሳኔ አሳልፏል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀው ረቂቅ አዋጅ መሠረት ለ2013 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት በጀት ከ2012 በጀት ዓመት ጸድቆ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር፤ ከ89 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መኾኑን ያመለክታል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት፤ በ2013 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች 133 ነጥብ 32 ቢሊዮን ብር፤ ለካፒታል ወጪዎች ደግሞ 160 ነጥብ 32 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 176 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር፤ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 6 ቢሊዮን በጀት እንዲያዝ ውሳኔ አሳልፏል። በ2013 በጥቅሉ የተያዘው በጀት 476 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ኾኗል። የቀጣዩ ዓመት በዚህ ስሌት መሠረት እንዲኾን የቀረበውን ረቂቅ በጀት የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ ከተወያየበት በኋላ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተላለፈው የ2013 ረቂቅ በጀት ከቀዳሚው አንፃር ሲታይ በ89 ቢሊዮን ጭማሪ እንዳለው ከማሳየቱም በላይ፤ ለመደበኛ፣ ለካፒታል እና ለክልሎች ድጐማ የተያዘውም በጀት በተለያየ መጠን ጭማሪ የታየበት ኾኗል።

ለ2012 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥቱ በጀት ኾኖ ጸድቆ የነበረው 386 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም። በወቅቱ ለመደበኛ ወጪ የተያዘው በጀት 109 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር ነበር። ለካፒታል በጀት ደግሞ 130 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞ እንደነበር አይዘነጋም። ለክልሎች ድጐማ በጀት ደግሞ 140 ነጥብ 77 ቢሊዮን ብር ነበር። (ኢዛ)

የጡረታ መቀጮና ወለድ መነሳት

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተላለፉ ውሳኔዎች መካከል፤ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ማስፈፀሚያ ደንብ ይገኝበታል። ይህ ረቂቅ ደንብ ወረርሽኙ በአገር ደረጃ በኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ፤ የግል ድርጅቶች ከሐምሌ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መጋቢት 2012 ዓ.ም. ድረስ ባልተከፈለ የጡረታ መዋጮ ላይ ሊከፈል የሚገባውን መቀጮና ወለድ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ የወሰነበት ነው።

የሚፈለግባቸውን ዕዳ ከከፈሉ በዕዳ ምክንያት የተያዙ ንብረቶችን ለድርጅቶቹ ለመመለስ የሚያስችሉ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ ቀርቦ፤ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ፤ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑ ታውቋል።

ከዚህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ሌላ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጡ የአስቸኳይ ጊዜ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ የተመለከቱ የትራፊክ ጥሰቶች በተፈጸሙ ጊዜ የሚጣሉ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ማስተካከያዎች በማድረግ፤ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር የተደረገ ለበረሃ አንበጣ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ላይ ሲሆን፤ በብድር የተገኘው ገንዘብ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ ከማስገኘቱ በተጨማሪ፤ ከወለድ ነፃና በረዥም ጊዜ የሚከፈል በመኾኑ፤ የብድር ስምምነት ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች መርቶታል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ባንኮችና የመለያ ዓርማ ቅያሬ ዘመቻ
ከ16ቱ የግል ባንኮች ስምንቱ ዓርማቸውን ቀይረዋል

በኢትዮጵያ በባንክ ኢንደስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲጠቀሙት የነበረውን መለያ ዓርማቸውን በመቀየር በአዲስ መለያ ብቅ ማለት የተለመደ ኾኗል። ሰሞኑንም ሕብረት ባንክ ላለፉት 22 ዓመታት ሲገለገልበት የቆየውን መለያ ዓርማ በመቀየር ስምንተኛው የግል ባንክ ኾኗል።

ለተሻለ አገልግሎትና በቀላሉ ባንኩን ለመግለጽ ታስቦ የተቀረጸው አዲሱ ዓርማ፤ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፤ አዲሱ የባንኩ መለያ ሕብረት ባንክ ከደንበኞቹ፣ ከአጋሮቹና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትስስር እንዲያንጸባርቅ ኾኖ የተቀረጸ ሲሆን፤ በሕብረትና በጋራ እድገት ላይ የተመሠረተ መስተጋብር ለመፍጠር ባንኩ የወሰደውን ቁርጠኝነትም የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።

ባንኩ ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ መሠረት፤ የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች አዲሱን የሕብረት ባንክ መለያ ዓርማ ለመሥራት ተወዳዳሪ የነበሩ መኾኑን ዓርማው ይፋ በተደረገበት ወቅት ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ ገልጸዋል። በጨረታ ውጤቱ መሠረት ስቱዲዮ ኔት የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ተመርጦ ዓርማው ሊሠራ መቻሉንም ገልጸዋል።

የሕብረት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ በበኩላቸው፤ አዲሱ መለያ መልእክትና ቀለም ብቻ ሳይሆን፤ አብረን ተባብረን ለሁላችንም የተሻለ ነገር ለመገንባት የምንገባው ቃልኪዳንም ጭምር ነው ብለዋል።

እንደ ሕብረት ባንክ ሁሉ ከዚህ ቀደም ስድስት ባንኮች በተመሳሳይ መንገድ በውጭና በአገር ውስጥ ኩባንያዎች ያሠሩዋቸውን አዳዲስ ዓርማዎች እየተጠቀሙባቸው ነው።

እስካሁን ለዓመታት ሲገለገሉባቸው የነበሩትን ዓርማዎች ቀይረው በአዲሱ ዓርማቸው መገልገል የጀመሩት ንብ ኢንተርናሽናል ባንከ፣ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ ዳሸን ባንክ እና ብርሃን ባንክ ሲሆኑ፤ ሕብረት ባንክም በዚህ ሳምንት በአዲሱ ዓርማው መጠቀም ጀምሯል።

ከእነዚህ ባንኮች ውስጥ ከብርሃን ባንክ እና ከኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በቀር ሌሎቹ ባንኮች ከ20 ዓመታት በላይ የተገለገሉበትን ዓርማ መቀየራቸውን ለማወቅ ተችሏል። ብዙዎቹ በውጭ ኩባንያ በማስጠናት ዓርማቸውን ገላጭ እንዲኾን በቀረበላቸው ምክረ ሐሳብ የቀየሩ ናቸው። ሕብረት ባንክ ዓርማ በመቀየር ስምንተኛ ባንክ ኾኖ መምጣቱ፤ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ 16ቱ ባንኮች ግማሽ ያህሉ ዓርማቸውን መቀየራቸውን ያሳያል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ