Ethiopia Zare's weekly news digest, week 40th, 2012 Ethiopian calendar

ከሰኔ 1 - 7 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አርባኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከሰኔ 1 - 7 ቀን 2012 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ታሪክ በተለዩ ሊታወሱ የሚችሉ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች የተወሰኑበት ነው ማለት ይቻላል። ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ላይ ውሳኔ መተላለፉ አንዱ ጉዳይ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ብዙ ሲያከራክር የነበረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዲራዘም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ያሳለፈውም ሳምንት ነው።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡትና በተለያዩ ጉዳዮች የመንግሥታቸውን አቋም ያሳወቁበትን ማብራሪያ የሰጡበት ነው። በዚህ ማብራሪያቸው የምርጫ ጉዳይ፣ የትግራይና የሕወሓት ወቅታዊ እንቅስቃሴ፣ የህዳሴ ግድብና የአገር ኢኮኖሚን በተመለከቱና በሌሎች ጉዳዮች ብዙዎችን ያስደመመ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሳምንቱ አነጋጋሪ የነበረው ሌላ ዜና ደግሞ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሒም በአንድ አገራዊ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ለፌዴሬሽኑ አባላት ጥሪ አስተላልፈው፤ እርሳቸው ግን ወደ መቀሌ ተጉዘው፤ ከመቀሌ ኃላፊነቴን ለቅቄያለሁ ማለታቸው ነው። ይህንንም ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዳዲስ አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ መርጧል።

የምርጫውን የመራዘም ውሳኔ ተከትሎ ኦፌኮ፣ ኦነግና ኢዴፓ የመረረ ተቃውሟቸውን በማሰማት ቀዳሚ ኾነዋል። ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ምርጫ የማራዘም ውሳኔን የፓርቲዎቹ አማራጮች ለተለያዩ ሚዲያዎች ፓርቲያቸውን ወክለው አስተያየት የሰጡት አመራሮች፤ መንግሥት ያልተገባ ተግባር ፈጽሟል ብለዋል። ምርጫውን ለማራዘም የተሔደበትም መንገድ አግባብ አልነበረም ብለው አስተያየት የሰጡ ሲሆን፤ ሁሉም በየፊናቸው በዚሁ ጉዳይ መግለጫ አውጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ጃዋር መሐመድን ያስጠነቀቀበት መግለጫም ከሳምንቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ዜናዎች ውስጥ የሚካተት ነው።

የህዳሴ ግድብና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተፋሰሱ አገሮች መካከል ያለው ውጥረት በዚህም ሳምንት በተለያዩ መንገዶች ትኩረት ስቦ የቆየየ ዜና ሲሆን፤ በቪዲዮ ኮንፈረንስም ውይይት እየተደረገበት ያለ ጉዳይ ኾኖ ሳምንቱን አሳልፏል። በመጨረሻ ላይ ከኢትዮጵያ የተሰጠው መግለጫ ግብጽ አሁንም እንቅፋት እየኾነች መኾኑን ነው። ግብጽ ለጦርነት እየተዘጋጀች ነው የሚለው ወሬ በብዙ እየተናፈሰ በመኾኑ፤ ከኢትዮጵያ ወገንም ከዚሁ አንጻር ምላሾች ሲሰጡ ሰንብተዋል። በተለይ የኢትዮጵያ መከላከያ ምክትል ኤታማዦር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ የሰጡት ቃለ ምልልስም ግብጽ እያደረገች ነው ለተባለው እንደምላሽ የሚታይ ኾኗል።

የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ጐልቶ የታየበትም ሳምንት ነው ማለት ይቻላል። በየዕለቱ ቁጥሩ እየጨመረ በመምጣቱ፤ በዚህ ሳምንት በየዕለቱ በርካታ ሰዎች መያዛቸው የተሰማበትና የተጠቂዎቹም ቁጥር ከ3 ሺህ በላይ የዘለለው በዚሁ ሳምንት ነው። ከሰሞኑ አነጋጋሪ ዜናዎች መካከል የቀድሞው ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሳሞራ የኑስ ከአንድ ሚዲያ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ተጠቃሽ ነው። ከሰሞኑ ሌላው አወዛጋቢ ሊባል የሚችለው ዜና የትግራይ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በክልል ደረጃ አካሒዳለሁ ማለቱና ከፌዴራል መንግሥት የተሰጠው ምላሽ ነው።

ኢኮኖሚያዊ ከኾኑ ዜናዎች መካከል የአፍሪካ የንግድ ቀጠና ሊጀመር መኾኑ አንዱ ነው። ሌላው ዐበይት ጉዳይ የ10 ዓመት የኢኮኖሚ ፕላን ይፋ መደረጉ ነው። ከሰባት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ አፈፃፀም የተሻለ ውጤት ያስመዘገበ መኾኑ የተገለጸበት ሳምንት ነው። የሳምንቱን አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች እንደሚከተለው በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል ተጠናክረው ቀርበዋል። መልካም ንባብ!

የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተቃውሞአቸው

በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ሊካሔድ የነበረውን ምርጫ መራዘምን ተከትሎ ብዙ አከራካሪ ሙግቶች ሲቀርቡ ነበር። ከወቅታዊው ችግር አንፃር ምርጫውን ለማራዘም ከመንግሥት አራት አማራጮች ቀርበው፤ ሕገ መንግሥት መተርጐም የሚለው ነጥብ ተለይቶ በዚሁ ጉዳይ ላይ ሲሠራ ቆይቶ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው እንዲራዘም እና የኮሮና ወረርሽኝ የአገሪቱ ሥጋት ኾኖ እስከቀጠለ ድረስ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተወስኗል።

ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀድመው ተቃውሞዋቸውን ያሰሙት የኦነግ፣ የኦፌኮና የኢዴፓ አመራሮች ኾነዋል። የድርጅቶቹ አመራሮች ለተለያዩ ሚዲያዎች የመንግሥትን ውሳኔ በመቃወም ከሰጡዋቸው አስተያየት በተጨማሪ፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ የፓርቲያቸውን አቋም የሚንጸባርቅ መግለጫም አውጥተዋል። በተለይ ኦነግና ኦፌኮ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በሕገወጥ መንገድ የመንግሥት የሥልጣን ጊዜ መራዘሙን አመልክተዋል። ይህ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ያሳደረባቸውን ሥጋት በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል። ድርጊቱ ሕገ ወጥና ሕግን ያልተከተለ፤ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን ከመጣሱም በላይ የአገሪቱን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥልም ነው የሚል እምነት እንዳላቸው በጋራ መግለጫ ላይ አንጸባርቀዋል።

“ከመጀመሪያውም ጀምሮ ሕገ መንግሥቱ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ማራዘም የማይፈቅድ መኾኑን ስንገልጽ ቆይተናል” ያሉት ኦነግና ኦፌኮ፤ በመኾኑም በጉዳዩ ላይ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረባቸውንም አስታውሰዋል። ኾኖም አማራጭ ሐሳባችን አልተደመጠም ይላሉ።

“መንግሥት ያቀረበውን አማራጭ በመቃወም ሌላ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ብናቀርብም፤ መንግሥት በተናጠል ውሳኔው ጸንተው የተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ካውንስል መርቶታል” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ካውንስሉም የመንግሥትን አቋም ከሚደግፉት ባለሞያዎች ጋር ብቻ የይስሙላ ውይይት ማድረጉን በመክሰስ፤ የተለየ ምልከታ ያላቸው ወገኖች የመደመጥ ዕድሉን ተነፍገዋል በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

ምርጫን ለማራዘም ምንም ዐይነት የሕገ መንግሥት መሠረት ሳይኖር አጠቃላይ ምርጫን ማንሳፈፍ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ የሚያስከትል እና ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ አዲስ የተመረጠ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይኖር፤ ማንኛውም መንግሥታዊ ውሳኔና ድርጊት ከሕገ መንግሥቱ የተጻረረ ነው። በግልጽ የተቀመጠውን የአምስት ዓመት የሥራ ዘመንን የሚጥስ ተግባር እንደኾነም በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) እና 58(3) እንዲሁም የምርጫ ሕጉ አንቀጽ 7 ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መደረግ እንዳለበት ይደነግጋል። የምርጫ ጊዜን ለማራዘም በር የሚከፍት ነገር የሚያሳይ መኾኑንም በማመልከት፤ ምርጫውን ለማራዘም የተለመደበት መንገድ ሕጋዊ አይደለም በማለትም ያላቸውን አቋም ገልጸዋል።

ስለሆነም የአካባቢያዊ እና የፌዴራል ምርጫን በተናጠል በአንድ ፓርቲ ብቻ የማራዘም ሥልጣንን አጥብቀው እንደሚቃወሙ በመግለጽ፤ “የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በዚህ መንግሥት ለሕዝብ የተገባው ቃል በመታጠፉ በቋፍ ላይ ያለውን የሕዝብ ቅራኔ የሚያባብስ ይኾናል” የሚለውንም ሥጋታቸውን ሳይገልጹ አላለፉም። “በመኾኑም ወደ አመጽ ሊያመራ የሚችል ሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሊቀሰቀስ እንደሚች ሥጋታችንን መግለጽ እንወዳለን” በማለት በጋራ መግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።

እንደ ኦነግና ኦፌኮ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ይፋዊ መግለጫ ያወጣው፤ አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)፤ “በተለመደ መንገድ የተለየ ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም! ሁሉን አቀፍ አገራዊ የውይይት መድረክ አሁኑኑ!” በሚል ርዕስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ተቃውሟል።

“የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ያለገደብ ለማራዘም የሰጠው ውሳኔ፤ በአገራችን የሕግ የበላይነት ዛሬም እንደትናንቱ ቦታ የሌለው መኾኑን አሳይቶናል” በሚል ተቃውሞውን ገልጿል። አብሮነት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማንኛውም ሕግ ያልተሰጠውን መብት ተጠቅሞ በሥልጣን ላይ የሚገኘውን መንግሥት የሥልጣን ዘመን ገደብ ለሌለው ጊዜ እንዲራዘም የሰጠው ውሳኔ፤ አገራችን ምን ያህል ወደ ለየለት አንባገነናዊ ሥርዓት እየተሸጋገረች ስለመኾኑ ማሳያ ነው በማለትም የእርሱን አተያይ አስፍሯል።

“የሰሞኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሁለት ዓመቱ የለውጥ ሒደት መክሸፍ የመጨረሻ ማሕተም ኾኖ አግኝተነዋል። ከእንግዲህ ከብልጽግና ፓርቲ አመራር ከ27 ዓመቱ አንባገነናዊ ሥርዓት የተለየ አዲስ የሚጠበቅ ለውጥ የለም” ያለው የአብሮነት መግለጫ፤ ውሳኔው አደገኛ መኾኑን አትቷል።

ይህንን ሰሞናዊ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ብልጽግና ፓርቲ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለሕዝብ ከገባው ቃል ኪዳን እና ከጠየቀው ይቅርታ በተፃራሪ አገሪቱን ወደ አደገኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የሚያስገባ ውሳኔ ኾኖ እንዳገኘው ጠቅሷል።

በዚህ ውሳኔ መሠረት አገሪቱ ወደፊት ለሚያጋጥማት ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ተጠያቂዎቹ ብልጽግና ፓርቲ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ብልጽግና ፓርቲ በሕገ-ወጥ መንገድ ሥልጣኑን ያለገደብ እንዲያራዝም ድጋፋቸውን የሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው በማለት አቋሙን ይፋ አድርጓል። የመግለጫውን መቋጫ የአገራችንን የወደፊት እድል ለመወሰን የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረክ በአስቸኳይ እንዲጠራ የሚያስችል ጫና ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እንዲያሳድር ጥሪዬን አቀርባለሁ ብሏል። አብዛኞቹ ፓርቲዎች ግን የምርጫውን መራዘም አግባብነት በተለያዩ መንገዶች የገለጹ ሲሆን፤ የተሻለ አማራጭ እንደሚኾን አመልክተዋል። (ኢዛ)

የኦሮሚያ ፖሊስ ጃዋርን ያስጠነቀቀበት መግለጫ

በዚህ ሳምንት በተሰሙ ዜናዎች የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ ነው። መግለጫው አቶ ጃዋር መሐመድን የተመለከተ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአቶ ጃዋር ጋር በተያዘ እንዲህ ያለ መግለጫ ሲወጣ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል።

መግለጫው አቶ ጃዋርን የሚያስጠነቅቅ ነበር። የማስጠንቀቂያው መነሻም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰላም እና መረጋጋትን ለማደፍረስ በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ከሚለጥፋቸው የተዛቡ መረጃዎች እንዲታቀብ የሚያስጠነቅቅ ነው። ማስጠንቀቂያው አቶ ጃዋር እስካሁንም ከሚለጥፋቸው ከእውነት የራቁ መረጃዎች በሕግ የሚጠየቅ መኾኑንም ያስታወቀበት ነው።

የኦሮሚያ ፖሊስ ወንጀልን ከመከላከል፣ የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ከማስከበር፤ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር የዘለለ ተግባር የሌለው መኾኑን የሚያመለክተው የኮምሽኑ መግለጫ፤ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ልዩ ኃይሉን በማደራጀት የሕዝቡ ሰላም እና የክልሉን ጸጥታ በማስጠበቅ ላይ እንደሚገኝም ያስታወቀበት ነበር።

ኾኖም የክልሉን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ አንዳንድ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሕዝብ መከታ የኾነውን ኃይል ስም በማጠልሸት የፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ መቻሉን የኮምሽኑ መግለጫ አመልክቶ፤ ስለኾነም ከአሁን በኋላ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን ስም የሚያጐድፉ ግለሰቦችንና ቡድኖችን እንደማይታገስ ያመለከተበት ነው።

ይህንንም ከአሁን በኋላ ማንኛውም ግለሰብ ወይንም ቡድን የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን ስም እና ዝና እንዲጐድፍ፤ እንዲሁም ለፖለቲካ ትርፍ እንዲጠቀምበት አንፈቅድም በማለት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮምሽን አስታውቋል።

እንዲህ ያለውን የኮምሽኑ መግለጫ ካወጣበት ምክንያት አንዱ፤ በዲንሾ ከተማ ተፈጽሟል የተባለው የአንድ ግለሰብ መያዝ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰራጨው አሉባልታ ሊገታ እንደሚገባ ፖሊስ ኮምሽኑ የገለጸ ሲሆን፤ በዲንሾ ከተማ የተፈጠረው ሁኔታ መነሻው የግለሰቦች ጸብ ሲሆን፤ ጉዳዩ በሕግ ተይዟል ተብሏል።

አንዳንዶች በተለይም አቶ ጃዋር ግን ከእውነታው ውጭ በፌስቡክ ገጹ ላይ የተዛባ መረጃን በመለጠፍ፤ ብዙዎችን የማሳት ተግባሩን የገፉበት በመኾኑ፤ ኮሚሽኑ በእንግሊዝኛ የተለጠፈውን እንዲሁም ሌሎች ተጨባጭ መረጃዎች ይዞ በሕግ አግባብ የሚጠይቅ ስለመኾኑ በዚሁ መግለጫው ላይ ጠቅሷል። (ኢዛ)

ሰሞናዊው ድርድርና አንደምታው

ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ዳግም ወደ ድርድር ቢመለሱም፣ በድጋሜ ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ለመሔድ እየተዘጋጀች ስለመኾኑ ተነግሯል። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግሥታት ከመውሰድ እንድትቆጠብና በድርድሩ እንድትገፋ ከማመልከቱም አንዱን ትምረጥ የሚል አንደምታ ያለው አቋሙን አንጸባርቋል። የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ግብጽ በታማኝነት በድርድሩ እንድትሳተፍ ጥሪውን ያቀረበው በዚህ ሳምንት ነበር።

እንደገና የተጀመረው የሦስቱ አገሮች ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው በሁሉም ተደራዳሪ አካላት መካከል መተማመን ሊኖር እንደሚገባ መግለጫው አመልክቶ፣ “ይሁንና የግብጽ አቀራረብ የሦስትዮሽ ድርድሩን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድና የውጭ ዲፕሎማቲክ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው” ብሏል።

ኢትዮጵያ የውኃ አሞላል ሒደቱ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳወቀችበት መግለጫ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህ እንዲሳካ የድርሻውን ይወጣ ብላለች። ዳግም የተጀመረው ድርድር በግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትንና ዓመታዊ አሠራርን በተመለከተ ብቻ ሊያተኩር እንደሚገባ ከማሳወቋም በላይ፤ ይህንንም የተመለከተ መመሪያና ሕግ አዘጋጅታ አቅርባለች ተብሏል። በሱዳን በኩልም ተመሳሳይ የራሷን አቋም የሚገልጽ ሰነድ አዘጋጅታ እንዳቀረበች የተገለጸ ሲሆን፤ ግብጽ ግን ድርድሩ አጠቃላይ የግድቡን የውኃ ሙሌት በተመለከተ ሊኾን እንደሚገባና ድርድሩም በአምስት ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ እንደሚገባው በመግለጽ የተለየ አቋሟን አንጸባርቃለች።

ኢትዮጵያ በተናጠል ውሳኔ የውኃ ሙሌት እንደማትጀምር ማረጋገጫ እንድትሰጣት ግብጽ የምትሻ ሲሆን፤ ይህንን ሐሳቧን የሚያሳይ አዲስ ሐሳብ ይዛ መምጣቷና ይህም እንደ ቅድመ ሁኔታ መታየት አለበት እያለች ነው። ይህ ጉዳይ ግን በኢትዮጵያ ወገን ተቀባይነት ባያገኝም ሦስቱ አገራት ውይይታቸውን ቀጥለዋል።

ሰሞናዊው ውይይት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ወገን የተሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው ደግሞ፤ የመጀመሪያው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የውኃ አሞላል የሚገዛበት መመሪያን በተመለከተ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሐሳብ ለመቀጠል ከመግባባት መደረሱን የሚገልጽ ነው። በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተካሔደ መኾኑን የሚገልጸው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በላከው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በድርድሩ ሁለት የቴክኒክና የሕግ ቡድኖች ቢኖሩ በሚል ያቀረበችውን ሐሳብ ሱዳን መቀበሏን ያስታወቀበት ነው። በዕለቱ በነበሩ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በተካሔደ ድርድር ኢትዮጵያ የግድቡን ውኃ አሞላል በተመለከተ ባቀረበችው ሐሳብ ላይ ንግግር መደረጉን ሚኒስቴሩ በመግለጫ አመልክቷል። በዚህም የመጀመሪያው ዙር የግድቡን የውኃ አሞላል የሚገዛበት መመሪያን በተመለከተ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሐሳብ ለመቀጠል ከመግባባት መደረሱንም ያትታል።

በድርድሩም በግብጽ በኩል ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሳትቀበለው የቀረችውን ረዘም ያለ ደረቃማ ዓመትና የድርቅ ጊዜን በተመለከተ፤ “ዝርዝር ሕግ መኖር አለበት” የሚለው ሐሳቧን በድጋሚ ለውይይት ማቅረቧ በዚሁ መግለጫ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፤ በሰሞኑ ውይይት የግብጽ ተደራዳሪዎች በዕለቱ የነበራቸው ተሳትፎ የተቀዛቀዘ እንደነበር ይኸው መግለጫ ያመለክታል።

የግብጽ ተደራዳሪዎች ድርድሩ እየተካሔደ የግድቡ ውኃ ሙሌት ሊካሔድ አይገባም ሲሉ ተቃውሞዋቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ እንደዚሁም እየተካሔደ ያለው ድርድር ሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ እና እስሁን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያስቀመጧቸውን በድርድሩ ለተገኙ ለውጦች እውቅና ያለመስጠት ፍላጎት እንደታየባቸው መግለጫው አመልክቷል። ነገር ግን አሁንም ድርድሩ እየተካሔደ ነው ተብሏል። (ኢዛ)

ግብጽና የኢትዮጵያ የምክትል ኢታማዡር ሹሙ ቆንጣጭ አንደበት

ከቅርብ ወራት ወዲህ እንደ ዋነኛ አጀንዳ ያለማቋረጥ አነጋጋሪ ኾኖ የዘለቀው የህዳሴ ግድብን የተመለከተና በዚሁ ጉዳይ ከግብጽ ጋር የተገባው እስጥ አገባ ነው። ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም በተለያየ መንገድ ከመግለጽ ባሻገር አቋሜን እወቁ በማለትም ከወትሮው ለየት ባለ መንገድ የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እያደረገች ነው። ከዚህ ጐን ለጐን በቀጣዩ ወር ግድቡን ውኃ ለመሙላት የቆረጠች ቢኾንም፤ ግብጽ ይህ የውኃ ሙሌት እንዳይጀመር እስከተባበሩት መንግሥት ድረስ አቤት ያለች ቢሆንም ኢትዮጵያ ጉዳዩ እንደቀድሞ መደራደሩ ይበጃል ብላለች። ይህም ድርድር ቢኾን ውኃውን ከመሙላት የሚያግደኝ የለም በማለትም ማሳወቋን ቀጥላለች።

ሁኔታው ግን አሁንም ከፊት ለፊቱ ብዙ ውጣ ውረድ ያለው ቢኾንም፤ ግብጽ ከግትር አቋሟ እንድትወጣ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ ግብጽ ኢትዮጵያ በያዘችው ዕቅድ መሠረት ውኃ የመሙላት ሥራዋን ስትጀምር ጦር አዘምታለሁ በሚል የሚናፈሰው ወሬ ግን የመኾን ዕድሉ ጠባብ ቢኾንም በቸልታ የሚታይ ያለመኾኑን የፖለቲካ ተንታኞች ሳይገልጹ አያልፉም።

ይህም ኾኖ ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ጦርነት ቢኖር እንኳን ዝግጁ መኾኑን በቁርጥ ያስታወቀበት መግለጫ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ተሰጥቷል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ሕልውናና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ስለመኾኑና ኢትዮጵያም ዝግጁ መኾኗን ያመለከቱት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ናቸው። የተሳሳተ የመሪዎቿ አስተሳሰብ ግብጽን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳትም ያመለከቱት ጄኔራል ብርሃኑ፤ ግብጾች ኢትዮጵያዊያን ጦርነት ከመጣ እንዴት ጦርነትን መሥራት እንደሚችሉ በሚገባ ያውቁታል በማለት ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ሕልውናና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ሕዝብ መኾኑን አይደለችም ግብጽ፤ ዓለም ያውቃል። በአገሩ ጥቅምና ሕልውና የሚደራደር ኢትዮጵያዊ የለም” ያሉት ጀኔራሉ፤ የጦር መሣሪያ በገፍ መሰብሰብ ብቻ በጦርነት ውስጥ ለድል እንደማያበቃና በጦርነት ውስጥ ለድል የሚያበቁ ሳይንሳዊ የኾኑ የጦርነት መሠረታዊ የሚባሉ ሕጎች እንዳሉም ከሰሞኑ በሰጡት ቃለምልልስ ጠቅሰዋል።

“ለድል የሚያበቁት የመሠረታውያኑ ቁልፎች በሙሉ በኢትዮጵያውያን እጅ ናቸው፤ ግብጾች 30 እና 40 ዓመት ሙሉ የሰበሰቡት ብዙ ዐይነት የጦር መሣሪያ አላቸው፤ በዚህ አስፈራርተው የጋራ የኾነውን ውኃ እንዳትነኩ ለማለት ይሞክራሉ ያሉት ጀኔራሉ፤ የግብጽ መሪዎቹ በዚህ መልኩ ማሰብ እንዳልነበረባቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም። ግብጻዊያን ከኢትዮጵያ ጋር በጭራሽ መጣላት ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን ተንከባክበው በመያዝ ውኃውን እንዴት አድርገን በጋራ እንጠቀም ማለት እንደነበረባቸውም በማስታወስ፤ ነገሩ ብዙ ጠላት ማፍራት ይኾንባታል ብለዋል።

“ግብጽ አሁን የያዘችው መንገድ ለአገሪቱ ብዙ ጠላት የሚያፈራባት ነው፤ ጠላትነት በጨመረ ቁጥር ጭራሹንም ውኃው ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው ወደሚል የእልህ መንገድ ይወስዳል” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ፤ መቼም ቢሆን የግብጽ ሠራዊት ኢትዮጵያ ገብቶ ምሽግ ሠርቶ የዓባይን ገባር ወንዞች አይጠብቅም በማለት አክለዋል። የግብጽ ሠራዊት የኢትዮጵያን ምድርንም መርገጥ እንደማይችል በመናገር፤ ወንዞቻችን ከጦርነትም በላይ ታላቅ አቅምና ጉልበት አላቸው ብለዋል። የግብጽ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ሚዲያቸውና ምሁራኑ የግብጽ ሕዝብ እንዲደነግጥ፣ እንዲፈራ፣ ውኃ የሚያጣ እንዲመስለው የረዥም ዘመን ሥራ መሥራታቸውን አስታውሰው፤ ይህም ዛሬ ችግር የፈጠረባቸው መኾኑንም ጄኔራሉ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል።

ግብጽ ጦርነት ውስጥ እገባለሁ የሚለውን አመለካከትና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ “ጠላትን መቀነስ፤ ወዳጅን ማብዛት የሚባል ስሌት አለ። መፎከር ሁሉም አማራጭ ጦርነትን ጨምሮ ጠረጴዛ ላይ ነው ያለው ማለት፤ የሐሰት ሪፖርት ጽፎ መበተን፤ ግዙፍ የሚዲያ ዘመቻ ከፍቶ ኢትዮጵያን ማጥላላት፤ በጠላትነት መፈረጅ ትርጉም የለሽ ነገር ነው” ብለውታል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሰፋ እና ጠንከር ያለ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን እያፋጠነች መኾኑ፤ ግድቡን ውኃ ሞልቶ ለጥቅም ለማዋል ቁርጠኛ መኾንዋን ገልጸው፤ ግድቡ ግብጾችንም የሚጠቅም በመኾኑ፤ ቢችሉ ሊተባበሩን፤ ካልቻሉ ግን ይተዉን ማለታቸው አይዘነጋም። (ኢዛ)

የቀድሞው ኤታማዦር ሹምና መፈንቅለ መንግሥት ጥያቄው

ከሰሞኑ የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በሰጡት ቃለምልልስ፤ ከዚህ ቀደም መፈንቅለ መንግሥት እንዲደረግ ተጠይቀን ነበር ይላሉ። ይህንንም “ኢሕአዴጎች በ2010 ጥልቅ ታኀድሶ አድርገው የአመራር ለውጥ እያደረጉ ባለበት ወቅት፤ ሠራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት እንዲያደርግ የሚጠይቁ መዓት ሰዎች ነበሩ” በማለት መግለጻቸው ብዙዎችን አስደምሟል። ጄኔራል ሳሞራ የኑስ የሰጡት አንድ ቃለምልልሰ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብዙ አስተያየት የተሰጠበት አነጋጋሪ ነበር ማለት ይቻላል። ሰዎቹ እነማን እንደነበሩ ግን ባይገልጹም፤ በወቅቱ የተሸረበ ሴራ እንደነበር ያመለከተ መረጃ የሰጡበት ነው።

የወታደር ሥራ አገር መጠበቅ በመኾኑ ፖለቲካው ውስጥ እንዳልገቡና መሪ በተለዋወጠ ቁጥር ጥሰት መጮህ ስለሌለበት ኢሕአዴጎች የወሰኑት ውሳኔ ላይ ጣልቃ ሳይገቡ መቅረታቸውን ተናግረዋል።

መፈንቅለ መንግሥት እንዳያደርጉ ከመጠየቃቸውና ለዚህም እኛ አያገባንም ብለው ከወሰዱት አቋም ባሻገር፤ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው፤ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እየሠሩ ስለመኾናቸው ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሰጡት ምላሽ ውስጥ የብልጽግና ፓርቲ አባል ለመኾን መስፈርቱን አላውቅም የሚል ነበር። ባውቅም መስፈርቱን የማሟላ አይመስለኝም የሚሉት ጄኔራሉ፤ እንደ ዜጋ ምክር ስጠየቅ ግን ለሕዝብ በሚጠቅም መለኩ ሐሳብ መስጠቴን እቀጥላለሁ በማለት፤ አሁንም ሥራ ላይ ስለመኾናቸው ጠቋሚ መልስ ሰጥተዋል። የትግራይንና የኢትዮጵያን ሕዝብ እስከጠቀመ ድረስ፤ በምፈልግበት ቦታ እሠራለሁ ያሉት ጄኔራሉ፤ በኢትዮጵያ ታክስ ከፋይ የተማርኩ በመኾኔ፤ በራሴ ፕሮግራም የኢትዮጵያንና የትግራይን ሕዝብ ከጠቀመ እገዛ አደርጋለሁ የሚል አንደምታ ያለው ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢዛ)

የትግራይ ክልል ውሳኔና የምርጫ አደርጋለሁ ውዝግብ

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት የ2012 ዓ.ም. ክልላዊ ምርጫን ለማካሔድ የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ ስለመወሰናቸው የተሰማው በዚህ ሳምንት ነበር። በአገር አቀፍ ደረጃ ምርጫው እንዲራዘም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠውን ውሳኔ በሚቃረን መልኩ የክልሉ ምክር ቤት የወሰነው ውሳኔ ግን፤ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ልዩነት ያሰፋ ኾኖ ተገኝቷል።

በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ መንግሥት ሥርጭቱን ለመግታት በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተፈጻሚ የሚኾን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ የሚታወቅና ምርጫን ለማካሔድ የማያስችል በመኾኑ፤ እንዲሁም በሕዝቡ ጤንነትና ደኅንነት ላይ ሥጋት መፍጠሩን ተከትሎ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገር አቀፍ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑ የሚታወቅ ነው።

ከዚህም ሌላ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም አሁን ያሉት የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች የወረርሽኙ ሥጋት ተቀርፎ ምርጫ እስከሚካሔድ ድረስ እንዲቀጥሉ መወሰኑ ቢታወቅም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በዚህ ሳምንት ምርጫን በክልል ደረጃ ለማካሔድ የደረሰበት ድምዳሜ ግን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ ማስነሳቱ አልቀረም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከሰሞኑ አስተያየት የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሴክሬተሪያት አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ “የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ ይካሔድ ብሎ መወሰኑ፤ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ስለኾነ መንግሥት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አክብሮ ያስፈጽማል” ብለዋል።

ምርጫን የማስፈፀም ሥልጣን የተሰጠው በሕግ መንግሥቱ አንቀጽ 102 የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ መኾኑን ያስታወሱት አቶ ንጉሡ፤ ሌላ አካል በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ልግባ ቢል፤ ከሥልጣን ገደቡ በላይ የምርጫ ቦርድን ሥልጣን መጋፋት እንደኾነም አስታውቀዋል። ድርጊቱ የምርጫ ቦርድን ሥልጣን መዳፈር ጭምር ስለሚኾን፤ መንግሥት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አክብሮ ይፈጽማል በማለት ገልጸዋል። በዚሁ በትግራይ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ንጉሡ፤ መከላከያ ሠራዊቱ ነፃና ገለልተኛ ኾኖ “የአገርን ሉዓላዊነትና ሕገ መንግሥቱን እንደሚያስከብር ሁሉ፤ ምርጫ ቦርድም የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ሁሉም አካል ሊያከብር ይገባል” ብለዋል።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምርጫን የማስፈጸም ሥልጣን ለአስፈጻሚው ስላልተሰጠ፤ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ነገር ሊያደርግ የሚችውና ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ያለው ምርጫ ቦርድ ብቻ መኾኑንም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ምርጫ ቦርድ የተሻለ እና ገለልተኛ ኾኖ እንዲቋቋምና ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መጎልበት በር እንዲከፍት ኾኖ እንደተደራጀ ያነሱት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊው፤ የክልልም ኾነ የፌዴራል መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት አይችልም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ዋና ትኩረት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል የህዳሴ ግድብ የሚገጥሙ ችግሮችን በማለፍ፤ ውኃ መሙላት መጀመር እና ለጥቅም ማብቃት ስለመኾኑ በመግለጽ፤ የምርጫው ጉዳይ ገለልተኛው እና በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ ሥራ መኾኑንም አስገንዝበዋል። አያይዘውም ምርጫ ቦርድ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሚያደርገውን ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው በመግለጽ፤ በክልል ደረጃ ምርጫ አደርጋለሁ ላለው የትግራይ ክልል ውሳኔ ላይ የመንግሥታቸውን አቋም የሚያንጸባርቅ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢዛ)

አዲሱ መሪ ዕቅድ

ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የልማት ተምሳሌት ለማድረግ የሚያስችል የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የተመከረው በዚህ ሳምንት ነበር። “ኢትዮጵያ 2022፤ ፍኖተ ብልጽግና” በሚል ሐሳብ የተዘጋጀው የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ፤ ለሚኒስትሮችና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ በውይይት መድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በሚቀጥሉት አስር ዓመት የኢትዮጵያን በነፍስ ወከፍ ገቢ በማሳደግ፤ ኢትዮጵያን አስተማማኝ መካከለኛ የኢኮኖሚ ገቢ ያላት አገር ለማድረግ የአስር ዓመት የብልጽግና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። መሪ ዕቅዱ የመልማት አቅምን መሠረት ያደረገና ወጥ የኾነ አገራዊ ራዕይን ለማሳካት እንደሚረዳ ገልጸው፤ ዕቅዱ በክልልና በአገር ደረጃ ተግባራዊ እንዲደረግ ወጥ የኾነ አዘገጃጀት እንዳለውም ተናግረዋል።

“ብልጽግናን ለማምጣትና ድህነትን ለመቀነስ ትርጉም ያለውና በዜጎች ሕይወት ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ዕቅድ ያስፈልጋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመኾኑም እያንዳንዱ ሴክተር ከፕላን ኮሚሽን ጋር ተናብቦ የሚሠራበት ተጨባጭ ለውጥ የሚያስገኝና የትውልድ የኑሮ ሥርዓትን የሚቀይር የብልጽግና ፍኖተ ካርታ ስለመዘጋጀቱም ጠቅሰዋል።

ከአገር የኢኮኖሚ አቅም በሻገር ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ሊያስገባ እንደሚገባውና ዕቅዱ ተግባራዊ ሲደረግ፤ ከዚህ ቀደም ላለመሥራት ምክንያት የማቅረብ ባህልን የሚያስቀርና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ለልማት ያለውን ግንዛቤ እኩል የሚያደርግ መኾኑንም ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ እስከ 2022 ዓ.ም. ድረስ አስተማማኝ ገቢ እንዲኖራት በማድረግ፤ የነፍስ ወከፍ ገቢን በ8 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን፤ ከ2013 ዓ.ም. እስከ 2022 ዓ.ም. ባሉት አስር ዓመታት የነፍስ ወከፍ ገቢን በአማካይ 8.2 በመቶ በማሳደግ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘውን ሕዝብ በ2012 ዓ.ም. ካለበት 19 በመቶ በ2022 ወደ ሰባት በመቶ እንዲቀንስ የሚያስችል ዕቅድ መዘጋጀቱንም የኮምሽኑ ኮምሽነር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ያስታወቁት በዚህ ሳምንት ነው።

የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የውጭ ንግድና የሸቀጥ ምርትን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት፤ በየዓመቱ 1 ነጥብ 36 ሚሊዮን አዳዲስ ሥራዎችን መፍጠርና ምርታማነትን በሁሉም ዘርፎች በመጨመር የዋጋ ንረትን መቀነስ የሚያስችል ስለመኾኑም ኮምሽነሯ ተናግረዋል። (ኢዛ)

ረቂቅ በጀቱ

ከሳምንቱ ዐበይት አገራዊ ኢኮኖሚን ከሚመለከቱ ጉዳዮች አንዱ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2013 በጀት ዓመት 476 ቢሊዮን ብር ኾኖ በቀረበው የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ በረቂቅ በጀቱ ዙሪያ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፤ የ2013 በጀት ግብዓትን ከውጤት ጋር የሚያዛምድ፤ እንዲሁም ኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ስለመኾኑ ነው፡፡ ምክር ቤቱም የቀረበውን ረቂቅ በጀት በመመልከት የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ በጀቱ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች አቅርበዋል፡፡ አቶ አሕመድ ሺዴም ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ከሰጡበት በኋላ፤ ጉዳዩ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ