Ethiopia Zare's weekly news digest, week 1st, 2013 Ethiopian calendar

ከመስከረም 4 - 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

 

የዓመቱ አንደኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከመስከረም 4 - 10 ቀን 2013 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት መሪ ዜና ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብዋ የኾነውን የብር ኖት ለውጥ ማድረጓ ነው። ከዚህ ዜና ባሻገር ከሳምንቱ አነጋጋሪና ትኩረት ሳቢ ዜናዎች ውስጥ የጤና ሚኒስትሯ ቀጣዩን ምርጫ በጥንቃቄ ማድረግ ይቻላል የሚል ሪፖርት ለፓርላማ ማቅረባቸው ተጠቃሽ ነው።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ያለው ኦነግ ሊቀመንበሩን ማባረሩና አዲስ የትግል ስልቴን እወቁልኝ ብሎ በተከታታይ ያወጣቸው መረጃዎች ካሳለፍነው ሳምንት ክንውኖች ውስጥ የሚካተት ነው። በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ የተከሰተው የጐርፍ አደጋ፤ ከ200 ሺሕ በላይ ዜጐችን ሲያፈናቅል፤ ግማሽ ሚሊዮን የሚኾኑትን ሥጋት ላይ ጥሏል። የጉዳት መጠኑና የተረጅዎችም ቁጥር እያሻቀበ ነው።

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ከመሔዱም በላይ፤ በቫይረሱ የተያዙ የሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር ከ1,300 በላይ መድረሱም የተነገረበት ሳምንት ነው።

በቤንሻንጉል ክልል የተፈጠረው ቀውስ ሌላው የሳምንቱ አነጋጋሪ ዜና ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን የጉዳዩን አሳሳቢነት አጠንክሮ እየተናገረ ነው። ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋር በመተባበር ኒውክሌር ለማልማት የሚያስችለው አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል።

በሜቴክ ሥር ያሉ ኩባንያዎች ተሰባስበው አዲስ ኩባንያ እንዲቋቋም የተወሰነውም በዚህ ሳምንት ነው።
የአገሪቱ ሁለተኛው የመንግሥት ባንክ በመኾን የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል። በእርሳቸው ምትክ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ቦታውን እንዲይዙ ተደርጓል።

ከሰሞኑ የብር ለውጥ ጋር በተያያዘ በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ገንዘቦች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባሉ ኬላዎች ጭምር እየተያዙ ነው።

በታማኝነት ከፍተኛ የኾነ ግብር የከፈሉ 200 ነጋዴዎች ኩባንያዎች እውቅና የተሰጣቸው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። በዚህ የእውቅና ፕሮግራም ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዳሚዎቹን ፈገግ ያሰኘ ንግግር የተናገሩበት ነበር። በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የተቀናበረውን የ2013 ዓ.ም. አንደኛ ሳምንት አንኳር ዜናዎች እነኾ!

የብር ኖቱ ለውጥ ተከትሎ ጉምሩክ ጥብቅ ቁጥጥር ላይ ነው

የብር ኖት ላይ ለውጥ መደረጉ በብርም ኾነ በውጭ አገር ገንዘብ የሚደረገውን ኮንትሮባንድ ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቆ፤ የሕገወጥ የገንዘብ ክምችት እና ዝውውር ወንጀለኞች እንዳሻቸው አገር እንዳትረጋጋ እና ሰላም እንዳትኾን የሚያደርጉ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች እንዲያስገቡ በር ከፍቶላቸው መቆየቱንም አስታውሷል።

ይህን በብርቱ ተፈታታኝ የኾነ ሕገወጥ ተግባር ለመቆጣጠርም የብር ኖት ለውጡ ለኮሚሽኑ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥርም፤ በብር ኖቱ ለውጥና ጠቀሜታ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽነሩ ደበሌ ቃበታ አስታውቀዋል።

የብር ኖቱ ለውጥ ይፋ ከተደረገበት ዕለት ጀምሮ ኮሚሽኑ በተለይም በድንበር አካባቢዎች እና በሁሉም ኬላዎች ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥር እያደረገ መኾኑንም በመግለጽ፤ በሦስት ቀናት ብቻ ከቶጎ ጫሌ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ የነበረ 200 ሺሕ ብር፤ በአሶሳ በኩልም በተመሳሳይ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ የነበረ ወደ 600 ሺሕ ብር መያዝ ተችሏል። (ኢዛ)

ለ200 ታማኝ ግብር ከፋዮች የአገልግሎት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ነው

ታማኝ ግብር ከፋዮች በመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚያስችል ሥርዓት እንዲዘረጋ መመሪያ ከተሰጠ በኋላ፤ የእነዚህ ተቋማት ስም ዝርዝርም ይፋ ኾኗል።

ታማኝ ግብር ከፋዮች በመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚያስችል ሥርዓት እንዲዘረጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መመሪያ በሰጡ ማግስት፤ በዚህ ተጠቃሚ ይኾናሉ የተባሉ ተቋማትና ግለሰቦች ስም ዝርዝራቸው ወጥቷል። ይህ መመሪያ በየትኛውም የአልግሎት መስጫ ተቋማት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኒህ ግብር ከፋዮች እንደ ሌሎች መሰለፍ የለባቸውም ነበር ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን መመሪያ ሰጥተው የነበሩት በሦስት ደረጃ በተሰጠው የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሽልማት ላይ እንደነበር አይዘነጋም። በዚህ ሽልማት በአጠቃላይ 200 ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጥቷቸዋል። በዚህም ግብር ከፋዮቹ 20 በፕላቲኒየም፣ 60 በወርቅና 120 በብር ደረጃ መሸለማቸው ይታወሳል። በሽልማት ፕሮግራሙ ላይ እንደተገለጸው በአጠቃላይ በ2012 በጀት ዓመት 270 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 233.7 ቢሊዮን መሰብሰቡም ተገልጿል። ገቢው ከ2011 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ35.5 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል። (ኢዛ)

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ጎምዛዛ መሰንበቻ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች ስለመፈጸሙ የሚያመላክተውን መግለጫ ያወጣው ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ቢያንስ በሁለት ዙር ተፈጽመዋል በተባሉ በእነዚህ ጥቃቶችም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ ማረጋገጡንም በዚሁ መግለጫ ጠቅሷል።

በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረሶች መታየታቸውን የጠቆመው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ ይህን ተከትሎም ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ እንዳሳሰቡት ኢሰመኮ አስታውቋል።

ጥቃት የተፈጸመባቸው የክልሉ አካባቢዎች በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ የሚገኘው አጳር ቀበሌ እና በወንበራ ወረዳ መልካ ቀበሌ መኾናቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አመልክቷል። ከእነዚህ አካባቢዎች “እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች” እየደረሱት መኾኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በቦታዎቹ ላይ ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግሥት ማረጋገጡንም አመልክቷል።

በዚህ አካባቢ የተፈጠረው ግጭት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች በርካታ ናቸው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን፤ ከሁኔታው አሳሳቢነት አንፃር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሰላም ሚኒስትሯ ወደ ቦታው አምርተው ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተጣርቶ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል። (ኢዛ)

ኢዜማ ዜጐችን ያልታደገ ስለብልጽግና ማውራት አይቻልም በማለት መንግሥትን ተቸ

“የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማክበር እና ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልጽግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም” በሚል ርዕስ ኢዜማ ያወጣው መግለጫ ከሳምንቱ ዜናዎች አንዱ ነበር።

ኢዜማ በዚህ ርዕስ ያወጣው መግለጫ በቤንሻንጉል ጉምዝ በተከሰተው አሳዛኝ ድርጊትን ተንተርሶ ነው። እንደ ኢዜማ በክልሉ በንጹኀን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ እና በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ችግር ፈቺ ያልኾኑ ምላሾች የችግሩ ምንጭ አካባቢውን ከሚያስተዳድረው የመንግሥት መዋቅር እና ችግሩን በቸልታ እያየ ያለው የፌዴራል መንግሥት ነው ብሎ እንዲያምን ያስገደደው መኾኑንም አመልክቷል።

“ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ጥቃቶች አጥፊዎች እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮች ላይ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ባለመወሰዱ ችግሩ አሁንም ቀጥሏል” ብሏል። ኢዜማ ክልሉን በሚመሩት ኃላፊዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ካልተወሰደ፤ ግድያና ማፈናቀሉ ይቆማል ብሎ እንደማያምን በዚሁ መግለጫው አስታውቋል።

“የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን የሕይወት መኖር ማክበር እና ማስከበር ነው። ይሄን ማድረግ ያልቻለ መንግሥት ስለ ልማት እና ብልጽግና የማውራት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም” በማለት በቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈጸመውን ድርጊት ኮንኗል። (ኢዛ)

የአቶ እስክንድር ነጋ አቤቱታና አስደማሚው ጥያቄ

ባሳለፍነው ሳምንት ከነበሩ የፍርድ ቤት ውሎች መካከል እነ አቶ እስክንድር ነጋን የሚመለከተው ይገኝበታል። እነ አቶ እስክንድር በተከሰሱበት ወንጀል ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ለችሎቱ ያሰሙት አቤቱታ ለየት ያለ ነበር ማለት ይቻላል። አቶ እስክንድር በችሎቱ ቀርበው የተናገሩት የአገሪቱ ሰላም እና ደኅንነት የሚፈለግ ከኾነ እርሳቸው እና አብረዋቸው የተከሰሱ ሰዎች በዋስትና ወጥተው፤ በመጪው ምርጫ ላይ መሳተፍ ይገባቸዋል የሚል ነው።

አቶ እስክንድር ይህን ያሉት ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ ዓቃቤ ሕግ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላቀረበው ክርክር በሰጡት ምላሽ ሲሆን፤ “እኛ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ የነበርን ነን። በዝግጅታችን ለሕዝባችን የፖለቲካ የበላይነት እንዳለን በማሳየታችን፤ በዚህ ምክንያት ገዥው ፓርቲ አስሮ ያመጣን መኾኑን እንድታውቁልን ያስፈልጋል” ብለዋል።

“እኛ ታስረን የሚደረግ ምርጫ፤ ዓቃቤ ሕግ የሚፈልገውን የአገሪቱን ሰላም እና ደኅንነት አያመጣም” በማለት ያከሉት አቶ እስክንድር ነጋ፤ በአገሪቱ ሰላም እና ደኅንነት እንዲመጣ ከተፈለገ በዋስትና ወጥተን በምርጫ መሳተፍ አለብን” ብለዋል። እነርሱ በሌሉበት የሚካሔድ ምርጫ ተቀባይነትም ኾነ ቅቡልነት እንደማይኖረውም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። (ኢዛ)

የአቶ ልደቱ ጠበቆች ስንብትና አዲስ ክስ

ባሳለፍነው ሳምንት ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ልደቱ አያሌው፤ አዲሱ ክስ ከመመሥረቱ በፊት በነፃ የጥብቅና አገልግሎት ሲሰጧቸው የነበሩ የሕግ ባለሙያዎችን አሰናበቱ የሚለው ዜና ሌላው የሳምንቱ ዜና ነበር።

አቶ ልደቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱበትን ምክንያት የፖሊስ እና የዓቃቤ ሕግ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ሲያገኙ እርሳቸው ያቀረቧቸው ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎች አንድም ጊዜ ተቀባይነት አለማግኘታቸውን በመጥቀስ፤ እንዲህ ባለ ሒደት ጠበቆቻቸውን ይዘው መቀጠሉ አስፈላጊ ባለመኾኑ ነው።

“የምርመራ ፋይሌ በፍርድ ቤቱ በተዘጋበት እና ምንም ዐይነት የጊዜ ቀጠሮ ባልተሰጠኝ ሁኔታ የዋስ መብት እንዳይኖረኝ ተከልክያለሁ” ያሉት አቶ ልደቱ፤ “በዚህም ምክንያት በፖለቲካ አመለካከቴ እንድታሰር የወሰኑብኝ የፖለቲካ ሰዎች፤ ስለወደፊቱ እድሌም የሚወስኑትን የፖለቲካ ውሳኔ በእስር ላይ ኾኜ እየተጠባበቅኩ እገኛለሁ” ብለዋል።

ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ከዚህ በኋላ በከተማው ፍርድ ቤት የሕግ ክርክር ማድረግ ባለመፈለጋቸው እንደኾነ በዝርዝር ባቀረቡት ደብዳቤያቸው ላይ አስታውቀዋል።

ይህንን መሰል ይዘት ካለው የአቶ ልደቱ ደብዳቤ በኋላ ዓቃቤ ሕግ አዲስ ክስ መሥርቶ ለክሱ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ ክስ ሲመሠረት ግን ጠበቆቻቸው ቀርበው የነበረ ሲሆን፤ የዋስትና ጥያቄያቸውን በተመለከተ ግን ለመስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ተሰናበቱ
የቀድሞው ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት ቦታውን ይዘዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ከኃላፊነታቸው ተነስተው አዲስ ፕሬዝዳንት መሰየሙ የተነገረው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

አቶ ኃይለየሱስ ኃላፊነታቸውን የለቀቁት በፍቃዳቸው ነው ቢባልም፤ ባንኩ ካለበት ችግር ጋር በተያያዘ ስለመኾኑ ይነገራል። የእርሳቸውን ከኃላፊነት መልቀቅ ተከትሎ ዶክተር ዮሐንስ አያሌው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ኾነው እንዲያገለግሉ ተሰይመዋል።

ዶክተር ዮሐንስ ወደዚህ ኃላፊነት ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቦርድ አባል ኾነው እያገለገሉ ነው።

በዋናነት ግን ዶክተር ዮሐንስ የሚታወቁት ከ15 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት ኾነው በማገልገላቸው ነው።

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኾኑ በኋላ ከምክትል ገዥነታቸው ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በዳይሬክተርነት አንዲዛወሩ ተደርገው ነበር። (ኢዛ)

ከ200 ሺሕ በላይ ያፈናቀለው ጐርፍ ለግማሽ ሚሊዮን ዜጐችም ሥጋት ላይ ጥሏል

ባሳለፍነው ሳምንት ጐልተው ከተሰሙ ዜናዎች በኢትዮጵያ ባልተለመደ ሁኔታ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጐርፍ ያስከተለው አደጋ ነው። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የሰላም ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት የጐርፍ አደጋ ባጋጠማቸው አካባቢዎች ከ217 ሺሕ በላይ ዜጎች በጎርፍ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት እስካሁን ከ217 ሺሕ በላይ ዜጎች በጎርፍ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉት ከአምስት ክልሎች ነው። በኢትዮጵያ የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እና የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂንየነር ስለሺ በቀለ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ በአምስቱ ክልሎች በሚገኙ 23 ዞኖች ላይ ጎርፍ የተከሰተ መኾኑን ነው። ከ580 ሺሕ በላይ ዜጎች የጎርፍ አደጋ እንደተጋረጠባቸው አመልክተዋል።

በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ አስቸኳይና ዘላቂ ተግባራት ተለይተው እየተሠሩ መኾኑንም ሚኒስትሮቹ አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት ለእነዚህ በጐርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጐች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ እርዳታዎችን እያቀረቡ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን በቂ እርዳታ እየደረሰ አለመኾኑ እየተገለጸ ነው። እንዲህ ባለ ደረጃ ጐርፍ አደጋ ፈጥሮ የማያውቅ ሲሆን፤ ዜጐችን ለማፈናቀል ሌላ ከፍተኛ የኾነ ንብረትም አጥፍቷል። ሰፋፊ እርሻ ላይ ያሉ ምርቶችንም መጉዳቱ ታውቋል። (ኢዛ)

በሜቴክ ሥር የነበሩ ኩባንያዎች ተሰባስበው በአዲስ ተቋም እንዲቋቋሙ ተወሰነ

በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሥር የነበሩ ተቋማትን በመነጠል “ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ” በሚል አዲስ ኩባንያ ለማቋቋም ተወሰነ። ቀደም ሲል በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሥር የነበሩና በብረታ ብረት፣ በአውቶሞቲቭ፣ የእርሻ መሣሪያዎች ምርት፣ የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪና ፕላንት፣ እንዲሁም የፖሊመር ምርት ዘርፎች የተሰማሩትን ተቋማት በኢትዮ ኢንጂንየሪንግ ግሩፕ ሥር እንዲኾኑ በማድረግ እንዲሠሩ የተወሰነው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው።

እነዚህን የቀድሞ የሜቴክ ተቋማት በማሰባሰብ አዲስ ኩባንያ እንዲደራጅ የተፈለገው የሀብት አጠቃቀሙን ውጤታማ ለማድረገ እና ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገር ለማስቻል የማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከተወያየበት በኋላ የተሰጡ ግብዓቶች ተካተው ረቅቅ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል። (ኢዛ)

ኢትዮጵያ ኒውክሌርን ለመጠቀም ከሩስያ ጋር ልትሠራ ነው

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለማዋል የሚያስችላትን የትብብር ስምምነት አዋጅ ይጸድቅ ዘንድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የኔውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም የተደረገ የትብብር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ይፋ የኾነው መረጃ ሁለቱ አገራት የ1968ቱ የኒውክሌር መሣሪያዎች እሽቅድምድምን የሚከለክለውን ዓለም አቀፍ ስምምነት እና ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የገቡትን የስምምነት ባከበረ መልኩ የኒውክሌር ኢነርጂን ለሰላማዊ ዓላማዎች ጥቅም ላይ ማዋላቸው በአገራቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መኾኑን ነው። በዚህም መሠረት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኒውክሌር ኃይልን በመጠቀም የሚያስችለው የማጸደቂያ ረቂቅ አዋጁን አዘጋጅቶ በማቅረብ፤ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል። (ኢዛ)

በኢትዮጵያ 1,300 የሕክምና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም የኢትዮጵያ ሥጋት ኾኖ የቀጠለ ሲሆን፤ እስካሁን ከ65 ሺሕ ሰዎች በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋል። በዚህ ሳምንት እንደተገለጸው ደግሞ፤ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከ1 ሺሕ 300 በላይ የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ነው።

ከጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ኮሮና ቫይረስ በተለይ በሽታውን በመከላከል ሥራ ግንባር ቀደም በኾኑት የሕክምና ባለሙያዎች ላይ መጠነ ሰፊ ችግር ማስከተሉን፤ እስካሁን በኢትዮጵያ 1 ሺሕ 311 የሚኾኑ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ ከእነዚህ መካከል 700 የሚኾኑት አገግመው ወጥተዋል፤ ቀሪዎቹ በሕክምና ተቋማት ሕክምና እየተደረገላቸው ነው። በዓለም ላይ እስካሁን 1.3 ሚሊዮን የጤና ባለሙያዎች በዚሁ ወረርሽኝ ተጠቅተዋል። (ኢዛ)

የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ተፈቱ

ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረዋል ተብለው በሕግ ጥላ ሥር ከነበሩት መካከል የአሥራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ከእስር የተለቀቁት በዚህ ሳምንት ነው።

ፍርድ ቤት ቀደም ብሎ በአሥር ሺሕ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ከወሰነ በኋላ ሳይፈቱ የቀሩ ቢኾንም፤ በዚህ ሳምንት ድጋሚ ፍርድ ቤት ቀርበው ቀደም ብሎ በተወሰነላቸው መሠረት ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት በመወሰኑ ሊለቀቁ ችለዋል። በዋስትና የተፈቱት እነዚህ የአስራት ሚዲያ የሚዲያ ባለሙያዎች በላይ ማናየ፤ ሙሉጌታ አንበርብር እና ምስጋናው ከፈለኝ ናቸው። ፍርድ ቤቱ ደግሞ በዋስ ይለቀቁ ያለው ከቀደመው ክስ የተለየ ክስ ስላልቀረበባቸው ነው። (ኢዛ)

በድሬዳዋ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ገንዘብ ተያዘ

ከሰሞኑ ከተደረገው የብር ኖት ለውጥ ጋር ተያይዞ እየተደረገ ባለ ሕግ የማስከበር ሥራ በሕገወጥ መንገድ ሲዛወር ተገኘ የተባለ ዜና እየተሰማ ነው። እስካሁን ከተሰሙት ውስጥ በድሬዳዋ ከተማ ተያዘ የተባለው አንዱ ነው። በሳምንቱ አጋማሽ በድሬዳዋ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የገንዘብ ኖቶች ውስጥ በዋነኝነት 944,110 የኢትየጵያ ብር፣ 1250 የአሜሪካን ዶላር፣ 165 የሳውዲ ሪያል፣ 745 ዩሮ ነው። ከእነዚህ ጋር አብሮም ከዘጠኝ በላይ የሚኾኑ አገራት የተለያየ መጠን ያላቸው የብር ኖቶች በቁጥጥር ሥር መዋሉን የድሬዳዋ ፖሊስ አስታውቋል።

ከጉዳዩ ጋር የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦችም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መኾኑንም ፖሊስ አስታውቋል። (ኢዛ)

በአዲስ አበባ ሕገወጥ 100 ሺሕ ዶላርና 5 ሚሊዮን ብር ተያዘ

በአዲስ አበባ የብር ኖት ቅያሪን ተከትሎ ሕገወጥ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በተከናወነ ተግባር 100 ሺ የአሜሪካ ዶላር እና 5 ሚሊዮን ብር መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያስታወቀውም ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

በጥናት ላይ ተመሥርቶ በተደረገ ክትትልና በሕግ አግባብ የተደረገ ብርበራ በጥቁር ገበያ ለምንዛሪ የቀረበ 100 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር፣ 5 ሚሊዮን ብር፣ ዩሮ እና የተለያዩ አገራት ገንዘብ መያዙን የሚጠቅሰው የፖሊስ መረጃ፤ ከዚህ በተጨማሪ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር የነበረ አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ ብር መያዙን አመልክቷል። እንዲህ ባለው ሕገወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች ሕገወጥ ተግባሩን የሚፈጽሙት ሕጋዊ የንግድ ፈቃድን ሽፋን በማድረግ ሲሆን፤ እንዲህ ያለው ድርጊት ሲፈጸምባቸው ነበሩ የተባሉ መደብሮችም ታሽገዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!