ስሜነህ ታምራት ከስዊድን

ከአዲስ አበባ ተነስተን ወደ ወሊሶ በሎንቺና ስጓዝ ነበር፤ ለመጀመሪያ ጊዜ አበራ ለማን ያገኘሁት። እናም “ኩል ወይስ ጥላሸት” የሚል መጽሐፍ በገፀበረከት አበረከተልኝ። “የማን መጽሐፍ ነው?” አልኩት፤ “እኔ የሞካከርኳት መጽሐፌ ናት” አለኝ - ለስለስ ባለ አንደበት። አመስግኜ ተቀበልኩት።

 

ከሸገር - ወሊሶ 115 ኪሎ ሜትርን እየተጫወትን ተጉዘን ደረስን። ከዚያ በኋላ ግን ግንኙነታችንን የምንቀጥልበት ጉዳይም አጋጣሚም አልነበረም። ዳግም ሳንገናኝ ለረዥም ዓመታት ቆየን። አልፎ አልፎ ግን ስሙን በአንዳንድ መጣጥፎች ላይና በራዲዮ ስሰማው በዚያች መጽሐፉ አስታውሰው ነበር። ዘለግ ያለ ቁመናውና ነጭ መነጽሩ የሱ ልዩ ማስታወሻዎቼ ናቸው።

 

በሕይወት ዙሪያ ብዙ ገጠመኞች በመኖራቸው ዛሬ እኔም እሱም ሁለት ጎረቤት በሆኑ ሀገሮች በስደት እንኖራለን። እሱ በኖርዌይ መኖሩን ያወቅሁበት አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። በኖርዌይ “ያራ” የተባለው የማዳበሪያ ሻጭ ድርጅት አቶ መለስ ዜናዊን (ብዙ ማዳበሪያ በመግዛት ይመስለኛል) ተሸላሚ አድርጎ ይመርጣቸዋል። በርካታ ኢትዮጵያውያን አድራጎቱን በመቃወምና የበርካታ ንፁኀንን ሕይወት ያጠፋ አምባገነን መሪ መሸለሙን ለማውገዝ በሽልማት ቦታው ይገኛሉ። እኔም ከስዊድን ኖርዌይ ተጉዤ ትንሿን ብሔራዊ ድርሻ ለመወጣት አጋጣሚ አገኘሁ። አበራ ለማን አገኘዋለሁ የሚል ሃሳብ ግን አልነበረኝም። በኢትዮጵያዊነትና በአክብሮት የጋራ ተቃውሞ ድምፃችንን ስናስተጋባ ዋልን።

 

አቶ መለስ የተገኙት በግል ድርጅት ተመርጠው እንጂ በመንግሥት ደረጃ አልነበረም። በመሆኑም በማዕረግና በኦፊሴል የተቀበላቸው መንግሥታዊ ባለሥልጣን አልነበረም። እንዳውም የጋበዛቸው ድርጅት ራሱ በተቃውሞ ሰልፉ ተደናግጦ ወደ ማረፊያቸው ግራንድ ሆቴል በጓዳ በር ይዟቸው ሄዷል። ከዚህ በኋላ በኖርዌይ የኢትዮጵያውያን ማኅበር ባዘጋጀልን መስተንግዶ ላይ ተገናኝተን በሰፊው ተወያየን። አድራሻ ተለዋውጠን ለመጠያየቅም ተስማማን።

 

የሁለት ሺህ ዓመት የሚሊኒየም ወቅት እየተቃረበ ሲመጣ በስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዓሉን ለወያኔ ብቻ አንተወውም እኛም የራሳችንን ዝግጅት ማድረግ አለብን ብለው ይስማማሉ። አንድ አዘጋጅ ኮሚቴ ከ13 የተለያዩ ድርጅቶች ተወክሎ ሲመሠረት፤ እኔም ከአንዱ ተወክዬ አዘጋጅ ሆንኩ። አንድ ቀን የኮሚቴው ሊቀመንበር ወቅታዊ ኢንፎርሜሽኖችን ሲሰጠን በፕሮግራማችን ላይ ከፊንላንድም ከኖርዌይም በርካታ ሰዎች ለመምጣት እንዳሰቡ ገልፆ፤ በተለይ አበራ ለማ የኢትዮጵያን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሳ ቅርስ የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ለማቅረብ እንደጠየቀና አዎንታዊ ምላሽም እንደተሰጠው ይገልጽልናል። እኔም ሌላ ደስታ ተሰማኝ። ከብዙ ዓመታት በፊት የምታውቁት ሰው በተመሳሳይ የስደት ኑሮ ለተመሳሳይ ብሔራዊ ድርሻ በድግግሞሽ መገናኘት የሚሰማውን ስሜት እናንተው አስቡት። በሚሊኒየሙ ወቅት ስንገናኝም የመጀመሪያዋን የሎንቺና ጉዟችንን አንስቼ ብዙ ተጫወትን። የኢትዮጵያ ህዝብ ባለውለተኛ ከሆኑትና በክብር እንግድነት ጋብዘናቸው ከነበሩት ከአውሮፓ ፓርላሜንት አባል ሚስስ አና ጎሜዝ ጋርም የመታሰቢያ ፎቶግራፍ ተነሳን።

 

ይህችን አጭር መጣጥፍ ለማስፈር ያነሳሳኝ የእኔና የአበራ የግንኙነት አጋጣሚ አይደለም። ይኼ የትዝታ ቅምሻ ነው። የጽሑፌ ዓላማ አበራ ለማ ሁለት አፍሪካውያንን የኖርዌይ ደራሲያን ማኅበር ተሸላሚዎች በማድረግ የፈፀመውን አኩሪ ተግባር ይዘክራል።

 

በመጀመሪያ ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክና ምጥቀት ታላቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱት ክቡር ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ይህን ሽልማት ያገኙት በአበራ ለማ ጠቋሚነትና አቅራቢነት ነበር። መልካም ሥራ በራሱ ምስክር ቢሆንም በሌላ ሰው ካልቀረበ ራሱ አፍ አውጥቶ አይናገርም። ከዚህ አኳያ የእኒህን ታላቅና እውቅ የጥበብ አባት ጥልቅ ኪነጥበባዊ ሥራ በዝርዝር ከነታሪኩ በማቅረብና በማሳመን አዎንታዊ ውጤት ማስገኘት በራሱ ታላቅ የዜግነት ክንዋኔ ነው።

 

በሌላ ጊዜ በስዊድን የኢትዮጵያ ኪነጥበባዊ ዝግጅት ለወጣቱ ትውልድ ለማስጨበጥና የጥበብ ሥራዎችንም ለማስተዋወቅ አንድ ዝግጅት ይዘጋጃል። ባለቅኔው ገጣሚ ኃይሉ ገሞራው በክብር እንግድነት በተገኘበት በዚህ መድረክ ላይም አበራ ተሳታፊ ነበር። በግሉም የኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ዕድገታችንን የቃኘ ጥናታዊ ማብራሪያና ሙያዊ መግለጫ በመስጠት ወጣቶችን አስተምሯል። የቀዝቃዛው አየር ንብረት ብዙ ለመወያየት ባያስችለንም በተመሳሳይ ተግባር ዴንማርክ ላይም ተገናኝተን ነበር።

 

ከጥቂት ሣምንታት በፊት “የወገን ጦር ትዝታዬ” በሚል ርዕስ ሻለቃ ማሞ ለማ ያዘጋጁትን መጽሐፍ አስመልክቶ አንድ ሂሳዊ ንባብ አቅርቧል። ግሩም ዕይታና የታሪክ ቅንብር ነውና በዚህም ምስጋናዬ ይድረሰው።

 

አሁን በመጨረሻ ደግሞ የብዕር ጀግኖችን ማወደስ ደስታን የሚሰጠው አበራ፤ የኤርትራ እና የስዊድን ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅን ለሽልማት በመጠቆምና በማሳመን የኖርዌይ ደራሲያን ማኅበር ሁለተኛው አፍሪካዊ ተሸላሚ አድርጎታል። የጋዜጠኛ፣ ደራሲና ፀሐፊ ተውኔት ዳዊት ይስኃቅ በኤርትራ ከታሰረ 9 ዓመት ከ6 ወር ሆኖታል። ማርች 13-14 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. ኖርዌይ ኦስሎ በሚደረገው መደበኛ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ስዊድን የሚኖሩት ባለቤቱና ልጆቹ ተገኝተው ሽልማቱን እንደሚቀበሉ ታውቋል።

 

እዚህ ላይ አንድ ትልቅ ነገር ልብ ማለት ያስፈልጋል። ደራሲ አበራ ለማ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ነው። ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅ ደግሞ ኤርትራዊ ተወላጅ ነው። ትናንትና እና ዛሬ ኢትዮጵያና ኤርትራ ያሉበት የግንኙነት ሁኔታ ይታወቃል። ከዚህ አኳያ አበራ አንዳችም ጠባብ ስሜት ሳይሰማው ለሙያውና ለማኅበሩ ዓላማ ተዓማኒነትና ክብርን ቅድሚያ ሰጥቶ ዳዊት ይስኃቅን በዕጩነት አቅርቦ፣ አሳምኖና አስወስኖ ለሽልማት ማብቃቱ እንደገና “ብራቮ! አበራ” ያስብላል።

 

ዛሬ እነመለስ ዜናዊ ኢትዮጵያውያንን ሊቀርጹበት የሚፈልጉት የዘርና የጎሣ ፖለቲካ በማናቸውም ጊዜና በየትኛው ቦታ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ውግዝ መሆኑን የአበራ ለማ አርቆ አስተዋይነት በገሃድ አረጋግጧል። በእሱ መልካም ተግባር በርካታ ኢትዮጵያውያን የመንፈሥ ኩራትና ደስታ ተሰምቶናል። አበራም ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ሰው ተኮር ተሟጋችና ዓለም አቀፋዊ አመለካከቱን በገሃድ አሳየ። ረዥም ታሪክ የሚጻፈው ትናንሾቹን ድርጊቶች እየመዘበጉ ከመሰብሰብ ነውና፤ ታሪክ ፀሐፊዎች የአበራ ለማን አርኣያነት ያለው ተግባር በምሣሌነቱ ሊዘክሩት ይገባል እያልኩ፤ አጭሯን መጣጥፌን በዚህ አበቃለሁ።


ስሜነህ ታምራት ከስዊድን

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ