በስዊድን ’’እውነትም እኛ …” ተመረቀ
ግምገማና ውይይት ተደረገ
Ethiopia Zare (ሰኞ ኅዳር 27 ቀን 2003 ዓ.ም. December 6, 2010)፦ በጋዜጠኛና ደራሲ አበራ ለማ ተገጥሞ በራሳቸው አንባቢነትና በአቶ ክብረት መኮንን የምስልና ድምፅ ቅንብር የተደረገለት ”እውነትም እኛ …” የተባለ ሃያ አምስት ግጥሞች የያዘ ዲቪዲ የግጥም መድብል ቅዳሜ ኅዳር 18 (ኖቬምበር 27) ቀን በስቶክሆልም ከተማ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ተመረቀ።
ገጣሚና ደራሲ አበራ በተገኙበት በዚህ የምረቃ ሥርዓት ላይ በስዊድንና አካባቢው የሚኖሩ የጥበብ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን እና የአንድነት ድጋፍ ማኅበር አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
የምረቃው ዝግጅት በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት ከሰዓት በኋላ በ9 (በ15፡00) ሰዓት የተጀመረ ሲሆን፣ የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ ማትያስ ከተማ ዝርዝር መርኀ ግብሩን እና ስለ ገጣሚ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ሥራዎች ለተሰብሳቢው በመግለጽ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
አቶ ማትያስ ባደረጉት ንግግር፤ የሀገራችንን ቋንቋ እና ድርሰት ቀደም ካለው ዘመን በመነሳት ጠቅሰው፣ አሁን ለደረሰበት ሁኔታ እንዲበቃ እገዛ ያደረጉትን ደራሲያንን አመስግነዋል። ደራሲ አበራ ለማም በግጥምና በአጭር ልብ ወለድ ጽሑፍ ብዙ አስጠዋጽዖ ያደረጉ እውቅ ጋዜጠኛና ደራሲ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህን በአይነቱ አዲስ የሆነ የግጥም ዲቪዲ ቀደም ሲል በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች እንደተመረቀ የገለጹት አቶ ማትያስ፤ በስዊድን በሚገኙ ወገኖቻቸው ለማስመረቅ በመምጣታቸው ደራሲ አበራን አመስግነዋል።
በስዊድን የአንድነት ድጋፍ ማኅበር ሰብሳቢ የሆኑት አቶ የራስወርቅ መንገሻ በበኩላቸው፤ ቋንቋችን ምጥቀትና ጥልቀት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ሃሳብን ለመግለጽና በጽሑፍ ለማስተላለፍ ብርታት ያለው እንደሆነ ምሳሌ በመጥቀስ አስረድተዋል።
ገጣሚ መስከረም አየለ፤ ደራሲ አበራ በጋዜጠኛ ሙያቸው ወቅት ብርቱና ደፋር ጋዜጠኛ ይባሉ እንደነበር አስታውሰው፤ ቀደም ሲል ”ፊያሜታ እንባባ” በሚል ደራሲው በጻፉት ግጥም ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት በመግለጽ ግጥም አቅርበዋል። ”ፊያሜታ እንባባ” ጋዜጠኛና ደራሲ በአሉ ግርማን ለማስታወስ በገጣሚ አበራ ለማ የተገጠመ ሲሆን፣ በዚሁ መድብለ ቪዲዮ ተካትቷል።
በመቀጠል ደራሲ አበራ ለማ ስለግጥም መድብሉ ይዘትና ዝግጅት ማብራርያ ሰጥተዋል። በተለይ የመድብሉ መጠሪያ የሆነው ”እውነትም እኛ …” እያንዳንዳችንን የሚመረምርና የሚነካ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ግጥም መነሻ የሆናቸው ቅስም የሰበረው የቅንጅት ጉዳይ እንደሆነ አልሸሸጉም።
ከደራሲ አበራ ንግግር በኋላ ”እውነትም እኛ ...” እና ”እርሱን አኑሩልኝ” የተሰኙት የግጥም ሥራዎች ለተሰብሳቢው ታይተዋል። ተመልካቹም ስለግጥሙ የራሱን ሃሳብ እንዲሰጥና ውይይት እንዲያደርግ ተጋብዞ፤ አቶ አለማየሁ ዲባባ ”እርሱን አኑሩልኝ” በተባለው ሥራ ላይ ሙያዊ ግምገማ አቅርበዋል። ከሳቸው ገለጻ በኋላም ተሰብሳቢው የራሱን አስተያየትና ሃሳብ ሰጥቷል።
በውቅቱ ዝግጅቱ በከረንት አፌርስ የውይይት መድረክ (ፓልቶክ) ይተላለፍ ስለነበር ከመቶ ሰማኒያ ቤተሰብ በላይ ሲከታተለው እንዳመሸ ታውቋል። ይሄው ዲቪዲ ለዚሁ የውይይት ክፍል ማሳደጊያ እንዲውል በአቶ ሙሉጌታ አሳሳቢነት ለጨረታ ቀርቦ 5000 ዶላር ሊያስገኝ እንደቻለ ታውቋል።
የዕለቱ የምረቃ ዝግጀት ከምሽቱ አራት (22፡00) ሰዓት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ደራሲ አበራ በማግስቱ እሁድ ኅዳር 19 (ኖቬምበር 28) በአቶ ዘነበ በቀለ ከሚመራው የኢትዮጵያ የሙዚቃና የድራማ አባላት ጋር ተገናኝተው ስለግጥሙ መድብል ውይይት ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ደራሲ አበራ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት ይሄንኑ ዲቪዲ ለማስመረቅ ወደ ሰሜን አሜሪካ ልዩ ልዩ ከተሞች እንደሚያቀኑ ለማወቅ ችለናል።