አከተመ ዘፈን

(ለቴዎድሮስ ካሣሁን ክብር ይሁን)

ትንሣዔ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ፍቅርን ካልነገረ ውበትን ኳኩሎ፣

ታሪክ ካልዘከረ አበጥሮ አንጓሎ።

ዘብጥያ ከሆነ በቂምና ቁርሾ፣

አከተመ ዘፈን ተተካ በሙሾ።

ከንግዲህ ለምኔ ማለት አበድኩልሽ፣

አፈቀርኩህ ማለት ከንግዲህ ለምንሽ፤

ብላቴናው ታስሮ የታናሼ ታናሽ።

የእስላም ክርስቲያኑ የማተቡ ጽናት፣

በፍቅር አይደለም ወይ የሚተሳሰሩት።

ከንግዲህ ፀሎት ነው ሱባዔ ልመና፣

ልዝፈን አትበሉኝ ታስሮ ብላቴና።

ቴዎድሮስ ካሳ ነህ ልሳን የብሶቴ፣

ሠላምና ፍቅር ቃሌም አንደበቴ።

ሲያስሩህ አስረውኛል ሲጎዱህ ተጎዳሁ፣

ሲጨክኑ ባንተ እኔም ዘፈን ጠላሁ።

እናንት ወገኖቼ የምታውቁ ዜማ፣

የቴዲን ዝፈኑ ሌላውን አልስማ።

እናንት ከሀዲዎች እነ ፍርደ ገምድል፣

ትናንትን ረስታችሁ የቁጣን ማዕበል።

እንዲሁ እንደናንተው በሰው የፈረዱ፣

ስንቶች መና ቀሩ ስንቶችስ አበዱ?

እናንት ከሀዲዎች አጋር የወያኔ፣

እንባችሁ አይቆምም እያላችሁ ወይኔ።

ቴዎድሮስ ወንድሜ ከእስር ሳይፈታ፤

ከእንግዲህ ለዘፈን ከእንግዲህ ለእስክስታ፣

ደግሞ ለአስረሽ ምቺው ከቶም የለኝ ቦታ፤

ፍቅርን ካልነገረ ውበትን ኳኩሎ፣

ታሪክ ካልዘከረ አበጥሮ አንጓሎ።

ዘብጥያ ከሆነ በቂምና ቁርሾ፣

አከተመ ዘፈን ተተካ በሙሾ።

ፀሎት ነው እንግዲህ እንግባ ሱባዔ

አምላክ እንዲያሳየን የኢትዮጵያን ትንሣዔ


 

እጅግ ከፍተኛ በሆነ ንቀት የተሞላ መንግሥትና ለፍርፋሪው ያደሩ የነቀዙ ባለሟሎች እያደረጉ ያለውን ክፋት በቁርጠኛነትና በአንድነት ልንታገላቸው ይገባል። በእርግጥም ለዘፈንና ለዳንኪራ የምንሞላቸው አዳራሾች ባዶ ይሁኑ። ቴዎድሮስ እስኪፈታ ድረስ የርሱን ገድል የማያነሱ የርሱን ነፃነት የማይጠይቁ ዘፈኖችን ባለመስማት አነስተኛ ግን አጋርነትን ገላጭ የሆነ ነገር እናድርግ የሚለውን የኢትዮጵያውያን ጥሪ እቀበላለሁ።

ትንሣዔ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ