እስትንፋስህ ተገታ (አብርሃም ሠለሞን)
እስትንፋስህ ተገታ
አብርሃም ሠለሞን - ከሚኒሶታ (አሜሪካ) (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ስሙ ሞት የሚባል የማይቀር እንግዳ፣
ሌሊት ከተፍ አለ በጥላሁን ጓዳ።
ምንኛ ክፉ ነው ሞት የሚሉት አውሬ፣
ታግሎ ይዞት ሄደ ጥላሁንን ዛሬ።
ኧረ በሕግ አምላክ! ሕግ ያግድህ ስማ፣
ወገን በተኛበት ደርሰህ በጨለማ፣
እንዴት ሀብታችንን ጨክነህ ወሰድከው፣
የኢትዮጵያን ብርሃን ይኼንን ታላቅ ሰው።
ደፋር አይደለህም ሞት ለካስ ፈሪ ነህ፣
ወገን በተኛበት ሌሊት ትመጣለህ።
ጥላሁን ገሠሠ የወገን አለኝታ፣
ክቡር እስትንፋስህ በዚች ቀን ተገታ።
ሀገሬን እያለ የሚጮኽው ድምፅህ፣
ኢትዮጵያን የሚለው ብርቅዬ አንደበትህ፣
ዳግም ላይናገር አሸለበ ለአንዴ፣
ተጠየቅ ጥላሁን እንዲህም አለ እንዴ?
አካል የሚያስቆርጥ ሕመም ያልደፈረህ፣
ከአንገትህ ያረፈው ስለት ያልገደለህ፣
እንዴት ሳትታመም አውርተህ ተጫውተህ፣
በሌሊት የመጣ ክፉ እንግዳ ያዘህ?
ይገርማል ጥላሁን በሠላም አምሽተህ፣
ሌባው ድንገት መጥቶ በሌሊት ወሰደህ።
በምድር እንዳትታይ ለአንዴም ለዘላለም፣
አትሞብህ ሄደ የሞትን ማኅተም።
ለምትወደው ህዝብህ እንዲያ ለምታምነው፣
ምሥጢር የሸሸግከው ዘንድሮ ብቻ ነው።
የወገንን መራብ አልቅሰህ ስትነግረው፣
የኢትዮጵያን ደስታ በመድረክ ስትገልጸው፣
ምን ነገር ተገኘ እንዴት ብትጨክን ነው?
እንዲህ ላትመለስ ወጥተህ ቅርት ያልከው።
እጅግ በምትወደው በሀገርህ በምድርህ፣
የእስትንፋስህ ማብቂያ ሆነ ስንብትህ።
“ዋይ! ዋይ!” ሲሉ ብለህ ያለቀስክላቸው፣
ለእነኛ ረሃብተኞች ዕንባ ለሌላቸው፣
መንታ መንታ ሲወርድ እንዲያ ሲፈስ ዕንባህ፣
የታሪክ ቅርስ ሆኗል የመድረክ ላይ ሲቃህ።
ዛሬም ሁሉ አዘነ ሁሉ አለቀሰልህ፣
“ዋይ! ዋይ!” ይል ጀመረ የምትወደው ህዝብህ።
አንገትህ በካራ በስለት ተወግቶ፣
ሀገሬን ይል ነበር ድምፁን አሰምቶ።
አካልህ ተቆርጦ ለአንተ ማሰብ ትተህ፣
“ወገን እባካችሁ ስለ ወገን” ብለህ፣
ታሰባስብ ነበር ገንዘብ ለደሃው ሰው፣
የሚታከምበት አጥቶ ለቸገረው።
ኢትዮጵያ አትረሳውም ይኸንን ውለታ፣
መልካም ማድረግህን ሥራህን ለአንዳፍታ።
የቆምክበት መድረክ ለኢትዮጵያ አንድነት፣
የእናት ሀገርህን ስም የጠራህበት፣
ባየኸው ጥላሁን ሰፈር እና ሀገሩ፣
የኀዘን ቤት መስሎ ከተማው መንደሩ።
ጥላሁን ገሠሠ ሞትህ ሞት አይደለም፣
ትውልድ ያነሣዋል ስምህን ዘላለም።
ሰው ሳያስታምምህ ወገን ሳይጠይቅህ፣
ጥላሁን በመንገድ ድንገት ወጣ ነፍስህ።
ለስንቱ የደረስክ በኀዘን በችግሩ፣
አቤት! በዚያች ሌሊት ሰው ጠፋ በምድሩ።
እባክህ እግዚአብሔር ይኼንን ታላቅ ሰው፣
እንደ ቅዱሳኑ ሞቱን ሞት አታርገው።
ተስፋ ላሟጠጥነው ለምንወደው ወገን፣
ጥላሁን አልሞተም አንቀላፍቷል በለን።
እንደ አልዐዛር ጠርተህ መግነዙን ፍታለት፣
ሞቱ ሞት እንዳይሆን የጥላሁን በእውነት።
ታማሚን ጠይቋል የታረዘ አልብሷል፣
ለተራበ አብልቶ እስረኛን ጎብኝቷል፣
ሙያው ብቻ ሳይሆን የልቡ ደግነት፣
ዋይ! ብሎ አስጩሆታል ለራብ ለጦርነት።
አባት መልካም ግብሩን ይኼን ቁጠርለት፣
ልጅህን ፈጣሪ አኑረው በገነት።
ጥላሁን ገሠሠ የወገን አለኝታ፣
ክቡር እስትንፋስህ በዚች ቀን ተገታ።
ሀገሬን እያለ የሚጮኽው ድምፅህ፣
ኢትዮጵያን የሚለው ብርቅዬ አንደበትህ፣
ዳግም ላይናገር አሸለበ ለአንዴ፣
ተጠየቅ ጥላሁን እንዲህም አለ እንዴ?
ደህና ሁን ጥላሁን እግዚአብሔር ያስብህ፣
በገነት ይቀመጥ የከበረ ነፍስህ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
አብርሃም ሠለሞን - ከሚኒሶታ (አሜሪካ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.