ሾሌ ያ ነጭ ጠላ (ክንፈ ሚካኤል)
ሾሌ ያ ነጭ ጠላ
ክንፈ ሚካኤል (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ሾሌ ያ ነጭ ጠላ
ለሙዚቃው አድባር ለታላቁ ጥላ
ጥላሁን ያ ጥላ ሁን
ከየት እናግኝህ አሁን
ማን ያጥላልን በዚህ ዘመን
እንዲያው ሃምሳ ዓመት መዝፈን
እስር ጨለማ ብርሃን
ሲፈራረቁብህ አልፈህ ሁሉን።
ምን ያረጋል ሞት አይቀር
ቀድመህ ብለሃል ደጋጉን ቢያስቀር
አንተም አንዱ ነበርክ ከሚቀሩት
ለኢትዮጵያ ብለው ከኖሩት።
ቢለወጥ ሞት-ተራ ለሚወዱት
ለጥላሁን ነበር የኔ ሕይወት
ግን አይቀርም ዕልፈት
ተለየን ከጥላሁን ድንገት።
ሾሌ ያ ነጭ ጠላ
ለታላቁ አድባር
ለታላቁ ጥላ
ከእችክ እችክ እስከ ኡኡታ አያስከፋም
ከእይዋት ስትናፈቀኝ እስከ መለያየት ሞት ነው
ከምክሬን ስምኝ እስከ እንጉዳዬ ነሽ
ከልጅቷ እስከ ኩሉን ማን ኳለሽ።
ካንዱ ቀን እስከ እያሳቀችኝ
ካራዊቱ እስከ የሕይወቴ ሕይወት
ካሳለፍነው እስከ የጥንቱ ትዝ አለኝ
ከምኞቴ ተሳካ እስከ አባት ደስ ይለዋል
ይህን ሁሉ ፀጋ ማን ያገኘዋል።
ካመልካች ጣት እስከ ሩቅ ምስራቅ
እንዲህ እንደ አሁኑ ሳንራራቅ
ከሰፊው ህዝብ እስከ ነገሥታት
ሾሌ ያ ነጭ ጠላ ዝንት ዓመታት
ከሌሊት ጨረቃ እስከ ዓይኔ ሁልጊዜ
ከዘምባባ ዛፍ ነሽ እስከ ሞናሊዛ
ዘፈን እንደ አሁኑ ሳይንዛዛ
ሙዚቃው ጣዕም ያለው ለዛ
አሳለፍነው በዋዛ ፈዛዛ።
ከዋይ ዋይ ሲሉ እስከ ግፋ በለው
ካገር የጋራ ነው እስከ ሀገር አለኝ
ሾሌ ያ ነጭ ጠላ ለጥላሁን
የማይሰለች እስከ አሁን።
ከምግብ አይነቶች እስከ እንቁጣጣሽ
ከዘንድሮ እስከ ምን ታደርጊዋለሽ
የታሰረበት ሦስት አልማዞች።
እማይሰለች እማይጠገብ
መድረክ አይበቄ ስግብግብ
በላንቃ ድምፅ በቲያትር
ባይን ጥቅሻ ሁለ ገብ።
ካገር ፍቅር ብሔራዊ
ኦልኬስትራ ኢትዮጵያ
ከሁሉ ሠርቶ ከባለ ሙያ
ካድናቆት በላይ ለሁሉ መለኪያ።
ከስግብግብ ጆሮዬ ለዕውነት እሞታለሁ
ከባለ ጠላ እስከ ሁሉን አይቼዋለሁ።
ትቶልን ካለፈው ይሁነኝ ማልቀሻ
ዘላለም እንዲሆን ለኛ ማስታወሻ።
ተጠልቆ ያልቃል ወይ ዓባይን በጭልፋ
የጥላሁን ሥራ ኦሜጋና አልፋ
ልሰናበተው እንግዲህ በይፋ
ለዘላለሙ እሱም ያንቀላፋ
በአርካን ፉኔ በሾሌ ያ ነጭ ጠላ
ለሙዚቃው አድባር ለታላቁ ጥላ
ክንፈ ሚካኤል (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፪ ሺህ ፩ ዓ.ም.